Saturday, 09 April 2016 09:28

ምነው ዶናልድ ትራምፕ በተመረጠ!

Written by  ገብረእግዚአብሄር ወንዳፈረው (ሌ/ኰሎኔል)
Rate this item
(8 votes)

    አዲስ አድማስ ባለፈው መጋቢት 24 ዕትሙ “ተቃዋሚዎች በአሜሪካ ምርጫ ማን ቢያሸንፍ ይመርጣሉ?” በሚል ርዕስ የተወሰኑ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር አባላትን አነጋግሮ የሰጡትን አስተያየት አስነብቦናል፡፡
የተቃዋሚ አመራር አባላቱ የሪፐብሊካ ተወካዩ ዶናልድ ትራምፕ እንዲመረጥ እንደማይሹና ለዚህም የሰጡትን ምክንያት ሳነብ ተገረምኩ፡፡ የአሜሪካን ፕሬዚደንት ሆኖ የሚመረጥ ሰው በግሉ የሚወስነው ነገር እንደሌለ ሊታወቅ ይገባል፡፡ የኋይት ሃውስ ስታፍ በርካታ የተለያዩ አማካሪዎችን (የፀጥታ፣ የወታደራዊ፣ የውጭ ጉዳይ፣ የአስተዳደር ሌሎችንም) ያካትታል፣ የኦቫል ኦፊስም የሚኒስትሮችን ስብስብ ጭምር ያቀፈ ነው፡፡ የሚኒስትሮችን ሹመትና የፖሊሲ ውሳኔዎች ኮንግሬሱ ማፅደቅ ይኖርበታል።
 እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ትራምፕ ቢመረጥ ምን እንደሚወስን አላውቅም ማለት ከፖለቲካ ሰዎች አይጠበቅም። አብርሃም ሊንከን በ1860 በተደረገው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ወቅት ከጅምሩ እንደ ትራምፕ እየቀደመ በመሄዱ፣ “ይህ ደንቆሮ እንዴት የአሜሪካ ፕሬዚደንት ይሆናል” እየተባለ ልክ እንደ አሁኑ ትራምፕ ብዙ ትችት ቀርቦበታል፣ ሆኖም ከተመረጠ በኋላ የሰበሰባቸው ሚኒስትሮች በሙሉ ጠንካራና በዕውቀት የመጠቁ ስለነበር ለጥቁሮች መብት መከበር እንደተጋና በዚያ ክፉ የእርስበርስ ጦርነት ወቅት አሜሪካንን ከጥፋት እንደታደጋት ታሪክ ያስረዳናል፡፡ ታላቅ መሪ ተብሎም ሲታወስ ይኖራል። አቶ ሞሼ ሰሙ በሰጡት አስተያየት፤ “ዲሞክራቶች ዕርዳታ ማድረግና ፀብ አጫሪነትን የማይሹ፣ ማስታረቅና ማረጋጋት የሚፈልጉ ናቸው፣ ሪፐብሊካኖቹ ግን ራሳቸውን የዓለም ሰላም አስከባሪ አድርገው ያያሉ” ብለዋል፡፡ አቶ ሞሼ ይሄን መረጃ ከየት ይሆን ያመጡት?  
ዲሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች በውጭ ጉዳይ ፖሊሲያቸው ላይ የሰፋ ልዩነት የላቸውም፣ ሁለቱም መሠረታዊ ዓላማቸው የአሜሪካንን ጥቅም ማስጠበቅ ነው፡፡ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ የተዋጋላት የጥንቷ ዩጎዝላቪያ ቀን ከሌት በአሜሪካ ቦምብ ተደብድባ የፈራረሰቺውና ስምንት ቁርጥራጭ አገራት የሆነችው በቀድሞ ፕሬዚደንት ክሊንተን (ዴሞክራት) ዘመን እኮ ነው፣                                                                                                            አሁን በኦባማ (ዴሞክራት) ዘመንም የሶርያ ህዝብ ለስደትና ለዚህ ሁሉ መከራ እየተዳረገ ያለው፣ አሳድ ከስልጣን ካልወረደ በሚል በአሜሪካ መራሹ የምዕራብና የአረብ ሃገራት ጥምረት ነው፡፡ ከአንድ ዓመት በላይ በአሜሪካን ሠራሽ ተዋጊ ጄትና ሚሳይል እንዲሁም በሳኡዲ አየር ኃይል የየመን ህዝብ ስቃይ እየበላ ያለው በኦባማ (ዴሞክራት) ዘመን አይደለም እንዴ? ከግማሽ ምዕተ ዓመት በፊት የኩባ ሚሳይል ክራይስስ (Cuban missile crisis) እየተባለ የሚታወቀው በይ ኦፍ ፒግስ (bay of pigs) ወረራ የተሞከረው በኬኔዲ (ዴሞክራት) ዘመን መስሎኝ፣ ከዚህ የበለጠ ፀብ አጫሪነትና የዓለምን ሠላም ማደፍረስ ከየት ሊመጣ ነው?
