Monday, 30 May 2016 09:25

ዋግ የመታው አፍሪካዊ ፍልስፍና!

Written by  ደረጀ ይመር
Rate this item
(2 votes)

    በግብና በዓላማ ያልተቀየደ መደመም የፍልሰፍናን በራፍ ለመቆርቆር ቀዳሚው መላ እንደሆነ ከጥንታዊያን  የግሪክ ፈላስፎች ምልከታ መገንዘብ እንችላለን፡፡ በእርግጥም ጠቢብ ሲጠበብ፣ ዘር ቀለምን ከቁጥር አይጥፍም፡፡ በባህልና በዘር ባልተቀነበበ ሰፊ የምናብ ሑዳድ ግዛት ላይ እንዳሻው ይናኛል፡፡ መናኛቱ እንደው በከንቱ ፣በደመነፍሳዊ መዋተት የሚከወን ግብር አይደለም፡፡ በጥልቅ እሳቤ፣በጥልቅ ተመስጦ ቆስቋሽነት ለዓይነ ሥጋ የሚበቃ የነፍስ በረከት እንጂ፡፡
ይህንን መሰሉ ፍልስፍናዊ ትንታኔ ከአፍሪካዊያን ልሂቃን ጉሮሮ አልውርድም ካለ ሰነባበተ፡፡ ልሂቃኑ ለአፍሪካዊያን ቁመና የሚመጥን አዲስ ፍልስፍናዊ ጭብጥ እውን ለማድረግ ላለፉት አስርተ ዓመታት ላይ ታች ዳክረዋል፡፡ አፍሪካዊ ፍልስፍና ከመደመም፣ከመደነቅ ይልቅ ቁጭት፣የበታችነት፣የዘር መድሎ፣ጭቆናን እንደ መነሻ ንጣፍ ተጠቅሞ የተቀለሰ የፍልሰፍና ዘውግ ነው፡፡ በእዚህም ምክንያት ፍልስፍና ግሪካዊያን የለገሷት ማዕረግ ተገፎ በዘርና በቀለም በተሸበበ አፍሪካዊ ምህዳር ውስጥ ሰፋሪ ሆና ቁምስቅሏን ታያለች፡፡
ቆስቋሽ ምክንያት
የምዕራቡ ዓለም ያበቀሏቸው ታላላቅ ጠቢባን፣ ስለ ሰው ዘር ጭንቅ ጥብብ ባሉበት ምናባቸው፣ ሌላ ያልተጠበቅ ክሽፈት የተጣባው አምክንዮ በየዘመኑ አስተጋብተው አልፈዋል፡፡ በእዚህ መሰሉ መናኛ አቋማቸው ምክንያት እንደ እምቧይ ካብ ለዓይን ሲቀሉ ለማስተዋል ጥቂት ፍሬ ነገራቸውን መልሶ መላልሶ መጎብኘት በቂ ነው፡፡ ጥልቅ እሳቤያቸው ስኳር እንደተለወሰ መራራ ኪኒን ትንሽ ተውተርትሮ ጠየፍ ሰብዕናው እርቃኑን ይቀራል፡፡ በአማላይ ጥበባዊ ምልከታ እያቄሉን ቆምጣጣ እሳቤያቸውን በግድ ሊግቱን በብርቱ ይፈታተኑናል፡፡
ጊዜና ቦታን አሳብሮ ለሰው ዘር የመንፈስ ከፍታ የሚታትረው ፍልስፍናዊ አቋማቸው ከደመነፍስ አፎት በተመዘዘ በካይ ምልከታ ድንገት ከል ይለብሳል፡፡ ኢማኑኤል ካንት፣ዲቪድ ሂዩም፣ሄግልና ሌቪ ብሩህልን በእዚህ ረገድ ተጠቃሽ መሆን የሚችሉ ጠቢባን ናቸው፡፡ ሄግል አፍሪካን ታሪክ አልባ፣እምነት አልባ፣ለዓለም ሥልጣኔ ጠብታ አስተዋጾ ማድረግ ያልቻለች ጨለማ አህጉር ብሎ ይፈርጃታል፡፡ በአንጻሩ ኢማኑኤል ካንት፤የሰው ልጅን አፈጣጠር በእርከን ፣በተዋረድ  እየከፋፈለ፣ ንድፈ-ሐሳባዊ ትንታኔውን ያቀርባል፡፡ አፍሪካዊያን ለሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚመጥን ብቁ ሰብዕናን በእናት ተፈጥሮ አልተቸሩም፡፡ ከእዚህ ይልቅ አካላዊ እንቅስቃሴ ለሚጠይቅ የጉልበት ሥራ በደንብ ከሠለጠኑ ጥሩ አገልጋይ /slaves/ መሆን ይችላሉ፡፡ በእዚህም ረገድ ከአሜሪካ ቀደምት ነዋሪዎች ቀይ ህንዳዊያን ጋር ሲነፃጸሩ የተራመዱ ናቸው ይለናል፡፡
“The race of Negroes, one could say, is completely the opposite of Americans; they are full of affect and passion, very lively, talkative and vain. They can be educated but only servants (slaves), that they allow themselves to be trained. They have motivating forces, are also sensitive, are afraid of blows and do much out of a sense of honor.
