Saturday, 14 May 2016 12:24

በፍጥነት እየተስፋፋ ያለው የደምና የማኅፀን ጫፍ ካንሰር

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(5 votes)

ወ/ሮ ዘኑ ደማ ቀጭን ጠይም፣ ቆንጆ ስትሆን 35 ዓመቷ ነው፡፡ መኖሪያዋ በአርሲ ዞን ሚጢ ቀበሌ ሲሆን በማቲዎስ ወንዱ ካንሰደር ሶሳይቲ ማዕከል ተጠልላ ነው ያገኘኋት፡፡
በፊት ጤነኛ ስለነበረች የወር አበባዋ ምንም ሽታ አልነበረውም፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ መሽተት ጀመረ። “በፊት የሌለብኝን የወር አበባዬ መሽተት ጀመረ” በማለት ለባሏ አጫወተችው፡፡ እሱም “የማኅፀን ችግር ሊሆን ይችላልና ሐኪም ቤት ሂጂ” አላት። እሷም በሻሸመኔ መስመር ሊፒስ ወደሚባለው የፈረንጆች ሐኪም ቤት ሄዳ ተመረመረች፡፡ ውጤቱ ጥሩ አልነበረም፡፡ “የማኅፀን ጫፍ ካንሰር ይዞሻል። አንደኛ ደረጃ ጨርሶ ሁለተኛ ደረጃ ጀምሯል። እኛ መሳሪያው የለንም እንጂ እዚሁ እንሰራልሽ ነበር፡፡ አሁን ለጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሪፌር እንጽፍልሻለን፤ እዚያ ካንሰሩን በጨረር ያጠፉታል ወይም ማኅፀንሽን አውጥተው ይጥሉታል” አሏት፡፡
ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል መጥታ መጥፎ ጠረን ያለው ደም እየፈሰሳት ለ8 ወር ተመላለሰች፡፡ በመጨረሻ ባለፈው መስከረም በወር አንድ ጊዜ ለ3 ጊዜ የጨረር ሕክምና ታዘዘላት፡፡ ሕክምናውን ጨርሳ ወደ ቤቷ ሄዳ 2 ወር ቆይታ በቀጠሮዋ መሰረት ተመልሳ መጣች፡፡ የሽንት፣ የሰገራና ደም ምርመራ ተደርጎላት የ3 ወር ቀጠሮ ተሰጥቷት ተመለሰች። በቀጠሮዋ ተመልሳ ስትመጣ “ደምሽ ወርዷል” ተባለች፡፡
የሁለት ወር ቀጠሮ ተሰጥቷት እንደተመሰለች ብዙ ደም (የወር አበባ) ፈስሷት ሀኪም ቤት ስትሄድ ሀኪሙ አይቷት፣ “ልትሞት 5 ደቂቃ ነው የቀራት። ደም የሚባል ነገር ጭራሽ የላትም፡፡ አራት ፒሲ ትውሰድ” ብሎ አዘዘና ሁለት ከረጢት ደምና ሁለት ከረጢት ጉሉኮስ ተሰጣት፡፡ መድኃኒቷን ጨርሳ ስትወጣ በጣም ደከማት፡፡ በአዲስ አበባ ዘመድም ሆነ የምታውቀው ሰው የላትም፡፡ 8 ወር ስትመላለስ ገንዘቧን በአልቤርጎ ጨርሳለች፡፡ ማረፊያ አጥታ አለቀሰች፡፡ አብሯት ያለው ባሏም የሚያደርገው ጠፍቶት ግራ ቢገባው በለቅሶ አጀቧት፡፡
ባልና ሚስቱ ሲላቀሱ የተመለከተች ዶ/ር ሄለን የተባለች ሀኪም “በቃ አታልቅሱ፡፡ አንተም ወንዱ እንደዚህ ማልቀስ የለብህም፡፡ እስቲ ቆዩ፣ መጠለያ ሊሰጣችሁ የሚችል አንድ ድርጅት አለ፡፡ እዚያ ደውዬ ልጠይቅላችሁ” ብላ ለማቲዎስ ወንዱ - ካንሰር ሶሳይቲ ደወለች፡፡ ሶሳይቲውም ዘኑን በደስታ ተቀበላት፡፡   
“ማረፊያ ሰጥቶት፤ የተመጣጠነ ምግብ እያበላኝ፣ የትራስፖርት 500 ብር እየሰጠኝ፣ ሳሙና ባዝሊን፣ ሻወር፣ ስደክምም ጉሉኮስና መድኃኒት እየሰጠ እየተንከባከበኝ ነው፡፡ አሁን “ደምሽ ወርዷል” ስለተባለ ደም ሰጥቼ ውጤቱን ለሰኞ ብለውኛል። ህመሜም እየዳነ እንደሆነ ነግረውኛል፡፡ ሐምሌ ተመለሺ ብለው የ3 ወር ቀጠሮ ሰጥተውኛል” በማለት ዘኑ ገልጻለች፡፡
