Saturday, 07 May 2016 13:27

ምና ድራማዎቻችን ሥጋት፣ ”ቃና” ወይስ ...?

Written by  አስናቀ ሥነስብሐት
Rate this item
(1 Vote)

• ባለሙያዎቻችን ራሳቸውን ለማብቃት ምን ያድርጉ?
• የ“ቃና አካሄድ” በወፍ በረር ቅኝት ምን ይመስላል?

 (የመጨረሻው ክፍል)
ባለፉት ሁለት ተከታታይ ጽሑፎች፣ ከቃና ቴሌቪዥን ጋር ተያይዞ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራት የተነሱ ሥጋቶችን መነሻ በማድረግ የቴሌቪዥን ድራማዎቻችንንና ፊልሞቻችንን ሁኔታ ጠቅለል ባለ መልኩ ለመቃኘት ሞክሬያለሁ፡፡ በእነዚያ ጽሑፎች የእስካሁኑ የኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ድራማ ሂደት በራሱ ሊፈታቸው ሲችል ያልፈታቸውን ችግሮቹን በመጠቆም የዘርፉ ችግር የሥራዎቹ በተገቢው ደረጃ ያለመቅረብ እንጂ የ”ቃና” መምጣት አለመሆኑን ከማንሳቴም በተጨማሪ፣ የዘርፉ ባለሙያዎች (በተለይም ደራሲዎች) ማድረግ ያለባቸውን ዝግጅቶች በጥያቄ መልክ በማቅረብ  የሥራዎቹን የጥራት ደረጃ መቃኘት ጀምሬ ነበር፤ ከዚያው ልቀጥል፡፡
በክፍል 2 ጽሑፌ ማጠቃለያ ላይ አንስቻቸው የነበሩትን ጥያቄዎች ከባለሙያዎቹ በሚገኝ ምላሽ፣ ወይም በድራማዎቻችን ላይ በሚደረግ ጥናት ለመመለስ ብንሞክር፣ አጥጋቢ መልስ እናገኛለን ብዬ አላምንም፡፡ ለምን? ቢባል፣ ሥራዎቹ ራሱ የሚናገሩት ይህንኑ ስለሆነ! እስቲ፣ እስከ ዛሬ ድረስ በአገራችን የቴሌቪዥን ቻናሎች የቀረቡትንና እየቀረቡ ያሉትን ድራማዎች በዓይነ-ልቦናችን እንመልከታቸው፡፡ ያለ ምንም ጉድለትና ግድፈት፣ ያለ ምንም አስተቺ አቀራረብ የተከታተልናቸው ድራማዎችን ማግኘት በጣም ይቸግራል፡፡ በእኔ ውሱን ግምገማ፣ ”እዚህ ላይ ልክ አይደለም” ሳይባል ያለፈ ሲሪያል ድራማም ሆነ ሲትኮም አላስታውስም፡፡ ይህንን ስል፣ በድራማዎቻችን ላይ ”ስለ ምን ጉድለት ተገኘ?” የሚል ጥያቄ እያነሳሁ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ፡፡ ጉድለትማ፣ እንኳን በእኛ አገር ጀማሪ የድራማ ሥራ፣ በታላላቆቹ የሆሊውድ ሥራዎችም ላይ አይጠፋም፡፡ ልዩነቱ፣ የእኛዎቹ በወረቀት ላይ ሊስተካከሉ ሲችሉ፣ ባለማወቅ ወይም በቸልተኝነት የሚፈጸሙት ግድፈቶች ብዙ መሆናቸው ላይ ነው፡፡ ባለፈው ጽሑፍ ላይ እንደጠቆምኩት፣ ”በወረቀት ላይ” ስል፣ በድራማው ድርሰት ላይ ሊደረጉ ስለሚችሉ ማስተካከያዎች ማለቴ እንደሆነ እናስታውስ፡፡ እኔ በእስካሁኑ የቴሌቪዥን ድራማ ተመልካችነት ልምዴ፣ በድራማዎቻችን የተሳታፊዎች መግለጫ (credit) ላይ የፊልሙን ድርሰት የሚያርምና ማስተካከያ የሚሰጥ ባለሙያ (Script Editor) ሲጠቀስ አላየሁም፡፡ ለዚህም ይመስለኛል፣ በተለይ በቅርብ ጊዜዎቹ ሥራዎች ላይ፣ ቋንቋና አገላለጽ፣ የታሪክ ፍሰትና የሁነቶች ቅደም-ተከተል መሥመር ሲስቱ ብዙ ጊዜ የሚያጋጥመን፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ፣ ሙያዊ የሆኑ ጉዳዮችን የሚያሳዩ ትዕይንቶች በሚጻፉበትም ሆነ በሚተወኑበት ጊዜ፣ የሙያዉን ሥነ-ምግባርና ትክክለኛ አሠራር ማሳየታቸውን ማረጋገጥ ላይ ድራማዎቻችን ግልጽ የሆነ ችግር አለባቸው፡፡ እንደ ምሳሌ፣ ፖሊስን የሚመለከት ትዕይንትን ብንወስድ፣ ሁሉም ማለት በሚያስደፍር ደረጃ፣ ድራማዎቻችን ፖሊስን በትክክል ለመግለጽ ይሳናቸዋል፡፡ የፖሊስ ሰላምታ አሰጣጥ፣ አለባበስ፣ የባለጉዳይ መስተንግዶ፣ የምርመራ ዘዴ፣ የተጠርጣሪ አያያዝ፣ ወዘተ …፣ በትክክል የተገለጸባቸውን የቅርብ ጊዜ ድራማዎቻችንን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ነገር ታዲያ፣ ጊዜ ወስዶ በማጥናት፣ የሙያውን ባለቤቶች በማነጋገር፣ ሙያው ያለው ሰው በተቆጣጣሪነት (supervision) እንዲመለከተው በማድረግ ሊስተካከል የሚችል እንጂ፣ ትልቅ ኢንቨስትመንት የሚጠይቅ ሥራ አልነበረም፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎቻችን ግን፣ በአብዛኛው አይጨነቁበትም፡፡
እንዲህ እንዲህ እያልን፣ የድራማዎቻችንን ግዙፍ፣ ግን በወረቀት ላይ ሊስተካከሉ የሚችሉ ስህተቶችን መዘርዘር እንችላለን፡፡ እነዚህን ውስጣዊ ክፍተቶች ማስተካከል ቢቻል ኖሮ፣ ሌሎቹ ውጫዊ ችግሮች በድርሰቱ ውጤታማነት ሊሸፈኑ ይችሉ ነበር፡፡ ሌሎችም ብዙ ውስጣዊ ችግሮች ቢኖሩም፣ ቀላሉን የድርሰት ላይ ችግር ካየን ለአሁኑ የሚበቃን ይመስለኛል፡፡ በመቀጠል ደግሞ፣  ”ቃና ቲቪ” በጀመረው አካሄድ ላይ ጥቂት ልበል፡፡
የ”ቃና” አካሄድ
ስለ #ቃና” ቲቪ አመሠራረትና የሥራ እንቅስቃሴ መቼም ብዙ ስለተባለ አሁን አልመለስበትም፡፡ ከርዕሳችን ጋር በተያያዘ ግን፣ ቻናሉ 70 በመቶ የሥርጭት ጊዜውን ለውጭ አገር ተከታታይ ድራማዎችና ፊልሞች በመመደብ በቀን የ24 ሰዓታት ሥርጭት የሚያቀርብ መሆኑን እንደ መነሻ ብንይዘው መልካም ነው፡፡ ”ቃና” በዚህ የፊልምና ድራማ አቅርቦቱ፣ ከህንድ፣ ከቱርክ፣ ከጣሊያን፣ እና ከደቡብ ኮሪያ፣ እና ከዩናይትድ ስቴትስ የተመረጡ ድራማዎችን፣ ተከታታይ ፊልሞችን (series) እና ሲትኮሞችን በአማርኛ ቋንቋ የድምጽ ትርጉም (dubbing) ያቀርባል፡፡
ድርጅቱ በተደጋጋሚ እንደገለጸው ከሆነ፣ ይህንን አቀራረብ የመረጠው የኢትዮጵያን የቴሌቪዥን ተመልካቾች ፍላጎት በሚመለከት ጥናት ካካሄደ በኋላ ነው፡፡ ድርጅቱ የኢትዮጵያዊያንን የሳተላይት ቴሌቪዥን ተመልካችነት ልምድና ምርጫ አስመልክቶ ባስጠናው ጥናት መሠረት፣ 50 በመቶ የሚሆኑት ተመልካቾች የውጭ ፕሮግራሞችን ያለ ምንም ባሕላዊ እሳቤዎች፣ በውጭ ቋንቋ እንደሚመለከቱ እንደተረዳ ይናገራል፡፡ በ12 ከተሞች መካሄዱ በተገለጸው ጥናት፤ 3,500 ሰዎች ቃለ-መጠይቅ የተደረገላቸው ሲሆን በጥናቱ ግምት መሠረት፤ በገጠርና በከተማ የሚኖሩና የሳተላይት ቴሌቪዥንን የሚከታተሉ 