Saturday, 07 May 2016 13:33

“የሚዲያ ብዝሃነት” በእርግጥ ተከብሯል?

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ዓለማቀፍ የፕሬስ ቀን ባለፈው ማክሰኞ ሚያዝያ 25 በሀገራችን የተከበረ ሲሆን በመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት አዘጋጅነት በፍሬንድሺፕ ሆቴል የግማሽ ቀን
የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡ በፓናል ውይይቱ ወቅት የሀገሪቱን የመገናኛ ብዙኃን ሁኔታ የሚዳስሱ ሶስት ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበው በሠፊው ውይይት ተደርጐባቸዋል፡፡
“የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች ሀገር - ኢትዮጵያ” የሚል መሪ ቃል የተሰየመለትን የዘንድሮ የፕሬስ ቀን መነሻ በማድረግ፣ በተለይ በአገራችን ያለውን ተጨባጭ እውነታ
በተመለከተ የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ የጋዜጠኝነት መምህራንን፣ የጋዜጠኛ ማህበራት አመራሮችን፣ ጋዜጠኞችን፣ ፖለቲከኞችንና ምሁራንን አነጋግሯል፡፡
ሃገሪቱ በመሪ ቃሉ ላይ እንደተጠቀሰው በእርግጥም የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች ሀገር ናት? አስተያየት ሰጪዎቹ በጉዳዩ ላይ ሃሳባቸውንና ዕይታቸውን ሰንዝረዋል፡፡

“ብዝሃነት መሬት ላይ ያለን ሃቅ
ለመደፍጠጥ የዋለ ቃል ነው”
በ1920 እና 30ዎቹ ጆርጅ ኦዌል “1984” የተሰኘ መፅሃፍ ነበረው፡፡ በዚህ መፅሃፍ ውስጥ “ፖለቲካና ቋንቋ” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ፅሁፍ፤ “መሬት ላይ ያለን የፖለቲካ ችግር በቋንቋ ለመሻገር መሞከር” ይለዋል፡፡ ቋንቋን በመጠቀም የተወሰነ ርዕዮተ ዓለማዊ ግብን መምታት ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለውን የሚዲያ ሁኔታ ገምግም ከተባልኩ በሁለት መንገድ ነው የማየው፡፡ አንደኛው ክፍል ራስን ሳንሱር በማድረግ (ሰልፍ ሴንሰርሺፕ) ውስጥ ያለ ነው፡፡ ሰልፍ ሴንሰርሺፑ አንዳንዴ ከመንግስት ጫና በላይም ሊሻገር ይችላል፡፡ አሁን እያየነው ያለው ያንን ነው፡፡ ደርግና ኢህአዴግ የሚለያዩት እዚህ ላይ ነው፡፡ ደርግ በግልፅ አታድርግ ይልሃል፡፡ ኢህአዴግ የሴንሰርሺፕ ተቋም አላቋቋመም፤ ነገር ግን “ይሄን ካደረግህ ዋ ኮንትራት አንሰጥህም” ይላሉ፡፡ “ብዝሃነት” የሚለው ቃል እንግዲህ ቋንቋ ሰርቆ መሬት ላይ ያለን ሃቅ ለመደፍጠጥ የዋለ ቃል ነው፡፡ ከዚህ ውጪ ምንም አይገልፀውም፡፡ ይሄን ካልን ብዙም “ብዝሃነት አለ፣ የለም” የሚል ክርክር ውስጥ መግባት አይጠበቅብንም፡፡

              ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ
(የፍልስፍና ምሁር)

=========================================

“ሚዲያው የሃሣብ ብዝሃነትን
የሚፈራ ነው”

ኤልያስ ገብሩ
(የ“አዲስ ገፅ” መጽሔት ዋና አዘጋጅ)

የፕሬስ ብዝሃነት ማለት የተለያዩ አስተሳሰቦች የሚስተናገዱበት ማለት ነው፡፡ ኢህአዴግን ደግፎም ሆነ ነቅፎ መፃፍ መቻል ማለት ነው፡፡ ብዝሃነት ቃሉን እንዲሁ ለፕሮፓጋንዳ ተጠቀሙት እንጂ አሁን መሬት ላይ ካለው ሃቅ ጋር ፈጽሞ የማይሄድ ነው፡፡ እስከ ዛሬ እንደውም ሚዲያው የሃሣብ ብዝሃነትን የሚፈራ ሆኖ ነው የሚታየው፡፡ ኢቢሲን ብንመለከተው ለአንድ ወገን ወግኖ የሚሠራ ነው፡፡ የተለያዩ ሃሳቦችን የሚያስተናግድ አይደለም፡፡ በምርጫ ክርክር እንኳ ተቃዋሚዎች በጣት የምትቆጠር ደቂቃ ነበር የተሰጣቸው፡፡ ይሄ ኢህአዴግን በሃሳብ የበላይነት አሸንፈን ስልጣን እንይዛለን ለሚሉ ተቃዋሚዎች ምን ይጠቅማቸዋል? ራሳቸውን እንኳ ለማስተዋወቅ የማይበቃ ጊዜ ነው፡፡ ታዲያ እንዴት ነው የሚዲያ ብዝሃነት ተፈጥሯል ልንል የምንችለው? መንግስት ብዝሃነትን አስቦ ቢንቀሳቀስ ኖሮ፣ እነ እስክንድር ነጋ፣ እነ ውብሸት ታዬ፣ እነ ተመስገን ደሣለኝና የመሳሰሉ ጋዜጠኞች አይታሠሩም ነበር፡፡ በሃሳብ ብዝሃነት የሚያምን መንግስት ቢኖር ኖሮ፣ ፖለቲከኞች በየጊዜው እየታሠሩ ባልተፈቱ ነበር፡፡
አለማቀፍ ተቋማት የሀገሪቱን የፕሬስ ሁኔታ አስመልክቶ የሚያወጡት ሪፖርት መሬት ላይ ያለውን ሃቅ የሚገልጽ ነው፡፡ እኛም ሪፖርት እንስራ ብንል ከዚህ የተለየ አይሆንም፡፡ በሚዲያ ጉዳይ ጥናት የሚያደርግ የሀገር ውስጥ ተቋም ቢኖር፣ ከእነሱ የከፋ ሪፖርት ሊያወጣ እንደሚችል አልጠራጠርም፡፡ ዛሬ ጋዜጠኝነት የአደጋ ቀጠና ሆኗል፡፡ በሙያው ተመርቀው የሚወጡ ተማሪዎች እንኳ ወደ ሙያው መቀላቀል አደገኛ መሆኑን እያዩ እየሸሹ ነው፡፡

================================

“ሚዲያዎች በሞኖፖሊ ስር ነው ያሉት”
አቶ ወንድወሰን ተሾመ
(የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት)

  በየአመቱ የሚከበረውን የፕሬስ ቀን በፊት ያከብር የነበረው የኢትዮጵያ ነፃ ጋዜጠኞች ማህበር (ኢነጋማ) ነበር፡፡ እለቱ ታሣቢ የሚያደርገው የታሠሩትን የተሰደዱትን፣ በሙያቸው ጫና እያረፈባቸው ያሉትን ነው፤ መከበር ያለበትም ከዚህ አንፃር ነው፡፡ አሁን ሞኖፖሊ የሠፈነበት ጊዜ ላይ ነው ያለው፡፡ የግል ፕሬስ አለ ማለት የማይቻልበት ደረጃ ላይ እየተደረሰ ነው፡፡ ሞኖፖሊ ሲበዛ የሚዲያ ብዝሃነት የምንለው ነገር ይጠፋል፡፡ የግል ፕሬሶች በወረቀት ዋጋ መናርና በሌሎች ምክንያቶች እየተዳከሙ ነው፡፡ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በግል የተያዙ ያሉ ቢሆንም ብዝሃነት ያለው ሃሣብ የማንሸራሸር አቅም ሲፈጥሩ አልታዩም፡፡ በሞኖፖሊ ስር ነው ያሉት፡፡ በሙያቸው ጋዜጠኛ ሆነው የምናቃቸው ሰዎች፤ መንግስት በሌላ ጉዳይ ወንጀለኛ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ በማለቱ አሁን በእስር ቤት የሚገኙ አሉ፡፡ መንግስት በዚህ ቀን እነዚህን ሙያተኞች ቢለቃቸው ምን ይጐዳል? እንደውም ክብር ያገኝበታል፡፡ የተከሰሱት በሌላ ቢሆንም እኛ የምናውቃቸው በጋዜጠኝነታቸው ነው፤ ቢለቀቁ በሙያው ላይ የራሳቸውን ድርሻ ያበረክታሉ፡፡ የመንግስትን ገጽታ በአለማቀፍ ደረጃ የሚያበላሸውና የተለያዩ ሪፖርቶች ላይ የሚንፀባረቀውም ይኼው ነው፡፡

