Saturday, 23 April 2016 10:30

ትናንት ዛሬን ሲበድለው

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የዮርዳኖስ ጉዕሽ ልቡሰ ጥላ ሲነበብ
ዕዝራ አብደላ
[ደራሲዋ፥ ዮርዳኖስ ጉዕሽ]


“`ውበትሽ ከሌሎች ይለያል። ውስጥ ውስጡን እየሰረሰረ የሚገባ ነገር አለሽ` ብሎ ዓይኖቹን በመነፅሩ ውስጥ ተከለብኝ። እዩት እንግዲህ አፉን ሲከፍት፤ ምናለ ስለውበት ምንም አስተያየት ሳይሰጥ እንደወደድኩት ብቆይ።”
[መልካም ግርማ -ገፀባህሪ-፥ ገፅ 52-53]
--ክፍል 2 --
ደራሲዋ በቋንቋ ብስለቷ አትታማም፤ የቃላት እጥረት አይፈትናትም። ሆኖም ለውበት ለዘይቤው አእምሯችን ውስጥ የሚፈካ ዐረፍተ ነገር ያጣራታል። አልፎ አልፎ ለምልክት ያክል ይንጠባጠባሉ። ለምሳሌ ሚልኪ እህት ወንድሞቿ አገልለዋት የተቆጨችበት ገለጣ ከምናባችን ይነዝራል።“በእናቴ ወሬ ጠልተውኛል ... ምናልባት እኔ የረገጥኳትን ፈንጂ የረገጡ ዕለት ይረዱኛል፤ አዝነው ያለቅሱልኛል።”ጊዜና ገጠመኝ ግለሰብን ያበስላል ከማለት የላቀ ነው። ወይም በእውቀት መረቧን ዘርግታ ያጠመደችው ቀጭን ወጣት አብረው አድረው በማግስቱ ትክ ብላ ስታጤነው የተጋባባት ስሜት። “ይሄ ልጅ ግሩም ፍጥረት ነው፤ ካለምንም ጥያቄ ነፍስን ይቀርባል። ከእኔ ገላ ጋር ይናበባል። ከርቤ፥ ናርዶስ ... ከገላው ይረጫል።” ትናንት ምሽት ተዋውቄው ለምን በአንድ ሌሊት አወላልቄ ገላዬን መዘመዝኩለት የመሰለ ተራነት አላፈናትም፤  በአካል መጣጣም፥ ለቁስ ሳይሆን ለስሜት መርበትበት፥ እና ለውበት ጊዜን ቆርሶ መለገስ ያጋባባትን ብርቅ ደስታ እንዴት ትግለጠው?
ደራሲ ዮርዳኖስ ትንፋሽ አላጠራትም፤ የህይወትን ውጣ ውረድ፥ የሴትን እንግልት፥ የኅላዌ ፍጥጫ ድርጊቱ እሳቦቱ በጥሬው ከቧጠጠን፥ በዘይቤ ጥፍሮቹን ማሾል ለምን ያስፈልገዋል ባይ ናት። “እንደ ለመድናቸው ድርሰቶች በቃላት ውበት ላይ፥ በዓረፍተ ነገር ቅንብር ላይ አልተጨነቀም። ትኩረቱ በጥልቁ አእምሮ ላይ ነው።” ብላለች ስለ ልቦለዷ። መቼም የሴት እንባ፥ የፈካና የነተበ ፈገግታዋ፥ ጥንካሬና ውበት፥ ተስፋና ስጋት ብሎም ሥነልቦናዊና ማኅበራዊ መዘዝ ሲታሰበን የበአሉ ግርማ ሉሊት ድቅን ትላለች። ለአምስት አሰርታት  ያልፈዘዘችበት አንድ ምክንያት በደራሲው የቋንቋ ምትሀት ለዘልአለም መፈጠሯ ነው። ልቡሰ ጥላ ዳግም ቋንቋው ተላልጦ ተከትፎ ቢታተም ጥበባዊ ደረጃው በበለጠ ያደናግዛል። ሆኖም አጻጻፏ ተራ አይደለም፤ ቋንቋዋ አይቸክም። ልቦለዷ ከመዋቅር አንፃር ዘመም እንዳይል የበጇት አራት አላባዊያን አሉ።
አንድ፥ ገፀባህሪያት ሲወያዩ ይመስጣሉ።
“ሃይ አብረን ብንጠጣ ምን ይመስልሃል?”
