Saturday, 16 April 2016 11:17

ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕጻናት...

Written by  ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

 ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕጻናት የትኞቹ ናቸው?
(one stop center) ምን አገልግሎት የሚሰጥበት ነው?
ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕጻናት ማለት የትኞቹ እንደሆኑ ለዚህ እትም የሚገልጹልን አቶ መኮንን በለጠ የስነልቡና ባለሙያ ናቸው። አቶ መኮንን በለጠ በአዳማ ሆስፒታል ውስጥ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ወንዶችና ሴቶች ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ተቋም በሚያገኙበት (one stop center) የስነልቡና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያ ናቸው። አቶ መኮንን እንደሚሉት ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕጻናት ማለት፡-
በተለያየ አጋጣሚ የድብደባ እና የአካል ጉዳት ሲደርስባቸው፣
የስነልቡና እና የሞራል ጉዳት ሲደርስባቸው፣
ተገዶ የመደፈር ወንጀል ሲፈጸምባቸው፣
የጉልበት ብዝበዛ ሲደርስባቸው፣
የወሲብ ትንኮሳ ሲፈጸምባቸው፣ እና የመሳሰሉት ጉዳት ሲደርስባቸው ሲሆን
ለእነሱ የሚገባውን፡-
የሕክምና
የስነልቡና
የህግ አገልግሎት ድጋፍ ለመስጠት የተቋቋመው ይህ (one stop center) የተባለው ክፍል ልዩ ፍላጎት ያላቸው ሕጻናት የሚገለገሉበት ነው።
ሕጻናቱ ሁሉን አገልግሎት የሚያገኙበት ሲባል፡-
 ከላይ የተዘረዘሩት ጉዳቶች ሲደርሱ በተለይም የወሲብ ጥቃት ሲፈጸምባቸው ቀደም ሲል የነበረው አሰራር ከማህበራዊና ስነልቡናዊ ችግሩ የተነሳ ብዙውን ጊዜ ተደብቆና በየመንደሩ በሽምግልና የሚያልቅ የነበረ ሲሆን ይህ አሰራር በበኩሉ የህጻናቱን የወደፊት ሕይወታቸውን የሚፈታተን የነበረ ነው። በሌላም በኩል ጉዳት አድራሾቹ በፈጸሙት ወንጀል ምንም ጥያቄ ሳይቀርብባቸው ተሸሽገው የሚኖሩ እና ጥፋቱንም በአንድ ጊዜ የማያቆሙ፣ በተደጋጋሚም በተለያዩ ወንድና ሴት ሕጻናት ላይ የሚፈጽሙት ይሆናል።  
one stop center የሚባለው ሁሉንም አገልግሎት በአንድ ተቋም ስር የሚያስተናግደው ክፍል ከመጣ ወዲህ ግን ቀደም ሲል በየመኖሪያ አካባቢው እና ሌሎች ስፍራዎችም የተፈጸሙ ወን ጀሎች ወደማእከሉ እየቀረቡ ልጆቹ የህክምናውን የሕግ እና የስነልቡናውን አገልግሎት በአንድ ስፍራ ስለሚያገኙ ወላጆችም እንደልባቸው የልጆቻቸውን ጉዳይ ይከታተላሉ። ልጆቹም በወደ ፊቱ የህይወት ጉዞአቸው ሊጎዳቸው የሚችለውን የስነልቡና ችግር ይታከማሉ፣ ጉዳት አድራ ሹም በህግ ይጠየቃል፣ በደረሰባቸው ጥቃት ምክንያት የተለያዩ ሕመሞች እንዳይደ ርስባቸውም ሕክምና ይደረግላቸዋል።