==================================

“ሁሉም አመለካከቶችና ሃሳቦች የሚንፀባረቁበት እድል አልተፈጠረም”

አቶ አንተነህ አብርሃም
(የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚደንት)
   የፕሬስ ቀን አከባበሩ ላይ እንድንገኝ ተጠርተን ነበር፤አልተገኘንም፡፡ ያልተገኘነው ክብር ስለነፈጉንና ስላዋረዱን ነው፡፡ አንደኛ፤ ተገቢውን እውቅና ነስተውናል፡፡ በበአሉ ላይ መጥታችሁ ቁጭ ትላላችሁ፤ከዚያ ሲያልቅ ትሄዳላችሁ ነው ያሉት፡፡ ስለዚህ ነው የተውነው፡፡ እኛ ተሳታፊዎች ብቻ መሆን አይገባንም፤ ባለድርሻዎች ነን፤ ንግግር ለማድረግ አስበን ነበር፡፡ እነሱ ግን እንደ ማንኛውም ሰው ትመጣላችሁ፤ የሚባለውን ሰምታችሁ ትሄዳላችሁ ነው ያሉን፡፡ እኛ ደግሞ ይሄ አምባገነንነት ነው፤አምባገነንነትን መሸከም አንችልም ብለናቸዋል፡፡ እኛ እስከ ዛሬ ከመንግስት ጋር በጋራ ስንሰራ ነበር፡፡ አሁን እኛን ከስርአቱ ጋር የማጋጨት ሥራ ነው የተሰራው፡፡ መንግስት በፊት ያደርግልን የነበረውን ድጋፍም አሁን እየነፈገን ነው፡፡ ድጋፍ ማድረግ አቁሟል፡፡ ለምን አቆመ? መንግስት ራሱ ነው የሚያውቀው፡፡ የፕሬስ ነፃነት ቀን አከባበር ላይም አያገባችሁም ተብለን ተገፍተናል፡፡  
ይሄ መገፋት ግን እኛን ለሀገራችን ከምናደርገው አስተዋፅኦ አያግደንም፡፡
አንዳንድ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የመንግስትን አቋም አይደለም እያንፀባረቁ ያሉት፤ የራሳቸውን ነው፡፡ ወደ ርዕሰ ጉዳዩ ስመለስ፤ “የሚዲያ ብዝሃነት” ማለት የተለያዩ ሃሳቦችና አመለካከቶች የሚንሸራሸሩበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር ማለት ነው፡፡
በዚህም ሁሉም እኩል የመናገር፣ የመደመጥና ሃሳቡን የማንፀባረቅ መብት ያገኛል ማለት ነው፡፡
 ከዚህ አንፃር ካየነው አሁን ላይ ሁሉም የዚህ እድል ተጠቃሚ ሆኗል ብዬ አላምንም፡፡ ሁሉም አመለካከቶችና ሃሳቦች የሚንፀባረቁበት እድል አልተፈጠረም፡፡ ይሄን ስል ክልከላ አለ ማለቴ አይደለም፤ ክልከላው ባይኖርም የበለጠ ሙሉ የሆነ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ይቻል ነበር፡፡ አሁን ጭራሽ ያለውና የነበረው ነገር እየኮሰመነ ነው፡፡
በተወሰኑ የመንግስት ኃላፊዎች የሚፈለገው፣የጋዜጠኞች ማህበራት እንዲዘጉ ነው፡፡ ይሄ የመንግስት አቋም አይደለም፤የግለሰቦች ነው፡፡ ውይይት የሚፈልግ ጉዳይ ነው፡፡
 ውይይት እናድርግ ስንል ደግሞ ፍቃደኛ አይደሉም፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች የአምባገነንነት አዝማሚያ ፍንጮች ናቸው፡፡ እነዚህን ሁኔታዎች ደግሞ እኛ ልንሸከማቸው አንችልም፡፡

================================

“ብዝሃነት ያለው ሚዲያ ቢኖርማ እኛም ባልተከራከርን”
ፕ/ር በየነ ጴጥሮስ
(የመድረክ ሊቀመንበር)

