Saturday, 07 May 2016 13:14

ተናዳፊ ግጥም

Written by  ዕዝራ አብደላ
Rate this item
(7 votes)

[ኄኖክ ስጦታው ሲያነብ የመሰጠው ግጥም ካለ፥ በአማርኛ እንዲነበብ ይተጋል]

ኄኖክ ስጦታው በአመዛኙ እሳቦት የነከሰ ግጥም፥ አንዳንዴ የከተማችን ድባብ ሲጫጫነን ደግሞ ፖለቲካዊ ይሆን ብልግናዊ ፍካሬ የነዘረበት የሆነ ቀልድ አነጣጥሮ ይወረውራል። በማኅበራዊ ድረገፀ በ facebook ከዕድሜያቸው ጊዜ እየሰረቁ የሚጽፉ ወጣቶች አሉ፤ እንደነገሩ የሆኑት ያመዝናሉ። በአንፃሩ የተሻለ እሳቦትና ጥያቄ ከሚለግሱት መካከል አንዱ ሄኖክ ስጦታው ነው።  ከአንድ ሁለት ዓመት በፊት “ሀ-ሞት” ብሎ ርዕስ የሾመለትን ሁለተኛ የግጥም ስብስቡን አሳትሞ ነበር። ይህን መፅሀፉን ሁለት ሶስቴ... ሊያሳትም ሲችል፥ በነፃ ሁላችንም እንድንመሰጥበት በድረ ገፁ ለቆታል። ገንዘብ እያጠረው ለሥነፅሁፍ ፍቅርና ልክፍት ማደሩን አስቀደመ።  ሀ-ሞት  በጥሞና ለመነበብና ለማወያየት ጥበባዊ አቅም የቋጠረ መፅሃፍ ነው። ለጊዜው አንድ ዘለላ የተዋጣ ግጥሙን አብረን እናብላላው።
 
-- ቁጥር 9 --
[ተናዳፊ ሥሩ ነደፈ ነው። ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ሲተረጉሙት የቃሉ ጨረር አይመክንም። (ገጽ 667) “ ንብ ነደፈ፥ በመርዙ ጠዘጠዘ ወጋ ጠቀጠቀ ” ወይም “ በፍቅር ተነደፈ ተያዘ ተቃጠለ ” እንዲሁም“ ባዘቶውን አፍታታ በረበረ ” ..... ግጥም ለጭብጡ፥ ለስንኝ አደራደሩ ወይም ለቋንቋው ምትሀት ምናባችንን ከቧጠጠ ተናዳፊ ነው፤ አንብበነው የምንዘነጋው፥ ጥፍሮቹ የተከረከመው ግን ኢ-ግጥም ነው።]
-------------------------------
ወፍ እና ማለዳ

