Saturday, 21 May 2016 16:02

የግንቦት 20 ስኬቶችና ጉድለቶች በፖለቲከኞች ተገምግሟል

Written by 
Rate this item
(14 votes)

የዘንድሮ የግንቦት 20፣ ሃያ አምስተኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዮ በአል - ባለፉት ዓመታት የተገኙ ስኬቶችንና ፈተናዎችን በመገምገም እንደሚከበር መንግስት የገለፀ ሲሆን አዲስ አድማስ ያነጋገራቸው ፖለቲከኞች የግንቦት 20ን ትሩፋቶች በመተቸትና በማወደስ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡
የቀድሞ የፓርላማ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ በሰጡት አስተያየት፤ በ1983 ዓ.ም ለውጡ ሲመጣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የተሳተፉበት አመራር ተፈጥሮ፤ ሀገሪቱ ለውጥ ታመጣለች የሚል ተስፋ ሰንቀው እንደነበር ጠቁመውና ዛሬ ላይ ሆነው ያለፈውን 25 አመት ሲገመግሙት ግን ያንን ተስፋቸውን በተግባር እንዳላዩት ይናገራሉ፡፡ የአንድ መንግስት ስኬታማነት በመሠረተ ልማትና በኢኮኖሚ እድገት ብቻ አይመዘንም ያሉት አቶ ግርማ፤ ዋናው ስኬት የሰው ልጅ ሠብአዊ መብትና ነፃነት ሲከበር ነው ብለዋል፡፡ የኢኮኖሚው እድገትም ቢሆን ከሀገሪቱ ህዝብ 20 ሚሊዮን ያህሉን ከእለት ተረጅነት አላወጣም ሲሉ ተችተዋል- አቶ ግርማ፡፡
“ባለፉት 25 ዓመታት ቃልና ተግባር አልተገናኙም” ያሉት ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፤ የግንቦተ 20 ትልቁ ትርፍ የደርግ መንግስት መወገዱ ነው ብለዋል፡፡ የመንግስት ለውጡ በሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አንድምታዎች ላይ ለውጥ ያመጣል የሚል ተስፋ እንደነበራቸው የጠቆሙት ዶ/ር መረራ፤ ሆኖም ባለፉት 25 አመታት ይህ እንዳልተሳካ አስረድተዋል፡፡
“ግንቦት 20 በኢኮኖሚ እድገት መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል” ያሉት አቶ ልደቱ አያሌው፤ በዚያው ልክ የሀገሪቱን አንድነት እስከዛሬ ድረስ ጥያቄ ውስጥ ከማስገባቱም በተጨማሪ ሀገሪቱን ወደብ አልባ ያደረገ ነው ብለዋል፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት የአንድ ፓርቲ የስልጣን የበላይነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረና ነፃ ሚዲያዎች እየደበዘዙ መምጣታቸውንም አቶ ልደቱ ተችተው ተናግረዋል፡፡ የኢህአዴግ የቀድሞው ታጋይና አመራር የሆኑት አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው በበኩላቸው፤ በ25 አመታት ውስጥ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊውና በፖለቲካዊው ዘርፍ በርካታ ድሎችና ስኬቶች መመዝገባቸውን ጠቅሰው በአሁን ወቅት ዋነኛ አደጋ የሆነውን የኪራይ ሰብሳቢነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታትም መንግስት በጠንካራ ትግል ላይ ነው ብለዋል፡፡   “ግንቦት 20 የመንግስት ሣይሆን የስርአት ለውጥ ነው ያመጣው” ያሉት የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሃላፊ ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፤  ስርአቱ እየተከተለ ያለው መሠረታዊ አቅጣጫ ትክክል መሆኑን ጠቁመው፤ የተገኙ ጠንካራ ድሎች የበለጠ የሚጠናከሩበትና ድክመቶች የሚታረሙበት ጊዜ ላይ ነን ብለዋል፡፡ ይሄን ስርአት ካለፉ ስርአቶች ጋር ማነፃፀር ተገቢ አለመሆኑን የገለፁት አቶ ጌታቸው፤ “ይሄ መንግስት ነገ ከነገ ወዲያ ሊሄድ ይችላል፤ የስርአት ለውጡ ግን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” ብለዋል፡፡ 

Read 5536 times