Saturday, 26 March 2016 11:43

ቋንቋ እና ለውጥ

Written by  ባዩልኝ አያሌው
Rate this item
(3 votes)

“ለውጥ ሳይነካው የሚያልፍ ነገር ቢኖር፣ ለውጥ ራሱ ብቻ ነው!”
                           
      ሰባት ቢሊዮን የሚደርሰው የዓለማችን ህዝብ (የተናጋሪዎቻቸው መጠን የተለያየ) ወደ 6,064 የሚደርሱ ቋንቋዎችን በአፍ መፍቻነት እንደሚናገር David Crystal የተባለው እውቁ እንግሊዛዊ የቋንቋ ምሁር “English as a Global Language” (1997) በተባለው መጽሐፉ ይገልጻል። ከእነዚህ ቋንቋዎች መካከል ወደ 2,000 ገደማ የሚሆኑት ደግሞ የሚነገሩት በዚችው በእኛዋ አህጉር (በአፍሪካ) ህዝቦች ነው፡፡ ይህም ማለት እንግዲህ፣ በዓለም ላይ ከሚነገሩት ቋንቋዎች ሲሶ ያህሉ የአፍሪካ ቋንቋዎች ናቸው ማለት ነው፡፡
አፍሪካ ውስጥ ከሚነገሩት 2,000 ገደማ ከሚደርሱት ቋንቋዎች መካከል 13 የሚሆኑት እያንዳንዳቸው ከአምስት ሚሊዮን የበለጠ ተናጋሪ አላቸው፡፡ ከእነዚህም ከፍተኛ የተናጋሪ ቁጥር ያላቸው ቋንቋዎች አረብኛ፣ ሀውሳ፣ ዩርባ፣ አማርኛና ኦሮሚኛ (አፋን ኦሮሞ) ናቸው። (የእኛዎቹ አማርኛና ኦሮሚኛ በተናጋሪ ብዛት ከአፍሪካ ቋንቋዎች ከመጀመሪያዎቹ ረድፍ መቀመጣቸውን ልብ ይሏል፡፡)… በዛሬው ጽሑፋችን ለሰው ልጅ መተኪያ የሌለው ሀብት የሆነው ቋንቋ፣ በዘመናት ሂደት ውስጥ ስለሚያስተናግዳቸው ለውጦችና የለውጦቹን ግፊቶች/ምክንያቶች፣ የመስኩን ተመራማሪዎች እማኝ አድርገን “ገብስ ገብሱን” እናወጋለን፡፡
ምንም እንኳን በየዘመናቱ የተነሱ የቋንቋ ተመራማሪዎች እንደተነሱበት ዓላማና እንደየሚቆሙበት ዲስፕሊን፣ ጽንሰ ሐሳቡን በተለያዩ አንጻሮች መመልከታቸው ባይቀርም ቅሉ፣ ሥነ ማህበረሰባዊ እሳቤን መሠረት ያደረገውና “ቋንቋ የአንድ ማህበረሰብ አባላት የሚግባቡበትና የሚተጋገዙበት፣ በዘፈቀደ የተፈጠረ፣ የአንደበታዊ ትዕምርቶች ሥርዓት ነው፡፡” የሚለው ብያኔ ብዙዎችን ያስማማና ያቀራረበ ይመስላል፡፡
በዓለም ላይ የለውጥን ያህል ገዢ ኃይል መኖሩን እጠራጠራለሁ፡፡ ግዑዙም እንበል የእሱ ተቃራኒ የሆነው ፍጥረት ሁሉ፤ በውሃ ውስጥም ይኑር በየብስ ላይ፣ በአየርም ላይ ይንሳፈፍ ከመሬት ውስጥ፣ ማንም ምንም ከለውጥ ውጪ አይደለም፡፡ በጥቅሉ ለለውጥ ሥርዓት ተገዢ ያልሆነና የማይለወጥ አንዳችም ነገር የለም!... ለዚህም ነው “በዓለም ላይ ለውጥ ሳይነካው የሚያልፍ ነገር ቢኖር፣ ለውጥ ራሱ ብቻ ነው” መባሉ።… በለውጥ ሂደት ውስጥ የነበሩ ነገሮችን ማጣትን የመኖሩን ያህል፣ ያልነበሩና ይልቁንም የተሻሉ ነገሮችን ማግኘትም አለ። “Don’t be afraid to change. You may lose something good but you may gain something better” ይላል ስሙን የዘነጋሁት ፀሐፊ፡፡
