Monday, 04 April 2016 07:23

አርቲስት ቴዎድሮስ፤ ከተመሰረተበት ክስ በነጻ ተሰናበተ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    የሴባስቶፖል ሲኒማና ኢንተርቴይመንት ባለቤት፣ የፊልም ደራሲና ዳይሬክተሩ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፤ በ“ሶስት ማዕዘን” ፊልም ምክንያት ከቀረበበት የ10 ሚሊዮን ብር የፍትሃ ብሄር ክስ በነፃ ተሰናብቷል፡፡
አርቲስቱ “ሶስት ማዕዘን” የተሰኘውን ፊልም ደራሲ አትንኩት ሙሉጌታ በ2000 ዓ.ም ካሳተመው “ፍቅር ሲበቀል” መፅሃፍ ወስዶ ነው የሰራው የሚል ክስ የቀረበበት ነሐሴ 13 ቀን 2006 ዓ.ም ሲሆን ከሳሽ ደራሲ አትንኩት፣ለደረሰባቸው የሞራል ጉዳት የ10 ሚሊዮን ብር ካሳ እንዲከፈላቸው ጠይቀው ነበር፡፡
አቤቱታው የቀረበለት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት 18ኛ ፍ/ብሔር ችሎት፣ በከሳሽ የቀረቡ የሰውና የሠነድ ማስረጃዎችን እንዲሁም በተከሳሽ የቀረቡ ተመሳሳይ ማስረጃዎችን ከመረመረ በኋላ የከሳሽ ማስረጃ ክሱን በአግባቡ የሚያስረዳ ሆኖ እንዳላገኘውና ክሱ ያለ አግባብ የቀረበ መሆኑን በመግለፅ ከትናንት በስቲያ ውድቅ አድርጎታል፡፡ አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ በክሱ ሂደት የደረሰበትን ጉዳትም በዝርዝር መጠየቅ እንደሚችል ፍ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
 የክሱን መመስረት ተከትሎ በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ የተሰራጩ ዘገባዎች፣ በስራውና በሞራሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዳደረሱበት የገለጸው አርቲስቱ፤በእቅድ የያዛቸው ስራዎችም እንደተሰናከሉበት ተናግሯል፡፡  

Read 1995 times