  እኛም ከተያያዝናቸው የትግል አጀንዳዎች አንዱና ዋነኛው ሃሳብን በነፃነት የመግለጽ ጉዳይ ነው፡፡ ባለፉት የፖለቲካ ትግላችንም ለዚህ ስንከራከር ቆይተናል፡፡ ብዝሃነት ያለው ሚዲያ ቢኖርማ እኛም ባልተከራከርን፤ በዚህ ላይ ጊዜያችንን ባላጠፋን ነበር፡፡ ህገመንግስቱ የሚዲያ ነፃነት እንደሚከበር ደንግጓል፡፡ ነገር ግን ስርአቱ በጉልበት ህገ-መንግስታዊ መብቱን ገድቦታል፡፡ የፕሬስ ነፃነት ጉዳይ ዝም ብሎ የሚታይ አይደለም፡፡ አሁን ያለው ሁኔታ መቀየር አለበት፡፡ መሬት ላይ ያለው ሃቅና በመንግስት የሚነገረው የተለያየ መሆኑ የሚታወቅ ነው፡፡ አለማቀፍ ሪፖርቶችም በየጊዜው የሃገሪቱ የፕሬስ ሁኔታ አደጋ ውስጥ እንዳለ እንጂ በመልካም ሁኔታ ላይ መሆኑን አያንፀባርቁም፡፡ ጋዜጠኞች ጠንከር ብለው መንግስትን ሲተቹ፣ ሽብርተኛ ተብለው እንደሚታሠሩ እናውቃለን፡፡
ይሄን ሽሽት ጋዜጠኞች ያልተሰደዱበት የአለም ሃገርም የለም፡፡ ይሄ እንዲህ ባለበት ሁኔታ “የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች ሀገር” ማለት የህዝብ ንቀት ነው፡፡

==============================

“በሌላው ሀገር መንግስት በፕሮፓጋንዳ አይፎክርም”

በፍቃዱ ኃይሉ (የዞን 9 ብሎገርና
የ“ውይይት” መፅሄት ዋና አዘጋጅ)

   በአገሪቱ የሚዲያ ምህዳር ውስጥ እየኖርኩበት ነው፤ዋጋም የከፈልኩበት ነው፡፡ ስለዚህ እኔ ከአለማቀፍ ሪፖርት ሳይሆን በዚህ መንገድ የሀገሪቱን የሚዲያ ምህዳር አውቀዋለሁ፡፡ “የሚዲያ ብዝሃነትን ያከበረች ሀገር - ኢትዮጵያ” የሚለውን መፈክር ስሰማ እንደ ስላቅ ነው የወሰድኩት፡፡ ፀሐፊዎቹ ራሳቸው አምነውበት የፃፉት አይመስለኝም፡፡ መፈክር ራሱ የፕሮፓጋንዳ ስራ ነው፡፡ በሌላው ሀገር መንግስት እንደዚህ በፕሮፓጋንዳ አይፎክርም፡፡ እኔ ከምኖርበት አንፃር ይሄን መፈክር ከስላቅ ለይቼ አላየውም፡፡ በምርጫ ማግስትና በምርጫ ዋዜማ ላይ የሚዲያዎች ቁጥር እኩል አይደለም፡፡ በምርጫ ዋዜማ ላይ ጠንካራ ፕሬሶች ይዘጋሉ፣ ይከሰሳሉ፣ ጋዜጠኞች ይሰደዳሉ፡፡ ይሄን በ2007 ምርጫ አይተነዋል፡፡ የፕሬሱ አስተዋፅኦ አስፈላጊ በሚሆንበት ሰአት ላይ በፍጥነት እንዲወገዱ ይደረጋል፡፡ ተፅዕኖ መፍጠር በማይችሉበት ወቅት ደግሞ ዝም ይባላሉ፡፡ በሀገሪቱ ያለው የሚዲያ ሃቅ ይሄ ነው፡፡ ይህም ሆኖ ዛሬ ከ10 ሺህ በላይ ኮፒ ያለው ጋዜጣ የለም፡፡ በየቀኑ የሚወጣ ጋዜጣ የለም፡፡ ሬዲዮ ጣቢያዎችም የግል ቢኖሩም ራስን በራስ በመመርመር የሀሳብ ተአቅቦ ያደርጋሉ፡፡ ፖለቲካ ሽሽት መዝናኛና ስፖርት ላይ ያተኩራሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የሚዲያ ብዝሃነት ፅንሰ ሀሳብን ራሱ መንግስት በቅጡ የተረዳው አይመስለኝም፡፡


===============================

“የሚዲያ ብዝሃነት አለመኖር ለመንግስት ውድቀት ነው”

