Monday, 04 April 2016 07:53

ስስ ፌስታል ከምርትና ከገበያ ውጪ ሊደረግ ነው

Written by  መታሰቢያ ካሣዬ
Rate this item
(0 votes)

      የውፍረት መጠናቸው 0.03 እና ከዚያ በታች የሆኑ፣ ለተለያዩ ዕቃዎች መያዣነት የሚያገለግሉ ስስ ፌስታሎችን ሙሉ በሙሉ ከምርትና ከገበያ ውጪ ለማድረግ የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁ ተገለፀ፡፡
የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር፤ “ህገወጥ የፕላስቲክ ከረጢቶች ምርትና ስርጭትን ለማስቆም” በሚል ርዕስ ሰሞኑን አዘጋጅቶት በነበረው አውደጥናት ላይ ጥናታቸወን ያቀረቡት የሚኒስቴር መ/ቤቱ የህግ ተከባሪነት ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ መሃሪ ወንድም አገኝ እንደገለፁት፤በአገሪቱ ተመርተው ለገበያ ከሚቀርቡት የፕላስቲክ ውጤቶች አብዛኛዎቹ መመረቻቸው አዲስ አበባ ሲሆን በከተማዋ ከ486 በላይ የፕላስቲክ ቁሳቁሶችን የሚያመርቱ ፋብሪካዎች አሉ፡፡ እነዚህ ፋብሪካዎች በዓመት ከ8ሺ -10ሺ ቶን የሚደርሱ ፌስታሎችን እያመረቱ ለገበያ ያቀርባሉ፡፡ የፕላስቲክ ምርቶችን አምርተው ለገበያ ከሚያቀርቡ ፋብሪካዎች መካከል ግን አንዳቸውም ያመረቱትን ምርት መልሰው ለመጠቀም (ለመሰብሰብ) የሚያደርጉት ጥረት የለም ብለዋል፤አጥኚው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በስምንት ክፍለ ከተሞችና በአስራአንድ ወረዳዎች ውስጥ በተደረገው ጥናት ውጤት መሠረት፤ ፋብሪካዎቹ ከሚያመርቷቸው የፕላስቲክ ምርቶች መካከል ከ50% በላይ የሚሆነው ለአንድ ጊዜ ብቻ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ ስስ ፌስታሎች ናቸው፡፡
የደረቅ ቆሻሻ አዋጅ እንደሚደነግገው፤ በባለስልጣኑ በሚወጣ መመሪያ ከሚወሰነው ቀን ጀምሮ በቀላሉ በስብሶ ወደ አፈር የሚደባለቅ መሆን አለመሆኑን የሚያሳይ ምልክት ያልተደረገበት፣ እንዲሁም ውፍረቱ 0.03 ሚ.ሜ እና ከዛ በታች የሆነ፣ በስብሶ ከአፈር ለመዋሃድ የማይችል የፕላስቲክ ከረጢት ማምረትም ሆነ ወደ አገር ውስጥ ማስገባት አይፈቀድም፡፡ ይህንን ህግና ደንብ በመተላለፍ በጤና፣ በአካባቢና በመሠረተ ልማቶች ላይ አደገኛ የሆነ ችግር የሚፈጥሩ ፌስታሎችን እያመረቱ ለገበያ የሚያቀርቡ በርካታ ፋብሪካዎች በአዲስ አበባ እንደሚገኙ የጠቆመው ጥናቱ፤ፋብሪካዎቹ ውስብስብ ቴክኖሎጂዎችን የማይጠይቁ፣ የሚጠይቁት ኢንቨስትመንት አነስተኛ መሆኑ፣ የሚባክን ጥሬ ዕቃ የሌላቸው መሆኑ ተመራጭ እንዳደረጋቸውና የሚያስገኙት ጠቀም ያለ የገንዘብ ትርፍም ብዙዎች ፊታቸውን ወደ ፌስታል ምርት እንዲያዞሩ ያደርጋቸው መሆኑን ገልጿል፡፡
የተጠቀሱትን ዓይነት ፌስታሎች ማምረትም ሆነ ከውጪ አገር ማስገባት በህግ የተከለከለ ቢሆንም በርካታ ፋብሪካዎች እነዚህን ምርቶች በማምረት በስፋት ወደ ገበያ እያስገቡ ይገኛሉ ያሉት የአካባቢ የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም፤እነዚህን ህገወጦች በመከታተልና በመቆጣጠር አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ጊዜ ሊሰጠው የማይገባ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡



Read 1040 times