እንኳንስ ችግኙ፥ ሰዎች የተከሉት
ሥር ይዝ ነበረ፥ አዕዋፍ የዘሩት።
ዘንድሮ ግን ወፎች፥ እንኳንስ ሊዘሩ
ናፍቆኛል ማለዳ፥ መስማት ሲዘምሩ።
    ወፎች ከማለዳ፥
    በምን ተቃቃሩ?!
    ፅልመቱ ሲገፈፍ፥
    እንዳላበሰሩ፤
    ማዜም ተስኗቸው፥
    ተዘግቶ ጀንበሩ
    ወደሚነጋበት፥
    ወዴትስ በረሩ?!
--------------------------------------------
 © ኄኖክ ስጦታው
 [ምንጭ = ሀ-ሞት፥ የግጥሞች ስብስብ]
--------------------------------------------
“ወፍ እና ማለዳ” አጭር እምቅ ተራኪ ግጥም ነው። ትረካው እንደ ማውጋት የሚወረዛ ሳይሆን ገጣሚውን ለመዘመዘ ጉዳይ መተንፈሻና ማውጠንጠኛ ሆነ። የርዕሱ ስክነት ረገቦ ለዘገባ ቢያመች እንጂ ለቅኔ አንድምታ ያዳፍናል።  ርዕሱ ግጥሙ ውስጥ ባደፈጠው ስንኝ በተተካ ያሰኛል፤ “ወፎች ከማለዳ በምን ተቃቃሩ?” የሚነሰንሰው አሻሚነት የሚኮሰኩስ፤ ከመነሻው በውስጠ-ምት -rhythm- የሚያባንን በሆነ። ተናጋሪው (persona) - የወንድም የሴትም አንደበት ሊሆን፤ የቆረቆረው፥ ያሳሰበው የመምከን አባዜ አለ፤ እንዴት ሳይሆን ለምን በበለጠ ያብሰከስከዋል።  
ደበበ ሠይፉ “ወፊቱ” በሚለው ግጥሙ ቀን-ቀን አየሩን እየቀዘፈች አድማስ ሳይወስናት የቦረቀች ወፍ፥ ለአይን ያዝ ሲያደርግ መደናገሯን ተቀኘበት።
ኧረ ምን መለሰሽ ?
ወደኋላ ያዘሽ ?
መሸት ከማለቱ ያደነቃቀፈሽ ?
ወፊቱ በሌሊት ምን ይሆን ታስቢ
እኔኑ መሰልሽኝ ጐጆሽ ስትገቢ።
ደበበ የተናጋሪውንና የወፊቱን የጓዳ ህይወት ቅዝቃዜ፥ የብቸኝነት ወጥመድ ... ህዋና የአራት ግድግዳ ስፋትና ጥበት የተወሳሰበበት ሥነልቦናዊና መቼታዊ ጣጣ አነፃፀረ። ሄኖክ ግን ጐህ ሲቀድ ይህች ወፍ የማለዳ ብርቅነቷ ነው የረበሸው። መዝሙሯን፥ የአዲስ ቀን ምስራቿን እንዴት ነፈገችን? ይቅርና እንደ ድምፅ ለእህልም -ወፍ ዘራሽ- ትበቃ የነበረው ከማለዳ ጋር ለምን ተቃቃሩ? ቅኔያዊ፥ ዘይቤያዊ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ሥር ከሰደደ ሥጋት ተፋትጐ የተቀጣጠለ ዕንቆቅልሽም ነው::
ተምሳሌቱ ግለሰብ ሆነ ማኅበረሰብ ለኑሮ ለውጥ በእልህ ከመዳከር ምን አቀዘዘው የመሰለ እሳቦት ያባብሳል።
እንኳንስ ችግኙ፥ ሰዎች የተከሉት
ሥር ይዝ ነበረ፥ አዕዋፍ የዘሩት።
ዛሬ ግን እንደ አማርኛው ፈሊጥ “ወፍ ዘራሽ” ብሎም “ገና ወፍ ሳይንጫጫ” ምን አደበዘዘው? ገጣሚው ቃላት ሳይከምር፥ እንደ ዘገባ ፊት ለፊት እሳቦቱን ሳይዘረግፍ ሰውኛ ዘይቤን በማጠላለፍ ዕምቅ ግጥም አስነብቦናል። በአርምሞ የአካባቢውን ቁሳዊና ህሊናዊ ዐውድ ከቃኘና ከታከከ በኋላ ጥያቄና ግርምት ያደነደነውን ስንኝ ያቀብለናል፤ ስናስብበት የተዳፈነው ረመጥ ለመጋል ይቅበጠበጣል።
ማዜም ተስኗቸው፥
ተዘግቶ ጀንበሩ
ወደሚነጋበት፥
ወዴትስ በረሩ?!
እኛ ዘንድ መንጋት አቆመ ወይ? መንደራችን ህይወታችን ለጨለማ ገብሮ፥ ለብርሃን ሽንቁር ሰስቶ እስከመቼ አቴቴ ቢስ እንሆናለን? ወፎች ጐህ ወደ ቋጠረው ተሰደው፥ ጀንበር እንደ ጣራ ተደፍኖ ሲቀር፥ ስጋቱ ያውካል። “ጀምበር ካለ እሩጥ፥ አባት ካለ አጊጥ” እንደ ቅዠት ሊፈረካከስ? ተስፋ ላለመቁረጥ፥ የሄኖክ ግጥም ጀርባ እንዳለው ማጤን ሊኖርብን ነው። የግጥሙን ተናጋሪ መጠራጠር እንጀምራለን፤ ቀን-ቀን እያንቀላፋ ለወፍ ዜማና ለንጋት መፍካት የሚቀሰቅሰውስ ካጣ? ይህንን ሄኖክ በሌላ ባለ አንድ አንጓ ግጥሙ “ታሽጓል” የሚለውን ግለሰብ ይገረምማል። እንዴት ቁልፍ በእጁ ይዞ፥ ከግሉ ከቤቱ ደጃፍ ተገትሮ የራሱን በር ያንኳኳል? የአደባባይ የተፈጥሮ ሳይሆን፥ ከውስጡ የተጋረደው ሥነልቦናዊ ንጋት ይብሳል።
ቢጠሩት ላይሰማ፥
ልቤ ተጠርቅሞ
የሚያንኳኳው ማንነው፥
ደጃፉ ላይ ቆሞ ?!
ይህ ግለሰብ ብንን ሲል፥ በወፍና ንጋት ልክፈት ተቀንብቦ ፍለጋውን አይገታም። እያደባ የደረሰባት ወፍ ግን “ጉጉት” ሆና ታሸማቅቃለች።
 ከእርግቦች መሐል፥
እርግብ ተመስላ፤
“እርግብ ናት”
ያልናቱ፥
ላባ ተከልላ፤
ሥትከፍተው አፏን፥
አየን ጥርስ አብቅላ።
ያቺ የምትዘምረው፥ ጨለማን ተርትሮ ብርሃን ሲያንሰራራ የሚትቦርቅ ወፍ ሲያልም ይኑር? ወይስ ተስፋን እያማሰለ እያቦካ የህይወት በገናውን እየቃኘ የግሉን ዜማ ያፍልቅ? ግጥሙ ሰክኖ ተዳክሞ አለማብቃቱ፤ ተደራሲ ከምናቡ እንደ ብስለቱ ለሚያክለው ቦታ አስተርፏል። ይህን ንባብ በህዝብ ቅኔ - መንፈስ ለማርገብ ያክል - እንቋጨው። ፀሐይ የተባዕት መጠሪያ ሆኖ እንደ ሰምና ወርቅ ቢዳዳውም፥ ለሄኖክ “ወፍ እና ማለዳ”  ማንፀሪያም ነው። ማለዳ የናፈቃት ያህል፥ ፀሐይ የሚፈታተናትም ሄዋን ታቃስታለች።
በሐምሌ በነሀሴ እንድያ ስዋትት
እንዴት በመስከረም በፀሐይ ልሙት?



Read 5161 times