Saturday, 23 April 2016 10:16

ክብር ለሚገባው የሰው ልጅ ክብር እንስጥ!!

Written by 
Rate this item
(10 votes)

“--- ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ አደርጎ ከንፈር መምጠጥ ብቻ በቂ አይደለም፡
ከሚቸረው የከንፈር መምጠጥና የሞራል ካሳ ጎን ለጎን፣ በኢኮኖሚያዊ
ካሳም የዜጎቻችንን እንባ ማበስ ያስፈልጋል፡፡----”
ሙሼ ሰሙ
     በቅድሚያ በግፍ ላለቁ ዜጎቻችን ጥልቅ ሃዘኔን መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡
ከደቡብ ሱዳን የተነሱ የሙርሌ ጎሳዎች ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ዘልቀው በመግባት በመሳርያ የታገዘ ጥቃት  በመሰንዘር በጋምቤላ ክልል በሚኖሩ ቁጥራቸው ከ200 ያላነሱ ዜጎቻችን ላይ እልቂት ፈጽመዋል፡፡ ድርጊታቸው በዚህ ሳያበቃም ቁጥራቸው ያልታወቁ ህጻናትና ሴቶችን አግተውና ከብቶች ዘርፈው  እየነዱ ወደ መጠቡት ተመልሰዋል፡፡
ይህ ድርጊት ለአዕምሮ የሚከብድ ከመሆኑ አንጻር እንኳን በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሊፈጸም ይቅርና ሊታሰብ የማይችል ድርጊት መስሎ የሚታየን በርካታ ሰዎች እንኖራለን፡፡ በእኔ ግምት ግን ወደድነውም ጠላነው፣ አፍሪካውያን ገና ከዘመናዊ አኗኗር ጋር ያላዋሃድናቸው ብዙ ጎሳዎችና ብሔሮች ያሉት ማህበረሰብ እንደመሆኑ መጠን እንደዚህ አይነት አሰቃቂ ድርጊት በቀጣይ ሊከሰት እንደሚችል የሚጠበቅ ነው፡፡ በበርካታ የአፍሪካ ሃገራት ውስጥ ከኋላ ቀርና ከአስከፊ ባህል ለመላቀቅ ብዙ ስራ የሚጠይቃቸው ሕዝቦች አሉን፡፡
ችግሩ ዘለቄታ ባለው መንገድ የማይፈታው ግን ስር ነቀል መፍትሔ ከመሻት ይልቅ አንደዚህ አይነት ድርጊት በተከሰተ ቁጥር እንዴት ተደፈርን የሚለው የበቀል ዛራችን እያገረሸ፣ በሕግ የበላይነት መንፈስ ሳይሆን ያስቆጣንና ያሳዘነን ሁሉ ለመፍጀት ከመነሳሳታችን ላይ ነው፡፡ ይህ ደግሞ ውሎ አድሮ በታሪክ ፊት እንደ ሕዝብ የሚያስተዛዝበን ጉዳይ ሆኖ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ በጋምቤላ በተከሰተው እልቂትም ዙርያ እየተመለከትን ያለነው የመፍትሔ አቅጣጫ ይኸው ነው፡፡ ይህ ወሬሳ የመምታት ስነልቦና ቀድሞውን ቢሆን በኋላ ቀር ባህልና አስተሳሰብ ተተብትበው ወረራ ከሚያካሂዱትና እልቂት ከሚደግሱት ጎሳዎች የማንሻል ያደርገናል የሚል ስጋት አለኝ፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ወደ ሃሳቤ መቋጫ ላይ እመለስበታለሁ፡፡