“ብቻውን የሚጠጣ ወንድን የምትጋብዝ ሴት!” ... በለበጣ የሰጠኝ መልስ።
“በል ዛሬ የእድልህ ቀን ነው። ብቻውን የሚጠጣ ወንድን የምትጋብዝ ገጠመችህ።” ሳይጋብዘኝ ከግራው ካለው ክፍት ወንበር ላይ ተቀመጥኩ። እኔን ለማየት እንዲመቸው ፊቱን ከነመጠጡ ወዳለሁበት ዞረ። [ገፅ፥ 98-99]
የተማረች፥ ደሞዝተኛ ወጣት ነፍሷን ለመቀሸር፥ ብቻዋን ሙዚቃ እያደመጠች ከስሜት ጭጋግ ለመላቀቅ ከቡና ቤት መጠጥ አዛ ቁጭ ብላለች። የሆነ ጥግ የተቀመጠ ወንድ ማረካት። ባህላችን ዛሬም እቺን የመሰለች እንስት እንደ ጋጠወጥ ይገላምጣታል። ስር የሰደድ ተራ አመለካከት የምትፃረር ዘመነኛ ሄዋን፥ የፈቀደችውን ስትናገርና ስትፈፅም ወንዱ ግር ብሎት ይበረግጋል። ይህን የመሰለ በውይይት የደመቀ ሁለት-ሶስት ክስተት ደራሲዋ ልቦለዱ ውስጥ ቀብራለች። ሴትና ወንድ ቦታ የመለዋወጥ አባዜ፥ ቢቀር ቢቀር እንስቷ ለተባዕት የተፈቀደውን በፆታዋ ምክንያት እንዳትነፈግ፥ የመኖር እልህ የልቦለዱ አንድ ጭብጥ ነው።
ሁለት፥  ግጭት። (አንድ ምሳሌ) ሚልኪ ትዳር ምርር ብሏት ከቤት ለመጥፋት ሞክራ አልተሳካላትም፤ ባሏም ችግሯን ለመገንዘብ ከሚያወያያት ሊቀጣት ብድግ አለ።
መላኩ ቀበቶውን ከወገቡ መዠረጠው።
“እና አሁን አንተ ልትገርፈኝ ነው?” ንቀት መላ አካሌን ወረረኝ። ቀበቶውን በድጋሚ ሲያወናጭፍ ፊቴን አገኘው። ቆዳዬ የተገፈፈ መሰለኝ። ግን አላለቅስም። እንባዬን አፍስሼ ለዚህ ደደብ እርካታ አልሰጥም። ... ቀበቶውን ደጋግሞ እላዬ ላይ አሳረፈው። ...
ተወረወርኩ። ከሶፋው ላይ አንገቱን አነቅኩት። ቀበቶውን አስለቀቅሁት። መሬት ላይ ተንፈራፍሬ ቀበቶውን በእጄ ላይ አስገባሁኝ። ቆምኩ፤ ቀበቶውን እንደማረኩ። አወናጨፍኩ ቀበቶውን።
“አንተ የወንድ አውደልዳይ አልጫ! ከቤቴ አርፌ በተቀመጥኩ ትገለኝ? አንገቴን ደፍቼ ስለተገዛሁ ታጐድፈኝ?” ቀበቶውን ሰነዘርኩ አንገቱ ላይ። ... አቀመስኩት ጀርባው ላይ።
ቀበቶውን ያዘው፤ ከቀበቶዬ ጋር ሳበኝ። ሶፋው ላይ ደፋኝ። የሞት ሞቴን ታግዬ ከእምነበረድ የተሰራውን የአበባ ባዝ አነሳሁት። ወረወርኩት። ጥሩ አልሞ ተኳሽ እንደሆንኩ አላውቅም ነበር። አናቱን መሀል ለመሀል ለሁለት ተረከኩት። ጩኸቱን አቀለጠው። [ገፅ፥ 146]
ይህ ግጭት ለሴራው ማድመቂያ ሳይሆን ደራሲዋ የሴት በደል ዝምታና ማቀርቀር እንደማይፈታው፥ ራስን ለማስጣል መወራጨት እንዲሚበጅም የተጠቀመችበት ተምሳሌታዊ ድርጊት ነው። ብዙ ጊዜ ውጭ እያደረ ሲፈቅድ ብቻ ወደ ጐጆው እየተመለሰ ለሰባት አመታት ሚስቱን አንገላታት፤ አቀርቅራ ቆዝማለች። የሥነልቦና፥ የአካልና የርዕይ መነጠቅ ስቃይ ተፈራርቆባት ነው መደባደብ ብቸኛ ደመነፍሳዊ ምርጫ የሆናት። መግቢያና ተገን የመቀማት እልህ የፈጠረው ምላሽ ነው።
