Saturday, 28 May 2016 15:32

መሆን ያለበትና እየሆነ ያለው

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

     በግል ህይወትም ይሁን በድርጅታዊ አሰራርና ዕድገት ውስጥ መሆን ያለበትና እየሆነ ያለው ለየቅል ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ ክስተት ደግሞ ብዙ ግዜ የሚያጋጥም ጉዳይ ነው፡፡ በርካታ ባለድርሻ አካላት ባሉባቸው ሰፊ ሃገራዊ ጉዳዮች ላይ ክፍተቱ ገዝፎ እንመለከታለን፡፡ እንደ ግለሰብ አንድ ሰው፣በህይወቱ ውስጥ መሆን ባለበትና እየሆነ ባለው ኩነት መካከል ሰፊ ልዩነት ሲኖረው፣ ወደ መፍትሔ የሚወስደው ተጨባጭ ርምጃ፣መጀመሪያ አሁን ያለበትን ሁኔታ በደንብ መረዳት፣ ቀጥሎም ምን መሆን እንዳለበት በግልፅ በማስቀመጥ ወደዛ የሚያደርሱትን መንገዶችና ስራዎች ብሎም በአጠገቡ ያሉ ሊያግዙት የሚችሉ አካላትን መለየት ይሆናል፡፡ አብዛኛው ሰው በየትኛውም አለም ይኑር ተመሳሳይ ሂደት ሲከተልም እናያለን፡፡ ይህ የለውጥ ሂደት ከግለሰብ ጀምሮ ለድርጅት፣ ለአገር ብሎም ለአለም የሚሰራ ነው፡፡ ለውጥ ለማምጣት ሙሉ ሂደቱን መጓዝ አለብን ፤ ግማሽ መንገድ ተጉዞ ሙሉ ውጤት ማምጣት አይቻልምና፡፡ ችግሩ በበርካታ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶች በአብዛኛዉ ባሉ ሁኔታዎች ላይ ብቻ በማተኮር መሆን ያለበትን ማስቀመጥ አለመቻላቸዉ ነዉ፡፡ ስለሆነም ቀጣዩና የሚፈለገዉ ሂደት መምጣት አለበት ፤ ውይይቶች ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገር አለባቸው፡፡ለምሳሌ ባለን የመገናኛ ብዙሀን ደስተኛ ካልሆንን ምን አይነት የመገናኛ ብዙሀን እንፈልጋለን? ያን የምንጓጓለትን የመገናኛ ብዙሃን ዕዉን ለማድረግስ ምን መስራት ይጠበቅብናል ብለን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ በተመሳሳይ በአገራችን ያለው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ዘርፍም የዚህ የውይይቶች ግማሽ መንገድ ላይ መቆም ችግር ማሳያ ነው፡፡ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት፣ ደጋፊ አካላት፣ የመገናኛ ብዙሀን፣ ምሁራን፣ የንግዱ ማህበረሰብ
ብሎም መላው ህብረተሰብ፣ በአገራችን ባለው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ዘርፍ (ሲቪክ
ማህበራት) ደስተኛ እንዳልሆኑ ይገልፃሉ፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅት አሰራር ከፅንሰ ሀሳቡ አንፃር መሆን ያለበትና እየሆነ ያለው ይለያያል የሚል አስተያየት ከብዙ አቅጣጫ ይደመጣል፡፡ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በኩል ደግሞ መንግስትና የመገናኛ ብዙሀን ለስራችን ተገቢውን እውቅና አይሰጡም በማለት ይወቅሳሉ፡፡ እነዚህ አስተያየቶች ከፊል እውነታ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ዋናው እውነታ ግን ውይይቱ ግማሽ ሂደት ላይ መቆሙ ነው፡፡ ይህ ማለት ከላይ የተዘረዘሩት ሁሉም አካላት በአገራችን ባለው የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ደስተኛ ካልሆኑ ቀጥሎ መምጣት ያለበት እና መሆን ያለበት ምንድነው? ምን አይነት የበጎ አድራጎት ድርጀቶችና ማህበራት ዘርፍ መፍጠር እንፈልጋለን? ምን መደረግስ አለበት? ከማን ምን ይጠበቃል? ወደሚል ሰፊ የውይይትና የመፍትሔ ደረጃ ማደግ ይኖርበታል፡፡ የአመለካከት ችግሩ የሚጀምረው የዘርፉን ሚና አሳንሶ ከማየት ነው፡፡ ይህ ክፍተት ሚናቸውን ከሚያመጡት ገንዘብ መጠን ጋር በዋናነት በሚያያይዙት የበጎ አድርጎት ድርጅቶችና ማህበራት ይጀምራል፡፡ መንግስት በበኩሉ ደግሞ ከዕለት ምጽዋት ጋር በሚመሳሰል መልኩ በጎ የማድረግ ስራ ብቻ አላቸው ብሎ ያስባል፡፡ ይህ የመንግስት አመለካከትም የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት
ወሳኝ የልማት አጋር ናቸዉ ከሚለዉ ብሂል ጋር ይጋጫል፡፡ ይህ ፅሁፍም እየሆነ ባለው ላይ ያተኮረ
ስላልሆነ ወደ ቀጣይና  የተሻለ ደረጃ እንዴት እንሸጋገር የሚለዉ ላይ ገንቢ ትንተና ያደርጋል፡፡
በእርግጥ ይህ ፅሁፍ ምን መሆን እንዳለበት በቀጥታ የማስቀመጥ አላማም ሆነ አቅም የለውም፡፡
የዚህ ፅሁፍ አላማ ውይይቶችን ማሻሻል ነው፤እየሆነ ባለው ላይ ከመወቃቀሰ ይልቅ መሆን
ወዳለበት እንድንመለከት ጥያቄውን ማንሳት ነው፡፡
መንግስት ምን አይነት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ዘርፍ ነው መፍጠር የሚፈልገዉ?
