Saturday, 09 April 2016 09:48

ሠርክ ጥፋት! ሠርክ ጣት መቀሳሰር!

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(2 votes)

      ለሚደርሰው ጥፋት ሁሉ ሌሎች ላይ ጣትን መቀሰር፣ ከ“መንግሥታችን” ጉልህ መለያዎች አንዱ ነው ብንል ስህተት አይሆንም፡፡ የትኛውንም ዘርፍ በኃላፊነት እያስተዳደርኩ ነው የሚለው ተቋም፣ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ እስከ ወረዳ ጽሕፈት ቤቶች፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሁሉም መገለጫ ከሆኑት መልኮች አንዱ፣ በህዝብና በሀገር ላይ ለሚደርሰውና እየደረሰ ላለው ጥፋት ሁሉ ሌሎች ላይ ወይም እርስ በርስ ጣት መቀሳሰራቸው ነው፡፡… ማንም በራሱ ግዴለሽነትና የድርሻውን ባለመወጣቱ ለሚደርሰው ጥፋት ኃላፊነትን መውሰድ ሞቱ ነው፡፡ አንዱ ሌላው ላይ ጣቱን እየቀሰረ እጁን ለመታጠብ ይጣደፋል፡፡ ማቆሚያ የሚያገኝ የማይመስል ቁልቁለት!...
ኃላፊነቱን ወስዶ ጥፋቱን ያልተቀበለ አካል በምንም አግባብ ስህተቱን ማረም አይችልም፡፡ ይህ አይነቱ አስተሳሰብ በተንሠራፋበት፣ ጣታቸውን ወደ ሌሎች ብቻ የሚቀስሩ ግለሰቦች ወንበር በያዙባት ሀገር፣ የትኛውም አይነት ጥፋት ዘላቂና ኗሪ ነው፡፡ የትኛውም ጥፋት የሚወገደው ስህተቱን ለመቀበል በማያፍርና ዳግም እንዳይፈጠር ለመትጋት ዝግጁ በሆነ አካል እንጂ በራሱ (በጥፋት) አይደለም። የትኛውም ጥፋት በራሱ አይጠፋም፤ ይልቁንም አቅሙንና አድማሱን ያሰፋል፡፡
በሌሎች ሀገሮች ሲሆን የምንሰማውና የምናየው በእኛ ሀገር እየሆነ ካለው በእጅጉ የተለየ ነው። በእነዚህ “የታደሉ” (መታደል እንጂ ሌላ ምን ይባላል?!) ሀገሮች አንዳች ጥፋት ሲደርስ፣ ጥፋቱ እንዳይደርስ የመትጋቱን ኃላፊነት የተረከበው ተቋም መሪ ከአንገቱ ዝቅ፣ ከወገቡ ሰበር ብሎ ህዝብንም ሀገርንም ይቅርታ ይጠይቃል፡፡ ይቅርታ መጠየቅ ብቻም አይደለም፤ ያለማንም ግፊትና አባራሪ “ኃላፊነቴን መወጣት አልቻልኩም” ብሎ ስልጣኑን ይለቃል፡፡ ራሱን ያሰናብታል፡፡ (እና ይሄ መታደል አይደለም?!)…
ህዝቦቿ ሠርክ መከራን አዝለው በሚቃትቱባት በእኛዋ ሀገር የሚሆነው ግን ሌላ ነው፤ ፍጹም ተቃራኒ፡፡ ለደረሰው ጥፋት ኃላፊነቱ የእሱ መሆኑ ፀሐይ የሞቀው፣ ወረቀት ያጸደቀው እውነት ቢሆንም ቅሉ፣ የትኛውም ተቋም ሌላው ላይ ጣቱን ጠቁሞ፣ ከደሙ ንፁህ ነኝ በማለት ተጣድፎ እጁን ይታጠባል፡፡ ይህንን ሠርክ ታዝበናል፡፡…
