Saturday, 26 March 2016 11:32

“ ያደኔ ቲባ …ያለፈውን ጊዜ ማስታወስ” (በዓሉ ግርማ፡- ሕይወቱና ሥራዎቹ)

Written by  ዳዊት ንጉሡ ረታ
Rate this item
(5 votes)

    አስፋው ዳምጤ በኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍ በተለየም ሂስን በተመለከተ ስማቸው በቀዳሚነት ይነሳል፡፡ እኚህ ሰው በሂስና በበዓሉ ግርማ ሞት ስማቸው ተደጋግሞ የሚጠራውን ያህል በሌላ አንድ ነገርም ይታወቃሉ። በኢትዮጵያ ስነ-ፅሁፍና ኪነ-ጥበብ ታሪክ ውስጥ ስላሉና ስላለፉ ሰዎች ህይወት፣ ልዩ-ልዩ ኹነቶች በጥበቡ ዓለም እንዴትና መቼ እንደተከናወኑ ልቅም አድርጎ በማስታወስም ጭምር! ታዲያ ሰዎች በእነዚሁ ጉዳዮች ማናቸውንም መረጃ ሲፈልጉ ስድስት ኪሎ ወደሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ በማምራት፤ “ጋሽ አስፋው እባክህ፤ ስለዚህ ሰው/ስለዚህች ሴት እንዲህ ዓይነት መረጃ ፈልጌ ነበር…” ማለታቸው የተለመደ ነው፡፡
አሁን አሁን በተመሳሳይ ጉዳይ ወደ ጋሽ አስፋው የሚመጡ ሰዎች ግን አንድ መልስ ይሰጣቸዋል አሉ፤ ከጋሽ አስፋው፡፡
“እኔን አታድክሙኝ ሂዱ ወደ ወጣቱ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ዘንድ! እሱ ከእኔ የተሻሉ መረጃዎችን አሳምሮ በመረጃም አስደግፎ ይሰጣችኋል!
ይህን የጋሽ አስፋውን አባባል እውነትነት ለማረጋገጥ ማንም ከእንዳለጌታ ከበደ ጋር ለጥቂት ጊዜያት አብሮ ለማሳለፍ የታደለ ሰው ወይንም ማንም እንዳለጌታ ከበደ ያሳተማቸውን በተለይ ሁለቱን መፅሃፍት /8ተኛውን መፅሃፉን “ማዕቀብ”ንና 10ኛውን “በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ስራዎቹ”ን/ ያነበበ ሰው በሙሉ አፉ ሞልቶ የሚመሰክረው ሃቅ ነው፡፡ እኔ ደግሞ በሁለቱም ታድያለሁ፡፡ ሁሉንም ያሳተማቸውን መፅሃፍቱን የማንበብና በመፅሃፍ ያልታተሙ በጥበቡ ዓለም የተከሰቱ አስገራሚና አዝናኝ፣ አስደንጋጭና አሳዛኝ ወዘተ ታሪኮቹን ከመሳጭ ትረካው ጋር ከራሱ አንደበት ለማድመጥ ችያለሁ!
ያደኔ ቲባ፡- በቅርቡ እንዳለጌታ ከበደ ያሳተመውና እጅግ የተመሰጥኩበት አስረኛ መፅሀፉ የበዓሉ ግርማን ህይወትና ስራዎቹን የሚዘክር ነው፡፡ እንዳለጌታ የመፅሃፉን ርዕስ “በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹ” ብሎታል፡፡ ለእኔ ግን መፅሃፉን የሚመጥነው ርዕስ ያደኔ ቲባ ነው እላለሁ፡፡ አንባብያን ፍረዱኝ፡፡ ያደኔ ቲባ የበዓሉ ወላጅ እናት ስም ነው፡፡ እንዳለጌታ በዚህ አዲስ መፅሃፉ ገፅ 15፣ ሦስተኛው አንቀጽ ላይ የያደኔ ቲባን ኦሮሚኛ ስያሜ ትርጉም እንዲህ ያፍታታዋል፡-
ያደኔ ቲባ ማለት ወደ አማርኛ ሲተረጎም ያለፈውን ዘመን ማስታወስ ማለት ነው፡፡ ትተው የሄዱትን ነገር መለስ ብሎ መቃኘት፡፡ ያደኔ በኦሮሚኛ መናፈቅ ሲሆን ቲባ ደግሞ ያለፈ ጊዜን ያመለክታል፡፡
ታዲያ የበዓሉን ያለፈ ህይወት ለመቃኘትና መለስ ብሎ ለማስታወስ ከዚህ የተሻለ ርዕስ ከየት ይገኛል?