እንደሌሎች ነገሮች ሁሉ፣ ቋንቋም (ለውጥ አይደለምና) ለለውጥ ይገዛል፤ ይገዛልናም ይለወጣል። በዚህም የነበሩትን ያጣል፤ ያልነበሩትንም የእርሱ ያደርጋል፡፡ በዓለማችን የሚገኝ የትኛውም ቋንቋ አሁን ያለው ህልውና ላይ ያለው፣ ትናንት የተለያዩ ለውጦችን አስተናግዶ ነው፤ ነገም ያስተናግዳል፡፡ ከነገ ወዲያም፤ ከዛም በኋላም እንዲሁ፡፡ ለውጥ ዘላለማዊ ነውና!... በቋንቋ ላይ የሚደርሰው ለውጥ አይነቱና ደረጃው ለመለወጡ ግፊት እንደሚሆኑት ጉዳዮች የተለያየ ነው፡፡
የአንድን ነገር መለወጥ ከምክንያቱ/ሰበቡ ነጥሎ ማየቱ ይገዳል፤ የቋንቋንም እንዲሁ፡፡ እንደሌሎች ነገሮች ሁሉ ለቋንቋም መለወጥ በምክንያትነት የሚጠቀሱ አስገዳጅ ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህም ሰበቦች የህዝቦችን አይነተ ብዙ ዕድገት፣ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስና የተለያዩ ማህበራዊ ግንኙነቶችን ተከትለው የሚመጡ ናቸው። ታላላቅ የሚባሉትን ግፊቶችና (ቋንቋን በመለወጥ ያላቸውን) ሚና በወፍ በረር ለመቃኘት እንሞክር፡፡
ለቋንቋዎች መለወጥ በዋና ሰበብነት ከሚጠቀሱት ጉዳዮች አንዱ፣ የማያቋርጥ የባህል ዕድገት መኖር ነው። እንዴት? በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ የማያቋርጥ የባህል ዕድገት ሲኖር በህብረተሰቡ ውስጥ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕለት በዕለት ያድጋል፤ ይዳብራልም፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የሚመጣው ዕድገት ደግሞ አዳዲስ ነገሮችን ከመፈልሰፍና ከመገንዘብ ባለፈ፣ ዕድገቱ ላመጣቸው አዳዲስ ነገሮች ስምን እስከመሰየም ይደርሳል፡፡ እነዚህ ስያሜዎችም ቀስ በቀስ የቋንቋው መድበለ ቃላት ውስጥ መግባታቸው፣ በዚህም በደንበኛው አገልግሎት ላይ መዋላቸው አይቀሬ ነው፡፡ ቋንቋው ቀደም ያልነበሩትን ቃላት አካተተ ማለት ነው፡፡…
አንድ ህዝብ የሚመራበት ሥርዓተ ማህበር መለወጥም እንዲሁ ቋንቋው እንዲለወጥ ሰበብ መሆኑን ተመራማሪዎቹ ጽፈዋል፡፡… ፈጣን ባይሆንም በሀገሮች ላይ የሥርዓተ ማህበር ለውጥ ይደረጋል፤ ተደርጓልም። በተለይም ለውጡ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ህዝብ የሚያሳትፍ ከሆነ በቋንቋው ላይ ለውጥ እንዲደርስ ማድረጉ አይቀሬ ይሆናል፡፡  በቅርቡ የምናውቀውን የሀገራችንን ታሪክ ለአስረጂ እንጥራ፡፡ ኢትዮጵያ የፊውዳልን ሥርዓት አሰናብታ፣ ሶሻሊዝምን አንጥፋ ስትቀበል፣ አማርኛ ቋንቋ ላይ ለውጥ ደርሶበታል፡፡ በፊውዳሉ ሥርዓት  