Saturday, 16 April 2016 11:28

የብራዚል ፕሬዚዳንት ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ነገ ይታወቃል

Written by 
Rate this item
(4 votes)

- የመፈንቅለ መንግስት ሴራ ተሸርቦብኛል፤ እስከመጨረሻው እታገላለሁ ብለዋል
በተለያዩ ውንጀላዎች የመከሰሳቸውና በስልጣን የመቆየታቸው ቀጣይ እጣ፣ ነገ በሚከናወን የምክር ቤቶች የድምጽ አሰጣጥ ስነ-ስርዓት የሚወሰንባቸው የብራዚል ፕሬዚዳንት ዲላማ ሩሴፍ፣ ከተጠያቂነት ነጻ ለመሆንና መንበራቸውን ላለማስነጠቅ እስከ መጨረሻዋ ደቂቃ ድረስ ተግተው እንደሚታገሉ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
የአገሪቱን ኢኮኖሚ የተሻለ ደረጃ ላይ ያደረሱ በማስመሰል ሃሰተኛ መረጃ አውጥተዋል፣ በሙስና ተዘፍቀዋል፣ በስልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ የበጀት ህጎችን ጥሰዋል  በሚል ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማቸው ፕሬዚዳንቷ፤ ድርጊቱን አለመፈጸማቸውን በመግለጽ፣ ተቀናቃኞቼ መፈንቅለ መንግስት በማድረግ ያለ አግባብ ስልጣኔን ለመቀማት የሸረቡብኝ ሴራ ነው፤ ድምጽ አሰጣጡ አግባብ ባለመሆኑ እስከመጨረሻው እታገለዋለሁ ሲሉ መናገራቸውን ዘገባው ገልጧል፡፡
65 አባላት ያለው የአገሪቱ የኮንግረስ ኮሚቴ ሰኞ ዕለት በአብላጫ ድምጽ ባሳለፈው ውሳኔ በስልጣን ቆይታቸው ላይ ድምጽ እንዲሰጥበት የተወሰነባቸው ፕሬዚዳንት ዲላማ ሩሴፍ፣ የመፈንቅለ መንግስት ሴራ ሸርበውብኛል ብለው ከጠቀሷቸው ፖለቲከኞች መካከል ምክትል ፕሬዚዳንቱ ሚሼል ቴምር እንደሚገኙበት ታውቋል፡፡
ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠማቸው ዲላማ ሩሴፍ ከሚመሩት ጥምር መንግስት ውስጥ ራሳቸውን ማግለላቸውን ማክሰኞ እለት ያስታወቁ ሁለት ፓርቲዎች፣ ነገ በሚደረገው ድምጽ አሰጣጥ ላይ ሴትዮዋ ስልጣን ይልቀቁ በሚል ድምጻቸውን እንደሚሰጡ መግለጻቸውንም ዘገባው አስረድቷል፡፡
ፕሬዚዳንቷ ከስልጣን እንዲለቁ የሚፈልጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ብራዚላውያን ውሳኔውን በደስታ መቀበላቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ በአንጻሩ የፕሬዚዳንቷ ደጋፊዎች የሆኑ በርካቶችም ጉዳዩን የፖለቲካ ጠላቶች የፈጸሙት ህገወጥ የስልጣን ቅሚያ ነው በማለት አውግዘውታል ብሏል፡፡
በአመት 2015 ነዳጅን ጨምሮ የተለያዩ የአገሪቱ ሸቀጦች ዋጋ መቀነሱን ተከትሎ፣ የብራዚል ኢኮኖሚ ባለፉት ከ30 በላይ አመታት ታሪኩ በከፋ ቀውስ መመታቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ የዋጋ ግሽበት ባለፉት 12 አመታት ከፍተኛው ደረጃ ላይ መድረሱንና የስራ አጥነት በ9 በመቶ ማደጉን፣ ይህም የፕሪዚዳንቷን አስተዳደር ክፉኛ ማስተቸቱን ገልጧል፡፡
ነገ አመሻሽ ላይ ይፋ ይደረጋል ተብሎ የሚጠበቀው በአገሪቱ ምክር ቤቶች በየደረጃው የሚከናወኑ ድምጽ አሰጣጦች አጠቃላይ ውጤት፣ የፕሬዚዳንቷን ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ይወስነዋል ተብሏል፡፡

Read 1712 times