Saturday, 16 April 2016 11:07

የፊልምና ድራማዎቻችን ሥጋት፣ “ቃና” ወይስ...?

Written by  አስናቀ ሥነስብሐት
Rate this item
(0 votes)

  ረቡዕ፣ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራት ”ቃና” የተባለው የሳተላይት ቴሌቪዥን እያቀረበ ባለው የፕሮግራም ይዘት ላይ ”አለን” ያሉትን ሥጋትና ተቃውሞ የሚገልጽ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር፡፡ በመግለጫው ላይ የተነሱት ሐሳቦች በሁለት ነጥቦች ተጠቃለው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ እነርሱም፡-
የቃና ቲቪ አካሄድ የአገር ውስጥ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችን ከጨዋታ ውጭ ያደርጋል፣
በቃና ቲቪ የሚቀርቡ ፕሮግራሞች ለባሕል ወረራ ያጋልጣሉ
የሚሉ  ናቸው፡፡
በመሠረቱ፣ እነዚህ ማኅበራት የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበብና ባሕልን አስመልክቶ የተቆርቋሪነት ሥጋታቸውን መግለጻቸው ከምንም በፊትና በላይ ያስመሰግናቸዋል። ነገር ግን፣  የእስከዛሬ ልምዳችንና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎቻችንን እንቅስቃሴ ጠለቅ ብለን ስንፈትሽ፣ ”የማኅበራቱ እውነተኛ ሥጋት ምንድን ነው?” ብለን እንድንጠይቅ የሚያስገድዱ ሁኔታዎችም አብረው ይመጣሉ፡፡ እኔም በመግለጫውና ከመግለጫው በኋላ በተሰሙትና በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ከተገለጹት ሐሳቦች በመነሳት አስተያየቴን ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡
የሥጋቱ ምንጭ ምንድን ነው?
የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ማኅበራቱ በመግለጫቸው የቃና ቲቪ አካሄድ ”ያስከትላቸዋል” ያሏቸውን ”ጉዳቶች” ከላይ በጠቀስኳቸው ነጥቦች አንፃር በሚከተለው መልኩ አስቀምጠዋቸዋል፡፡
”ጣቢያው አጭር ዕድሜ ያለውን የቴሌቪዥን ድራማ ታሪካችንን በማቀጨጭ የፊልም ኢንዱስትሪውን ዕድገት የሚያሰናክል በመሆኑ ፕሮግራሙን በድጋሚ ሊከልስ ይገባዋል፡፡”
”በጣቢያው የሚቀርቡት የውጭ አገር ፊልሞች ንግድ-ተኮር በመሆናቸው ምንም ዓይነት ትምህርታዊና ሞራላዊ ይዘት የላቸውም፡፡”