“በየመንገዱ ላይ ተቆፍረው የተተዉ ጉድጓዶች ለሰው ህይወት መቀጠፍ ምክንያት እየሆኑ ነው” ይባላል፡፡ ችግሩ የእኛ ሳይሆን እከሌ የተባለው መስሪያ ቤት ነው ይለናል ባለቤቱ፣ ቅንጣት እፍረት ሳይሰማው፡፡… “በመብራት መቆራረጥ ምክንያት በሆስፒታሎች ውስጥ የህሙማን ህይወት በየጊዜው እያለፈ ነው” እንላለን፡፡ ችግሩ የእኛ ሳይሆን ኃይልን የሚያቀርበው መስሪያ ቤት ነው ይሉናል ሆስፒታሎቹ፣ እንዴት እኛ እንጠየቃለን በሚል ድንፋታ፡፡… “በልማት ሰበብ በርካቶች መጠለያ አጥተው ጎዳና ላይ እየወደቁ ነው” ይባላል፡፡ ለዚህ ጥፋት ተጠያቂው የእከሌ መስሪያ ቤት ነው እንጂ እኛ አይደለንም ይላል፣ ጎጆዋቸውን የናደው ተቋም፡፡… “ማህበረሰቡ በዋጋ ጭማሪ የሚይዘውን እያጣ ነው”- ለዚህ ተጠያቂዎቹ እነእከሌ ናቸው ይለናል ባለቤቱ፣ የሥራ ድርሻው ላይ የተቀመጠውን አንቀጽ ክዶ።… “ከዕለት ዕለት እየበዛ የመጣው የትራፊክ አደጋ የዜጎችን በሰላም ወጥቶ በሰላም መግባት ሰቀቀን እያደረገው ነው” ይባላል፡፡ ለአደጋው ተጠያቂዎቹ አሽከርካሪዎች ናቸው ይለናል፣ ለአሽከርካሪዎቹ የመንጃ ፈቃዱን የሚሰጠው ተቋም፡፡… መዘርዘሩ ያደክማል፡፡… ሠርክ ጥፋት! ሠርክ ጣት መቀሳሰር!  
ዛሬም መፍትሔው ሌሎች ላይ ጣትን ከመቀሰር ስላልተፋታ የብዙዎችን ህይወት፣ ተስፋና ህልም እየቀጠፈ ያለው የትራፊክ አደጋ ከዕለት ዕለት የጥፋት አድማሱን እያሰፋ የበርካቶችን ቤት የሐዘን ማቅ ማልበሱን ቀጥሎአል፡፡ ስህተቱን ተቀብሎ፣ ጥፋቱን ቢያንስ ለመቀነስ ኃላፊነት ተሰምቶት የምሩን የሚተጋ አካል ባለመኖሩ ዛሬም በርካቶች ህይወታቸውን እያጡ ነው፡፡… ባለፈው ሰኞ ረፋድ ኮልፌ ላይ የሆነውም ይኸው ነው- የብዙዎች እንባ ገና ባልጠፈፈባት ኮልፌ!...
የዛሬ 5 ዓመት ግድም፣ በተቀጣጣይ ኬሚካል የተመላ ኮንቴይነር የጫነ ተሳቢ መኪና ዛሬም ድረስ የብዙዎችን ልብ በሐዘን ተሰብሮ እንዲቀር ያደረገ አደጋን አድርሶአል፡፡ በአደጋው ከአረጋዊ እስከ ቦርቀው ያልጠገቡ ህጻናት፣ ጫጉላዋን ካልጨረሰች አዲስ ሙሽራ፣ ከሳምንት በኋላ ጋዎናቸውን ለብሰው እስከሚመረቁ ባለ ብዙ ህልም ወጣቶች በወጡበት ቀርተዋል፡፡ ክስተቱ መቼም የማንረሳቸውን ቤተሰቦቻችንንና ወዳጆቻችንን ነጥቆናል፡፡… ሐዘኑ ሲያስቆጭና ሲያም የሚኖር የእግር እሳት ነው፡፡ አረሳነውም፡፡ አንረሳውምም!...