ታሪኩ ታዬ የ10 ዓመት ሕፃን ሲሆን መኖሪያው በደሌ ከተማ 01 ቀበሌ ነው፡፡ ታሪኩ የደም ካንሰር ታማሚ መሆኑን ያወቀው ኋላ ነው፡፡ በፊት ያልነበረ ነገር ይሰማው ጀመር፡፡ መጫወት አቃተው፣ በጣም ይደክመዋል፤ ትንሽ ሄዶ ማረፍ ነው፣ ትንሽ ሄዶ መቀመጥ ሆነ፡፡ ቢቸግረው በደሌ ሆስፒታል ሄዶ ተመረመረ፡፡ “የልብ ድካም ነው” ብለው ሳምንት አስተኝተውና ቀጠሮ ሰጥተው ሸኙት፡፡
በቀጠሮው ቀን ሲመለስ ካርዱ ቢፈለግ ቢፈለግ ጠፋ፡፡ እዚያው ከተማ ውስጥ ሌላ ሐኪም ቤት ሄዶ ተመረመረ፡፡ አልትራሳውንድ አንስተውና ሺሮፕ ሰጥተው ለሳምንት ቀጠሩት፡፡ በቀጠሮው ሲሄድ ለነቀምት ሆስፒታል ሪፈራል ጻፉለት፡፡ እዚያም ችግሩን አላወቁለትም፡፡ ሪፈራል ጽፈው ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ላኩት፡፡ ሆስፒታሉም ራጅ አንስቶና መርፌ ወግቶ “ከሳምንት በኋላ ተመለስ” ብሎ ቀጠረው፡፡
በመሃሉ ክፉኛ ነሰረውና ደሙ አልቆም አለ፡፡ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ ወዳለ ሀኪም ቤት ተወስዶ ሀኪሞች አይተውት “በፍጥነት ጥቁር አንበሳ አድርሱት” አሉ፡፡ ጥቁር አንበሳ ሲሄድ የራጅ ውጤት አልደረሰም፡፡ “ድንገተኛ ክፍል ተኛ” ተባለ፡፡ ድንገተኛ ክፍል እያለ የራጁ ውጤት ደረሰና ሕመሙ የደም ካንሰር መሆኑ ታወቀ፡፡ ወደ ሰባተኛ ተላከና ከዚያ መድኃኒት ወሰደ፡፡ አባቱ “ገንዘቤን ጨረስኩ፣ አሁንም ምን አባቴ ልሁን?” በማለት ሲጨነቁ ሲስተር ቀፃላ የተባለች ሴት “አይዞህ አትጨነቅ፤ ልጅህን የሚያሳርፍልህ ድርጅት ይኖራል” በማለት ለማቲዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ ደወለች፡፡ ሶሳይቲውም ተቀብሎት ማረፊያና ምግብ ችሎ ለትራንስፖርት 500 ብር ሰጥቶ እየተንከባከበው መሆኑን ታሪኩ ተናግሯል፡፡
ማቲዎስ ወንዱ - የኢትዮጵያ  ካንሰር ሶሳይቲ የተመሰረተውና የተሰየመው በአራት ዓመት ህፃን ስም ነው፡፡ ማቲዎስ ከሁለት ዓመቱ ጀምሮ የደም ካንሰር ተጠቂ ነበር፡፡ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ሲደረግለት ቢቆይም ህይወቱን ግና ማትረፍ አልተቻለም፡፡
አልተሳካም እንጂ የማቲዎስ ወላጆች የልጃቸውን ህይወት ለማትረፍ ከፍተኛ ጥረት አድርገው ነበር፡፡ ጥረቱ ሳይቋረጥ ተጠናክሮ በሕመሙ የሚሰቃዩትን ሌሎች ወገኖቻቸውን ለመርዳት የማቲዎስ ወላጆችና 15 ወዳጆቻቸው ሆነው በ1996 ዓ.ም “ማቲዎስ ወንዱ - የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ” መሰረቱ፡፡