18.5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን የአገር ውስጥና የውጭ አገር ፕሮግራሞችን እንደሚመለከቱ ተመልክቷል፡፡ ከ”ቃና” መሥራቾች መካከል አንዱ የሆኑት ኤሊያስ ሹልዝ ለሪፖርተር ጋዜጣ በሰጡት ቃለ-ምልልስ እንደገለጹት፣ ጣቢያቸው የውጪዎቹን ፕሮግራሞች ለኢትዮጵያዊው ተመልካች እንዲስማሙ በጥንቃቄ የመረጠ ሲሆን በራሱ ከሚያዘጋጃቸው የፕሮግራም ይዘቶች በተጨማሪ፣ የተመረጡ የአገር ውስጥ ፕሮግራሞችን ከውጭ ተባባሪዎች ጋር ለማቅረብ በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነው፡፡
ይህንን የ”ቃና”ን ሐሳብ እንደ መነሻ ሐሳብ ጥሩ ነው ብለን ልንቀበለው የምንችለው ቢሆንም፣ ”ቃና” በኢትዮጵያ ሥራውን ለመጀመር ሲነሳ፣ በአገር ውስጥ ጥሩ ሥራዎች መኖር አለመኖራቸውን ለማወቅ የሞከረ አልመሰለኝም፡፡ ተሞክሮ ከሆነ እሰየው! ካልተደረገ ግን፣ ስህተት ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም፣ ጥሩ ሥራ በአገር ውስጥ ከተገኘ፣ ከቱርክም ሆነ ከህንድ፣ ከጣሊያንም ሆነ ከኮርያ፣ የተሻለ ቅርበት ያለውን ሥራ ተመልካቹ ይፈልጋል ብዬ ስለማምን ነው፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን፣ ”ቃና” ይህንን ቢያስብበት መልካም ይሆናል እላለሁ፡፡ በተጨማሪም፣ ”ቃና” ያለውን አቅም ለአገር ውስጥ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ለማካፈል ፈቃደኛ ቢሆንና የልምድ ልውውጥ ቢደረግ፣ አሁን ያለውን የ70/30 ምጣኔ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለአገር ውስጥ ሥራዎች በሚያመች መልኩ ለማስተካከል ያስችላል የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡
ለኢትዮጵያ የፊልምና የቴሌቪዥን ድራማ ዘርፍ ዕድገት ምን ይደረግ?
ስለ ቴሌቪዥን ድራማዎቻችን ድክመቶች በመጠኑ ጥቆማ ለመስጠት መነሻ የሆነኝ ”ቃና” የጀመረው አቀራረብ ያስነሳው አቧራ ይሁን እንጂ፣ ፊልሞቻችንና ድራማዎቻችን ሊያሻሽሏቸው ስለሚገቡ ነገሮች ማሰብ ከጀመርኩ ቆይቻለሁ፡፡ በኪነ-ጥበብ ማኅበራቱ የመጋቢት 21 መግለጫ ላይ እንደተመለከተው፣ የቴሌቪዥን ድራማ ታሪካችን በዕድሜው ትንሽ ነው፤ በዚህም ምክንያት ብዙ ማደግና መብሰል ይጠበቅበታል፡፡ ለማደግ፣ ለመብሰልና ለመሻሻል ደግሞ ሊያደርጋቸው የሚገቡ በርካታ ሥራዎች አሉት፡፡ ከእነዚህ ሥራዎች መካከል፣ አሁኑኑ ሊያከናውናቸው የሚችሉትን ጥቂቶቹን እነሆ፡-