ሶስት፥ እሳቦት። ገፀባህሪያት ከራሳቸው ሲወያዩ አልያም በአንድ ነገር ተመስጠው ሲያውጠነጥኑ ለተራም ሆነ ለአንኳር ጉዳይ በየገፁ ጥያቄ ይጫራሉ።
“አሁን በቀን ሶስቴ በልቶ ማደር በህይወት አለሁ ያስብላል? ፈጣሪንስ `ቁርሴን፥ ምሳዬን እራቴን ስላበላኸኝ አመስግናለሁ!` ለመባል ይገባዋል? እግዜርስ ቢሆን ዓይን የለውም? የፈጠረው ሰው ስንት ነገር መፍጠር የሚችል ወርቅ ጭንቅላቱን ለመብላት፥ ተኝቶ ለመነሳት እና ከእጁ፥ ከነፍሱ መንጭቆ ብር በማካበቱ ብቻ `ተመስገን` እያለው ሲኖር እሱስ ምን ይሰመዋል?
እኔ ግን ፈጣሪዬን `ለምን በእኔና በህዝቤ ላይ ተነሳህ? ለምን አዕምሯችንን ንፍጥ በመሰለ የኑሮ ትርኪምርኪ አነተብከው?` እያልኩ ሁሌ እጨቀጭቀዋለሁ። መልሱን የሰጠኝ ቀን ምናልባት አመስግነው ይሆናል። እስከዚያው ግን ስራው ያውጣው።
እናቴን አስታወስኳት፤ ፈጣሪዋን እንዳመሰገነች ሳትጠይቀው ከዚች አለም እልም አለች። አሁን ለምን ይሆን ካልጠፋ ሰው እሷን `ነይ ብሎ` የወሰዳት? [ገፅ፥ 32-33]
በእውቀት የምትኖርበት ማኅበረሰብ የነቀዘ እየመሰላት፥ የኑሮ ከንቱነት እንደብል ወኔዋን በአንድ ወቅት ስለአነተበው ራሷን ለመግደል ሞክራ ነበር። ይህ ከሰው እስከ እግዜር የተወጠረ የኅላዌ ጭንቀት ተባዕት በሴት (የእናቷ ታሪክ) ያደረሰው በደል ታክሎበት ውስጧ የተላወሱ ጥያቄዎች የጥሞና መልስ ይሻሉ። ለሰው ባዶነት፥ ብሎም የምር ሳይሆን በመንሳፈፍ ዕድሜውን እየተረተረ ለተኮፈሰ ፍጡር፥ ... እግዜርን መነዝነዝ የመሰለ እሳቦትም እንደ ማፈንገጥ ነው።
በግለሰብ የዕለት እንቅስቃሴ ሆነ የስሜት ፍላጐት መልካም ስለፍቅር ያጤነችው አያሌ እንስትን ይጐረብጣል።
“እኔ በህይወቴ ውስጥ ሁሌም ወንድ እንዲኖር እፈልጋለሁ። ማለት ሴሰኝነት ምናምን ሳይሆን ፍቅር ሲይዘኝ በህይወት የምር መኖሬ ይሰማኛል። ልቤ ከበሮ ይመታል፤ ጥርሴ አስሬ መስተዋት ፊት ይፈግጋል። ፀጉሬ በሳምንት አንዴ ይተኮሳል። ዘፈን ከከንፈሬ ይለቀቃል። ፍቅር የእኔን ባዶነት ይሞላል። ስለዚህ ከሥራ በኋላ ፍቅር በየቦታው ይፈለጋል።
     እኔ እኮ ፍቅርን እንደሰው `ሙሽራዬ` ተብዬ ተድሬ ከእናቴ ቤት ወደ ባሌ ቤት ለመግባት፥ ወይ ልጆች ወልዶ ዓይኔን በዓይኔ ለማየት አይደለም የምፈልገው። `የእናት ቤት ማደጊያ እንጂ መጦሪያ እንዳልሆነ` ድሮ እናቴ ስለነገረችኝ ቤት ለመከራየት አቅም አዳብሪያለሁ። ግን ብቸኝነትን በጣም እፈራለሁ። እኔ ፍቅር ለመተንፈስ፥ መኖሬን ለማወቅ ነው የምፈልገው።” [ገፅ፥ 41-42]
