Monday, 30 May 2016 09:24

አንጀሊና ጆሊ በታዋቂው ዩኒቨርሲቲ ታስተምራለች

Written by 
Rate this item
(3 votes)

     የኦስካር ተሸላሚዋ የፊልም ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ በታዋቂው የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ በቀጣዩ አመት በሚጀመረው የሁለተኛ ዲግሪ ፕሮግራም የሴቶች፣ የሰላምና የደህንነት ኮርስ ተጋባዥ መምህርት ሆና ለማስተማር መመረጧን ዩኒቨርሲቲው አስታወቀ፡፡የፊልም ተዋናይቷ ከታዋቂዎቹ የእንግሊዝ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ በሆነው የለንደን ስኩል ኦፍ ኢኮኖሚክስ ከሴቶች፣ ከሰላም፣ ከደህንነት፣ ከሰብዓዊ መብቶችና ከጾታ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን ከማስተማር በተጨማሪ፣ በተለያዩ ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ንግግር እንደምታደርግ፣በአውደጥናቶችና በህዝባዊ ዝግጅቶች ላይም እንደምትሳተፍ ታውቋል፡፡
 “ተማሪዎችን ለማስተማርና ከእነሱም ለመማር ጓጉቻለሁ” ያለቺው አንጀሊና ጆሊ፣ከተማሪዎቿ ጋር ልምዶችን እንደምትለዋወጥና በጉዳዩ ዙሪያ ከተለያዩ የአለማችን አገራት መንግስታትና ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በትብብር እንደምትሰራም ገልጻለች፡፡
አንጀሊና ጆሊ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስደተኞች ተቋም የበጎ ምግባር አምባሳደርና ልዩ መልዕክተኛ ከመሆኗ በተጨማሪ በአለማቀፍ ደረጃ በሚከናወኑ የሴቶች የመብት ጥሰቶች፣ ጾታዊ ጥቃቶች፣ የህጻናት ደህንነት እንክብካቤዎችና በሌሎች የበጎ ምግባር እንቅስቃሴዎች ላይ በመሳተፍ ትታወቃለች፡፡

Read 1400 times