ቁጭት!፡- በመረጃና በማስረጃ የበለፀገውንና ከእስከዛሬው የደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ስራዎች በእኔ እይታ ልቆ የተገኘውን ይህንን “በዓሉ ግርማ ሕይወቱና ሥራዎቹን” መፅሃፍ ሳነብ አንድ ቁጭት ተሰማኝ፡፡ ይኸውም ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር በሙዚቃው ንጉስ የክብር ዶ/ር ጥላሁን ገሰሰ ህይወት ላይ አተኩሮ ያሳተመው መፅሃፍ “ምነው ከዚህ ከበዓሉ መፅሃፍ ወዲህ ቢሆን የታተመው?” የሚል፡፡ ምክንያቱም ደራሲ እንዳለጌታ የአንድን ሰው የህይወት ታሪክ በምን ያህል ጥልቀትና ብስለት መፃፍ እንደሚቻልና እንደሚገባም ጭምር ያሳየበት በመሆኑ፣ አርዓያነቱ ለዚያውም በጉጉት የተጠበቀ ግን ደግሞ እንደተጠበቀው ላልተገኘ የጥላሁን ገሠሠ የህይወት ታሪክ መፅሃፍም ይተርፍ ስለነበር!
የእንዳለጌታ አምስቱ ገፅታዎች፡- የእንዳለጌታ አስሩ መፅሃፍት ደራሲው በአምስት ገፅታዎች ወደ አንባቢያን እንደደረሰና ችሎታውም ዘርፈ ብዙ እንደሆነ ይመሰክርልናል፡፡ ቀደምት መፅሃፍቱ የቀረቡበት መንገድ ልብ ብለን ካስተዋልነው በአጫጭር ልቦለዶች መልክ፣ በግጥም፣ የማህበረሰብን ወግና ባህል በሚያጠናው በፎክሎር ዘርፍ፣ በረዥም ልቦለድና ፣ በምርመራ ጋዜጠኝነት መልኩ ነው፡፡ ይህም ደራሲው ራሱን እያሳደገ የሚገኝባቸው አቅጣጫዎች ዕውነትም ዘርፈ ብዙ ናቸው እንድንል ያስገድደናል፡፡ እንግዲህ “ማዕቀብ”ንና ይሄኛው ስለበዓሉ የተፃፈውን መፅሃፍ ስንመለከት፣ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ስነ-ምግባርና መርህ በተከተለ መልኩ ነው ለማለት ያስደፍረኛል፡፡
ሰውዬው በዓሉና ደራሲና ጋዜጠኛው በዓሉ፡- እንዳለጌታ ከበደ ለእኔ ገኖ በወጣበት በዚህ አስረኛ መፅሃፉ እጅግ የተደሰትኩበትና ነፍሴ እርካታን የተጎናፀፈችበት ዋናው ምክንያት ስለ ሰውዬው በዓሉ ማለትም ስለ ግላዊ ሰብዕናው፣ ቤተሰቦቹና ቤተሰባዊ ኑሮው ወዘተ በስፋት የገለጠበት፣ እንደዚሁም ስለ ደራሲው በዓሉ ግርማ ስራዎች ዝርዝር በዕኩል ሚዛን ቀንብቦ የቀረበበት በመሆኑ ነው፡፡