ባለፈው ሰኞ ረፋድ ላይም የቀደመው መከራ ያንስ ይመስል፣ ኮልፌን የሐዘን ማቅ ያለበሰ ሌላ መዓት ሆነ፡፡ ነዋሪው የእለት ጉርሱን ለማግኘት በመጣደፍ ላይ ሳለ ድንገት ተወርውሮ የመጣ ከባድ የጭነት መኪና 18 ማዞሪያ አደባባይ ላይ ከፊቱ ያገኘውን ሁሉ እየጠራረገ፣ ስድስት መኪኖችን ከጥቅም ውጪ አድርጎ፣ ከአንድ መድሐኒት ቤት ውስጥ ገባ። ክስተቱን በመሳል ብቻ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ መገመቱ የሚከብድ አይደለም፡፡… መሻገሪያው ላይ ያገኛቸውንና በጨፈለቃቸው መኪኖች ውስጥ የነበሩትን ሰዎች ጨምሮ በመድሐኒት ቤቱ ውስጥ መድሐኒት በመግዛት ላይ የነበሩ ሰዎችን ህይወት ቀጠፈ፡፡ ነገሩ ከማስደንገጥ በላይ የሚያስደነግጥ ነገር አለው፡፡ ሰዎች ለታመመ ሰው መድሐኒት እየገዙ ህይወታቸውን አጡ፡፡ መድሐኒት ሲፈልጉ ሞቱ!...
በዚህ አደባባይ ላይ የዚህ አይነቱ ልክ የለሽ የትራፊክ አደጋ ሲደርስ ይሄ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ለመቁጠር እስኪታክት ድረስ ተደጋግሞአል፡፡ ሁሌም እንደሚስተዋለው አደጋውን የሚያደርሱት ከላይ ከወደ አጠና ተራ ቁልቁል የሚመጡት መኪኖች ናቸው፡፡ የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? (የመስኩ ባለሙያ ባለመሆኔ እዚህ ውስጥ ገብቼ ባልዘባርቅም፣ ችግሩ መፍትሔ እንዳለው ግን በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ።)… አስገራሚውና አናዳጁ ጉዳይ ግን ትናንትም ዛሬም ችግሩ እንዲወገድ ኃላፊነቱ በተሰጠው አካል ምንም አይነት እርምጃ አለመወሰዱ ነው፡፡ ንቀትም ይመስላል፡፡… ይልቁንም ተቋሙ ዛሬም እንደትናንቱ (እንደተለመደው)፣ ጣቱን አሽከርካሪዎች ላይ እየቀሰረ ነው፡፡ ወደ ራሱ መቀሰር ሞት ሆኖበታልና ጥፋቱ ነገም ይቀጥላል፡፡ ነገም በዚሁ ቦታ ብዙዎች ህይወታቸውን ያጣሉ፡፡...
ጥፋቱ አብዝቶ ኮልፌ ላይ መደጋገሙን ማሳያ አድርጌው እንጂ፣ የአደጋው መከሰትና በዚህም የብዙዎች ህይወት መጥፋቱ በመላ ሀገሪቱ የትም እየሆነ ነው፡፡ ኤፍ. ኤምዎቻችንና ማህበራዊ ድረ ገጾቹ በየዕለቱ የሚያረዱን ብዙ ነው፡፡… ሴክተሩን ሊያስተዳድር ገንዘብና ኃላፊነትን ተረክቦ “የቆመው” (ቆሞአል ማለቱ ቢከብድም ቅሉ) ተቋም “ኃላፊዎችም” እየደረሰ ላለው ሀገራዊ ጥፋት (የበርካታ ዜጎች ህይወት በወጡበት መቅረት ከሀገራዊ ጥፋትም በላይ ነው) ዛሬም እንደ ትናንቱ በአሽከርካሪዎች ላይ ጣታቸውን እንደቀሰሩ አሉ።… እንዲሁ ነው፡፡ እንደሌሎች “ወንድሞቻቸው” ተቋማት (ወንድም ማለቴ አባታቸውም ግብራቸውም አንድ በመሆኑ ነው) ሁሉ ጣታቸውን ሌላው ላይ ቀስረው ይቀመጣሉ፡፡…
ጣት ቅሰራው በራሱ የሚያናድድ አይነት ፌዝ ነው፡፡ የተዝረከረከና ስልት የለሽ ጣት ቅሰራ። ሲጀመር ተቋሙ ሠርክ ጣቱን ለሚቀስርባቸው አሽከርካሪዎች የመንጃ ፈቃዱን የሚሰጠው እኮ ራሱ ነው፡፡ ነገሩን አሜን ብለን ለአደጋው ተጠያቂዎቹ አሽከርካሪዎች ናቸው ብንል እንኳን፣ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ከአሽከርካሪዎቹ ጀርባ የተቋሙ እጅ አለ፡፡ እየጠፋ ላለው የሰው ህይወትና ንብረት በዚህም ለሚፈሰው የበርካቶች እንባና ለሚሰበረው ልብ ተቋሙና ኃላፊዎቹ ተጠያቂ ናቸው፡፡ በሙስና የመንጃ ፈቃድ የምትሰጡ፣ ገንዘብ ተቀብላችሁ ብቁ ያልሆነ ተሽከርካሪን የቴክኒክ ፍተሻ የምታሳልፉ ሁላችሁ፣ ባይመስላችሁም ከዚህ ሁሉ ጥፋት ጀርባ እጃችሁ አለበት፡፡
እውነቱ ይኸው ነው፡፡ በየሰበቡ የሰበሰባችሁት ጥቅምም ኃላፊነታችሁን ተወጥታችሁ ያተረፋችሁት የላባችሁ ፍሬ ሳይሆን ለብዙዎች ደምና እንባ መፍሰስ ምክንያት የሆነ ዕዳችሁ ነው። ህሊናው ላለው የምንጊዜም ፀፀት የሚሆን ዕዳ!...   
