Saturday, 28 May 2016 15:28

ቴሌቪዥን፣ልጆችና የወላጆች ኃላፊነት!

Written by  አስናቀ ሥነስብሐት
Rate this item
(1 Vote)

     ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በብዛት ከምንሰማቸው ጉዳዮች መካከል  አንደኛው ”ፊልም፣ ቴሌቪዥንና  ሕጻናት”  ነው፡፡ የዚህ ጉዳይ ዋነኛ መነሻ በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ፕሮግራሞችና ፊልሞች በሕጻናትና ታዳጊዎች ላይ የሚያሳድሩት ተጽዕኖ ይመስለኛል፡፡ በተደራጀ መልኩ ባይሆንም፣ ይህ ጉዳይ በአገራችንም የመወያያ ርዕስ ሆኗል፡፡ውይይቱ መጀመሩ መልካም ነው፣ ሆኖም የውይይቱ ተሳታፊዎች ብዙውን ጊዜ ሲያነሱት
የማልሰማው አንድ ጉዳይ ቢኖር የወላጅ/አሳዳጊ ኃላፊነት ነው፡፡ ወላጆችና አሳዳጊዎች ልጆቻቸው ስለሚመለከቷቸው የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ምን ያህል ያውቃሉ?  የሚመለከቱትን ፕሮግራም እንዴት መቆጣጠር ይችላሉ? ለእነዚህና መሰል ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት የተደረገ ሙከራ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም አላገኘሁም፤ወላጆች ልጆቻቸው ቴሌቪዥንን ጨምሮ ከቴክኖሎጂ መሣሪያዎች ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዴት ጤናማ ማድረግ እንደሚችሉ ምክር ከሰጠ አንድ የልጆች አስተዳደግ መጽሐፍ በስተቀር፡፡”ቴሌቪዥን፣ ልጆችና የወላጅ ኃላፊነት” የሚለውን ርዕሰ-ጉዳይ በጥልቀት መመልከት ጀመርኩት ከአሥራ ሦስት ዓመታት በፊት ነው፡፡ የዛሬ አሥራ ስድስት ዓመት ገደማ በያኔው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አማካይነት በአገር ውስጥ ይተላለፍ የነበረውን ”ቲቪ አፍሪካ” የተባለ ቻናል ታስታውሱታላችሁ? በወቅቱ ይህ ቻናል ለብዙ ተመልካቾች የመረጃና የመዝናኛ አማራጭ ሆኖ በመቅረቡ ተወዳጅነትን ለማትረፍ ጊዜ አልፈጀበትም፡፡ የተወዳጅነቱን ያህል ባይሆንም፣ ትችቶችንም አስተናግዷል፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባል ሰዎች ”ቲቪ አፍሪካ ልጆቻችንን እያበላሸ ነው” በማለት በተደጋጋሚ ሲወቅሱት ይሰማ ነበር- በጊዜው፡፡
ከእነዚህ ትችቶች መካከል ይበልጥ ትኩረቴን የሳበውንና ስለ ወላጅ ኃላፊነት እንዳስብ ያደረገኝን ሐሳብ የሰማሁት በ1995 ዓ.ም. ነበር፡፡ በወቅቱ አንድ ዕውቅ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር በአንድ ስብሰባ ላይ የትውልዱን ሥነ-ምግባር አስመልክተው  ሲናገሩ፤ ”እኔ እኮ ዛሬ ልጆቼን አላሳድግም፣ ልጆቼን የሚያሳድግልኝ ቲቪ አፍሪካ ነው” ብለው ነበር፡፡ ይህ አባባል የስብሰባውን ተሳታፊዎችና ያዳመጥነውን ሁሉ ፈገግ አሰኝቶን ነበር፣ ንግግራቸው ግን ቀደም ሲል በቻናሉ ላይ
ሲሰነዘሩ ከሰማኋቸው ቅሬታዎች ጋር ተዳምሮ ጥያቄ ፈጠረብኝ፡፡ ”የቴሌቪዥናቸውን አንቴናና
የቻናሉን ፍሪኩዌንሲ አስተካክለው ቤታቸው ያስገቡት ራሳቸው ወላጆች ሆነው ሳለ፣ ቻናሉን ለምን
ይተቻሉ? ስለሚተላለፉት ፕሮግራሞች የሚሰጠውን ማሳሰቢያስ ለምን አይከታተሉም?” ብዬም
ጠየቅሁ፡፡ ”ከቻናሉ የጎደለ ነገር ካለ” በማለትም የፕሮግራሞቹን ይዘትና የስርጭት መርሐ-ግብር