ሶሳይቲው በአሁኑ ወቅት ከመንግስትና ከጤና ጥበቃ ሚ/ር ጋር በመተባበር፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ሕዝቦችና አዲስ አበባ ጤና ቢሮዎች ጋር በሕፃናት የደም ካንሰር፣ በሴቶች የማኅፀን ጫፍ ካንሰርና በትንባሆ ላይ እየሰራ ነው፡፡ ሴቶችን በመግደል የጡት ካንሰር ቅድሚያውን ሲይዝ የማኅፀን ጫፍ ካንሰር ይከተላል፡፡ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከ1996 እስከ 2008 ባጠናቀረው መረጃ ከተለያዩ ካንሰሮች መካከል 30.3 በመቶ የማኅፀን ጫፍ ካንሰር ነው፡፡ የማኅፀን ጫፍ ካንሰር በቀላሉ ሊከላከሉት የሚችልና የሚድን፣ ካልታከሙት ግን ገዳይ ነው ይላል፤ የማቲዎስ ወንዱ ካንሰር ሶሳይቲ ፕሮግራም ማናጀር አቶ ዘላለም መንግሥቱ፡፡
የማኅፀን ጫፍ ካንሰር የሚይዘው Human Papilloma Virus (MPV) በተባለ ቫይረስ ነው። ይህ ቫይረስ ዕድገቱ ዘገምተኛ ነው፡፡ 30 ዓመት ቆይቶ ነው መታየት የሚጀምረው፡፡ ከ9-13 ዓመት ላሉ ታዳጊ ሴቶች ክትባት ይሰጣል፡፡ ከ30-49 ዕድሜ (በመውለድ ክልል) ያሉ ሴቶች በየ 5 ዓመቱ የማኅፀን ጫፍ ምርመራ ማድረግ እንዳለባቸው አቶ ዘላለም ተናግሯል፡፡ አሁን ሶሳይቲው በሴቶች ካንሰር ላይ አተኩሮ እየሰራ ያለው በማኅፀን ጫፍ ካንሰር ላይ ነው፡፡ ህክምናው በጣም ቀላል ነው፡፡ ማኅፀን ጫፍ ላይ መድኃኒት ይቀባል፡፡ መድኃኒቱ በ3 ደቂቃ ውስጥ ቫይረሱ መጀመር ያለመጀመሩን ያሳያል። ነፃ የሆኑት ከ5 ዓመት በኋላ እንዲመለሱ ቀጠሮ ይሰጣቸዋል፡፡ ቫይረሱ የታየባቸው ደግሞ ወዲያውኑ መድኃኒት ተሰጥቷቸው ህክምና ይጀምራሉ፡፡ ደረጃው ከፍ ያለ ከሆነ ደግሞ ሌሎች ህክምናዎች አሉ፡፡ ከኤችአይቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ለዚህ ቫይረስ የተጋለጡ ናቸው፡፡ በትንሽ ዕድሜ (ከ18 ዓመት በታች) የግብረ - ስጋ ግንኙነት የሚጀምሩ ሴቶችና ብዙ የወሲብ ጓደኛ ያላቸው፣ ሲጋራ አጫሽ ሴቶች በማኅፀን ጫፍ ቫይረስ የመያዝ ዕድላቸው ከፍተኛ መሆኑን አቶ ዘላለም ገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሶሳይቲው እያደረገ ያለው ኅብረተሰቡ ስለማኅፀን ጫፍ ካንሰር ግንዛቤ እንዲኖረው ማስተማር ነው፡፡ ማርች 8ን ምክንያት በማድረግ ለአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን ሰራተኞች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠታቸውንና 270 ያህል ሰዎች ትምህርቱን መከታተላቸውን፤ በሀዋሳ፣ በሶዶ፣ በአዳማ፣ በቢሾፍቱ፣ በአሰላ ከተሞች ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ለተቋማት መሪዎች፣ ለሴቶችና ወጣት ማኅበራት መሪዎች፣ ለኤክስቴንሽን ሰራተኞች፣ … ማንኛዋም 30 ዓመት የሞላት ሴት የማኅፀን ጫፍ ካንሰር ምርመራ እንድታደርግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠታቸውን አቶ ዘላለም አስረድቷል።
