Saturday, 04 June 2016 11:54

በ15ኛው የአውሮፓ ዋንጫ

Written by  ግሩም ሠይፉ
Rate this item
(3 votes)

     ለአስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ 24 ሚሊዮን ዩሮ በጀት ተመድቧል ከ90ሺ በላይ የፀጥታ ኃይሎች ይሰማራሉ፡፡ እስከ 1.49 ቢሊዮን ዩሮ መዋዕለ ንዋይ ይንቀሳቀሳል፡፡ 301 ሚሊዮን ዩሮ የሽልማት ገንዘብ ቀርቧል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር እስከ 500 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ ይጠበቃል፡፡ የሚሳተፉት 552 ተጨዋቾች እስከ 4.72 ቢሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመን አላቸው፡፡ 1 ጨዋታ በአማካይ 150 ሚሊዮን ተመልካች በዓለም ዙርያ ያገኛል፡፡ 15ኛው የአውሮፓ ዋንጫ አዘጋጇ ፈረንሳይ ከሮማንያ በስታድ ደ ፍራንስ በሚያደርጉት የመክፈቻ ጨዋታ ይጀመራል፡፡ ፈረንሳይ የአውሮፓ ዋንጫን የምታስተናግደው በውድድሩ ታሪክ ለ3ኛ ጊዜ ሲሆን ሁለቱን ያስተናገደችው በ1960 እኤአ እና በ1984 እኤአ ነበር፡፡ የአሜሪካ መንግስት የአውሮፓ ዋንጫው ለሽብር ጥቃት የተጋለጠ መሆኑን ከወር በፊት ያስጠነቀቀ ሲሆን፤ አዘጋጇ ፈረንሳይ 51 ግጥሚያዎች በሚካሄድባቸው 10 ከተሞች እና 10 ስታድዬሞች ከ90ሺ በላይ የፀጥታ ኃይል በማሰማራት ከፍተኛ ጥበቃ እና ክትትል ታደርጋለች፡፡ የአውሮፓ ዋንጫውን ከ2.5 ሚሊዮን በላይ ተመልካቾች በስታድዬሞች በመገኘት እንደሚከታተሉት የሚጠበቅ ሲሆን 1.5 ሚሊዮን ያህሉ በእንግድነት በፈረንሳይ የተለያዩ ከተሞች የሚገቡ ቱሪስቶች ናቸው፡፡ የፈረንሳይ መንግስት በአገሪቱ ያለውን ፀጥታ ለማጠናከር ሲተገብር የቆየውን ልዩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በአውሮፓ ዋንጫውም ላይም እንደሚቀጥል ያመለከተ ሲሆን ለአስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ 24 ሚሊዮን ዩሮ በጀት መመደቡን ለማወቅ ተችሏል ፡፡ ፈረንሳይ 15ኛውን የአውሮፓ ዋንጫ እንድታስተናግድ የተመረጠችው ከ6 ዓመታት በፊት ሲሆን ጣሊያንና ቱርክ መስተንግዶውን ለማግኘት ተፎካካሪዎቿ ነበሩ፡፡ የአውሮፓ ዋንጫውን በ10 የፈረንሳይ ከተሞች ቦርዶ፤ ሌንስ፤ ሊል፤ ሊዮን፤ ማርሴይ፤ ኒስ፤ ፓሪስ፤ ሴንት ዴኒስ፤ ሴንት ኢተንና ቱሉስ የሚገኙ 10 ስታድዬሞች የሚስተናገድ ሲሆን ሁሉንም ስታድዬሞች በአዲስ መልክ በመገንባት በማደስ እስከ 1.6 ቢሊዮን ዩሮ ወጭ ተደርጓል፡፡ 15ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በ24 