“ፍቅር ሲይዘኝ በህይወት የምር መኖሬ ይሰማኛል” ቀላል ጉዳይ አይደለም። ልጅነቷን የቦረቦራት ብቻነት፥ እናቷም ጭምር የገፈተሯት ህፃን ሆና ማደግ፥ እውስጧ ያደባው የአለመፈለግ ስጋት በደመነፍስም ቢሆን የሆነ የወንድ ጠባብ ጥግ እንኳን ለመውረስ መዘመዛት። ጐጆ እስከ መቀለስ ባይሆንም፥ ከዳር ከጠርዙም ቢሆን የተባዕት የልብ ትርታ የሚሾርበት የሆነ የኅላዌ ምሽግ ያስፈልጋታል። ለህይወት መፍካት ሆነ መጠውለግ፥ ትንሽ-ትልቅ ብሎ የጉዳይ ድንበር መከለል ሳይሆን ሁለቱም ሴትን ሊኮሰኩሳት ይችላል።
አራተኛው እና ልቦለዱ ሳይሰለች -ቢድግሙትም- እንዲነበብ ያደረገው የአተራረክ አትኩረት ማለትም የአንፃር ምርጫ ነው። ሶስቱም የተማሩ ወጣት ሴቶች ተራ በተራ ያወጋሉ። በአንደኛ ደረጃ አንፃር `እኔ` እየተባለ ሲተረክ ከአንባቢ ጋር ቅርበት ይፈጥራል። የሶስቱም አኗኗር ህልምና እሳቦት የተለያየ በመሆኑ ድግግሞሽ አይደለም። የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳሉ ነው የተዋወቁት። በእውቀትና መልካም ተመርቀው ራሳቸውን ችለዋል። ሚልኪ ሳይሳካላት ቀርቶ ትዳር መስርታ ልጅ ወልዳለች። የሴትን ህይወት ጥንቃቄና ድፍረት ከሶስት አቅጣጫ ተተክሮበታል። የትረካውን ፍስት የሚገድብ የሁነቶች መጐማመድ አንባቢን ያደናግራል።
እያንዳንዷ ገፀባህሪ በሶስት አራት ገፅ ብቻ ህይወቷን ስትተርክ በፈረቃ ስለሆነ፥ በተለይ የመልካምና የበእውቀት ቤትና ልጅነት ያደናግራል። ሶስቱ የትረካ አቅጣጫ እንደተጠበቁ ሆነው በቁርጭራጭ ሳይሆን እስከ ጥግ ቢያወጉ ይመረጣል፤ ምክንያቱም ሶስቱም ስለ አንድ ጉዳይ አያወጉም፤ የየግል እንቅስቃሴያቸውን ነው የሚተርኩት። ዮርዳኖስ፥ ዳግም ልታሳትመው ካሰበች ሶስቱ ገፀባህሪያት እስከሚገናኙበት ክስተት ምዕራፎችን መገጣጠም ይኖርባታል። እንድታቅማማ የሚገፋፋት ለምሳሌ በእውቀት ስታወጋ ድንገት የሚልኪ ስም ቢጠቀስ፥ አዳም ረታ እንደአደረገው በግርጌ ማስታወሻ ከአርታኢው ተብሎ ስለሚልኪ ይጦቀማል።
ደራሲዋ ለልቦለዷ “ልቡሰ ጥላ” የሚል ርዕስ ብትጠቀምም ምን እንደሆነ አታብራራም። ይህን ቃል መጀመሪያ የተጠቀመው በ “አድፍርስ” ልቦለዱ ዳኛቸው ወርቁ ነበር። ርዕሱ ግራ የገባው በድረገፅ መፅሃፉን የሚሸጠው imaginary shadow ብሎታል፤  ምናባዊ ጥላ እንደማለት። እንደ ዳኛቸው አጠቃቀም ቃሉ ለ subconcious  ታህተ-ንቃት ያደላል። “`ልቡስ ጥላ` ለአደፍርስ ገፀባህሪይ መያዣ መጨበጫ የሌለው ምስቅልቅል ሁኔታ ነው። ከአእምሮ ክፍሎች በአነስተኛው ልዩ ልዩ ነገሮች ማየትና ማውጠንጠን ከጀመርንበት ጊዜ አንስቶ የሚጠራቀም ነው።” ከኑሮ  ከንባብ ከባህል ልብ ሳንለው አእምሯችን ውስጥ እየቃረምነው የሚዘቅጥ ተግባራችንን ሊጫን የሚችል ጥርቅም ነው።