“ማቲዎስ ወንዱ - ካንሰር” ሶሳይቲ ከአሰላ፣ ከቢሾፍቱ፣ ከሀዋሳ፣ ከሶዶ፣ ከይርጋለም ሆስፒታሎች ጋር እየሰራ ነው፡፡ እነዚህ ሆስፒታሎች የማኅፀን ጫፍ ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ ካንሰሩ ከፍተኛ ደረጃ ደርሶ ሕሙማኑ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲላኩ፣ ከተለያ የአገሪቱ ክፍሎች መጥተው በሆስፒታሉ ኬሞ ትራፒ፣ የጨረር ሕክምና ለሚያደርጉና የደም ካንሰር ላለባቸው ህፃናት ሶሳይቲ ወጪያቸውን እንደሚችል በማዕከሉ እንዲያርፉ እንደሚያደርግ፣ ምግብ እንደሚያቀርብ፣ ሳሙና፣ ቅባት፣ ሻወር፣ …. እንደሚሰጥ አቶ ዘላለም ገልጿል፡፡
አቶ ወንዱ በቀለ የማቲዎስ አባትና የሶሳይቲው ፕሬዚዳንትና ከመስራቾች አንዱ ናቸው፡፡ አቶ ወንዱ ማዕከሉን በማቋቋም ሂደት ከፍተኛ ውጣ ውረድ ማየታቸውን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት በሦስት የካንሰር ዘርፎች፡- በማኅፀን ጫፍ ካንሰር፣ በሕፃናት የደም ካንሰርና በትንባሆ ላይ እንደሚሰሩ ገልጸዋል፡፡
በሕፃናት ደም ካንሰር ለ70 ሕፃናት ድጋፍ እያደረጉ ነው፡፡ ሕፃናቱ ብቻ ሳይሆኑ ለሚያሳክሟቸው 70 ወላጆቻቸው መጠለያ ይሰጣሉ፤ መድኃኒት ይገዛሉ፡፡ “የላቦራቶሪው ሕክምና በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የማይሰጥ ከሆነ ለምሳሌ ኤምአይአር፣ ወጪውን እንሸፍናለን፣ ከአገራቸው ሲመጡና ሲሄዱ ወጪያቸውን እንችላለን፡፡ ሕፃናቱ ሆስፒታል ሲተኙ እናቶቻቸው ምን እየበላን ነው የምናጠባው? ስለሚሉ በወር 500 ብር እንሰጣቸዋለን፡፡
“መንግሥት ለካንሰር ህክምና ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ በፊት ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ብቻ ነው የጨረር ህክምና የሚሰጠው፡፡ አሁን በመቀሌ፣ ጎንደር፣ ጅማ፣ ሀዋሳ፣ ሀሮማያ የጨረር ህክምና ይሰጣል፡፡ የማኀፀን ጫፍ ካንሰር ህክምና መስጫ መሳሪያ ክራዮቴራፒ የሚባለው በውድ ዋጋ ተገዝቶ ለ18 ሆስፒታሎች እየተከፋፈለ ነው፡፡ የመሳሪያና የመድኃኒት አቅርቦት እየተሟላ ነው፡፡ የመግዛት አቅማቸው አነስተኛ ለሆኑ ሰዎች ጤና ጥበቃ ዋጋ እየተጋራ ነው፤ ባለሙያዎች እየሰለጠኑ ነው፡፡
በማኅፀን ጫፍ ካንሰር በደቡብ፣ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ ለመስራት ከጤና ጥበቃ ጋር የሦስት ዓመት ውል ተፈራርመናል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የጡት ካንሰር እየተስፋፋ ነው፡፡ በእሱ ላይ ገንዘብ ፈልገን ለመስራት ዕቅድ ይዘናል፡፡ ትልቁ ፕሮጀክታችን ትንባሆ ላይ ነው፡፡ በዚህ ላይ ሁለት ፕሮጀክቶ አሉን፡፡
“ወደፊት ካንሰር ላይ ብቻ ሳይሆን ተላላፊ ባልሆኑ ሕመሞችም ላይ የመስራት ዕቅድ አለን። ማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ፣ የኢትዮጵያ ስኳር ህመም ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ኩላሊት ሕመም ማኅበር፣ የኢትዮጵያ ልብ ማህበር፣ የኢትዮጵያ ካንሰር አሶስዬሽን አባል ሲሆኑ እኔ ደግሞ አስተባባሪ ነኝ” ብለዋ አቶ ወንዱ በቀለ፡፡   

Read 4527 times