አሁን አወዛጋቢ ወደሆነው የተጠያቂነት ጉዳይ ልምጣ፡፡ ከቅድመ ዝግጅት መጓደልም ሆነ ከንህዝላልነት በመነጨ ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው መጠየቅ የሚገባቸው የመንግስት ተቋማት፣ ባለስልጣናትና ግለሰቦች ጉዳይ እንደተጠበቀ ሆኖ እንደዚህ አይነቱን ድርጊት ዝንተ ዓለማችንን ሰራዊት ዘብ በማቆም ወይ ድንበር በማጠር ብቻ የምንፈታውና ልንቋቋመው የምንችለው ጉዳይ እንዳልሆነ እምነት አለኝ፡፡ ምክንያቱን ላቅርብ፡፡
ይህ እልቂት የተከሰተው መንግስት በሁለት ምክንያት በአካባቢው ያለውን የኃይል ሚዛን የሚያናጋ ድርጊት በመፈጸሙ እንደሆነ መጠርጠር ይቻላል፡፡ አንደኛው በቅርቡ በጋምቤላ በተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት ምክንያት የአካባቢው ነዋሪን ጨምሮ የክልሉ ታጣቂ ሃይሎች በሙሉ ትጥቅ በመፍታታቸው የሃይል ሚዛኑ ላይ ክፍተት በመፈጠሩ ሲሆን ሁለተኛ ደግሞ በሃገሪቱ ውስጥ በኦሮሚያና በተለያዩ ክልሎች የተነሳውን ሕዝባዊ ቁጣ ለማብረድ መንግስት ሰራዊት ከየአካባቢው  በማንቀሳቀሱ በተፈጠረው የሃይል መሳሳት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ በማንኛውም መንገድ ማለትም በቅድመ ዝግጅት ማነስም ሆነ በንዝላልነት ክፍተት ሲፈጠር ወረራው የሚከሰት ከሆነ፣ ዝንተ ዓለም ታጥቀንና ሰንቀን ጠላት በመጠበቅ ስራ ላይ መሰማራታችን ብቻ ለመፍትሔው በቂ  ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበት ያሳያል፡፡
ከደቡብ ሱዳን ተነስተው ጥቃት የፈጸሙት የሙርሌ ጎሳ አባላት ኢትዮጵያ ውስጥ በተለምዶ በለሊት በር እያንኳኳን በልመና ስራ ካልተሰማራን አንቆመጣለን እንደሚሉት ዜጎቻችን ሁላ ወረራ ካላካሄድን መቅሰፍት ይደርስብናል የሚል እምነት ያላቸው ሕዝቦች ናቸው። በዚህም ምክንያት ሙርሌዎቹን ከዚህ እምነታቸው ማላቀቅ ካልተቻለ በስተቀር እድል በሰጣቸውና ሁኔታው በፈቀደላቸው ጊዜና  መጠን ወረራ ከማድረግና እልቂት ከመፈጸም የሚመለሱ አይደሉም ማለት ነው፡፡ ለምን ቢባል  በመንግሰት በኩል ዜጎችን ከእልቂት በመታደግ ረገድ ከታየው ንዝህላልነት ባልተናነሰ የሙርሌዎች የኋላቀር ባህል ቁራኛነት ሌሌው ችግር ነው፡፡
መንግስት ለችግሩ ወቅታዊ መፍትሔ ከመሻት ባሻገር ዘለቄታዊ አማራጭን ተደራድሮ ከማምጣት አኳያ ምን ያህል ድክመት እንደነበረበት ከዚህ መረዳት ይቻላል፡፡ ችግሩ ስር የሰደደ፣ ባሕላዊና ስነልቦናዊ መንስኤ ያለው  መሆኑ እስከታወቀ ድረስ ታጥቆና ሰንቆ ከመጠበቅ በተጨማሪ ቅድመ መከላከል እውን የሚያደርግ፤ ዙርያ ገብ የሆነና የድንበር ላይ እንቅስቃሴን የሚቆጣጣር በተለይ ደግሞ ሰርጎ ገብ ዜጎቹን ስርዓት የማስያዝ ኃላፊነትን በደቡብ ሱዳን መንግስት ላይ የሚጥል ስምምነት ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር መደረስ ነበረበት፡፡ በተለይ ደግሞ እንደ ሙርሌ ዓይነት የወራሪነትና የዘራፊነት ባህላዊ ዝንባሌ ያለውን ጎሳ ትጥቅ ማስፈታት እንዲሁም በከፋ መልኩ ወራሪነት የተጠናወተው