ሙያዊ ዕውቀትን ማዳበር፡- በተደጋጋሚ ሲገለጹ ከሚሰሙት የዘርፉ ችግሮች መካከል አንደኛው የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት በዘርፉ የሚሰማሩ ሰዎች የተለያዩ መንገዶችን በመጠቀም ዕውቀታቸውን ሊያዳብሩ ይገባል፡፡ ዕድሉ ያላቸው ትምህርት ቤት ገብተው ሙያውን ሊማሩ ሲችሉ፣ ያልቻሉት ደግሞ አማራጭ መውሰድ አለባቸው፡፡ ከሰሞኑ የ”ቃና” ጉዳይ ጋር ተያይዘው ሲነሱ ከሰማኋቸው የዘርፉ ችግሮች መካከል አንደኛው ዘርፉን በሚመለከት ለመማሪያነት በሚያገለግሉ መጻሕፍት ላይ የተጣለው ከፍተኛ ታክስ ነው፡፡ ችግርነቱ ላይ ብስማማም፣ ባለሙያዎቹም ሆነ በዘርፉ ላይ ለመሠማራት የሚፈልጉ ሌሎች ሰዎች፣ ባሉን ጥቂት አብያተ- መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን መጻሕፍት ለማንበብ መሞከር ቀርቶ ከነመኖራቸውም የሚያውቋቸው አይመስለኝም፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የንባብ ባሕላችን ደካማነት ነው፡፡ ሌላው ቢቀር፣ በዚህ የመረጃ ዘመን፣ ውቅያኖስ ከሆነው የኢንተርኔት መድረክ ውስጥ ለቁጥር የሚያታክቱ ዋቢ መጻሕፍት በነፃ ይገኛሉ፡፡ እነዚህን ሁሉ በመጠቀም ዕውቀትን ማዳበር ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፣ የሌሎች አገሮችን ፊልሞች በደፈናው ”ባሕል አደፍራሽ” ብሎ ከማውገዝ፣ ቀረብ ብሎ እንዴት እንደተሠሩ ማየት ሌላው የመማሪያ መንገድ ነው፡፡ በተለይ፣ በታሪክና በባሕላዊ ይዘታቸው ለእኛ ቀረብ የሚሉትን አገራት ፊልሞች ፈልገን ብንመለከት፣ ከታሪክ አወቃቀር አንስቶ እስከ ድኅረ-ዝግጅት ድረስ ብዙ ልንማርባቸው እንችላለን፡፡ ”የት እናገኛቸዋለን?” ከተባለ የተለያዩ መንገዶች አሁንም አሉ፡፡ በየዓመቱ በአዲስ አበባ (አልፎ አልፎ በሌሎች ከተሞች) የሚካሄዱ የውጭ አገራት የፊልም ፌስቲቫሎች አሉ፡፡ የአውሮፓ የፊልም ፌስቲቫል፣ አይቤሮ-አሜሪካን የፊልም ፌስቲቫል፣ የኢራን የፊልም ሳምንት፣ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እንዳለመታደል ግን፣ ብዙዎቹ የዘርፉ ተዋንያን እነዚህን መድረኮች ሲታደሙ አላይም፣ ከነመኖራቸውም አያውቋቸውም፡፡ እናም፣ ባለሙያዎቻችን ዓይንና ጆሯቸውን ከፍተው ቢመለከቱ ብዙ የዕውቀት ምንጮች አሉ፤ መጠቀም የእነርሱ ፋንታ ነው፡፡
በትብብር መሥራት፡- እስከ ዛሬ እንደተመለከትነው፣ አብዛኞቹ የቴሌቪዥን ድራማዎቻችን በአንድ ፕሮዲዩሰር (የፕሮዳክሽን ድርጅት) ብቻ የሚሠሩ ናቸው፡፡ ይህ የተበታተነ አሠራር ደግሞ ምሉዕነት የጎደለው ሥራ ለተመልካች እንዲቀርብ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ የተለያዩ ሐሳቦችና ዕውቀቶች በአንድ ላይ ተዋሕደው ሲቀርቡ ሊገኝ የሚችለውን መልካም ፍሬ እያሳጣን  ይገኛል፡፡ ስለዚህ፣ የዘርፉ ባለሙያዎች፣ በአገር ደረጃ የተጠናወተንን የግለኝነትና የ”ጥሎ-ማለፍ” አባዜ ሰብረው በመውጣት፣ ሁለትና ሦስት የፕሮዳክሽን ድርጅቶች በአንድ ፕሮጀክት ላይ አብረው ቢሠሩ፣ በሐሳብ፣ በገንዘብ፣ በመሣሪያ፣ በልምድና በሌላውም ያላቸውን አቅም አዋሕደው በመሥራት ውጤታማ የኪነ-ጥበብ ሥራዎችን ለተደራሲው ከማቅረባቸውም ባሻገር፣ ለዘርፉ ዕድገት ማነቆ የሆኑትን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች ለማስወገድ የሚችል ጠንካራ ግንባር መፍጠር ያስችላቸዋል፡፡
