Saturday, 14 May 2016 11:47

ለወልቂጤ ከተማ የመጀመሪያው ሎጅ ዛሬ ይመረቃል

Written by  በማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(2 votes)

በጉራጌ ዞን፣ በዕዣ ወረዳ ከአዲስ አበባ 189 ኪ.ሜ ላይ የተገነባውና ለወልቂጤ ከተማ የመጀመሪያው ነው የተባለው “ደሳለኝ ሎጅ” በዛሬው ዕለት ይመረቃል፡፡   
ምስራቅና ምዕራብ ጉራጌን በእኩል ቦታ ላይ የሚያገናኘው ሎጁ፤ 30ሺ ካ.ሜ መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ግንባታው 7 ዓመት እንደፈጀ ተገልጿል፡፡
ሎጁ፤ በጉራጌ ባህላዊ የቤት አሰራር የተገነቡ ሁለት የባህል አዳራሾች፣ ዘመናዊ የምግብ አዳራሽ፣ 300 ሰዎችን የሚይዝ የመሰብሰቢያ አዳራሽ፣ 600 ሰዎች የማስተናገድ አቅም ያለው የሚይዝ ሁለገብ አዳራሽ እንዲሁም በ3 ደረጃ የተዘጋጁ 50 የመኝታ ክፍሎች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል፡፡  
ቱሪስቶችን በመሳብ መዳረሻዎችን ለማስፋት ታስቦ የተገነባ ግዙፍ ኢንቨስትመንት ነው መሆኑ የተነገረለት “ደሳለኝ ሎጅ”፤ ለ60 ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል ተብሏል፡፡
በቀጣይም በሎጁ ዙሪያ የሚገኘውን ከ20ሺህ ካሬ ሜትር የሚበልጥ ቦታም የዱር አራዊትና የተለያዩ አእዋፋት የሚጠበቁበት ሥፍራ በማድረግ የሎጁ ማስፋፊያ ስራዎችን ለማከናወን መታቀዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡  
ሎጁን ያስገነቡት ባለሀብት በአዲስ አበባ የሚገኘው የደሳለኝ ሆቴል ባለቤት ሲሆኑ ለረጅም አመታት በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያካተበቱትን የዘመናዊ ሆቴል አገልግሎት ተሞክሮ በመጠቀም፣ ደረጃውን የጠበቀ ስራ በመስራት ለትውልድ አካባቢያቸው ዕድገትና ልማት የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት አስበው እንደገነቡት ተገልጿል፡፡

Read 2714 times