ሁላችንንም የሚያስደስተንና እንደ አገር የምንኮራበት ዘርፍ ለመፍጠር መንግስት ምን ለማድረግ
አቅዷል? እንደመፍትሄ ሃሳብም ዘርፍ መሻሻልና ማደግ ካለበት መሪ ይፈልጋል፤ስለዚህ መንግስት
ሴክተሩን የመምራትና የማገዝ ሃገራዊ ግዴታ አለበት፡፡ ይህ ማለት የዘርፉ ነፃነት እንደተጠበቀ ሆኖ፣
መንግስት የመንግስት ሚናውን በመወጣት ለዘርፉ የተሻለ የስራ ማዕቀፍ በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ
ድጋፍ ማድረግ አለበት ማለት ነው፡፡
የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ሀላፊዎች በበኩላቸዉ፤በጎ የማድረግ ፅንሰ ሀሳብንና አሁን
በተግባር እየሆነ ያለውን ማነጻጸርና ራስን መገምገም፣ ከዚህ አልፎም መሆን ወዳለበት አቅጣጫ
መምጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ማህበረሰባችን አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ዕይታዎችን
የሚያንጻባርቀዉ፣ከሚያየዉና ከሚሰማዉ በመነሳት ነዉ፡፡ ስለሆነም አሉታዊ አመለካከት ቢኖር
ሁልጊዜ ስህተት ነዉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ መስራት ማለት ጥሩ
ደሞዝ ከማግኘት የዘለለ ትርጉም እንዳለው በአሰራራቸንና አኗኗራችን ማሳየት አለብን፡፡ ዋናው
ጉዳይ የሚኮረኩረን ፣የማያስተኛንና የተነሳንበት ዓላማ ህዝብን የመደገፍና የመርዳት ብሎም
የመንግስትና የህዝብ ወሳኝ የልማት አጋር መሆናችንን ማስረገጥ ላይ ነዉ፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅት ሀላፊ፤በህብረተሰቡ በበጎ ስራው እና ተግባሩ የሚከበር መሆን ያለበት ሲሆን አሁን ያለው አመለካከት ግን ሙሉ በሙሉ ከዚህ ጋር አብሮ ይሄዳል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ይህ ማለት ግን ማህበረሰባችን በሙሉ ተመሳሳይና ለሴክተሩ የተዛባ አመለካከት አለዉ ማለት አይደለም፡፡ መልካም የሚሰሩ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸዉ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት እንዳሉ ሁሉ፣ በአግባቡ የማይሰሩ የሴክተሩን ስም ጥላሸት የሚቀቡ በጣም ጥቂት ድርጅቶች እንዳሉም ይታመናል፡፡ይህን ጉዳይ ከስር መሰረቱ ስንመረምረው፣ማየት ያለብን በአገራችን መፍጠር የምንፈልገውን ዘርፍ አሁን ካለበት ደረጃ ጋር በማነፃፀርና የህዝባችንን አኗኗር፣ ባህልና ወግ ግምት ዉስጥ በማስገባት እንጂ በቀጥታ ከሌላ አገር ጋር በማነፃፀር መሆን የለበትም የሚል ዕምነት አለን፡፡ ይህ ማለት ግን ጠቃሚ ተሞክሮዎች ከዉጭ አይወሰዱም ማለት አይደለም፡፡ በማንኛዉም ሰአትና
ጊዜ አገራችንን እና ህዝባችንን የበለጠ ተጠቃሚ ሊያደርግ የሚችል የአሰራር ስርአት ቢኖር ልምድ