በኔ በኩል የትራምፕ ፍልስፍና ተመችቶኛል፣ አሜሪካ እጇን ስብስባ ኢኮኖሚዋን ታሳድግ ነው የሚለው፡-
በሩቅ ምስራቅ ጃፓንና ኮሪያ ያለው 60ሺ ጦር ከ2ኛው ዓለም ጦርነት ማግስት ጀምሮ ለሰባ ዓመታት መስፈሩ አክስሮናልና አስወጣለሁ፣ አለበለዚያ አገራቱ ወጪውን ይሸፍኑ፣
በሜክሲኮ በኩል ድንበሬን አጥራለሁ፤ ወጪውንም የሜክሲኮ መንግሥት ይሸፍናል፣
እስልምና ተከታዮችን እንዳስፈላጊነቱ እያጣራሁ እንጂ ዝም ብዬ በጅምላ ወደ አሜሪካ ማስገባት አቆማለሁ
የኔቶ (NATO) አባል መሆናችን ትርጉም የለውም፣ ቀዝቃዛው ጦርነት አሜሪካ ከፍተኛውን መዋጮ በማድረጓ ጎድቶናል፣ የዓለም ሠላም የተረጋጋ በመሆኑ በአውሮፓ ያለውን ጦር አስወጣለሁ፣
ቻይና ያለቀረጥ ሸቀጥ እያስገባች ተጠቃሚ ስትሆን የአሜሪካንን ኢኮኖሚ በብርቱ ጎድታለች፣ በኔ ዘመን ቀረጥ እንድትከፍል አደርጋለሁ፣ በዚህም የአሜሪካንን ኢኮኖሚ በአጭር ግዜ አሳድጋለሁ፣
ባጠቃላይ በስምንት ዓመት ውስጥ 19 ትሪሊዮን ዶላር የአሜሪካን ዕዳ ነፃ አደርጋለሁ፣ የሚል ራዕይ ይዞ የመጣን የንግድ ሰው እኛ እንዴት እንቃወማለን? ለአገሩ ዕድገት በተመኘ ለምን እንሳደባለን፣ ተመርጦ የሚሰራውን ማየት አይሻልም!
የአላስካ አገረገዥ የነበረችውና አሁን የትራምፕ ደጋፊ የሆነችው ሣራ ፔለን ያለችውን በመድገም ሃሳቤን ልቋጭ፣ “እኛ ፖለቲከኞች ዲፕሎማሲያዊ ቃላቶችን በመጠቀም፣ ለመመረጥ ስንል ብቻ ህዝቡን በማታለልና የማናደርገውን እናደርጋለን በማለት ቃል እንገባና ሥልጣን ላይ ከወጣን በኋላ ግን ቃላችንን ሳናከብር በአግባቡ የተናገረውን ሳንፈፅም እንቀራለን፣ ትራምፕ ለኔ ሃቀኛ ሰው መሆኑን ከፊት ለፊት ንግግሩ መረዳት አያዳግትም፣ በንግዱ ዓለም እዚህ ደረጃ መድረሱ ጠንካራ ሰው መሆኑን ያሳያል፣ እስኪ የኛን ሥራ ከፖለቲካ ውጭ የሆኑ ሰዎች ይሞክሩት” ዶናልድ ትራምፕ ፕሬዚደንት ሆኖ ከተመረጠ የተናገረውን ሁሉ እንደሚፈፅም መገመት ይቻላል፣ ለመፈፀምም የሚከብድ ነገር የለበትም፣ የአሜሪካንን ጥቅም ሙሉ በሙሉ የሚያግዝና ኢኮኖሚውን ባጭር ግዜ ውስጥ እንደሚያሳድግ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል፣ ድጋፍም ያገኝበታልና ያደርገዋል፡፡ የአሜሪካ ጦርም እዚያው በክልሉ ይሆናል ማለት ነው፣ በመቶ ሺዎች ለሚቆጠረው የአሜሪካ ጦር በመቶ ቢሊዮኖች ዶላር የሚቆጠር የወታደራዊ ተልዕኮ ወጪ ለሌላ ልማት ሥራ ይውላል፣ በአውሮፓና ሩቅ ምስራቅ ያለው ጦር ወደ አገሩ ሲመለስ ዓለም ሠላም ይሆናል፤ እፎይታ ያገኛል፡፡ ይሄን ጊዜ ልማትና ዕድገት ለዓለም ህዝብም ለአሜሪካንም በተገቢው መንገድ መጣ ማለት ይመስለኛል። እንደ እኔ ከሆነ ምነው ትራምፕ በተመረጠ!!
ፀሐፊውን በኢ-ሜይል አድራሻቸው  This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

Read 3953 times