አቶ መኮንን ቀደም ያለውን ሁኔታ ያስታውሳሉ።
“...የወሲብ ጥቃት የደረሰባቸው ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ልጆች በመጀመሪያ ሕክምናውን የሚያገኙት እንደማንኛውም ታካሚ በሆስፒታሉ ተራ ጠብቀው ወረፋ ይዘው ነበር። የህክምናውን መረጃም ካገኙ በሁዋላ ያገኙትን መረጃ ይዘው ወደፖሊስ ይሄዳሉ። ከዚያም በሁዋላ ምናልባት የስነልቡና ችግር ከደረሰባቸው ወደስነልቡና የምክር አገልግሎት ይመለሳሉ። እንግልታቸው ከፍተኛ ነበር። በዚህ አካሄዳቸውም ወላጆችም ሆኑ ልጆቹ የሰዎች መጠቋቆሚያ ስለሚሆኑ እና ከወዲያ ወዲህ በሚሄዱበት ጊዜ የጥቃት አድራሹ ሰው ወገኖች ሊተናኮሉአቸው የሚችሉ መሆኑ ስለሚያሳስባቸው እንዲሁም ከምንም በላይ ጥቃቱ የደረሰባቸው ልጆች በየ ቦታው የሚያገኙዋቸውን ወንዶች በጥቃት አድራሹ አይን በመመልከት ስለሚጠሉዋቸው ጉዳዩ ከዳር ሳይደርስ መና ሆኖ ይቀር ነበር። በዚህም ምክንያት በሕጻናቱ የወደፊት ሕይወት ላይ ጠባሳ ጥሎ ያልፍ ነበር። አሁን ግን ሁሉም ባለሙያዎች በአንድ ማእከል ስለሚገኙ ተጎጂዎቹን ከወዲያ ወዲህ የሚያሰኛቸው ነገር የለም። ሌላ ታካሚ በሌለበት፣ ወረፋ ሳይጠብቁ፣ ከክፍል ክፍል በመሄድ ምስጢራቸው ሳይባክን ...የምክር አገልግቱ ተሰጥቶ፣ ሕክምናውንም ያገኛሉ። የፖሊስና የአቃቤ ህግ ቢሮውም እዚሁ ማእከል ውስጥ ስለሆነ ከክፍል ክፍል በመግባት ጉዳያቸውን ሁሉ በአንድ ቦታ ጨርሰው ጉዳት አድራሹም ሳይውል ሳያድር በህግ እንዲጠየቅ ማድረግ ይችላሉ።” ብለዋል።  
በአዳማ እና ዙሪያውን ባሉ አካባቢዎች በተለይም በወንዶች ላይ ተገዶ የመደፈር ጥቃት ሲደርስ ተጎጂዎቹን በህክምና የሚረዱት ዶ/ር ደሳለኝ ፈቃዱ ናቸው። ዶ/ር ደሳለኝ በአዳማ ሆስፒታል የቀዶ ሕክምና ስፔሻላይዜሽን ትምህርት የሚከታተሉ ናቸው።
“...የወንዶች ተገዶ የመደፈር ሁኔታ በተለይም በአዳማ እና ዙሪያውን ባሉ አካባቢዎች በጣም የተለመደ ሆኖአል። ጥቃት የደረሰባቸው ሕጻናት በአማካይ በቀን ሁለትና ከሁለት በላይ ሊታከሙ ይመጣሉ። በእድሜያቸውም የሶስትና የአራት አመት ሕጻናት እንዲሁም ከአስር እስከ ሀያ አመት የሆኑትም ብዙ ጥቃት እየደረሰባቸው አገልግሎት ፍለጋ ይመጣሉ። ይህ ችግር በህብረተሰቡ ውስጥ ያለ ሲሆን በተለይም በትምህርት ቤት ከፍ ከፍ ባሉ ተማሪዎች አማካኝነት እንዲሁም በከተማው ውስጥ ባሉ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለይም በወጣቶች የሚፈጸም ወንጀል ነው። ወንዶቹ ልጆች የወሲብ ጥቃት ሲፈጸምባቸው የተለያዩ ጉዳቶች ይደርስባቸዋል።
ለኤችአይቪ መጋለጥ፣
ለሄፒታይተስ በሽታ መጋለጥ፣
የስነልቡና ጉዳት፣
በፊንጢጣ በኩል መድማት ...ወዘተ የመሳሰሉት ሕመሞች ይገጥሙዋቸዋል።  
ወንድ ሕጻናቱ ተገደው ከተደፈሩ በሁዋላ በደፋሪዎቹ ማስጠንቀቂያም ይሁን እራሳቸው በማፈር ምክንያት ወዲያውኑ ለቤተሰባቸው አያሳውቁም። ጥቃቱ እንደደረሰባቸው ሳይናገሩ በመቅረታ ቸውም ምክንያት ተላላፊ በሽታዎቹን በጊዜው ተከታትሎ ሕክምና ለመስጠት አዳጋች ይሆናል። እንዲሁም በአካላቸው ላይ የሚደርሰው መቁሰል ወደከፍተኛ ደረጃ ስለሚደርስ ቶሎ ለማገገም የማያስችላቸው ይሆናል።”