መወሰዱ በበጎ ጎን የሚታይ ነዉ፡፡  የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ከተለመደው የበጎ አድራጎት ስራ በዘለለ በአገራችን ሁለንተናዊ ዕድገት ውስጥ ብዙ ሚና መጫወት ይችላሉ፤አለባቸውም፡፡ የሙያ ማህበራት የአንድን ሙያ ጥራት ከመጠበቅ እና ከማሳደግ አንፃር ትልቅ ስራ መስራት ይችላሉ፡፡ የተለያዩ አገር አቀፍ ህጎችና ፖሊሲዎች ሲወጡ ከሙያቸው ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ዙርያ ጠቀሚ ግብአቶች መስጠት ይችላሉ፡፡ የተለያዩ ሀገራዊ እና ህዝባዊ የለውጥ ንቅናቄዎች ለማምጣት ሰንፈልግ የብዙሀን ማህበራት ንቅናቄውን መምራትና ማቀጣጠል ይችላሉ፤ ሌላም ሌላም፡፡  መንግስት አንድን አገር ሲመራ ሁሉንም ዘርፍ በእኩል መምራት ይጠበቅበታል፡፡ ይሄም በወሳኝ መልኩ ተቀራርቦ መስራትን ይጠይቃል፡፡ በዋናነት የአሰራር አቅጣጫ ከሚያስቀምጠው ከፍተኛው አመራር ማለትም፤ ከጠቅላይ ሚኒስትራችን ምን አይነት የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት መፍጠር እንደሚፈልጉና ምን ምን እንዳቀዱ ማወቅ እንሻለን፤ይህ የሚሆንበት አሰራር መፈጠር አለበት፡፡ ከሙያ ማህበራት ጋር በተያያዘ የተለያዩ የሙያ ማህበራት እንዳሉ በራሱ ግንዛቤ የለም፡፡ ለምሳሌ
የጋዜጠኞች ማህበር፣ የሙዚቀኞች ማህበር፣ የሰአሊያንና ቀራፅያን ፣ የፊልም ሰሪዎች፣ የደራስያን
ወዘተ እያለ ይቀጥላል፡፡ ዘርፉ ይህን ሁሉ ይዞ ነው ሚናውን አሳንሰን እያየን ያለነው፡፡ ለእነኚህ
አካለትም የተመቻቸ የአሰራር ስርአት መፍጠር፤ ስራዎቻቸዉን ማየትና መገምገም፣ ለአሰራር
የማያመቹ ሁኔታዎችን በጋራ መለየትና መፍትሄ ማበጀት ሌላዉ የመንግስት ወሳኝ የስራ ሃላፊነት
ነዉ ተብሎ ይታመናል፡፡ ከዚህ ባለፈ በአገራችን የሚገኙ ደጋፊ አካላትም አሁን ባለው ዘርፍ ብዙም ደስተኛ አለመሆናቸውን ሲገልፁ ይደመጣል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት በኩል የደጋፊ አካላት የአሰራር ስርአቶች በተለይም ለሃገር በቀል ድርጅቶች የማያመቹና ይልቁንም ዉስብስብ መሆናቸዉ ይገለጻል፡፡ ይህም “እንዳያማህ ጥራዉ፣እንዳይበላ ግፋዉ” የሚለዉን የአባቶች ብሂል ያስታዉሰናል፡፡ ስለሆነም
ደጋፊ አካላት የሚያደርጉት እገዛ፣ የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንዲችል ከታመነ በተለይም አገር በቀል
ድርጅቶች ያላቸዉን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ግምት ዉስጥ በማስገባት ለህዝብ እጅግ የቀረቡ
በመሆናቸዉ ይህንኑ መጠቀም መቻል ብልህነት ነዉ፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት:
መንግስትና የንግዱ ማህበረሰብ በጋራ የምንጋራው ዓላማና ራዕይ ይዘን ነገር ግን የተለያየ ሀላፊነት
ያለብን ባለ ድርሻ አካላት እንጂ ለብቻችን ተነጥለን የምንሰራው ስራ እንደሌለ በመገንዘብ፣ ተቀራርቦ ወደ መስራት በመምጣት ጠንካራ ዘርፍ መፍጠር እንደምንችል እናምናለን፡፡ የበጎ አድራጊነት ፅንሰ ሀሳብና አሁን የምንንቀሳቀስበትን ማዕቀፍ በመፈተሸ፣ ከፅንስ ሀሳቡ ጋር የሚሄድ አሰራርና እንቅስቃሴ መፍጠር መቻል አለብን፡፡ እነዚህንና በተጨማሪም እናንተ አንባብያን ባለድርሻ አካላት ምትጨምሩዋቸው ሀሳቦችን አንድላይ በማምጣት አሁን ካለን ደካማ የሆነ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ዘርፍ ወደምንፈልገው እና መሆን ወዳለበት መውሰድ እንደምንችል ጠንካራ እምነት አለን፡፡ ይሄም የሚጀምረው ጉዳዩን ወደ ጋራ ውይይት በማምጣት ሲሆን ፤ ሂደቱን  ሀ ብለን ይሄው ዛሬ በዚህ ፅሁፍ ጀምረነዋል፡፡











Read 1798 times