ትጉሁ ጋዜጠኛውና ጸሐፌ ተውኔቱ ቴዎድሮስ ተክለ አረጋይ ከወራት በፊት በፌስ ቡክ ገጹ ላይ ያሰፈረው ጥያቄ (ለኤሌክትሪክ ኃይል መስሪያ ቤት ኃላፊ ይመስለኛል) ሰሚ ልብን ቢያገኝ ታላቅ በትር ነው፡፡ የተቋሙን ኃላፊ ባገኛቸው “አንድ ጥያቄ እጠይቃቸው ነበር” ብሎ የተለመዱ ጥያቄዎችን እያነሳሳ እንዲህ ብዬ አልጠይቃቸውም ሲል ቆይቶ፣ በመጨረሻ ግን ኃላፊውን ይህን ጠየቀ፡፡ (ሐሳቡን እንጂ ቃል በቃል አልቀዳሁትም) ማታ ሥራውን በሚገባ እንደፈጸመ ሰው እንቅልፍ ይወስዶታል ወይ?... ያስደነግጣል! እኔም የቴዎድሮስን ጥያቄ የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ “ኃላፊዎችን” እጠይቃለሁ፡፡
“ኃላፊነታችሁን ሳትወጡ ሌሎች ላይ ጣታችሁን የምትቀስሩ እናንተ፣ እውነት ማታ ስትተኙ ኃላፊነቱን እንደተወጣና ሥራውን እንደከወነ ሰው እንቅልፍ ይወስዳችኋል?!”… የሚገባው ተቋምና ግለሰብ ሁሉ ይህንን ጥያቄ ይውሰድ፡፡…
“ሀይ” ባይ ያጣው ጥፋት ብዙዎችን እያስነባ ነው፡፡ መንግሥት ለዚህ የዜጎች የሠርክ ሰቀቀን ለሆነ አደጋ፣ የምር የሆነ ትኩረት መስጠትና አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ በመውሰድ ጥፋቱ ላይ የመስራት ኃላፊነት፣ ውዴታ ሳይሆን ግዴታ አለበት። ጣት መቀሳሰሩን አቁሞ ማስቆም፣ ኃላፊነትን ወስዶ ማስወሰድን ሊማር ይገባል፡፡ የራስን የቤት ሥራ ሳይሰሩ የትኛውንም አይነት ጥፋት ሌሎች ላይ ማሳበብ፣ የትኛውንም አይነት ጥያቄ ሸፋፍኖና አለባብሶ ለማለፍ መትጋት፣ በየትኛውም መስፈርት ጥፋቱን ያሰፋዋል፣ ጥያቄውን ያገዝፈዋል እንጂ አያከስመውም፡፡ ይልቁንም እያደር መዘዙ ይከፋል፡፡… ሲመስለኝ፣ የህዝቦች አመፅ ሰበቡም፣ የብዙ መልስ ማጣቶች ጥርቅም ነው፡፡
መልካም ሰንበት!   

Read 1419 times