Saturday, 09 April 2016 09:09

የመንግስት የውጭ እዳ 20 ቢ. ዶላር ደረሰ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

• መንግስት በዓመት ለውጭ እዳ ከ900 ሚሊዮን ዶላር በላይ ይከፈላል
• የወለድ ክፍያው ብቻ በዓመት ወደ 300 ሚ. ዶላር ይጠጋል
• የአገር ውስጥና የውጭ ጠቅላላ እዳ 770 ቢ. ብር ሆኗል

     ባለፉት አምስት አመታት በፍጥነት እየገዘፈ የመጣው የመንግስት የውጭ እዳ 20 ቢ. ዶላር እንደደረሰ ሰሞኑን ከገንዘብ ሚኒስቴር የተገኘ መረጃ ያስረዳል፡፡ በስድስት ወራት ውስጥ ለውጭ እዳ ክፍያ 450 ሚ. ደላር ተከፍሏል፡፡ ከዚህም ውስጥ 140 ሚ. ዶላር የወለድ ክፍያ ነው፡፡
በ2001 ዓ.ም የመንግስት የውጭ እዳ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በታች እንደነበረ የሚታወስ ሲሆን፤
በታህሳስ ወር የእዳ ክምችቱ ሃያ ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡ ከዚያ ወዲህ ባሉት ወራት እስከ ሰኔ የበጀት መዝጊያ ድረስ የሚመጡ ብድሮች ሲጨመሩበት፣ እዳው ወደ 22 ቢሊዮን ዶላር ሊጠጋ ይችላል፡፡
በአምስት አመታት ውስጥ ወደ አራት እጥፍ ከገዘፈው የእዳ ክምችት ጋር፤  እዳ ከነወለዱ
ለመመለስ አገሪቱ የምታጣው ገንዘብም በእጅጉ ጨምሯል፡፡ በ2001 ዓ.ም፣ እዳ ለመመለስ ኢትዮጵያ የከፈለችው 80ሚ. ዶላር አይሞላም ነበር፡፡የዘንድሮው ክፍያ ከ900 ሚ. ዶላር በላይ ይሆናል፡፡
 ከዚህም ውስጥ የብድር ወለድ ለመክፈል የሚውለው ገንዘብ ወደ 300 ሚ. ዶላር ይጠጋል ተብሎ
ይገመታል፡፡ ከአምስት ዓመት በፊት ግን የወለድ ክፍያው ከ30 ሚ ዶላር በታች ነበር - አምና 250 ሚ.ዶላር፡፡ በሌላ በኩል፤ የመንግስት የአገር ውስጥ ብድርም እንዲሁ፤ በአምስት ዓመታት ውስጥ፣ ከመቶ
ቢሊዮን ብር ወደ 350 ቢሊዮን ብር ጨምሯል፡፡ እስከ ታህሳስ ወር ድረስ ጠቅላላ የመንግስት የአገር ውስጥና የውጭ እዳ 770 ቢ. ብር እንደደረሰ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ይገልጻል፡፡  



Read 3656 times