Saturday, 07 May 2016 13:23

የፍቅር ባንዲራ!

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

        ትንሳዔ በመጣ ቁጥር የማስታውሰው አንድ ታሪክ አለ፡፡ ደራሲው ሄንር ቫን ዳይኬ (Henry van Dyke) ነው፡፡ ዳይኬ፤ ‹‹The Story of the Other Wise Man›› በሚል የፃፈው አጭር ኖቭል (Short Novel) ወይም ረጅም አጭር ልቦለድ (Long Short Story) ነው፡፡ ርዕሱ ወደ አማርኛ ሲመለስ፤ በቀጥታ ‹‹የሌላኛው (ታሪክ ያላወቀው) ሰብአ ሰገል ታሪክ›› ሊባል ይችላል። በለዛ መተርጎም ከፈለግን ‹‹የአራተኛው ሰብአ ሰገል ታሪክ›› ማለት ይቻላል -- ሰብአ ሰገል ሦስት እንደሆኑ ስለሚታመን፡፡ የጓደኛዬ አባት አለቃ አያሌው ደግሞ ‹‹ሰብአ ሰገል ኢትዮጵያውያን ናቸው›› ይሉ ነበር፡፡ ይህንንም ‹‹አዲስ አድማስ›› ጋዜጣ በመጀመሪያ ዕትሟ ዜና አድርጋ አውጥታው ነበር፡፡ ዘወትር በትንሳዔ የማስታውሰው የሄንር ቫን ዳይኬ ድርሰት በ1895 ዓ.ም (እኤአ) የታተመ ነው፡፡ ከዛ ወዲህ ብዙ ጊዜ ለእንደገና ህትመት በቅቷል፡፡ የቴሌቭዥን ድራማ ሆኖ ቀርቧል። ‹‹The Fourth Wise Man›› በሚል ርዕስ በፊልም መልክ ተሰርቶ ታይቷል፡፡ ዳይኬ አዲስ ታሪክ ፈጥሯል ለማለት አይቻልም፡፡ ይልቅስ በማቴዎስ ወንጌል የምናነበውን ታሪክ አምልቶና አስፋፍቶ ጽፎታል ማለት ይቻላል፡፡ የታሪኩ ባለቤት አርጣባን (Artaban) ነው፡፡ ይህ ሰው እኛ የሰገል ሰዎች በሚል ከምንጠቅሳቸው (ሌሎች ‹‹ማጂ›› ይሏቸዋል) አንዱ ነው፡፡ እንደ ፀሐፊው ሐሳብ፤ አርጣባን ‹‹የተወለደው የአይሁድ ንጉስ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና›› እያሉ ከምሥራቅ ወደ ኢየሩሳሌም ከመጡት ሦስት ሰዎች ኋላ መባ ይዞ ኢየሩሳሌም የደረሰ አራተኛ ሰብአ ሰገል ነው፡፡ አርጣባን የፍቅር ባንዲራ ነው፡፡ እንግዲህ ዳይኬ ስለ አራተኛው የሰገል ሰው የሚተርከው ታሪክ በአጭሩ እንዲህ ነው፡-