ጠቢባኑ በጥቁር ሕዝብ ላይ ያሳዩት ንቀት፣በዘመኑ ከኖረ ከአንድ ተራ አውሮፓዊ አድሃሪ የሚጠበቅ ነበር፡፡ ፈላስፎቹ በአፍሪካዊያን ላይ ያራመዱት የትምክህት አመለካከት ውሎ አድሮ ይዞ የመጣው ዳፋ የከፋ ሆነ፡፡ በእነዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪ ፈላስፎች አማካኝነት በመላው አውሮፓ ሲብላላ የኖረው የዘረኝነት ዕሳቤ ኋላ ላይ አውሮፓዊያን አፍሪካን በቅኝ ግዛት ለመቀራመት ለመካለባቸው አንዱ ተጠቃሽ ምክንያት እንደሆነ ከታሪክ ድርሳናት መረዳት ይቻላል፡፡
ሥልጣኔ ያልገባቸው እጅግ ኋላቀር /savage/ ሕዝቦች መናኽሪያ የሆነችውን አፍሪካን እናቅና በሚል ጭምብል የአህጉሪቷን ሕዝቦች ለዘላቂ ባርነትና ጭቆና ሊዳረጉ ችለዋል፡፡
ይህ የጭቆና ቀምብር መልኩን ቀይሮ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን  በእጅ አዙር ቀኝ ግዛት ስም ቀጠለ፡፡ ከባሪያ ፍንጋላ አንስቶ እስከቆምንበት ዘመን ደረስ የተከሰተውን ታሪካዊ ዳራን ስንፈትሽ፣ በአፍሪካዊያን ላይ የወረደው የመከራ ዶፍ ከየተኛውም የሰው ዘር ጋር ለንጽጽር የሚቀርብ አይሆንም፡፡ ይህን ሁሉ ስቃይ ሲቀበል የኖረ ሕዝብ፣ የውስጡን ረመጥ በአደባባይ ለማሰማት በአገኘው አጋጣሚ ቢያጉረመርም የሚደንቅ አይሆንም፡፡
አፍሪካዊያን በጭቆና ብዛት ገመምተኛ የሆነውን ስሜታቸውን ለማስታመም በውጭም በውስጥም ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ጀምሮ በየፊናቸው እንጉርጉሮ ማሰማት ጀመሩ፡፡
ከትውልድ ቀያቸው በባሪያ ፍንገላ የተፈናቀሉ ጥቁር አፍሪካዊያን ብሉስን፣ጃዝንና ሬጌን እንደ ልሳን በመጠቀም ድፍን የዓለምን ሕዝብ ቀልቡን እንዲያውሳቸው በፍቃዱ ማረኩት፡፡
የተቀሩት የአህጉሪቷ ልሂቃን እንጉርጉሮውን በፍልስፍናዊ ዲስኩር ቀይረውት፣ከጫፍ እስከ ጫፍ በአፍሪካዊ ፍልስፍና ስም ማቀንቀናቸውን ተያያዙት፡፡
ቀዳሚ ተሞክሮ
አፍሪካዊያን ይህንን በምዕራብያዊያን ታላላቅ ጠቢባን የተበጃጀውን የጠለሸ ገጽታ መዋጋት በይፋ የጀመሩት ኢኤ.አ ከ1920 ጀምሮ ነበር፡፡ የጥቁር ሕዝብን እንደ መርግ ተጭኖ የኖረውን የበታችነት ስሜት ማብቂያው መቃረቡን  በውስጥም በውጭም የነበሩት ልሂቃን በልበ ሙሉነት ይዘው በአደባባይ ትግላቸውን አሀዱ ብለው ጀመሩ፡፡ በእዚህም ረገድ ከውጭ ማርክስ ጋርቬዬን፣ ከውስጥ ኩዋሜ ንክሩሃማን መጥቀስ ይቻላል፡፡