እንግዳወርቅ ታደሰ
(በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ፣ የጋዜጠኝነት መምህር)

ባለፉት 25 ዓመታት ፕሬሶች ቁጥራቸው አንዴ ይጨምራል፣ ሌላ ጊዜ ይቀንሳል፡፡ የመንግስት ሚዲያዎችን ካየን በቁጥር እየጨመሩ ነው፡፡ የብሮድካስት ዘርፍ በቁጥር ደረጃ ከፕሬሱ የተሻለ እየተስፋፋ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ለኛ ሀገር የሚያስፈልገን የሃሳብ ብዝሃነትን ሊያመጣ የሚችል ሚዲያ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የግል ፕሬስ በቁጥር ሊያድግ ይገባዋል፡፡ በብሮድካስቱ ከሚገኙ የግል ጣቢያዎች ውስጥ እንኳ መረጃ ከማግኘት አንፃር ግልፅ ልዩነት ይታይባቸዋል፡፡ ፋና ከመንግስት የሚያገኘውን መረጃ ያህል ሌሎቹ አያገኙም፡፡ ያሉትን ውስን የግል ጋዜጦችም ብንመለከት መረጃ አያገኙም፤ራሳቸውን በራሳቸው ሳንሱር የማድረግ ችግርም አለባቸው፡፡ የሃሳብ ልዩነት በሰፊው የሚያንሸራሽሩ ጋዜጦች እድሜያቸው አጭር ሲሆን አይተናል፡፡
በብሮድካስት በኩል እየበዛ ያለው በቁጥር እንጂ የተለያዩ አስተሳሰቦችን በማንፀባረቅ ደረጃ አይደለም፡፡ በየክልሉ የተመሰረቱ ብሮድካስት ሚዲያዎች ከኢቢሲ ጋር ተመሳሳይ ይዘት ነው ያላቸው፡፡ እንደኔ በቁጥር መስፋፋታቸው ጥሩ መስሎ የሚታየኝ፣ ስቱዲዮዎች ከመገንባታቸውና መሰረተ ሚዲያው ከመዋቀሩ አንጻር ነው፡፡ ኢቢሲን ነጥለን ብንመለከት ብሮድካስት ኮርፖሬት ሲሆን ራሱን እያስተዳደረ መንግስትን ሳይሆን ህዝብን እንዲያገለግል ተብሎ የተዋቀረ ነው፡፡ ግን አሁን ይሄን በተግባር እየሰራ ነው ወይ? የሚለውን መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ከህትመት ሚዲያው፣ጠንካራ ጉዳዮችን የሚዘግቡት ከሁለት አይበልጡም፡፡ ይሄን ስናይ በቁጥርም በይዘትም ብዝሃነት አለው ለማለት እንቸገራለን፡፡ የሚዲያ ብዝሃነት ከሌለ ደግሞ መንግስት ድክመቶቹን መረዳት የሚችልበት አማራጭ አያገኝም፡፡ ይሄ ለመንግስት ውድቀት ነው፡፡ ብዝሃነት ስንል የሃሳብ ብዝሃነት እንጂ ቁጥር ላይ ካተኮርን ስህተት ነው፡፡ ለምሳሌ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በአሁን ሰአት ሃሳባቸውን የሚያቀርቡበት አማራጭ የላቸውም፡፡ ፕሬሱም የሚገባውን ያህል ቦታ እየሰጣቸው ያለ አይመስለኝም፡፡ በጥቂቱ የማየው አንዳንድ ጋዜጦች በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሲያወያዩዋቸው ብቻ ነው፡፡ ይሄ ጥቂትም ቢሆን የነሱን ሀሳብ ማግኘት ለሚፈልግ ህዝብ እጅግ ጠቃሚ ከመሆኑም በላይ መንግስት አቋማቸውን በተዘዋዋሪ እንዲረዳና ምክራቸውን የሚቀበል ከሆነ እንዲቀበል ይረዳዋል፡፡ በዚህ መንገድ ውስጥ ያሉ ፕሬሶች የሃሳብ ብዝሃነት ትርጉሙ የገባቸው ይመስለኛል፡፡ መንግስት በበኩሉ፤የሚዲያ ፖሊሲውን ልማታዊ ብሎ ጠቅልሎ ጨርሶታል፡፡


===============================


“ራስን በራስ ሳንሱር የማድረግ ችግር አለ”