አራተኛው ሰብአ ሰገል
አራተኛው ሰብአ ሰገል፤ እንደ ሌሎቹ የሰገል ሰዎች የአይሁድ ንጉስ በይሁዳ ቤተልሔም መወለዱን በምሥራቅ ባየው ኮከብ ተረድቶ ወደ ይሁዳ ለመሄድ ተነሳ፡፡ ሕፃኑን በዓይኑ ለማየት አስበው በሳጥናቸው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም ይዘው እንደመጡት ወገኖቹ፤ እርሱም ለህፃኑ የሚሰጥ የሰንፔር ድንጋይና ዋጋው እጅግ የበዛ እንቁ ይዞ ነበር፡፡ ይህን ይዞ ጉዞ ጀመረ፡፡
ታዲያ በመንገዱ ለሞት የሚያጣጥር አንድ ሰው አግኝቶ፣ እርሱን ሲያስታምምና ሲረዳ ብዙ ጊዜ ቆየ፡፡ ወደ ኋላ ቀረ፡፡ ወደ ኢየሩሳሌም ይጓዙ ከነበሩት ሦስቱ የሰገል ሰዎች ጋር ለመገናኘት እንዳይችል ሆኖ ወደ ኋላ ቀረ፡፡ በርሃውን አቋርጦ ይጓዝ ከነበረው ቅፍለትም ተለየ፡፡ ከተጓዦቹ ጋር መገናኘት አልቻለም፡፡ አሁን በረሃውን ብቻውን ማቋረጥ ሊኖርበት ነው፡፡ ግን በረሃውን በፈረስ ሊያቋርጥ አይችልም፡፡ ስለዚህ ለህጻኑ ከያዘው መባ አንዱን ነገር በመሸጥ፤ ግመልና ለጉዞው አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ነገሮችን መግዛት ግድ ሆነበት፡፡ የሚያስፈልገውን ነገር ከገዛ በኋላም ጉዞ ጀመረ፡፡ ከብዙ እንግልት በኋላ ቤተልሄም ደረሰ፡፡ ግን የደረሰው ሦስቱ ሰብአ ሰገሎች ከሄዱ በኋላ ነበር፡፡ እነሱ ከሄዱ በኋላ ደግሞ፤ ‹‹የጌታ መልአክ በህልም ለዮሴፍ ታይቶ - ሄሮድስ ህፃኑን ሊገድለው ይፈልገዋልና ተነሣ፣ ህፃኑንና እናቲቱንም ይዘህ ወደ ግብጽ ሽሽ›› ተባለ፡፡ ዮሴፍ ህፃኑንና እናቲቱን በሌሊት ይዞ ወደ ግብጽ ሄደ። ስለዚህ አርጣባን ቤተልሔም ሲደርስ ኢየሱስ ወደ ግብጽ ወርዶ ነበር፡፡ ሊያገኘው አልቻለም፡፡ እናም ወደ ግብጽ ለመሄድ ተነሳ፡፡ ሆኖም አንድ ያልታሰበ ነገር ገጠመው፡፡ አርጣባን የአንድ ህጻንን ህይወት ለማትረፍ  ከያዘው መባ አንድ ነገር መሸጥ ግድ ሆነበት፡፡ ይህን አድርጎ የህጻኑን ህይወት አተረፈ። እንደገና ወደ ግብጽ ለመሄድ ጉዞ ጀመረ፡፡ በብዙ መከራ በረሃውን አቋርጦ ግብጽ ደረሰ፡፡
እዚያም ደርሶ፤‹‹የአይሁድ ንጉስ ኢየሱስ ወዴት ነው? ኮከቡን በምሥራቅ አይቼ ልሰግድለት መጥቻለሁና›› እያለ ጠየቀ፡፡ የጠየቃቸውም ሰዎች፤ ‹‹ከእናቱ ጋር በዚህ ቆይቶ፤ አንተ ወዲህ ከመምጣትህ በፊት ወደ እስራኤል አገር ሄደ›› አሉት፡፡ እንደ ገና ጌታውን ፍለጋ ወደ እስራኤል ተመለሰ፡፡ እስራኤልም ደርሶ፤ ‹‹ክርስቶስ ወዴት ነው?›› ብሎ ሲጠይቅ፤ ‹‹ትናንት ወደዚህ ከተማ ሄደ›› ይሉታል፡፡ ይሄዳል፡፡ ይጠይቃል፡፡ ‹‹ትናንት ወደዚያ አውራጃ ሄደ›› ይሉታል፡፡ ኢየሱስን ፍለጋ በብዙ አገር ተንከራተተ፡፡ ለብዙ ዓመታት ከሐገር- ሐገር ሲዞር በመንገድ የእርሱን ዕርዳታ የሚሹ ሰዎች እየገጠሙት ብዙ ደግነት እያደረገ፣ 33 ዓመታትን ሲንከራተት ኖረ፡፡