አፍሪካዊያን የራሳቸውን ማንነት ከኋላ ታሪካቸው፣ባህላቸውና እምነታቸው ፈትሽው ማግኘት ነበራቸው፡፡ ይህ የተዳፈነ ማንነት እንደ አዲስ ነፍስ መዝራት ሲጀምር ብቻ ነው አውሮፓዊያን ከሚያስወነጭፉት የዘረኝነት ፍላፃ መከላከያ ግምብ መትከል የሚቻለው፡፡
ይህንንም ገቢራዊ ለማድረግ ባህልና እምነት ተኮር የሆነው የፍልስፍና ዘውግ /ethinophilosophy/ በአሁጉሪቷ ልሂቃን ዘንድ እጅግ ተመራጭ ሆነ፡፡ ኢትኖፊሎሶፊ የፍልስፍናን ዓለም አቀፋዊነት በመሻር ለአንድ ሕዝብ ወይም ባህል ብቻ የሚሠራ እውነታ ላይ ማኅለቁን ይጥላል፡፡ የአፍሪካዊያን ባህል፣እምነትና አመለካከት የግድ ባህር እንዲሻገር መጠበቅ አይኖርበትም፡፡ ይህ የምዕራባዊያን መለኪያ ነው፡፡ ለአፍሪካ ብቻ የሚሠራ፣የተሰበረውን የጥቁር ሕዝብ የሚጠግን አዲስ ፍልስፍና እውን መሆን አለበት በሚል እሳቤ አፍሪካዊ ፍልስፍና በአህገሪቱ ልሂቃን ዘንድ በብርቱ መቀንቀኑን ተያያዘው፡፡ ነገሩን ወለፈንዲ የሚያደርገው ቀዳሚው የእዚህ አቋም አራማጅ ፀጉረ ልውጥ የባዕድ ሃገር ሰው መሆኑ ነበር፡፡ ፕላሲድ ቴምፕል የተባለ ፈረንሳዊ የካቶሊክ ቄስ፣ለአፍሪካዊያን የብቻ ማንነት በልክ የተሰፋ ብሎ ያሰበውን ‘የባንቱ ፍልስፍና’ የድርሳን ግርማ አላብሶ ለሕትመት ብርሃን በማብቃት ጎህ ቀደደ፡፡
የተዳፈነውን ማንነት ፍለጋ
በማንነት ቀውስ ግራ ቀኝ መላጋት ለአንድ አፍሪካዊ ብርቁ አይደለም፡፡ በእውነተኛው አፍሪካዊ ማንነቱና በተውሶ ማንነቱ መካከል የማያቋርጥ ቁርቋሶ መኖሩ ግድ ነው፡፡ ታዋቂው ሴኔጋላዊ ባለቅኔ ሴዳር ሴንጎር፤“እንደ ሽል የሚገላበጠው እውነተኛው አፍሪካዊ ማንነት ለመወለድ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች አኑረውት የሄዱት የአካልና የመንፈስ እግር ሙቅ እንክትክት ብሎ መሰባበር ይኖርበታል፡፡” ሲል አስረግጦ ተናግሯል፡፡  
The equilibrium you admire in me is an unstable one, difficult to maintain. My inner life was split early between the call of the Ancestors and the call of Europe, between the exigencies of black-African culture and those of modern life.