እነዚህ የማኅበራቱ ”ሥጋቶች” ”መነሻቸው ምንድን ነው?” ብለን ስንጠይቅ፣ በይፋ የምናገኘው መልስ ”ለዘርፉ ሕልውና ከመጨነቅና የኢትዮጵያን ባሕል ከወረራና ከመበረዝ ለመከላከል ከማሰብ” የሚል ነው፡፡ የተሸፈነውና ትክክለኛው ምላሽ ግን አሁን ያሉት የዘርፉ ተዋንያን ”የእንጀራ ገመድ መበጠስ” ጉዳይ ነው ባይ ነኝ፡፡ አንድ የዘርፉ ባለሙያ እንደገለጹት፤በአሁኑ ወቅት በኪነ-ጥበቡ (በፊልምና የቴሌቪዥን ፕሮዳክሽኖች) ዘርፍ የሚሠሩ 10‚000 ያህል ”ባለሙያዎች” አሉ (”ባለሙያዎች” የሚለውን ቃል በትዕምርተ-ጥቅስ ውስጥ ያስቀመጥኩት በዕውቀት የተደገፈ ሥራ የሚሠሩት ሰዎች ቁጥር ይህን ያህል ደርሷል ብዬ ለማመን ስለሚከብደኝ ነው)፡፡ የእነርሱ ሥጋት ”እነዚህ ሁሉ ”ባለሙያዎች” በቃና ቲቪ አካሄድ ምክንያት ሥራ-አጥ ይሆናሉ” የሚል ነው። ሁለተኛውና ከባሕል ወረራ ጋር የሚገናኘው ሐሳብ የመጀመሪያውን ሐሳብ ለመደገፍና ለማኅበራቱ አቋም ጉልበት ለመስጠት የመጣ እንጂ በእውነት ማኅበራቱ ዛሬ ላይ ተቆርቁረውበት የሚያነሱት ነው ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቴን ወደፊት እመለስበታለሁ፡፡
የሥጋቶቹ የተጨባጭነት ልክ
በኪነ-ጥበብ ማኅበራቱ የተነሱት ሥጋቶች ትክክለኛ ሥጋት መሆናቸውን ለመፈተሽ፣ ወቅታዊውን የኢትዮጵያን የቴሌቪዥንና የፊልም ዘርፍ ሁኔታ መቃኘት የሚያስፈልግ  ይመስለኛል። በአሁኑ ጊዜ በኢትዮጵያ የቴሌቪዥን ቻናሎች ቁጥር (በሳተላይት ከውጭ የሚተላለፉትን ጨምሮ) ወደ 20 ገደማ ደርሷል፡፡ ከእነዚህ ቻናሎች መካከል ቀዳሚ የሚባሉት ብሔራዊና የክልል ቴሌቪዥኖች እንዲሁም የግል ቻናሎች ለቴሌቪዥን ድራማዎችና የአገር ውስጥ ፊልሞች ሰፊ የአየር ሰዓት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡ እንደ ማሳያ ኢቢሲና ኢቢኤስን ብንወስድ፣ ኢቢሲ አምስት ድራማዎችን (አራት ሲሪያልና አንድ ሲትኮም) ሳምንቱን በሙሉ በሁለት ቻናሎች የሚያቀርብ ሲሆን፣ ኢቢኤስ በበኩሉ አራት ድራማዎችን (ሁለት ሲሪያልና ሁለት ሲትኮም) ያቀርባል፡፡ በፊልም በኩልም ሁለቱም ቻናሎች ሳምንታዊ የታላቅ ፊልም (feature films) ፕሮግራሞች አሏቸው። እዚህ ላይ ሁሉም ድራማዎችና ፊልሞች ከመደበኛ ቀናቸው በተጨማሪ በድጋሚ የሚቀርቡ መሆናቸውን ልብ ይሏል፡፡
ከዚህ አንፃር ዛሬ ላይ በተለይ ለቴሌቪዥን ድራማዎች ቀን ወጥቶላቸዋል ማለት እንችላለን፡፡ ሚዲያዎቹም ተጨማሪ ድራማዎችን እንደሚፈልጉ እየሰማን ነውና በብዛት ደረጃ አንፃራዊ በሆነ መልኩ ዕድሉ ሰፍቷል ብንል የተሳሳትን አይመስለኝም፡፡ ቀጣዩ ጥያቄ ”ጥራት ላይ እንዴት ናቸው?” የሚለው ይሆናል፡፡
ምናልባትም የአሁኑ የማኅበራቱ ሥጋት እውነተኛ መነሻ ከዚህ ጋር የሚያያዝ ሊሆን ይችላል፡፡
የጥራትን ጉዳይ ከይዘት ጋር አጣምሮ መመልከት የተሻለ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ይዘት ሐሳብን፣ መልዕክትንና አቀራረብን የሚወስን በመሆኑ፡፡ ይዘት (content) ለተደራሲው ልናቀርብ የፈለግናቸውን ጉዳዮችና የምናነሳቸውን ጥያቄዎች በአንድነት ሰብስቦ የሚይዝ ቋት እንደመሆኑ፣ የይዘት ምርጫና ውሳኔ በሚተላለፈው ሐሳብና መልዕክት ጥራት ላይ ቀጥተኛ ተጽዕኖ ያሳርፋል። ከዚህ አኳያ፣ የቴሌቪዥን ድራማዎቻችን ይዘት በሚዲያዎቹ ምርጫ የሚወሰኑ ከሆነ፣ የደራሲዎችና የሐሳብ አመንጪዎች ምናብ በሚዲያው ምርጫ፣ አለፍ ሲልም ጫና ምክንያት ሊገደብ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ተጨባጭ ማስረጃ ለማቅረብ ቢያዳግተኝም፣ የጊዜያችን የቴሌቪዥን ድራማዎች የዚህ አካሄድ ሰለባ መሆናቸውን በተባራሪ ከምሰማቸውና እንደ ተመልካችም ከማስተውላቸው የሐሳብ መሳሳቶች በመነሳት መናገር እችላለሁ፡፡
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተመለከትናቸውንና እየተመለከትናቸው ያሉትን የአገራችንን የቴሌቪዥን ድራማዎች ከይዘትና ጥራት አንፃር ስገመግማቸው፣ የሚያነሷቸውን ርዕሰ-ጉዳዮች በአጠቃላይ ”በጣም ጥሩ” የሚል ደረጃ እሰጣቸዋለሁ፡፡
የአብዛኞቹ መነሻ ታሪክ ትኩረትን የሚስብ፣ አንዳንዴም የሚያመራምርና የሚያወያይ ነው፡፡ የሚያነሱት ጭብጥ በአብዛኛው ለኢትዮጵያዊያን ቅርብ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር በመሆኑ ድራማዎቻችን ከፍተኛ የተከታታይ ቁጥር አስመዝግበዋል ማለት ይቻላል፡፡
በሌላ በኩል ግን፣ ድራማዎቻችን ቀላል የማይባሉ ቴክኒካዊ ግድፈቶችን የተሸከሙ መሆናቸው ግልጽ ነው፡፡
አንዳንዶቹ ድራማዎች መነሻቸውን እንጂ መድረሻቸውን የማያውቁ፣ ሌሎቹ በአንድ ድራማ ውስጥ በርካታ ሐሳቦችን አጭቀው ሁሉንም ለማሳየት የሚውተረተሩና ያልተሳካላቸው፣ ከሞላ ጎደል፣ ሁሉም ደግሞ ድርሰቶቻቸውን በበቂ ጥናትና መረጃዎች ያላስደገፉ፣ በተለይም ደግሞ ሙያ-ነክ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ከፍ ያለ የተአማኒነት ጉድለት ያለባቸው ናቸው። እነዚህ ሁሉ ችግሮች፣ በእኔ አመለካከት፣ በወረቀት ላይ ተስተካክለው ሊቀርቡ የሚችሉ እንጂ፣ አሁን በቃና ቲቪ ጉዳይ ላይ እንደሚነሳው ከገንዘብ አቅም ማነስ፣ ከግብዓቶች ውድነት፣ ወዘተ፣ ጋር የሚያያዙ አይደሉም። ይህንን እንዲሠሩ የሚጠበቅባቸው ባለሙያዎቻችን ናቸው እንግዲህ አዲስ አቅጣጫ ይዞ የመጣውን ሚዲያ በገና-ለገና ”ከገበያ ያስወጣናል” በሚል ሥጋት፣ እርምጃ እንዲወሰድበት እየወተወቱ ያሉት፡፡
ከላይ የዘረዘርኳቸውን ጉድለቶች በጥቅሉ ያስቀመጥኩት፣ አሁን በማኅበራቱ የተነሱት ሥጋቶች በተወሰነ ደረጃ መሠረት ያላቸው ቢሆኑም፣ ዋነኛው ችግር የሥራዎቹ በተገቢው ደረጃ ያለመቅረብ እንጂ የቃና መምጣት አይደለም ለማለት ነው፡፡
በቀጣይ ይህን ሐሳቤን በዝርዝር ለማቅረብና የአገራችንን የቴሌቪዥን ድራማ ወቅታዊ ሁኔታ ከቃና ቲቪ አካሄድ አንፃር ለመገምገም እሞክራለሁ፤ እግረ-መንገድም ”ቃና” ያስተዋወቀውን አቀራረብ በሂሳዊ ዓይን ለመመልከት። በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ የፊልምና የቴሌቪዥን ድራማ ዘርፍ ምን ቢያደርግ የተሻለ ደረጃ ላይ ሊደርስ እንደሚችል የምሰጠው አስተያየት ይኖረኛል፡፡

Read 2289 times