Saturday, 14 May 2016 12:26

ሶስና በኢትዮጵያ

Written by  ዲ/ን ዳንኤል ክብረት
Rate this item
(19 votes)

“የሀገራችን የወንጀል ፍርድ ከፈሰሰ የማይታፈስ …”

   በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙ አስደናቂ የፍርድ ታሪኮች አንዱ የሶስና ፍርድ ነው፡፡ እሥራኤል ወደ ባቢሎን ተማርከው በነበሩ ጊዜ ኢዮአቄም እና ሶስና የተባሉ ባልና ሚስቶችም ተማርከው ነበር፡፡ የባቢሎን ሥርዓተ መንግሥት ከየሀገሩ የተማረኩ ፈላስያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ፈቅዶ ነበር። በዚህም የተነሣ የራሳቸውን ፍርድ ቤቶች አቋቁመው የራሳቸውን ጉዳዮች ይዳኙ ነበር፡፡ በዚህ የእሥራኤል ዳኝነት አንድ ጉዳይ ቀረበ፡፡
ሶስና የምትባል በመልኳ ይህ ቀረሽ የማትባለው የኢዮአቄም ባለቤት በሞት በሚያስቀጣው የአመንዝራነት ወንጀል ተከሰሰች። በዚያ ዘመን በሀብት ሻል ያሉ የባቢሎን ሰዎች ቤታቸውን በኤፍራጥስ ወንዝ አቅራቢያ ሠርተው በወንዙ ዳር በሚገኙት የአትክልት ሥፍራዎች ውስጥ የገላ መታጠቢያዎችንና የመዋኛ ገንዳዎችን ያዘጋጁ ነበር፡፡ እነዚህ የመናፈሻ ሥፍራዎች በአጥር የታጠሩ ሆነው የራሳቸው በር ነበራቸው፡፡
ኢዮአቄምና ሶስና  ከፈላስያኑ ወገን በሀብትም በክብርም ላቅ ያሉ ስለነበሩ ይህ ሀብት ነበራቸው፡፡ ሀብት ክብር ብቻ ሳይሆን መዘዝም ያመጣል፡፡ በኢዮአቄም ቤት ለችሮታም፣ ለመጠለልም፣ ከባቢሎን ባለ ሥልጣናት ለመገናኘትም እያሉ የሚሰበሰቡ ብዙ ነበሩ። ከእነዚህ መካከል ሁለቱ የተከበሩ የሕዝብ መምህራን ናቸው፡፡ ሕዝቡ በዐዋቂነታቸውና በወንበራቸው ያውቃቸዋል፣ ያከብራቸዋል፡፡ ‹በካባ ውስጥ ያለን ኃጢአት፣ በኮት ውስጥ ያለን ጽድቅ እግዜር ብቻ ነው የሚያውቀው› እንዲሉ እነዚህ ሁለት የተከበሩ ባለ ካባዎች ጠባያቸው እንደ ካባቸው አልነበረም፡፡ የኢዮአቄምን ሚስት ሶስናን ለመኝታ ይፈልጓት ነበር፡፡ ነገር ግን አመቺ ጊዜ አላገኙም፡፡