የሕግ ማዕቀፍ እንዲፈጠር መጣር፡- የኪነ-ጥበብ ማኅበራት ”ሥጋታችን ነው” ባሉት የ”ቃና” ቴሌቪዥን አካሄድ ላይ ያሳዩትን ኅብረት፣ በመንግሥት ላይ ግፊት ለማድረግም ሊጠቀሙበት ይገባል፡፡ መንግሥት ዘርፉ የሚመራበትን የሕግ ማዕቀፍ ለመፍጠርና ያለውንም ከባቢ ለማጠናከር እንዲሠራ እነዚህ ማኅበራት ግፊት ማድረግ አለባቸው፡፡ እስካሁን ግን ይህንን እያደረጉ ስለመሆኑ እጠራጠራለሁ፡፡ አንድ ምሳሌ ላንሳ፤ የኢትዮጵያ የፊልም ፖሊሲ ረቂቅ ለባለድርሻ አካላት ውይይት ከቀረበ ወደ ሁለት ዓመት እየተጠጋ ነው፡፡ የዘርፉ የሙያ ማኅበራት ከዚያ ውይይት በኋላ ፖሊሲውን ሥራ ላይ የማዋሉ ሂደት ምን ላይ እንደደረሰ ጠይቀዋል? ተከታትለዋል? እኔ አላውቅም፡፡ ፖሊሲው በቶሎ ጸድቆ ሥራ ላይ ቢውል እኮ፣ አሁን የምንወያይባቸውን ችግሮች ለመፍታት በጠቀመ ነበር፡፡ የባሕል መበረዝን ለመከላከል፣ የፊልሞችን ደረጃ ለማውጣት፣ የዕድሜ ገደብን ከአገራችን ሁኔታ ጋር አጣጥሞ ለመወሰን፣ ለዘርፉ ሊሰጡ የሚገባቸውን ማበረታቻዎች ለመስጠት የሚያስችሉ ህጎችን ለማውጣት፣ወዘተ-- የፖሊሲው መጽደቅ ወሳኝነት አለው፡፡ ማኅበራቱ ለዚህ ቢተጉ ያስመሰግናቸዋል፡፡
ማጠቃለያ
በተከታታይ ጽሑፎቼ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራት ”ቃና”ን አስመልክቶ የተነሳውን ቅሬታ ለመሞገት ስሞክር፣ እስካሁን በዘርፉ የተሠሩትን ሥራዎች ዕውቅና በመስጠትም ጭምር እንደሆነ ከግንዛቤ እንዲገባልኝ እፈልጋለሁ፡፡ በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ የቴሌቪዥን ድራማዎችን እያቀረቡልን ላሉት የዘርፉ ባለድርሻዎች ምስጋናዬ ከፍ ያለ ነው፡፡ ከተነሳው ቅሬታ ጋር ያለኝ ብቸኛ ልዩነት ”በእጃችን ባለው አቅም ልናስተካክለው በምንችለው ጉድለት የሚፈጠረውን የተመልካች አማራጭ ፍለጋ በውጭ አካል ላይ ማላከክ አግባብ አይደለም” የሚል ነው፡፡ የራስን ችግር ሳይፈቱ ሌላውን ለመውቀስ መሯሯጥ ሥራዎቹን ከነድክመታቸውም ጭምር በትዕግሥት የሚመለከተውን ተመልካች አለማወቅና አለማክበር ይሆናል፡፡ ውጫዊ ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መሥራትን ከለመድንና በውስጥ ችግራችን ላይ ከፍ ያለ ትኩረት ሰጥተን ሥራዎቻችንን በአግባቡ ከሠራን (ምንም እንኳን ሥራው ከባድና ረዥም ጉዞ ያለው ቢሆንም) ”ቃና”ም ሆነ ሌላ የቴሌቪዥን ጣቢያ፣ አይደለም ሰባ በመቶ፣ መቶ በመቶ የሥርጭት ሰዓቱን ለውጭ ፊልምና ድራማ ቢሰጥ ሥጋት ሊሆን አይችልም፤ የራሱን ታሪክ በራሱ ቋንቋ መመልከት የሚፈልግ ተመልካች እስካለ ድረስ፡፡ ስለዚህ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቻችን፣ ”ሥራውን ከራሳችሁ ጀምሩ!”

Read 3241 times