ዶ/ር ነገረ ሌንጮ
(በአ.አ.ዩ.የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ት/ት ክፍል ዲን)

የአንድ ሚዲያ እድገት የሚለካው አንደኛ የተቋሙ ብቃት፣ የህግ ማዕቀፉ አሠሪነት ምን ያህል አሳታፊ ነው የሚሉት መታየት አለባቸው፡፡ የባለሙያ ደረጃውስ ምን ይመስላል የሚለውንም ማየት አለብን፡፡ ከፕሬስ ነፃነት ጋር ተያይዞ የሚነሳው የፖለቲካል ኢኮኖሚው ለሚዲያ የሚሰጠው ግምት ምንድን ነው የሚለውን ማየት ይኖርብናል፡፡ ከዚህ አኳያ የኛን ሀገር ስንመለከት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ስለ ሚዲያ ነፃነት መናገር ከጀመርን ሁለት አስርት አመታት ብቻ ነው ያስቆጠርነው፡፡
ስርአቱ ራሱ የሚዲያ ጉዳይን ህጋዊ አድርጓል፡፡ በህገመንግስቱም፣ በሚዲያ ህጐችም የሚዲያ ነፃነት ተደንግጓል፡፡ መረጃ ማግኘት የዜጐች መብት እንደሆነ፣ መንግስት ደግሞ ስልጣኑን የሚያገኘው ከህዝብ እንደሆነ ተደንግጓል፡፡ ይሄ እንዴት ነው ተግባር ላይ እየዋለ ያለው ስንል፣ የጋዜጠኞች ብቃትንና የሚዲያ ተቋማትን ጥንካሬ ይጠይቃል፡፡ በአተገባበሩ ላይ ክፍተቶች እንዳሉ የማይካድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ሁሉም ሃላፊነት ተሠምቷቸው በትክክል ይሠራሉ ብለን ብንጠይቅ፣ የሚሠሩም አሉ የማይሰሩም አሉ፡፡ ከመንግስት ባለስልጣናትም ህጉን በተገቢው የማያስፈጽሙ ይኖራሉ፡፡ በአለማቀፍ ሪፖርቶች፣መንግስት ሚዲያን ያፍናል የሚል ሪፖርት ይወጣል፡፡ እንደዚህ አይነት ችግር ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን በትክክል የጋዜጠኝነትን ሙያዊ መሠረቱን ጠንቅቀው አውቀው የሚሠሩት ናቸው የሚታሠሩት? የሚሰደዱት? ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ እንደኔ ጋዜጠኞቹም መንግስትም ጋ ችግር አለ፡፡ አንዳንድ ጋዜጠኞችም ራሣቸውን በራሳቸው አላስፈላጊ ሳንሱር ያደርጋሉ፡፡ ይሄ ሲሆን ለህዝብ የተሰጠው መረጃን የማግኘት መብት ይጨፈለቃል፡፡ እኔ ችግር ያለው ከህገ-መንግስታዊ ስርአቱ አይመስለኝም፤የግለሰቦች ችግር ነው፡፡ ባለፉት 20 አመታት በእነዚህ ውጣ ውረዶች ውስጥ አልፎ የመጣ ፕሬስ እየተገነባ ነው የሚል እምነት አለኝ፡፡
“የሚዲያ ብዝሃነትን በእርግጥስ ያከበረች ሀገር ነች ወይ” የሚለው ጥያቄ፣ በኢትዮጵያ ይቅርና አደጉ በተባሉ ሃገሮች እንኳ “አዎ” እና “አይደለም” በሚል የሚመለስ አይደለም፡፡ ለምሣሌ መጽሐፍት የፈለጋቸውን ሃሳብ እያንፀባረቁ ይታተማሉ፡፡ አልፎ አልፎ ደግሞ ገደብ የሚጣልበት ሁኔታ አለ፡፡ ይሄ ተገቢ አይሆንም፡፡ የህዝብ ሚዲያዎች ላይ ሃሳብ ምን ያህል ብዝሃነት አለው የሚለውን ስናይ፣ ትንሽ ችግር አለ፤ተከልክለው አይደለም፡፡ የግለሰቦች ራስን በራስ ሳንሱር የማድረግ ችግር ነው፡፡ በመርህ ደረጃ ብዝሃነት ይኑር የሚል አመለካከት አለ፤ ይሄን ወደፊት በተግባር ማምጣት አለብን፡፡



Read 3130 times