ሴንጎር የቃተተው በጥቁር አፍሪካዊ ሕዝብ ስም ነው፡፡ የውስጡን ቅራኔ ለመፍታት በጥበብ መንገድ ላይ ያለ ፋታ በመመላለስ ዕድሜ ዘመኑን የባተተ አፍሪካዊ ልኂቅ ነበር፡፡ ቅኔን የሰነቁ ጥልቅ ስንኞችን እየደረደረ፣ያሸለበውን አፍሪካዊ ማንነት በኪነጥበቡ ዘርፍ ለማንቃት በብርቱ ታትሯል፡፡ የሴንጎር “ኔግርቲዩድ” ጽንሰ ሐሳብ፤ከፍልስፍናዊ ትንተና ይልቅ አፍሪካዊ አርበኝነት ያረበበት ነው፡፡ “እኛ ጥቁሮች በነጭ ዓይን ሚዛን እየተሰፈረልን የምናዘግም ምስኪን ፍጥሮች መሆን የለብንም፡፡ ተፈጥሮን በፍቅር እንጂ እንደ አውሮፓውያን በኃይል መውረር ወግም፣ልማዳችንም ሆኖ አያውቅም“ ይላል ሴንጎር፤አፍሪካዊ ማንነትን ከአውሮፓዊያን ማንነት ጋር ያለውን ልዩነት ጉልህ አድርጎ ለማሳየት ሲሞክር፡፡
ታሪክን አሰሳ
ቀዳሚ የአፍሪካ ፍልስፍና አራማጆች በአፍሪካ ስም ታሪክን ለመቀለስ “አፍሮሴንትሪዝም” የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ ነበር የሙጥኝ  ያሉት፡፡ የእዚህ ጽንሰ ሐሳብ ዋንኛ አትኩሮትአፍሪካን በጥንታዊ የግብጽ ሥልጣኔ ሥር ማሰባሰብ ነው፡፡ ግብጻዊያን ከአውሮፓ ይልቅ ከሰሐራ በታች ካሉ ጥቁር ሕዝቦች ጋር የጠበቀ ቁርኝት ነበራቸው፡፡ በእዚህም ምክንያት የግብጽ ሥልጣኔ ላይ የአፍሪካዊያን አሻራ በጉልህ አርፏል፡፡ ግብጻዊያን ደግሞ መላው አውሮፓ ላይ ሳይንስና ቴክኖሎጂ በስፋት እንዲጎመራ ምክንያት ለሆነው የግሪክ ሥልጠኔ እርሾ ናቸው፤ይላሉ የእዚህ ፍልስፍና ዘውግ አራማጆች፡፡
ይህንን መሰሉ አመክንዮ ግን ብዙም መራመድ አልቻለም፡፡ በግብጽና በተቀረው የአፍሪካ ሕዝብ መካከል የብረት መጋረጃ እንደነበረ የታሪክ ተመራማሪዎች በተጨባጭ መረጃ ያስረዳሉ፡፡ ከእዚህም በተጨማሪ የግብጾችና የግሪኮች ሥልጣኔ ለየቅል የሚያደርጋቸው በርካታ እውነታዎች አሉ፡፡ የግብጻዊያን ኪነሕንጻ ላይ ያተኮረ ሲሆን በአንጻሩ ግሪካዊያን ደግሞ በአምክንዮ ማበብ የተቀለሰ ሥልጣኔ ነው፡፡ኢትዮጵያን ያንጓለለ ፍልስፍናዊ አቋም የአፍሪካ ፍልስፍና ከፍልስፍና ይልቅ በርዕዮተ ዓለማዊ ዘይቤ የታሸ ብሔርተኝነት ያይልበታል፡፡ ይህም ሆኖ በእስካሁን ሒደት ውስጥ የአፍሪካዊያንንም ሆነ የሌሎች ዓለማትን ሕዝቦች ልብ የታሰበውን ያህል መግዛት እንደተሳነው ጥቂት አስርተ አመታት አስቆጥሯል፡፡ ለእዚህም እንደ ምክንያት የሚቀመጠው አንድም የተከተለው አቅጣጫ ውሉን መሳቱ ሲሆኑ ሌላው ደግሞ የልሂቃኑ “ፍልስፍናዊ” ማጠንጠኛ በምዕራብዊያን  ሲሰነዘር የኖረውን አድሎአዊ አመለካከት /Prejudice/ መመከት ላይ ብቻ ማተኮሩ ነው፡፡ በእዚህም የተነሳ በአፍሪካ ፍልስፍና ላይ የተሰማሩ ልሂቃን እርስ በእርስ በቡድንተኝነት ስሜት ጫና ውስጥ ሊወድቁ ችለዋል፡፡ ከፊሉ በአህጉሪቱ ጥላ ሥር የሚቀለስ ፍልስፍናዊ አቋም መኖር የለበትም ብሎ ሲሞግት፣ የተቀረው ቡድን ደግሞ ጥቆር የቆዳ ቀለምን እንደ ማዕከላዊ ሰብዕና በመውሰድ በፍልስፍና ሥም አፍሪካዊ ብሔርተኝነትን ይሰብካል፡፡