የዮርዳኖስ ልቦለድ አንድ ጭብጥ፥ ከልጅነት ጀምሮ ከውስጠ አእምሮ ያደባው ጥርቅም የዛሬ እኛነታችንን መበደል መቻሉ ተተኩሮበታል። ህይወትን ለማወክና ለማመሳቀል አቅም አለው። ሚልኪ የአባቷ ግፍ የእናቷ መሽቆጠቆጥ ከአእምሮዋ ተቀብሮ ለራሷም ለእናቷም እንግልት እንደ መበቀል ባሏን ገድላ ተገላገላለች።
መልካም፥ እናቷ ከተለያየ ወንድ ስትዝናና፥ አባቷ በቅናት ሲበግን፥ እሷም እንደ ትርፍ ተቆጥራ መገፍተሯ፥ ዛሬ ብቻዋን መሆን እያሰጋት፥ከሆነ የወንድ ጉያ ውስጥ ለመወሸቅ አበቃት። በእውቀት እናቷን ጠይም ልዕልት ብላ ነው የምትጠራት። በአስራ ስድስት አመቷ ለአዛውንት ተድራ ለሰባት ዓመታት በአካልም በሥነልቦናም ከማቀቀች በኋላ፥ ወጣት ሳለች ከወንድ ሸሽታ ደስታን ተነፍጋ አልፋለች። ዛሬ በእውቀት ለእናቷም ጭምር እድሜዋን እያጣጠመች፥ የፈቀደችውን እያደረገች ከማኅበረሰቡ ተላትማ ትኖራለች። ምናልባት ደራሲዋ ይህ ልቦለዷ “... ከድርጊት እና ከንግግር ጀርባ ወዳለው ጥልቅ አለም ይወስደናል።” ስትል ያው ልቡሰ ጥላችንን እንደ መቦርቦር ነው። ለሌላው ተሸፋፍነን የምንቀርብ ብንሆንም ለራሳችን ግን ዥንጉርጉር ነን እንደ ማለት።
ስር የሰደደ ለእንስት የተፀናወተንን ንቀት፥ ይህ ልቦለድ ለመጋፈጥ ሞክሯል። የመረጠችውን ህይወት እየወለወለች፥ በራሷ ብቻ ተማምና ያማራትን እየላጠች፥ በግልፅ የምትናገርና የምታውጠነጥን  አዲስ ሴት ገፀባህሪ ተመልምላለች። ጥንትም አርስጣጣሊስ እንዳወጀው “The female is female by virute of a certain lack of qualities.” እንስት፥ እንስት የሆነችው የአይነት የጥራት ፀጋ ስለሚጐድላት ነው። ብዙ ሰው የሚያምነው “A woman is an imperfect man” በሚለው ነው። ሴት ያልተሟላ ጐደሎ ወንድ ናት እንደ ማለት። በአገራችንም አሁንም ድረስ የወረስነው ለሄዋን ዝቅተኛ አመለካከት ከኢ-ንቁ አእምሮ እያደፈጠ አንደበታችንና ልባችን እኩል አይነዝሩም። “የሴት እውቀትና የዶሮ ሩጫ፥ከአውድማ አያልፍም”  ብሎ እንስትን ለሚገላምጥ ማኅበረሰብ፥ የዮርዳኖስ ጉዕሽ ልቦለድ ፈታኝ ነው።
የፆታ ጥያቄ ሳይሆን ሴትና ሰው፥ ለበጐም ለክፉም የማይሰነጣጠቁ ውስብስብ ኅላዌ ናቸው። ታድያ ዝምታዋ እየዳደረ ብትዘገይም፥ ዮርዳኖስ ለምን ተጨማሪ አዲስ ልቦለድ ነፈገችን?


Read 2082 times