ባሕላቸው ጎጅነትና አደገኛነት ላይ ትምህርት በመስጠት ከዚህ ዓይነቱ ኋላ ቀር ባህል የማላቀቁ ስራ መሰራት ነበረበት፡፡ ይህ አልተደረገም፡፡ ቅድመ መከላከሉ መዘንጋቱ ሳያንስ ደግሞ በአናቱ ላይ ሕዝቡን ከእልቂት ለመከላከል የሚያስችል ሃይል ሳይተካ ነዋሪዎቹን፣ ሰራዊቱን፣ የፖሊስና የአካባቢ ጥበቃውን መሳሪያ ማስፈታቱ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ለእልቂቱ በር ከፋች ነበር፡፡
እግዚአብሔር ምድርን ከዘረጋ በኋላ በምድር ላይ ያሰፈነው ስርዓት እንደሆነ የሃይማኖት መጽኃፍት ይገልጻሉ፡፡ ስርዓት በተዘረጋበት ዓለምም ላይ ከፍጡራን ሁሉ እጅግ የላቀውን ክቡር የሆነው የሰው ልጅ በበላይነት እንዲኖርበት እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖአል፡፡ ኢ-አማኒ በሆኑ ሰዎችም ዘንድም ስለ ሰው ልጅ ክቡርነት ልዩነት ያለ አይመስለኝም፡፡ ይህ በሁላችንም ዘንድ የተከበረና የጋራ ስምምነት የተደረሰበት እምነት ግን ሁሌ ሲፈተን እንደማየት የሚከብድ ነገር የለም፡፡
ዛሬ ላይ ኢህአዴግ በቁሳዊ ብክነትና በሃብት ዘረፋ እንዲሁም በመልካም አስተዳደር እጦት ላይ ዘመቻ እያደረገ ነው፡፡ ሙስናን መታገል የሚያስመሰግን ስራ ነው፣ ነገር ግን ለነዚህ ሁሉ ዜጎች እልቂት ምክንያት የሆኑ ሹመኞችና ሕገ መንግስታዊ ኃላፊነት ያለባቸውን ተቋማት የሚመሩ ሃላፊዎች የተጠያቂነት ጉዳይ ላይ ግን ባለቤት ለማበጀት ፍላጎት አይታይም፡፡ የሙስና ትግሉና የመልካም አስተዳደር ግንባታ ጥረቱ የሰው ልጅን ክቡርነት ለማረጋገጥና የሕልውናውን ልዕልና ለማስጠበቅ መሆን አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ ግን፣ የሙስና ትግሉም ሆነ የመልካም አስተዳደርን የማረጋገጥ ውጣ ውረዱ በስልጣን ለመቆየት ከሚደረግ ትግል ዘልቆ ሊሄድ አንደማይችል ግልጽ ነው። ከቁሳዊ ጉዳይ ይልቅ በኃይማኖት፣ በሞራልም ሆነ በሕገ መንግስቱ ቅድሚያ ለሚገባውና ለተሰጠው ከቁሳቁስም የሰው ልጅ ሕይወት ክብርና ቅድሚያ ይሰጥ፡፡
ወደ ሃሳቤ ማጠቃለያ አነሳዋለሁ ወደአልኩት ጉዳይ ልምጣ፡፡ ሰሞኑን ከግራም ከቀኝም የሚነሳውን ምሬትና ቂም ተበቃይነት ላጤነው፣ የሰው ልጅን ክቡርነት ከማስቀደምና የሰው ልጅን ልዕልና ማዕከል ከማድረግ የታላቅነት መንፈስ ይልቅ ደርሶ ተደፈርንና ተጠቃን በሚል የተሸናፊነት ስነልቦና  ዙርያ የሚያጠነጥን  የእልቂት ደጋሽነት አዙሪት ውስጥ መሆናችንን መረዳት አያዳግተውም፡፡  ለሕግ የበላይነት ቅድሚያ መስጠት የሚገባው አዕምሮአችን፣ ጦር ለመስበቅ የገነባው ፍላጎት ምን እየተፈታተነው በዚህ ደረጃ እንዳሽቆለቆለ ለመረዳት አዳጋች ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የመንግስት ተወካዮች “እያሳደድን እንቀጣለን” ሲሉ እንደ መስማት አስፈሪ ነገር የለም፡፡ የዚህ ዓይነቱ አሰቃቂ ድርጊት የአሁኑን አያህል  እንጂ በተደጋጋሚና በተለያየ ጊዜ ይፈጸም እንደነበረ መገናኛ ብዙሃን በዘገባቸው እያስታወሱት ነው፡፡ ከላይ ለማሳየት እንደሞከርኩት፤ እውነታው ይህ ከነበረ የመጀመርያው ጥያቄ መሆን ያለበት መንግስት ወይም ጉዳዩ የሚመለከታቸው መንግስታዊ ተቋማት ለጉዳዩ እልባት ከመስጠት አኳያ እስከ ዛሬ የት ነበሩ የሚል መሆን ሲገባው፣ “አባረህ በለው” የሚለው የጦረኝነት ጥሪ ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ስነልቦና አሳዛኝ ነው፡፡
እርግጥ ነው የታሰሩትን ዜጎቻችንን ማስለቀቅ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አሌ የምንለው ጉዳይ አይደለም፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት በተሻለ ደረጃ የጦር መሳርያ የታጠቀ በመሆኑ ብቻ ሰራዊት አዝምቶ የታገቱትን ለማስመለስ በሚል እልህ፣ እልቂት መደገሱ ግን ህሊና ሊቀበለው የሚችል ጉዳይ አይደለም። ዓለም በዚህ መንገድ የምትመራ ቢሆን ኖሮ አሜሪካ፣ ቻይን፣ ጃፓንና ፈረንሳይ ሌሎችንም ጨምሮ ዜጎቻቸው በታፈኑ ቁጥር ስንት አይነት ጦርነትና ወረራን ባሳዩን ነበር። የኢትዮጵያ መንግስትም የታገቱ ዜጎችን ለማስመለስ ማንኛውም የዓለም መንግስት እንደሚያደርገው፣ቅድሚያ ማድረግ ያለበት ከደቡቡ ሱዳን መንግስትና ከአካባቢው መስተዳድር ጋር በመተባበር መፍትሄ መሻት ነው፡፡
መንግስትና በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች በተለይ ደግሞ የኢህአዴግ ደጋፊዎች  በተቃራኒው እየጋለቡት ያለው “ምታ ነጋሪት ክተት ሰራዊት” የሚል ዓይነት በኋላቀር ስነልቦና የሚመራ የጦርነት ዘመቻ፣ በውጤቱ የበቀል ጥማቸውን ያረካ እንደሆነ እንጂ የሃገራችንን በጎ ታሪክ የሚያጎድፍና የእልቂትና የጨፍጫፊነት ምዕራፍ ከማከል የዘለለ ሚና እንደማይኖረው ማሳሰብ ያስፈልጋል የሚል አምነት አለኝ፡፡  ይህ ከኢህአዴግ ካድሬዎች እየሰማነውና እያየነው ያለው የመጣሁባችሁና አትችሉኝም አይነት ስነልቦና ሃገር ውስጥ በሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችም ላይ የለመድናቸው ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ ኢህአዴግ እንደ መንግስት ወሳኝ ሕገ መንግስታዊ ግዴታዎችንና ኃላፊነቶቹን በቅጡ መወጣት ሲያቅተው ወይም የደረሰውን ጥፋት ለማድበስበስ ሲፈልግ፣ “ያዙኝ ልቀቁኝ፤ አሳያችኋለሁ” ማለቱ ድርጅታዊ ባሕል ነው፡፡