አብዛኛው የአፍሪካ ፍልስፍና አራማጆች የፈሩት ከምዕራብ አፍሪካ በመሆናቸው የተነሳ የአህጉሪቱን ነባራዊ እውነታ ከበቀሉበት አካባቢ አንጻር ብቻ በመተንተን ማቅረብ ወደ አንድ ጎን ይለጥቱታል፡፡ አህጉሪቷ ላይ በአንድ ወቅት በቅለው የከሰሙ ጥንታዊ ሥልጣኔዎች በተፈለገው ረገድ ተፈትሽው ገሃድ መውጣት አልቻሉም፡፡ በተለይ ለጥንታዊቷ አቢሲነያ /ኢትዮጵያ/ የተሰጠው ድርሻ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የአክሱም ሀውልትን ተመልከተን ወደ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን ፊታችንን ስንመልስ፣ አንደ ከበስተጀርባው አድብተን የምንይዘው ፍሬ ነገር ይኖራል፡፡ ይህም ጥንታዊ ጥቁር የሐበሻ ሕዝብ የሚገዛበት የአምክኖዋዊ ሥርዓት ከምዕራባዊያን ጋር በአንድም ሆነ በሌላ የሚዛመድበት ወሽመጥ መኖሩ ነው፡፡ ኪነ ሕንጻ ያለ ጥልቅ ዕሳቤ፣ፍልስፍና ለፍሬ ሊበቃ አይችልም፡፡ የኢትዮጵያዊን የመንፈሳዊ፣ባህላዊ ሥርዓትና የእሴት ሽግግር ከሠለጠኑት ዓላማት ጋር ኩታ-ገጠመኑት እንደሚያይል ይገመታል፡፡
በኢትዮጵያ ምድር ላይ ፈክተው የነበሩት የሥልጣኔ አሻራዎች በተገቢው ረገድ  ቢበረበሩ ተመዝዘው የማያልቁ ቱባ ፍልስፍናዊ እውነታዎችን ለመቃረም እንደማንቸገር እሙን ነው፡፡ አፍሪካዊ ፍልስፍና መነሻው የተሰበረ ልብን በመጠገን ቀና ብሎ በኩራት ለመሄድ የሚደረግ ስነልቦናዊ የመውተርተር ውጤት ነው፡፡ ለእዚህ ዓላማ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ቀለማት ያላቸው ጥንታዊ የጥቁር ሕዝቦች ታሪክና ሥልጣኔ ኹነኛ ድጋፍ መሆን እንደሚችሉ ለመገመት ሊቅ መሆንን አይጠይቅም፡፡ “አፍሪካዊያን ከአፈ-ታሪክ የዘለለ በጽሑፍ የተላለፈ የዳበረ የፍልስፍና ባህል የላቸውም; በሚል የሚሟገቱትን አውሮፓዊያን አፍ ለማዘጋት የታዋቂውን ኢትዮጵያዊ ፈላስፋ ዘርያቆብን ፍልስፍና እንዲሁም በብራና ላይ በግዕዝ ቋንቋ የሠፈሩ የምርምር ውጤቶችን ዋቢ ማድረግ ቢቻል የተዛባውን አመለካከት በተጨባጭ መረጃ ለማምከን ያግዝ ነበር፡፡ አፍሪካዊ ፍልስፍና  የትኩረት አቅጣጫው ላይ ክለሳ ማድረግ ካልተቻለ፣ ዋግ እንደመታው አዝመራ እንደተንጨፈረረና ፍሬ ማፍራት እንደተሳነው ዘመናትን እንደሚሻገር ከወዲሁ ለመገመት አያዳግትም፡፡

Read 1618 times