ሕጻናቱ የደረሰባቸውን ጥቃት ለመደበቅ የሚገደዱት ወላጆች አስቀድሞ ማድረግ ያለባቸውን ዝግጅት ባለማድረጋቸው ምክንያት መሆኑን (RAINN : Rape Abuse and Incest national network) የተሰኘው ድረ ገጽ እንደሚከተለው ይገልጻል።  
በወሲባዊ ጥቃት ዙሪያ ከልጆች ጋር ውይይት ማድረግ ይገባል።
ሕጻናቱን እያንዳንዱን የሰውነታቸውን ክፍል ምን እንደሚባል አስተምር።
ሕጻናቱ ስለሰውነታቸው ክፍል መጠሪያ ሲያውቁ ያንን የሰውነት ክፍል ምንነት መግለጽና ስለሰውነት ክፍሉም የፈለጉትን ጥያቄዎች ከማንሳትም በላይ ጥንቃቄ እና እንክብካቤ ሊያደርጉ ይችላሉ።
የተወሰኑ የሰውነት ክፍሎች የግል መሆናቸውን ማሳወቅ፡
ሕጻናቱ እነዚህን የግል የተባሉ የሰውነት ክፍሎች ካለ ሕክምና ባለሙያ በስተቀር ሌላ ሰው እንዳይነካ እና በየቦታውም ተጋልጠው መታየት እንደሌለባቸው እንዲያውቁ ይረዳል። በእርግጥ ንጽህናን ለመጠበቅ ወይንም በተለያየ ምክንያት መታየት ቢያስፈ ልጋቸው የቅርብ ቤተሰቦች ማለትም እንደወላጅ...እናት... ወዘተ ሊያዩዋቸው ይችሉ ይሆናል።  
አንዳንድ ጊዜ እምቢ ወይንም አይሆንም ማለት ትክክል እንደሆነ ማስረዳት፡-
ሕጻናቱ የግል አካል እንደሆነ በተነገራቸው አካባቢም ይሁን በሌላ በማይፈልጉት የሰውነት ክፍል፣ በማይፈልጉት ሰው ሰውነታቸው እንዲነካ አለመፍቀድን እንዲማሩ ማድረግ ይጠቅማል። በእርግጥ ይህ መልእክት ለልጆች ግልጽ ላይሆን ወይንም እንዴት መግለጽ እንዳለባቸው ሊቸገሩ ይችላሉ። በዚህ ግዜ ወላጆችም ልጆቻቸውን ማገዝ ይገባቸዋል። ለምሳሌ በቤተዘመድ ግብዣ ወይንም ዝግጅት ላይ ልጆቹን በማቀፍ ወይንም በተለያዩ አላስፈላጊ ቦታዎች መነካካት አይነት ለማጫወት መሞከር በሚታይበት ጊዜ ዘመድ ነው ወይንም የቅርብ ሰው ነው ብሎ ለመከልከል እፍረት ቢሰማ ትክክል አይደለም።  ሁኔታው ልጆቹን ከማስጨነቁ በላይ በተጨማሪም መረሳት የሌለበት የወሲባዊ ጥቃት አድራሾች ማንነት ሲፈተሸ በተለይም በቅርብ ካለ ሰው፣ ከቤተሰብ፣ በስራም ይሁን በትምህርት ከለመዱዋቸው ...ወዘተ ሰዎች መሆኑን ነው።  
ምስጢር ስለሚባሉ ጉዳዮች በግልጽ መነጋገር፡-
አስገድደው የሚደፍሩ ሰዎች ብዙ ጊዜ ወንጀላቸውን የሚደብቁት ህጻናቱን ምስጢር ስለሆነ ለማንም እንዳትናገር፣ እንዳትናገሪ ስለሚሉዋቸው ነው። ነገር ግን ሕጻናቱ በየትኛውም ውሎ አዳራቸው የሚገጥማቸውን ነገር ለወላጆቻቸው ካለመደበቅ እንዲናገሩ ከተማሩ የጥቃት አድራሾቹን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ ስለማያደርጉ ሕጻናቱ በጊዜ ወደመፍትሔ እንዲሔዱ ይረዳል። ሕጻናቱ በራሳቸውም ብቻ ሳይሆን አንድ ሰው ሌላ ሕጻን ሲነካ ካዩም ለወላጆችም ሆነ በቅርብ ላለ ሰው እንዲናገሩ ማዘጋጀት እና እንደዚህ ያለው ነገር ምስጢር በሚል የሚደበቅ አለመሆኑን እንዲያውቁ ማድረግ ይገባል።  
ይቀጥላል

Read 2918 times