Monday, 04 April 2016 08:54

ተናዳፊ ግጥም

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በዕውቀቱ የተቀኘው “የባይተዋር ገድል”
               ምርጫና ሂስ ፥ ዕዝራ አብደላ
                        [ተናዳፊ ሥሩ ነደፈ ነው። ተሰማ ሀብተ ሚካኤል ሲተረጉሙት የቃሉ ጨረር አይመክንም። (ገጽ 667) “ ንብ ነደፈ፥ በመርዙ ጠዘጠዘ ወጋ ጠቀጠቀ ” ወይም “ በፍቅር ተነደፈ ተያዘ ተቃጠለ ” እንዲሁም“ ባዘቶውን አፍታታ በረበረ ” ..... ግጥም ለጭብጡ፥ ለስንኝ አደራደሩ ወይም ለቋንቋው ምትሀት ምናባችንን ከቧጠጠ ተናዳፊ ነው፤ አንብበነው የምንዘነጋው፥ ጥፍሮቹ የተከረከመው ግን ኢ-ግጥም ነው።]
-- ቁጥር 4 --
-------------------------------
የባይተዋር ገድል

በቁም መስተዋት ፊት መቆምኽ ሲጨንቅህ
የቁም መስተዋቱ፥ “ሰውነትህ የታል?” ብሎ
ሲጠይቅህ
ግድግዳው ላይ ያለች፥ የገደል ማሚቶ፥ ዝም
ማለት ፈርታ
ሳሎንህን ስትሞላው ዝምህን አባዝታ
ሕልም የቀላቀለ፥ የዝናም ነጠብጣብ፥ ጣራኽን
ሲመታ
ከመስኮትኽ ማዶ፥ የሌሊት ወፍ ሞታ
የጊዜ ስውር ክንድ
የጓሮህን ዋርካ ያላጋር ሲያስቀረው
በሌሊት ወፍ ምትክ፥ የኑሮ ገባር ወንዝ፥ አልጋህን
ሲገምሰው
“መንሳፈፉስ ይቅር፥ መስጠም ያቅተዋል ሰው?”
ሲያሰኝህ ዕድልህ
ያኔ ይጀምራል፥ የባይተዋር ገድልህ።
-------------------------------
©በዕውቀቱ ስዩም
 [ስብስብ ግጥሞች፥ ገፅ 72]
-------------------------------
ገድል፥ የፃድቃንና የሰማእታት ሣይሆን አንድ ግለሰብ ከማኅበረሰቡ ሲፋተግ፥ አለበለዚያ ሥነልቦናዊ ቁስሉ፥ ስጋቱ ሲመዘምዘው ገና የሚጠብቀውን ዕንግልት ይጦቅማል። የተወለድንበት ቀዬ ናፍቆት እና የመንደራችን ትዝታ አገርሽተው ከአዲስ አካባቢ መኖር ስንጀምር ባይተዋር ያደርጉናል። አዲሱን ስንላመድ ናፍቆት እየፈዘዘ፥ ትዝታም እያፈገፈገ መንፈሳችን ወከክ ተርከክ ይላል። ይህ የስፍራ ባዳነት ትንፋሽ ያጥረዋል፤ ከራስ ጋር መላተም ነው ጥልቅ ስሜት። በዕውቀቱ የተቀኘለት ግለሰብ ግን የስፍራ ለውጥ፥ የናፍቆት የትዝታ ሰለባ አይደለም። ውስጡ የደቀቀ ንቃተ-ህሊናው ለመርገብ ያልፈቀደለት ብቸኛ ይመስላል። በሁለቱም -በብቸኝነት እና በብቻነት- የሚማቅቅ ነው። ብቻነት ከሌላው ለመቀላቀል ጉጉት እያለው ተገፍትሮ ሌጣውን የቀረ ነው። ማኅበራዊ መተሳሰር፥ ፍቅረኛ ወዳጅ ቢያገኝ ሊተርፍ ይችላል። `ብቸኝነት` ግን ከሰዎች መካከል ሆኖ፥ ቤተሰብም ኖሮት ጣዕማቸው ሲሟጠጥ፥ ከነሱ ጋር መኖር የግድ ሆኖበት ሲጐመዝዘው ባይተዋር ነው። አንድ ግለሰብ ብቸኝነት ሲመዘምዘው፥ ሲገለል፥ ለራሱ ለሌላውም ባዳ ሲሆን ለአካላዊ ሆነ ሥነልቦናዊ እንግልት ይዳረጋል። ለዚህ ባይተዋር ነው በዕውቀቱ ገለልተኛ ተራኪ መልምሎ የተቀኘው። ዝነኛ አሜሪካዊቷ ገጣሚ Sylvia Plath ባለቤቷን ተከትላ ሁለት ህፃን ልጆቿን እያባበለች ለሥነጽሑፍ አድራ ማቀቀች። ለጥልቅና ውብ ግጥሞች ወይስ ለትዳሯና ለልጆቿ ትኑር? አቃስታለች። ስለ ኅላዌ ብሎም ዕጣ ፈንታዋ እየተብሰከሰከች ግራ ተጋብታ፣ ለራሷም ጭምር ባይተዋር ሆነች፤መሸሸጊያ የሆነ ጥግ ተነፈገች። በዕውቀቱ እንዲሚለው፤ “መንሳፈፉስ ይቅር፥ መስጠም ያቅተዋል ሰው?” ሲልቪያ ጭንቅላቷን ከጋዝ ምድጃ ወትፋ ትሞታለች። ብርሃኑ ድንቄ ከኑሮ ልምድ ያጠነፈፈው ሀቅ አለ። “ብቻህን ለመቆም ተዘጋጅ፤ ልጅ፥ ወንድም፥ እህት፥ ዘመድ የሚባሉት ነገሮች የምቾት ጊዜ ጌጦችና አጫፋሪዎች ናቸው።” [አልቦ ዘመድ፥ ገፅ 1] ይህ አባባል ሰክነው የልጃቸውን ምስል እያዩ ለሚፈነድቁ ይጐመዝዛል፤ ለእንደነ ሲልቪያ ግን የርዕይ መነጠቅ ውጤት ነው። አበራ ለማ በአንድ ግጥሙ ተመስጦበታል። “ያ መረቡ ልቤ ረገበ እምቢ አለ/ አንድ እራሱን ማስገር አቃተው ዋለለ።” ይህ ነው የባይተዋር ዕንቆቅልሽ።
ተራኪው አንባቢን ነው የሚያናግረው። አንተ/አንቺ ባይተዋሩን ብትሆኑ ኖሮ እያለ ከገፀባህሪዩ ተላቆ እኛን ያሳስበናል። ገላቸው እያለቀ፥ ክፍላቸው በዝምታ ተውጦ -የሌላ ሰውን አለመኖር የሚያጐላ- ብሎም በሌላው መረሳት ሰቆቃው መዘመዛቸው። የሳርተር ህልውናነት ተከታይ ይመስል፥ አንድ ውጫዊ ሃይል -እግዜር- አለ ይደርስልኛል ብሎ የሚያምን አይመስልም፤ መንፈሳዊ ምርኩዙን የተቀማ አይነት ነው። ስለት፥ ተማፅኖ፥ ፀሎት ... እንደ የተስፋ ስንቅ አይታወሱም። ገጣሚው በጥቅስ ያደመቀው መፍትሄ አሳሳቢ ነው። “`መንሳፈፉስ ይቅር፥ መስመጥ ያቅተዋል ስው?`/ ሲያሰኝህ ዕድልህ/ ያኔ ይጀምራል የባይተዋር ገድልህ።”  እዚህ ላይ ተወሳሰበ። ራስን እስከማጥፋት እንደ የደነበረ በሬ ያሚያሯሩጥ፥ የሚፈገትር ብቸኝነት ሆነ። ገጣሚው ከደረደራቸው የሰቆቃ ምስሎች በኋላ “መስመጥ ያቅተዋል ሰው?” ብሎ ይጠይቃል። ከዕለታዊ ሥነልቦናዊ ማኅበራዊ ስቃይ -the pain of life- ለመገላገል ራስንም የማጥፋት ምርጫ እንዳለ ጠቋሚ ነው።
በግል ጉዳይ ሰው ተነጥቆ ከመንደሩ በብቸኝነት የተተበተበ ግለሰብ ሲማቅቅ ልብ አይል ይሆናል:: አለማየሁ ገላጋይ በ<ኩርቢቷ> አጭር ልቦለድ ሰዎች መካከል ሆና ብቸኝነት የቆረፈዳት ወጣት እናት ስሏል:: ድንገት የሞተው ባሏ ቤቱንና ንብረቱን በእናት አባቱ ስም ስላስመዘገበ ለልጇ ብላ ሁሉን ነገር ተነፍጋ፣ ተቸግራ ዝምታን ለምዳ አለማምዳም እንደ ጥላ ያለ ኮሽታ ትንቀሳቀሳለች:: ህፃን ልጇም ታዘበቻት። “እዚህ አያቶቼ ግቢ ዉስጥ የኖረችዉ በመንፈስ ህልውና ነው ማለት እችላለሁ:: ስትሄድ ኮቴዋ አይሰማም:: ለዚህ ዓለም ሙቀትና ቅዝቃዜ ምንም አይነት ምላሽ ስትሰጥ አይታይም:: አትስቅም፣  አታለቅስም:: ሆዷ ተከፍቶ ስትበላና ስትጠጣ አጋጥሞኝ አያውቅም::”[ ገፅ 53] ብቸኝነት የመጠጣት እናት አንድ ጠዋት ብድግ ብላ ጠፋች:: የባይተዋር ገድሏ የጀመረው፥ ትዳር እንደ ቀለሰች ነበር።
ስለ ባይተዋር እንግልት በወግ በትረካ ለመፃፍ አያዳግትም፤ የበዕውቀቱ ግጥም ልዩ የሆነበት ምክንያት ምንድነው? በሥነግጥምና በዕውነታ መካከል መመሳሰልስ አለ ወይ? ግጥም የተለያዩ ገሃዶች (ማኅበራዊ፥ ሃይማኖታዊ፥ ፖለቲካዊ ...) ማንዘፍዘፍ ይችላል ወይ? የምናፈጥበት ሳይሆን የምናዋቅረው ቃላዊ-ዕውነታ -constructed verbal reality- ከምናብ ያንሰራራል፤ ጥበባዊ ነው። ሥነግጥም የሚዳሰስ አይደለም፤ ፈጠራ ነው። የስንኝ ትርታ፥ የተወለወለ አንጓ፥ ግጥማዊ ቅርፅ፥ ሙዚቃዊ ምት የግድ በውብ ምስላዊ ቃላት መወርዛት አለበት። ባለአንድ አንጓ ግጥም አስራ ሶስት ስንኞች ነዘሩበት። በስንኞች መካከል ክፍተት ወይም ቦግታ ሣይኖር መታፈጉ የባይተዋሩን የጭንቀት ድድርነት ይወክላል። ገፅ ላይ ተኮራምተው እንጂ ተበታትነው ስንኞቹ ለብርሃን -ለነጭ ባዶ መስመር- ስፍራ ነፍገውታል፤ የባይተዋር ገድሉ ጀመረ።