አንድ ቀን ገላዋን ልትታጠብ ወደ ኤፍራጥስ ወንዝ ስትወርድ እነርሱም በድብቅ ወደ መታጠቢያው የአትክልት ሥፍራ ገቡና ተደበቁ። አገልጋዮቿ የመታጠቢያ ነገሮችን ሊያመጡ በኋላው በር ሲወጡ ከተደበቁበት ወጡና ያዟት። ከዚያም ‹ከአንቺ ጋር መተኛት እንፈልጋለን› አሉ፡፡ እርሷ ግን ሰማይ ዝቅ ምድር ከፍ ቢል ፈቃዳቸውን ለመፈጸም እንደማትፈልግ በቁርጥ ነገረቻቸው፡፡ እንደዚያ ካልሆነ ‹ከጎረምሳ ጋር አይተናታል ብለን እኛ ምስክር ሆነን እንከስሻለን› አሏት፡፡ ነገሩ ምን ቢያስጨንቃት የእነዚህን ምግባረ ቢሶች ፈቃድ ከመፈጸም ሞትን መረጠቺና ጮኸች፡፡ ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮኻል እንዲሉ፤ እነዚያም ሰዎች አብረዋት ጮኹ፡፡ አንደኛውም ሮጦ የአጥሩን በር ከፈተው። የአካባቢው ሰዎች ጩኸቷን ሰምተው ሲመጡ እነዚያ ሰዎች ‹ሶስናን ከጎረምሳ ጋር ተኝታ በዚህ ቦታ አየናት፡፡ እርሱንም ልንይዘው ስንል ኃይለኛ ነበርና በሩን ከፍቶ አመለጠን› ብለው ተናገሩ። የተናገሩት ሰዎች የከበሩ መምህራን ስለነበሩ ሊጠራጠራቸው የቻለ ሰው አልነበረም፡፡
የሕዝቡ ሸንጎ በማግሥቱ ተሰብስቦ ጉዳዩን አየው፡፡ እነዚያ ሁለት መምህራን አይተናል ያሉትን ተናገሩ፡፡ ሰዎቹ የሚከበሩ በመሆናቸው ቃላቸውም ተከበረና በሶስና ላይ የሞት ፍርድ ተፈረደባት፡፡ ወደ ፍርድ መፈጸሚያው ሥፍራ ልትሄድ ስትል ግን ፍርዱን እንደገና ለማየት የሚያስገድድ ነገር ተፈጠረ፡፡ ነቢዩ ዳንኤል፤ ‹እኔ በዚህ ፍርድ አልስማማም› አለ፡፡ በባቢሎን ቤተ መንግሥት ያደረገውን ያውቁ ስለነበር ሕዝቡ ሁሉ ሊሰሙት ፈለጉ፡፡ ዳንኤል አንዱ ያንዱን ቃል ሊሰማ በማይችልበት ቦታ ሁለቱን ሰዎች ለየብቻ አቁሞ የትኛው ዛፍ ሥር ተኝታ እንዳዩዋት ጠየቃቸው፡፡ አንዱ በኮክ ዛፍ ሥር ሲል ሌላው በሮማን ዛፍ ሥር ነው አለ፡፡ ይህንን ሲመለከቱ፣ የሕዝቡ ሸንጎ የሞት ፍርዱን እንዲከልስ ተገደደ። ሶስናን በነጻ አሰናብቶ በምስክሮቹ ላይ የቅጣት ውሳኔን አስተላለፈ፡፡
ሶስና ኢትዮጵያዊት ሆና፣ ድርጊቱ የተፈጸመው ዛሬ ቢሆን ኖሮ ግን የመትረፍ ዕድል አልነበራትም፡፡ ምንም ንጹሕ ብትሆን፣ ምንም ምስክሮቹ የሐሰት ምስክሮች መሆናቸው በኋላ ቢረጋገጥ፣ ምንም እንኳን ከፍርዱ ውሳኔ በኋላ የፍርዱን ውሳኔ የሚያስገለብጥ ማስረጃ ቢገኝ፣ ሶስና ከመሞት ውጭ አማራጭ አልነበራትም፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ፣ በወንጀል ጉዳይ የተሰጠ ውሳኔ እንደገና የሚከለስበትን ዕድል ስለማይሰጥ፡፡ በታች ፍርድ ቤት የታየ ጉዳይ በይግባኝ በላይኛው ፍርድ ቤት ይታይ ይሆናል እንጂ አንድ የወንጀል ፍርድ ከተሰጠ በኋላ የቀረበው ማስረጃ ስሕተት ነበረ፣ የተፈረደበት ሰው በስመ ሞክሼ ነው፤ ተፈጸመ የተባለው ድርጊት አለመፈጸሙ ተረጋገጠ፣ የወንጀሉን ፍርድ ሊያስገለብጥ የሚችል ሌላ ማስረጃ ተገኘ ቢባል እንኳን የሀገራችን የወንጀል ፍርድ ‹ከፈሰሰ የማይታፈስ› ነው፡፡
በፍትሐ ብሔር መሥመሩ እንደገና ሊታይ የሚችልበት ዕድል በመጠኑም ቢሆን ገርበብ ብሎ ተከፍቷል፡፡ በወንጀል ሕጉ ግን የተከረቸመ በር ነው፡፡ ከወጣ ከግማሽ ምእተ ዓመት በላይ የሆነው የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጋችን በዚህ ሁሉ ዘመን በሩን እንደዘጋው ይገኛል፡፡
ሰሞኑን ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሄጄ በነበረ ጊዜ ሁለት ‹የሶስና ፍርዶችን› ሰምቼ መጣሁ፡፡ አንደኛው ሰውዬ ሰው ገደልክ ተብሎ ይከሰሳል፡፡ ምስክርና ማስረጃ ይቀርብበታል። ሰውዬው አልገደልኩም ብሎ ቢከራከርም በመጨረሻ በሰባት ዓመት ጽኑ እሥራት ይቀጣል፡፡ እርሱም ወኅኒ ወርዶ ፍርዱን ማድረስ ይቀጥላል፡፡ ለሁለት ዓመታት ያህል ከታሠረ በኋላ ግን ሞተ የተባለው ሰው ወደ መንደሩ ይመጣል፡፡ በእርሱ ምክንያት ሰው መታሠሩንም ይሰማል፡፡ ሰውዬውም ወደ ፍርድ ቤቱ ይመጣና ‹ተገደልኩ የተባልኩት ሰው አለሁ፤ ገደለኝ የተባለውን ሰው ፍቱልኝ› ይላል፡፡ ልክ በ“ሞገደኛው ነውጤ” ላይ አበራ ለማ እንደጻፈው፡፡ ዳኞቹ ሁኔታውን ሲያጣሩ በርግጥም ሞተ የተባለው ሰው ይህ ከፊታቸው የቆመው ነው፡፡ አሁን ችግሩ ‹ቀጥሎ ምን ይደረግ?› የሚለውን የሀገራችን የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕግ አለመመለሱ ነው፡፡ በወንጀል የተሰጠን ፍርድ እንደገና ለመከለስ የሚያስችል ዕድል የለም፡፡ በዚህ የተነሣ አለመግደሉ የተረጋገጠው ሰው የእሥር ጊዜውን ከመጨረስ ያለፈ ውሳኔ ሊያገኝ አልቻለም፡፡
ይህን የተዘጋ በር እስከ ዛሬም ብዙዎችን ንጽሕናቸው እንዳያድናቸው፣ ዘመን በወለደውና ጊዜ በወደደው ሰው እጅ እንዲወድቁ፣ በአንድ ወቅት በተፈጠረ ስሕተት በተሰጠ ፍርድ እንዲማቅቁ አድርጓቸዋል፡፡ የዚህን በር መከፈት በመቃወም የሚከራከሩ ወገኖች የሚያነሡት ሁለት ጉዳይ ነው፡፡ አንደኛው የወንጀል ፍርድ እንዴትና በማን ነው ሊከለስ የሚችለው? ሁሉም የወንጀል ችሎቶች ይህ ሥልጣን ከተሰጣቸው ላልተገባ ተግባር የመዋል ዕድል አይኖረውም ወይ? የሚል ነው፡፡ በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ጉዳዩ መጀመሪያ ለቀረበበት ችሎት ነው የሚቀርበው፡፡ የወንጀል ጉዳዮች ሀገርንና ማኅበረሰብን የሚመለከቱ ስለሆኑ ይህንን ነገር ሊያዩ የሚችሉ ችሎቶችን መመደብ ወይም ከፍ ያለ ሥልጣን ለተሰጠው የፍርድ አካል መስጠት ይቻላል፡፡ በሌላም በኩል “አንድ ንጹሕ በስሕተት ከሚታሠር ዐሥር ወንጀለኞች ቢለቀቁ ይሻላል” የሚለውን የሕግ ምክር ተግባራዊ አድርጎ መጠቀም ነው፡፡
ሌላው የሚነሣው ጉዳይ ደግሞ የካሣ ጉዳይ ነው፡፡ ‹በስሕተት ነው የታሠርከው› የተባለ ሰው ለተፈጸመበት ነገር ምን ሊደረግለት ይችላል? መንግሥትስ ለእነዚህ ሰዎች ካሣ ለመክፈል ኢኮኖሚያዊ ዐቅም አለው ወይ? የሚለውን የሚያነሡ አሉ፡፡ በስሕተት የተፈረደበት ሰው ኢኮኖሚያዊ፣ ሞራላዊና ማኅበራዊ ኪሣራ ያገኘዋል፡፡ ከሥራው ይወጣል፣ ንግዱ ይበላሻል፣ በሞያው ያፈራቸውን ደንበኞች ያጣል፡፡ ወንጀለኛ ተብሎ ስለተፈረደበት በማኅበረሰቡ ዘንድ ይገለላል፣ ስሙ ይጠፋል፣ ክብሩ ይቀንሳል። በእነዚህ ሁለት ምክንያቶችም ሞራሉ ይነካል፡፡ የፍርዱ ዘመን ረዥም ከሆነም የማይተካው እድሜው ይወሰድበታል፡፡
መንግሥት ለእነዚህ ነገሮች ሦስት ካሣዎችን ማዘጋጀት ይችላል፡፡ የሞራል፣ የማረሚያና የገንዘብ፡፡ የሞራል ካሣው ሰውዬው በስሕተት እንደታሠረ የሚገልጥ ማስረጃ (የምስክር ወረቀት) በመስጠት፣ አመቺ በሆነው ሚዲያ ወይም በአካባቢው ሊለጠፍ በሚችል ማስታወቂያ በስሕተት የታሠረ ንጹሕ ሰው መሆኑን በመግለጥ መካስ ይቻላል፡፡ የማረሚያ ካሣ ደግሞ ወደ ሥራው እንዲመለስ፣ በመታሠሩ ምክንያት ያጣቸው ጥቅሞች እንዲከበሩለት፣ የተወሰደበት እንዲመለስለት፣ ያለፉት ነገሮች ካሉ እንዲሟሉለት ማድረግ ይችላል፡፡ የሀገሪቱ ዐቅም በሚፈቅደው መጠንም የገንዘብ ካሣ መስጠት ነው፡፡መንግሥት በፍርድ ሂደት የሚያገኛቸው ገቢዎች አሉ፡፡ ከገንዘብ መቀጮዎች፣ ከውርሶች፣ ወዘተ፡፡ ከእነዚህ ሸረፍ አድርገው ሙሰኞቹ ከሚወስዱ ንጹሐኑ ቢካፈሉ ምን አለ?