በደማቁ አገልግሎት ላይ የነበሩት (ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ለመግለጽ ያገለግሉ የነበሩት) እንደ ጭሰኛ፣ ምስለኔ፣ ጭቃሹም… የመሳሰሉት ቃላት የሥርዓተ ማህበሩን መቀየር ተከትለው ከመድበለ ቃላቱ ጠፍተዋል፡፡ በአንጻሩም እንደ አናርኪ፣ አብዮት ጠባቂ… አይነት ቃላት ሶሻሊዝምን ተከትለው የቋንቋውን መድበለ ቃላት ተቀላቅለዋል፡፡ በኋላም ሶሻሊዝምን በቃኸኝ ብለን ካፒታሊዝምን ጓዳችን ስናስገባ፣ አሁንም ለውጡን ተከትሎ ሌሎች ቃላት የቋንቋው ቤተኛ ሆነዋል፡፡ (ስንቱን እንጥቀስ?!)…
ወረራና ስደትም ሌሎች ለቋንቋ መለወጥ ምክንያት የሚሆኑ ሰበቦች ናቸው፡፡ ምስክር ለመጥራት ሩቅ አንሄድም፡፡ የታሪክ መዛግብት እንደሚነግሩን፣ አውሮፓውያን አፍሪካውያንን ቅኝ በገዙባቸው ዘመናት የተገዢዎቹ ቋንቋ እንዳይነገር በአዋጅ እስከማስደንገግ፣ በዚህም አፍሪካዊ ቋንቋዎች እንዲጠፉ እስከመትጋት ደርሰዋል፡፡ ገዢዎቹ የተገዢዎቹ ቋንቋ እንዳይነገር ሲያግዱ፣ በተቃራኒው ደግሞ የእነሱ ቋንቋ ብቻ እንዲነገር ያስገድዱ ነበር፡፡ ይህም በርካታ የገዢዎቹ ቋንቋዎች ቃላት በተገዢዎቹ ቋንቋዎች ውስጥ እንዲሠርጽ አድርጎአል፡፡ (በኢጣሊያ የወረራ ዓመታት በርካታ የጣሊያንኛ ቃላት ወደ አማርኛ ገብተው እስካሁን ድረስ እያገለገሉ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡)… ያም ሆኖ ምንም እንኳን የለውጡ መጠን የሚያይለው በተወራሪዎቹ ህዝቦች ቋንቋ ላይ ቢሆንም፣ የወራሪዎቹም ቋንቋ ከለውጡ አላመለጠም፡፡ ተጋልጦው (Exposure) እስካለ ድረስ ለውጡ ለተጽዕኖ ፈጣሪው ቋንቋም አይቀሬ ነው፡፡… ለውጥ አያዳላም ልበል?!
አንድ ህዝብ ከነበረበት (ህዝብ) ተነስቶ ወደሌላ ባዕድ ህዝብ ሲሄድ፣ በስደት በሄደበት አዲስ ቋንቋ ይገጥመዋል። ያም ሆኖ ሰው ነውና ከሄደበት ህዝብ ጋር ልዩ ልዩ ማህበራዊ ግንኙነቶችን መፍጠሩ፣ መተባበሩ ባህሪው ነው፡፡ በዚህ የዕለት ተዕለት ግንኙነት ውስጥም አዳዲስ ቃላትን ይወርሳል፤ ያለምዳልም፡፡ በዚህም የራሱ ቋንቋ ብቻ ሳይሆን ተሰዶ የሄደበት ቋንቋም ጭምር እንዲለወጥ ምክንያት ይሆናል፡፡ ይህንንም የሚያደርገው ሆን ብሎና አቅዶ እንዳልሆነ ሁሉ፣ እንዳይሆን ሊያደርገውም አይችልም፡፡
እንደ ስደት ሁሉ የንግድ እንቅስቃሴና የሃይማኖት ግንኙነትም ለቋንቋ መለወጥ “ቀሊል” የማንላቸው ሰበቦች ናቸው፡፡ በንግድ ሂደት ሸቀጦች ወደ አንድ ሀገር የሚገቡት፣ በተሠሩበት ሀገር የተሰጣቸውን ስም ይዘው ነው፡፡ ምንም እንኳን ስያሜዎቹ ንግድን ምክንያት አድርገው የገቡ ቢሆንም ቅሉ፣ ህዝቡ የሚገለገላቸው በስማቸው (ይዘውት በመጡት) በመሆኑ ቃላቱ የቋንቋው መድበለ ቃላት ውስጥ ይካተታሉ፡፡… ሁለት የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ህዝቦች በሃይማኖት ሰበብ በሚያደርጉት ግንኙነት ምክንያትም በቋንቋ ላይ ለውጥ ሊደርስ ይችላል፡፡ እንዴት? ለሚል፣ እንደ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን… የመሳሰሉት ቃላት ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የቋንቋው አካል የሆኑት፣ የኢትዮጵያና የግሪክ አብያተ ክርስቲያናት በነበራቸው ግንኙነት ነው እንላለን፡፡
በእነዚህ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግፊቶች አማካይነት፣ በአንድ ቋንቋ ላይ የሚደርሰው ለውጥ በአይነቱ የተለያየ መሆኑን የሚገልጹት የመስኩ ተመራማሪዎች፣ የለውጡን አይነቶችም የለውጡን መጠን መስፈርት በማድረግ ሥነ ድምጻዊ (Phonetic Change)፣ ሥነ አገባባዊ/ሰዋስዋዊ (Syntax Change) እና ሥነ ፍቺያዊ (Semantic Change) ለውጥ በማለት ይጠሩዋቸዋል፡፡ ሥነ ድምጻዊ ለውጥ፣ በአንድ ቋንቋ ድምፅ ላይ የሚደርስ ለውጥ ሲሆን ይህም በቋንቋው ውስጥ ባሉት አናባቢ (vowels) እና ተነባቢ (consonants) ድምጾች ላይ የሚደርስ ነው፡፡… ይህም አናባቢው ወይም ተነባቢው ድምጽ ቀድሞ የነበረውን ባህሪ በተለያዩ ምክንያቶች ሲለውጥ ወይም ከነአካቴው ሲጠፋ የሚፈጠር ነው፡፡
በአንድ ቋንቋ ላይ ሥነ አገባባዊ ወይም ሰዋስዋዊ ለውጥም እንዲሁ በተለያየ መንገድ ሊካሄድ ይችላል። በተለይም ቀደም ሲል በቋንቋው ውስጥ ያልነበሩ ቅርጾች፣ የቋንቋውን የቃላት ሥርዓት ጠብቀው ቋንቋው ውስጥ መግባታቸው ቋንቋውን ለሰዋስዋዊ ለውጥ ያጋልጠዋል። ምክንያቱም ቃላቱ የቋንቋውን ሥርዓት ጠብቀው ይረባሉና፡፡ (ታይፕ- ተያቢ- አተያየብ- ትይብ- ትየባ…)
ሥነ ፍቺዊ ለውጥ በየትኛውም ቋንቋ ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊታይ ወይም ሊከሰት የሚችል እጅጉን ፈጣን የለውጥ አይነት ነው፡፡… የአዳዲስ ቃላትን መፈጠር፣ የነባር ቃላትም ፍቺያቸውን ማጣት፣ የነበረን ፍቺ መስፋትና አፅንኦት መቀየር፣ የቃላት በሀራምነት (taboos) ተነውረው ከቋንቋው መድበለ ቃላት መወገድ እንዲሁም ከመድበለ ቃላቱ የወጡ ወይም ሊወጡ የተቃረቡ ቃላት እንደገና አገልግሎት ላይ መዋል… ለሥነ ፍቺያዊ ለውጥ መከሰት ሰበቦች ናቸው።  
ከለውጥ አይነቶቹ እጅግ ፈጣን የሆነው ሥነ ፍቺያዊ ለውጥ የመሆኑን ያህል፣ እጅግ በጣም አዝጋሚ የሆነው ደግሞ ሥነ ድምጻዊ ለውጥ ነው፡፡ “በአንድ ቋንቋ ውስጥ ሥነ ድምጻዊ ለውጥ ለመካሄድ፣ ምናልባትም የምዕተ ዓመት ዕድሜን ሊወስድ ይችላል” ይሉናል ለውጡን ያጠኑት ምሁራን፡፡
መልካም ሰንበት!

Read 4743 times