የበዕውቀቱ ስዩም ስብስብ ግጥሞች ለአማርኛ ሥነጽሑፍ ፈርጥ ናቸው። “ግድግዳው ላይ ያለች፥ የገደል ማሚቶ፥ ዝም ማለት ፈርታ/ ሳሎንህን ስትሞላው ዝምህን አባዝታ” በዓሉ ግርማ የዛሬ አርባ አመት “ከአድማስ ባሻገር” ልቦለዱን በዝምታ ነው የበረገደው። “ቤቱን የዝምታ አዘቅት ውጦታል” በማለት ከዝምታ ሙዚቃ  ሲመነጭም ይሰመዋል። ደበበ ሰይፉ “ባለአደራ” በሚለው ግጥሙ በዘመን ጭራ ታስራ ስለተጐተተች የገደል ማሚቶ ተቀኝቷል። በየግጥሙ የሚያባባው ምስል ነው። “የገደል ማሚቶ ትንቃ፥ ከእንቅልፍ ትራሷ ትከንበል/ ከቦዘን ህልሟ ትፈንገል/ አንደበታችንኮ ዝጓል እማምዬ፥ አእምሯችን በክሎ/.../ የጆሮን ታሪክ በዝምታ አብጠልጥሎ” የበዕውቀቱ ገደል ማሚቶ እንደ ግዙፍ ተናዳፊ ሸረሪት ድሯን ስትተበትብ ቤቱን በዝምታ ታፍነዋለች። ይህ ተንቀሳቃሽ ዝምታ፥ የገደል ማሚቶ ምስል ብዙ ሊያወያይ ይችላል። መስተዋት ግዑዝ ሳይሆን በጥያቄ ሲያፋጥጥህ፥ የገደል ማሚቶ ግድግዳው ላይ በመንፏቀቅ ድምፅ ተነፍጋ ስታፍንህ፥ የሌሊት ወፍ ከበራፍህ ሲሞት (አስፈሪነቱ)፥ ጊዜ እንደብል እድሜን ሲያደቀው፥ እንቅልፍ ሲሸሽህ፥ በሌሎች መረሳት ሲመዘምዝህ ባይተዋር ነህ።
“መንሳፈፍ ይቅር፥ መስጠም ያቅተዋል ሰው?” መንሳፈፍ እንደ ነገሩ መኖር ከሆነና ይህ ከሰቀቀህ፥ ይህ ሥነልቦናህን ቀጥቅጦ ካንገላታህ መፍትሄው -የማያቅትህ- መስጠም ነው፤ ራስን አጥፍቶ የመገላገል ምርጫም አለ ባይ ነው። ግለሰብ እንዲህ ለማሰብ ሲነሳሳ “ያኔ ይጀምራል፥ የባይተዋር ገድልህ” ሲል ገድል ደግሞ የስቃይ ታሪክ ከሆነ የገድል መጀመር፥ የእንግልት ቅፍለት ያስደነግጣል። የዘመነኛ ንቁ ሰው እጣ ፈንታው በህይወት መፍካት ሣይሆን ለኅላዌ ጭንቀት ይገጣጠባል። በሌሎች መገለል መረሳት ነባር የቃል ግጥም ያስታውሰናል። “እህል ዱር አደረ፥ ብቻውንም ዋለ/ ጠላት እንደሌለው፥ ሰው እንዳልገደለ” ለባይተዋሩ ከእህል በበለጠ የሰው -የብጤው- ረሃብ ያንገላተዋል። በዕውቀቱ ግለሰብ ከራሱ ሲላተም ነው በበለጠ የሚያሰጋው። “መሽቷል አትበል” በተሰኘ ግጥሙ የባይተዋርን ገድል ከግለሰብ ውስጠት አፍርጦታል። “በውስጥህ ላለው ብርሃን/ ግርዶሽ የኾንህ ለ`ታ/ ያን ጊዜ ኾኗል ጽልመት/ ያን ጊዜ ኾኗል ማታ።”  ከግጥሞቹ ፈቀቅ ብለን “ከአሜን ባሻገር”ን ብናነብ በዕውቀቱ አሁንም ባለቅኔና ጥልቅ እንጂ ግልብ አይደልም።

Read 4844 times