ኢህአዴግ ዛሬ ላይ ደርሶ ድንበር አቋርጦ በመሄድ በግዢ ባሰባሰበው መሳርያ ተማምኖ በሌሎች ያውም እጅግ ኋላ ቀር  የሆኑ ሕዝቦችን በጀት፣ በመድፍና በታንክ እየታገዘ ሌላ ፍጅት መጋበዙ፣ በእኔ እምነት ዘመኑ የማይፈቅደው ሌላ ዓይነት ጭካኔ ነው፡፡ በመጀመርያ በዚህ ዘመቻ አማካኝነት የሚገኝ አንድም ለውጥ አይኖርም፡፡ ምናልባትም ታግተው የተወሰዱት ላይ ተጨማሪ እልቂትን ላለመጋበዙም ማረጋገጫ የለም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ወረራውን የፈጸሙት ኃይሎች  ወደ ሃገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከአካባቢው ሰላማዊ ሕዝብ ጋር መቀላቀላቸው ስለማይቀር ወረራው ሌላ ጭካኜ የተሞላበት የሰላማዊ ዜጎችን እልቂት ላለማስከተሉ እርግጠኛ መሆን ያስቸግራል፡፡    
ሌለው አስገራሚ ጉዳይ እንደተለመደው የመንግስት መገናኛ ብዙኃን፣ የማህበራዊ ድረገ-ጾች በተፈጠረው ንዝህላልነት የተከሰተው እልቂት በየትኛውም የኢትዮጵያ ምድር  በድጋሚ  እንዳይከሰት አስተማሪ በሆነ መልኩ አጥቂዎቹና ንዝህላሎቹ ለፍርድ እንዲቀርቡ ከማበረታታት፣ ገንቢ ተጽእኖ ከመፍጠር ወይም ወደፊት እልቂቱ የማይደገምበትን መንገድ ከመሻት ይልቅ ስለ በቀልና የሃዘን ቀን ትኩረት ሰጥተው በሰፊው ሲደሰኩሩ ነበር፡፡ አዎ፡፡ እራሳቸውን መከላከል ሳይችሉ የተፈጁት ዜጎቻችን ተገቢውን ሃዘኔታ ሊያገኙ ይገባል፡፡ ይህም ሆኖ በዘመናዊ መንገድ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ አደርጎ ከንፈር መምጠጥ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ከሚቸረው የከንፈር መምጠጥና የሞራል ካሳ ጎን ለጎን በኢኮኖሚያዊ ካሳም የዜጎቻችንን እንባ ማበስ ይስፈልጋል፡፡ በዚህ መልኩ ተገቢውን ካሳ ከመክፈል ባሻገር፣ እልቂቱ የተከሰተበትን ክፍተት አጣርቶ  ተጠያቂውን በመቅጣት፣ቀሪዎቻችንም ወይም ያልሞትነው ተረጋግተን ሕይወታችንን ለመምራት እንድንችል ለሁሉም ነገር ባለቤት ሊበጅለት ይገባል። ዜጎቻችንን ለዚህ አደጋ የዳረጉ ንህዝላሎች ወደፊትም ለዚህ አይነት አደጋ ወይም ከዚህ ለከፋ አደጋ ማለትም አንደ አልቃይዳና አይሲስ ላሉ ነፍሰ በላዎች አሳልፈው እንደማይሰጡን መተማመኛ ያስፈልገናል፡፡ መተማመኛው ደግሞ የሕግና የሞራል የበላይነት፣ መንግስት በአጥፊዎች ላይ ተገቢውን ሕጋዊ እርምጃ ሲወስድ ብቻ ነው፡፡
ዜጎቻችን በእልቂቱ የደረሰባቸው መከራ ቤተሰቦቻቸውን በሞት በመነጠቃቸው ብቻ የሚያበቃ አይደለም፡፡ ለአቅም አዳም የደረሱና ሰርተው የሚደጉሟቸውን የኑሮአቸውን፣ የሕይወታቸውን ማገርና ወጋግራ አባወራዎቻቸውን የተነጠቁ በመሆኑ ለዘለቄታው የሚቆይ ኢኮኖሚያዊ ኪሳራም በሕይወታቸው ላይ ደርሶባቸዋል፡፡
በዋነኛነት የሱዳን መንግስት በተጓዳኝ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት የዜጎቹን ሕይወት ከአደጋ ለመከላከል ካለበት ሕገ-መንግስታዊ ግዴታ በመነሳት፣ ለተፈጠረው ሰብአዊና ቁሳዊ ኪሳራ ተገቢውን ካሳ በመክፈል ለሰው ልጅ ክቡር ሕይወት ተገቢው ሁሉ ይደረግ፡፡ አሟሟታቸውም ከንቱ፣ ደማቸው ደመ ከልብ አይሁን ፡፡

Read 6506 times