ለማወቅ የቲቪ አፍሪካን ድረ-ገጽ ጎበኘሁ፡፡  በኢቲቪ-2  የሚተላለፈው የቲቪ አፍሪካ ስርጭት
ከቀኑ 11 ሰዓት እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ የሚዘልቅ ቢሆንም፣ ቲቪ አፍሪካ ግን ለ24 ሰዓታት
የተለያዩ ፕሮግራሞችን (ዜና፣ ድራማ፣ ሶፕ ኦፔራ፣ ፊልም፣ ሙዚቃ፣…) የሚያቀርብ ነጻ ቻናል
መሆኑን ከድረ-ገጹ ላይ ለመረዳት ቻልኩ፡፡ በድረ-ገጹ ላይ የተቀመጠው የፕሮግራሞች ዝርዝር
የእያንዳንዱን ፕሮግራም ዓይነትና ይዘት፣ እንዲሁም የተመልካቾች የዕድሜ ገደብ የሚገልጽ አጭር
መግለጫ የያዘ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የፕሮግራሞች የዕድሜ ገደብ መግለጫ፣  በተለይ ፊልሞችና ድራማዎች በቴሌቪዥን
መቅረብ ከመጀመራቸው በፊት፣ በግልጽ ቋንቋ ለተመልካቾች ይነገር ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ ነው
እንግዲህ የወላጆችን ኃላፊነት አስመልክቶ ማሰብ የጀመርኩት፡፡ የቴሌቪዥን ቻናሉ ”የማስተላልፈው ፕሮግራም ከዚህ ዕድሜ በላይ ላሉ ተመልካቾች የሚሆን ነው” ብሎ ካሳወቀ፣
ቀሪው ኃላፊነት የወላጅ፣ የቤተሰብ፣ የአሳዳጊ ወይም የሞግዚት ነው፡፡ ይህንን ማድረግ የማይችሉ
ወላጅና ቤተሰቦች፣ ቻናሉን ጥፋተኛ አድርገው ለመውቀስ የሚያስችላቸው ምንም ዓይነት ምክንያት
አለ ብዬ አላምንም፡፡ ሥራቸውን አልሰሩማ!        ”ታሪክ ራሱን ይደግማል” ሆነና፣ ዘንድሮ
ይህንኑ ዓይነት ክስተት በ”ቃና” ቲቪ ዙሪያ እያየን ነው፡፡ ይኼኛውን ለየት የሚያደርገው፣ ”ቲቪ አፍሪካ” በብሔራዊው ቴሌቪዥን በአንቴና የሚመጣ ሲሆን
”ቃና” ግን በሳተላይት የሚሠራጭ መሆኑ ነው፡፡ ምናልባትም፣ በ ”ቲቪ አፍሪካ”  ላይ ይነሳ
የነበረው ትችት በግለሰቦች ብቻ የሚቀርብና የተበታተነ ሲሆን  ”ቃና”ን የሚተቹት ወገኖች ግን
ኮሚቴ አዋቅረው የሚንቀሳቀሱ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራት መሆናቸው ሌላ ልዩነት ሊሆን
ይችላል፡፡ በሁለቱም ክስተቶች ውስጥ ብቸኛ ተወቃሽ ሆነው የቀረቡት ሚዲያዎቹ ናቸው፤ ለሚዲያዎቹ
በራቸውን ወለል አድርገው የከፈቱት ቤተሰቦች/ወላጆች ግን በዝምታ ታልፈዋል፡፡በዚህ ርዕስ
በተከታታይ በሚቀርበው ጽሑፍ፣ የቴሌቪዥንን አዎንታዊና አሉታዊ ተጽዕኖዎች በመለየት ወላጆች
በልጆቻቸውና በቴሌቪዥን መካከል ጤናማ ግንኙነትን ለመፍጠር ምን ሊያደርጉ እንደሚገባ
ሳይንሳዊ ጥናቶች የሚሉትን እንመለከታለን፡፡ በተጨማሪም ከቴሌቪዥን ጋር በተገናኘ የአገራችንን ወላጆች የእስካሁን ተመክሮን (track record) በመቃኘት፣ በልጆች የቴሌቪዥን ዕይታ ላይ ተገቢ የሆነ ቁጥጥር ለማድረግ ያስችላሉ
የምላቸውን ጥቆማዎች ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡(ማስታወሻ፡-  ይህ ተከታታይ ጽሑፍ ባለፈው ዓመት “The Way I See It …” በተሰኘው የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ጦማር (blog) ላይ ቀርቦ የነበረ ሲሆን፣ የአሁኑ ጽሑፍ ወቅታዊውን የአገራችን ቴሌቪዥን-ነክ ርዕሰ-ጉዳይ መነሻ በማድረግ ተጨማሪ ሐሳቦችን አካቶና ተሻሽሎ የቀረበ ነው፡፡ ቀዳሚዎቹን ተከታታይ ጽሑፎች በድረ-ገጽ አድራሻ asnakesinesibhat.blogspot.com ላይ
ማንበብ ይቻላል፡፡)

Read 1983 times