ቡድኖች መካከል መካሄዱ በውድድሩ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ሲሆን፤ ለመጀመርያ ጊዜ የሚሳተፉት አምስት አገራት አልባንያ፤ አይስላንድ፤ ሰሜን አየርላንድ ፤ ስሎቫኪያ እና ዌልስ ናቸው፡፡ ተሳታፊዎቹ 24 ብሄራዊ ቡድኖች በ6 ምድቦች የተደለደሉ ሲሆን ከየምድቡ 1ኛ እና 2ኛ ደረጃ የሚያገኙት እንዲሁም ከስድስቱ ምድቦች ጥሩ ሶስተኛ የሆኑት 4 ብሄራዊ ቡድኖች ወደ ጥሎ ማለፍ ምእራፍ ይሸጋገራሉ፡፡ አዘጋጇ ፈረንሳይ፤ 13ኛውና 14ኛውን የአውሮፓ ዋንጫዎችን በተከታታይ ያሸነፈችው ስፔን፤ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጀርመንና በአዲስ ትውልድ የተዋቀረው የእንግሊዝ ብሄራዊ ቡድኖች ለዋንጫው ከፍተኛ ግምት ያገኙ ሲሆን በርካታ ምርጥ ተጨዋቾችን ያሰባሰበው የቤልጅዬም ብሄራዊ ቡድንም ለዋንጫው ፉክክሩ የታጨ ሆኗል፡፡ የአውሮፓ ዋንጫው ላይ በርካታ ምርጥ ብቃት ያላቸው አጥቂዎች በብዛት በመኖራቸው በጎሎች ብዛት እንደሚደምቅም ግምት አለ፡፡ በተለይ በኮከብ ግብ አግቢነቱ ፉክክር ደግሞ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር፤ የፈረንሳዩ አንቶኒ ግሪዝማን፤ የፖርቱጋሉ ክርስትያኖ ሮናልዶ፤ የእንግሊዙ ሃሪ ኬን እንዲሁም የፖላንዱ ሮበርት ሌዋንዶውስኪ እንደሚፎካከሩ ቅድሚያ ግምት ተሰጥቷቸዋል፡፡ ክርስትያኖ ሮናልዶ በፖርቱጋል ብሄራዊ ቡድን በመሰለፍ በ4 የአውሮፓ ዋንጫዎች ግብ ያስቆጠረ ተጨዋች ለመሆን የሚያነጣጥር ሲሆን ለተመሳሳይ ታሪክ የስዊድኑ ዝላታን ኢብራሞቪች የሚፎካከረው ይሆናል፡፡ ሁለቱ ተጨዋቾች በተሳተፉባቸው ያለፉት ሶስት የአውሮፓ ዋንጫዎች እኩል 6 ጎሎችን ለብሄራዊ ቡድኖቻቸው አስመዝገበዋል፡፡ በየብሄራዊ ቡድኖቻቸው ሳይመረጡ በመቅረታቸው የአውሮፓ ዋንጫው ካመለጣቸው ተጨዋቾች መካከል ፊሊፕ ሴንድሮስ ከስዊዘርላንድ፤ ጃቪ ማርቲኔዝ ከስፔን፤ ዳኒ ድሪን ዎተር ከእንግሊዝ፤ ሃቴም ቤን አርፋ ከፈረንሳይ፤ ማርዮ ባላቶሊ ከጣሊያን፤ ዲያጎ ኮስታ ከስፔን፤ ካሪም ቤንዜማ ከፈረንሳይ እና ፈርናንዶ ቶሬስ ከስፔን ይጠቀሳሉ፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በ2012 እኤአ ላይ ፖላንድ እና ዩክሬን አዘጋጅተው ከነበሩት 14ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በ50 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ገቢን ከ15ኛው የአውሮፓ ዋንጫ እንደሚጠብቅ ገልጿል፡፡ የአውሮፓ ዋንጫው በ24 ብሄራዊ ቡድኖች መካሄዱ ከ10 በላይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን በስፖንሰርሺፕ በማቀፍ ዳጎስ ያለ ጥቅም የሚያስገኝ ሲሆን እሰከ 1.49 ቢሊዮን ዩሮ መዋዕለንዋይ ይንቀሳቀስበታል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በዝርዝር እንዳስታወቀው ከአውሮፓ ዋንጫው ከ450 እስከ 500 ሚሊዮን ዩሮ ትርፍ ይጠበቃል፡፡ ከትኬት ሽያጭ እና መስተንግዶ 500 ሚሊዮን ዩሮ፤ ከቴሌቭዥ ስርጭት መብት እስከ 1 ቢሊዮን ዩሮ ገቢ እንደሚገኝ ነው፡፡ የአውሮፓ ዋንጫው በመላው ዓለም በ230 የስርጭት ቀጠናዎች በቴሌቭዥን የቀጥታ ሽፋን የሚያገኝ ሲሆን አንድ ጨዋታ በአማካይ 150 ሚሊዮን የቲቪ ተመልካች እንደሚኖረው ተገምቷል፡፡ የአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር ለአውሮፓ ዋንጫው ያቀረበው የሽልማት ገንዘብ ከ301 ሚሊዮን ዩሮ በላይ ሲሆን ካለፈው የአውሮፓ ዋንጫ በ194 ሚሊዮን ዩሮ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ በውድድሩ ተሳታፊ ሚሆኑ 24 ብሄራዊ ቡድኖች በተሳትፎ ብቻ በነፍስ ወከፍ 8 ሚሊዮን ዩሮ ሲከፋፈሉ በየምድብ ጨዋታው ለሚያሸንፍ 1 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም አቻ ለሚወጣ 500ሺ ዩሮ ይታሰባል፡፡ ጥሎ ማለፍ የሚገቡ 16 ብሄራዊ ቡድኖች 1.5 ሚሊዮን ዩሮ፤ ሩብ ፍፃሜ የሚደርሱ 8 ብሄራዊ ቡድኖች 2.5 ሚሊዮን፤ ለግማሽ ፍፃሜ የሚበቁ 4 ብሄራዊ ቡድኖች 4 ሚሊዮን ዩሮ ሲሰጣቸው በዋንጫ ጨዋታው ለሁለተኛ ደረጃ 5 ሚሊዮን እንዲሁም ለሻምፒዮኑ አገር 8 ሚሊዮን ዩሮ እንደሚበረከትም ለማወቅ ተችሏል፡፡ ዋንጫውን የሚያሸንፍ ብሄራዊ ቡድን እስከ 27 ሚሊዮን ዩሮ፤ በሁለተኛው ደረጃ የሚያጠናቅቀው እስከ 24 ሚሊዮን ዩሮ የሚያገኙ ሲሆን ለደረጃ የሚጫወቱት ሁለት ብሄራዊ ቡድኖች በነፍስ ወከፍ እስከ 19 ሚሊዮን ዩሮ ከሽልማት ገንዘቡ የሚታሰብላቸው ይሆናል፡፡ ከ15ኛው የአውሮፓ ዋንጫ በፊት ስፔን እና ጀርመን እያንዳንዳቸው እኩል 3 ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰኑን ሲጋሩ ፈረንሳይ በ2 ጊዜ አሸናፊነት ትከተላለች፡፡
እያንዳንዳቸው እኩል አንዴ ሻምፒዮን ለመሆን የበቁት ስምንት ቡድኖች ደግሞ የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት፤ ጣሊያን፤ ቼክ ሪፖብሊክ፤ ሆላንድ ዴንማርክ እና ግሪክ ናቸው፡፡ ጀርመን በአውሮፓ ዋንጫ የተሳትፎ ታሪኳ 43 ጨዋታዎችን በማድረግ ፤ 23 በማሸነፍ እና 65 ጎሎች በማስቆጠር ግንባር ቀደም ትሆናለች፡፡ በአውሮፓ ዋንጫ ላይ 9 ጎሎች በማግባት የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አግቢነቱን የሚመራው የፈረንሳዩ ሚሸል ፕላቲኒ ሲሆን፤ የማጣርያ ጨዋታዎችን ጨምሮ ከዋናው ውድድር ጋር 26 ጎሎች በማስመዝገብ የፖርቱጋሉ ክርስትያኖ ሮናልዶ ተጠቃሽ ይሆናል፡፡