አንዳንድ ልሂቃን፤ ‹የተወሰኑ የሕግ አካላት በሠሩት ስሕተት እንዴት መንግሥት ይቀጣል?› የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ መንግሥት ድሮውንም በሰዎች የሚመራ መዋቅር ነው። መንግሥት የሾማቸው ሰዎች ለሚሠሩት ስሕተት አንዱ ተጠያቂም ራሱ መንግሥት ነው። ለዚህም ነው በሌሎች ሀገሮች የበታች አካላት ለሠሩት ስሕተት ከፍተኛ ኃላፊዎች ሥልጣን እስከ መልቀቅ የሚደርሱት፡፡
ይህ በር እንደተዘጋ ከቀጠለ ግን ከባድ ማኅበራዊ ኪሣራ ያመጣል፡፡ ሰዎች ንጽሕናን እንዲጠየፉ ያደርጋል፡፡ ዘመኑ በተራቀቀበት በዚህ ወቅት ማስረጃዎችን መፈብረክ ቀላል ነውና አያሌ ንጹሐን ለዚህ በተዘጋጁ ማስረጃ ፈብራኪዎች እጅ እንዲወድቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ያለ ሥራቸው ወንጀል ሠርታችኋል የተባሉትንም ለበቀል ያነሣሣል፡፡
ሁለተኛውን ታሪክ እዚህ ላይ ላውጋችሁ። ሰውዬው በነፍስ ግድያ ተከሰሰ፡፡ በርግጥ ተኩሶ ሰው መትቷል፡፡ ሲተኩስም ሰዎች አይተውታል፡፡ በተኮሰበት ቦታም ደም ፈስሷል። ይህንን ሰውዬውም አልካደም፡፡ ምስክሮችም መስክረዋል፡፡ የሟች አስከሬን ግን ሊገኝ አልቻለም፡፡ ከተኩሱ ቦታ በታች ዝንጀሮ ብቻ የሚወርደው ገደል አለ፡፡ እዚያ ውስጥ ስለገባ ሊገኝ አልቻለም ተባለ፡፡ ተኳሹ ግን ‹በርግጥ ተኩሻለሁ ግን አልገደልኩትም› ብሎ ተከራከረ። ፍርድ ቤቱ የምስክሮችንና የማስረጃውን ነገር መዝኖ አምስት ዓመት ፈረደበት፡፡ ከዓመታት በኋላ ሞቷል የተባለው ሰው ሌላ መንደር እንደሚኖር ተሰማ፡፡ የታሣሪው ዘመዶችም ሄደው አረጋገጡ፡፡ ሰውዬው በጥይት ተመትቶ ነበር፡፡ ሲመታ ቢያውቀው ገደል ተንከባልሎ ገባ፡፡ በጋቢው ቁስሉን አሥሮ ገደል ለገደል ተንኳቶ ሌላ ሀገር ተደበቀ፡፡ እዚያ ጥይቱን አስወጥቶ ታክሞ ዳነ፡፡ ወደ መንደሩ ለመመለስ ስለፈራ ሌላ ቦታ ጎጆ ቀልሶ ተቀመጠ፡፡ ታሪኩ ይሄ ነው፡፡
ታሣሪው ሰው ይህንን ሲሰማ አልተናደደም። እንዲያውም ደስ አለው፡፡ ‹ለማንም አትናገሩ› ብሎ ዘመዶቹን አስጠነቀቀ፡፡ አምስት ዓመቱን ጨረሰና ከወኅኒ ቤት ወጣ፡፡ ጠመንጃውን ወለወለ፣ ጥይቱን አቀባበለ፡፡ ‹ሟች› ይኖርበታል ወደተባለው ሥፍራ ሄደና ሰው በተሰበሰበበት ቦታ ተኩሶ ገደለው፡፡ ሲገድለው ሰው አይቷል፡፡ እርሱም አልተደበቀም፣ ቤቱ ነው የተቀመጠው። ፖሊስ ግን እንዴት ይክሰሰው፡፡ አንድ ሰው ሁለት ጊዜ ሊሞት አይችልምና፡፡ በፍርድ ቤት ውሳኔ አሁን የተገደለው ሰው ከሞተ አምስት ዓመት አልፎታል፡፡ ይፈረድበት ቢባልም በአንድ ወንጀል ሁለት ጊዜ ፍርድ የለም፡፡ የተዘጋ የፍትሕ በር ዕዳው ይኼ ነው፡፡


Read 14502 times