Saturday, 26 March 2016 12:01

አይሲስ አውሮፓን ገና ብዙ መከራ አሳያታለሁ አለ

Written by 
Rate this item
(6 votes)

 በመላ አውሮፓ እጅግ የከፉ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ዝቷል
      ባለፈው ማክሰኞ በቤልጂየም መዲና ብራስልስ በፈጸማቸው የሽብር ጥቃቶች ከሰላሳ በላይ ሰዎችን ለሞት፣ ከ300 በላይ የሚሆኑትን ደግሞ ለመቁሰል አደጋ የዳረገው አሸባሪው ቡድን አይሲስ፣ ገና ምን አይታችሁ፤ አውሮፓንና ሊያጠፉኝ የተነሱ አገራትን በሽብር በማናወጥ እጅግ የከፋ ጥፋት አደርሳለሁ ሲል መዛቱ ተዘግቧል፡፡
የሽብር ቡድኑ ባሰራጨው መግለጫ፣ በእኔ ላይ ተባብረው በተነሱ የአውሮፓ አገራትና አጋሮቻቸው ላይ ሌሎች የከፉ የሽብር ጥቃቶችን እንዲፈጽሙ አደገኛ ፈንጂዎችንና የጥፋት መሳሪያዎችን ያስታጠቅኳቸው ወታደሮቼ፣ በቀጣይም ገና ብዙ ጥፋት ያደርሳሉ ሲል መዛቱን ዘ ኢንዲፔንደንት ዘግቧል፡፡
አይሲስ በህቡዕ ያደራጃቸውና 600 ያህል በከፍተኛ ሁኔታ የሰለጠኑ ወታደሮችን ያቀፉ ከመቶ በላይ የሽብር ህዋሶች በተለያዩ የአውሮፓ አገራት ውስጥ ከባድ ጥቃት ለመፈጸም በተጠንቀቅ ላይ እንደሚገኙ የዘገበው ዘ ሰን በበኩሉ፣ ጽንፈኛው ቡድን ለንደንና በርሊንን ጨምሮ በታላላቅ የአውሮፓ ከተሞች ከፍተኛ ጥቃት የሚያደርሱ ጥቃቶችን ለመሰንዘር ተዘጋጅቷል ብሏል፡፡
የአይሲስ ከፍተኛ አመራር በየአገራቱ ለሚገኙት የሽብር ህዋሶቹ መሪዎች የሽብር ጥቃቶችን ለመፈጸም ዝግጅታቸውን እንዲያጠናቅቁና ጥቃቶቹ የሚፈጸሙባቸውን ቦታዎችና አፈጻጸማቸውን ሲመርጡ፣ በአህጉሪቱ ከፍተኛ ቀውስ የሚፈጥሩና የብዙዎችን ህይወት የሚቀጥፉ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት መሆን እንዳለበት መመሪያ መስጠቱንም ዘገባው ገልጧል፡፡
የብራስልሱን አሰቃቂ የሽብር ጥቃት ተከትሎ የአውሮፓ አገራት የደህንነት ሃይላቸውን በማጠናከር ተጠምደው መሰንበታቸውን የዘገበው ቢቢሲ፣ ፈረንሳይ ተጨማሪ 1 ሺህ 600 ፖሊሶችን በባቡር ጣቢያዎች፣ በአውሮፕላን ማረፊያዎችና በድንበር አካባቢዎች ማሰማራቷን ጠቁሞ፣ አስቸኳይ ስብሰባ የጠሩት የእንግሊዙ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩንም የአገሪቱ የደህንነት ቁጥጥርና የፖሊስ ሃይል እንቅስቃሴው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጠናከር ማዘዛቸውን ጠቅሷል። ጀርመንና ሌሎች የአውሮፓ አገራትም ዜጎቻቸውን ከአይሲስ ሊፈጸም ከሚችል የሽብር ጥቃት ለመከላከል የተጠናከረ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

Read 3272 times