በ24ቱ ተሳታፊ ብሄራዊ ቡድኖች የሚሰለፉ 552 ጨዋታቸው የዝውውር ገበያ የዋጋ ተመን 4.972 ቢሊዮን ዩሮ ነው፡፡ በተጨዋቾች ስብስብ የዋጋ ግምት አንደኛ ደረጃ የሚወስደው 658.5 ሚሊዮን ዩሮ የሚተመነው የስፔን ብሄራዊ ቡድን ሲሆን፤ ጀርመን በ566.33 ሚሊዮን ዩሮ ፤ ፈረንሳይ በ492.6 ሚሊዮን ዮሮ፤ ቤልጅዬም በ452 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም እንግሊዝ በ447 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመናቸው እስከ 5ኛ ደረጃ ያገኛሉ፡፡ ከተጨዋቾች በ92.9 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመኑ ግንባር ቀደም የሆነው የፖርቱጋሉ ክርስትያኖ ሮናልዶ ሲሆን፤ የጀርመኑ ቶማስ ሙለር በ70.73 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም የቤልጂዬሙ ኤዲን ሃዛርድ እና የፖላንዱ ሮበርት ሎዋንዶውስኪ በ66.26 ሚሊዮን ዩሮ የዋጋ ተመናቸው ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡ በተያያዘ በአውሮፓ ዋንጫው በሚሳተፉ 24 ብሄራዊ ቡድኖች ተጨዋቾቻቸውን ላቀረቡ ከ580 በላይ ክለቦች የሚከፈልም 150 ሚሊዮን ዩሮ ተዘጋጅቷል፡፡ በአውሮፓ ዋንጫው 12 ተጨዋቾችን ለየብሄራዊ ቡድኖቻቸው በማሰለፍ ግንባር ቀደም የሆኑት የእንግሊዙ ክለብ ሊቨርፑል እና የጣሊያኑ ክለብ ጁቬንትስ ሲሆኑ ሌላው የእንግሊዝ ክለብ ቶትንሃም 11 ተጨዋቾች በማሳተፍ ይከተላል፡፡ የስፔኑ ባርሴሎና እና የጀርመኑ ባየር ሙኒክ እያንዳንዳቸው 9፤ ሪያል ማድሪድ 8፤ አትሌቲኮ ማድሪድ እና ፓሪስ ሴንትዠርመን 4 ተጨዋቾችን በአውሮፓ ዋንጫው ያካፍላሉ፡፡ ሌሎቹ የእንግሊዝ ክለቦች አርሰናል እና ማንችስተር ዩናይትድ እያንዳንዳቸው 10 ተጨዋቾችን ፤ ማንችስተር ሲቲ 7፤ ቼልሲ 6 እንዲሁም በርካታ የፕሪሚዬር ሊጉ እና የአንደኛ ዲቪዝዮን ክለቦች ለአውሮፓ ዋንጫው ከሌሎች የአውሮፓ ክለቦች በላቀ ብዛት በመልቀቅ ይጠቀሳሉ፡፡ የ15ኛው የአውሮፓ ዋንጫ 6 ምድቦች ምድብ 1 ፈረንሳይ ፤ሮማንያ አልባንያና ሲዊዘርላንድ ምድብ 2 እንግሊዝ ፤ ሩሲያ ፤ዌልስ እና ስሎቫኪያ ምድብ 3 ጀርመን ፤ዩክሬን፤ፖላንድና ሰሜን አየርላንድ ምድብ 4 ስፔን፤ ቼክ ሪፐብሊክ፤ ቱርክና ክሮሽያ ምድብ 5 ቤልጂየም ፤ጣልያን፤ አየርላንድንና ሲዊድን ምድብ 6 ፖርቹጋል፤ አይስላንድ፤ኦስቲሪያና ሃንጋሪ፡፡

Read 3758 times