አርጣባን 33 ዓመት ሙሉ ጌታውንና ብርሃንን የሚፈልግ መንፈሳዊ ተጓዥ ሆኖ ኖረ፡፡ ከወጣትነት ወደ አዛውንትነት ተሸጋገረ፡፡ ከ33 ዓመታት በፊት ለህጻኑ የሚሰጥ መባ ብሎ የያዘው ንብረት ሁሉ አለቀ፡፡ አሁን ክርስቶስ የመጨረሻውን ራት በልቷል፡፡ ከሚያንገላቱትና ከሚሰቅሉት እጅ ገብቷል፡፡ መስቀሉን ተሸክሞ ወደ ጎለጎታ ሊወጣ ትንሽ ሰዓታት ብቻ ቀርተውታል፡፡ በአርጣባን እጅ የቀረች አንዲት እንቁ ብቻ አለች፡፡ በመጨረሻው ሰዓት ጌታውን ፍለጋ ሲሄድ፤ በመንገድ አንዲትን ወጣት በባርነት ለመሸጥ የሚደራደሩ ሰዎችን አገኘ፡፡ በእጁ የነበረችውን የመጨረሻ እንቁ ሰጥቶ ወጣቷን ከባርነት ነጻ አወጣት፡፡ 33 ዓመታት የተንከራተተው አርጣባን፤ጌታውን ለማግኘት ሲባዝን፣ ከአንድ ጣሪያ የወደቀ ድንጋይ አናቱ ላይ ወድቆበት፤ በጠና ታመመ፡፡ ሊሞት ያጣጥር ጀመረ፡፡ ይህን ሁሉ ዓመታት ኢየሱስን ለማግኘት ሲንከራተት ቆይቶ እንዳሰበው ኢየሱስን ባያገኘውም፤ በመንገዱ ብዙ የደግነት ሥራ እየሰራ ዘመኑን አሳለፈ፡፡ አሁን ለሞት የሚያሰጋ አደጋ ገጥሞት ከአልጋ ውሏል፡፡ በመጨረሻ ለሞት ማጣጣር ሲጀምር፤ ‹‹እውነት እልሃልሁ፤ ከሁሉ ለሚያንሱ ከእነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረግከው ለእኔ አድርገኸዋል›› የሚል አንድ ድምጽ ሰማ፡፡
እናም እርጋታን በተጎናጸፈ የመደነቅ ብርሃንና በሐሴት ተውጦ ምድሪቱን ተሰናበተ። ከ33 ዓመታት በፊት ይዞት የመጣው መባም ተቀባይነት አገኘ፡፡ አራተኛው ሰብአ ሰገል ለ33 ዓመታት ከፈለገው ንጉስ ጋር ተገኛኘ፡፡ ትንሣዔ ሆነ፡፡ ሁሌም በትንሣዔ ዋዜማ የማስታውሰው ታሪክ ይህ ነው፡፡
የክርስትና እምነት ተከታዮች የሆናችሁ፤ የዚህ ጽሑፍ አንባቢያን፤እንኳን ለብርሃነ ትንሳዔው አደረሳችሁ፡፡ ይህ ታሪክ፤ ከመቃብራቸው ባሻገር ፀንቶ ለሚኖር የሰው ልጆች አገልግሎት ህይወታቸውን ለማዋል የሚቀኑትን፤ በቀኖና ወይም በሐይማኖታዊ ስርዓት ያልተቀነበበ መልካም ፈቃድ ያላቸውን፣ በመፈቃቀድና አንዱ አንዱን ለማገልገል ዝግጁ የሚሆንበትን ስርዓት የሚናፍቁትን ሰዎች ልብ የሚያነሳሳ ታሪክ ነው፡፡
በዋልት ዊትማን  ግጥም ልሰናበት፡፡ እንዳላበላሸው፤ አልተርጉመው፤
 “O Spirit, as a runner strips
Upon a windy afternoon
 Be unencumbered of what troubles you—
 Arise with grace
And greatly go, with the wind upon your face.”


Read 2093 times