ይህም ከዚህ በሁዋላ ለሚሰሩ መሰል ስራዎች አርዓያነቱ የጎላ ነው፡፡ ብዙ የታተሙ የሕይወት ታሪክ መጻሕፍት የሚያጎድሉብን ሰውዬውንና ባለሙያውን በዕኩል ዓይንና ሚዛን አይተው ሁለቱንም መረጃዎች በእኩል ደረጃ ለማቅረብ አለመቻላቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ስለ ቀድሞ ጠቅላይ ሚ/ር መለስ ዜናዊ ስራዎች ብዙ ዘገባዎች ተሰርተዋል፣ ነገር ግን ሰውዬው መለስ ዜናዊን እስካሁን አናውቃቸውም፡፡ እንደ ባል፣ እንደ አባት፣ እንደ ጓደኛ በትርፍ ጊዜያቸው፣ ወዘተ
በመፅሃፉ ሰውዬው በዓሉ ገጠሬ፣ በአባቱ ደስተኛ ያልሆነና እስከ መጨረሻውም ዘመን ስለ ወላጅ አባቱ ማውራት የማይፈልግ ስለመሆኑ፣ ሽክና ፀዳ ያለ እንደሆነ፣ ዝምታ እንደሚያጠቃው፣ መኪና ውስጥ ሆኖ መጠጥ መቀማመስ እንደሚወድ፣ ለሴት ያለው ፍቅር ብርቱ ስለመሆኑ፣ ውሽማም እንደነበረችው፣ ከእርሱ በፊት ትዳር ይዛ ሦስት ልጆች የወለደችውን ሚስቱን ከመስሪያ ቤት ገንዘብ ተበድሮ በልጃገረድ ወግ እንዳገባት፣ ለሚስቱ ፅኑ ፍቅር እንደነበረውና ሆኖም ግን ለትዳሩና ለልጆቹ በቂ ጊዜን መስጠት ያልቻለ እንደነበር፣ ከተወዳጅዋ ድምፃዊት ብዙነሽ በቀለ ጋር በፍቅር ወድቆ ስለነበረው በዓሉ ወዘተ ሰፋፊ፣ አዝናኝ፣ አስገራሚ፣ አሳዛኝና የሚያስቆጩ መረጃዎችን እንዳለጌታ የበዓሉ የትውልድ መንደር ሱጴ ድረስ ወርዶ፣ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል የሙያና የስራ ባልደረቦቹን አነጋግሮ በሚጥም ስነ-ፅሁፍ ፈትፍቶ አጉርሶናል፡፡
እንደገናም ደግሞ ደራሲው በዓሉን ያመጣና በ“ከአድማስ ባሻገር” ሙሽት ስለጀመረው የደራሲነት ህይወቱ ጀምሮ ባልታወቀ ሁናቴ እንዲሰወር ምክንያት እስከሆነበት “ኦሮማይ” መፅሃፍ ድረስ ሰፊ ምርመራ በማድረግ የደራሲውን ስራዎች በስፋት ያስቃኘናል፡፡ ጋዜጠኛው በዓሉን ከእንግሊዝኛ ዜና አንባቢነት ጀምሮ ለታላቅ ተልዕኮ ኤርትራ ምድር አስመራ እስከከተመበት “የቀይ ኮከብ ጥሪ” ድረስ አስፍቶ ያስተዋውቀናል። የማስታወቂያ ሚ/ር ቋሚ ተጠሪውንና ባለስልጣኑን በዓሉን በምናብ ያሳየናል፡፡ ያደኔ ቲባ ተብሎ የለ!
የሰው ባለሃብቱ እንዳለጌታ ከበደ፡- እንዳለጌታ ትሁት ነው፡፡ ታዛዥም ነው፡፡ ትጉህም ነው፡፡ በእሱ ደረጃ በርካታ የጥበብ ሰዎችን የሚያውቅና የሚግባባ፣ ወዳጀ ብዙ የሆነ ሌላ ደራሲ ወይም ጋዜጠኛ አላውቅም። ከትልቁ ጋር ትልቅ ከትንሹም ጋር ትንሽ መሆን የሚችል ሰው ነው! ታዲያ በዚህ በሰው ሃብት መበልፀጉ ምን ያህል እንደጠቀመው በበዓሉ ግርማ ህይወትና ስራዎች መፅሃፍ ላይ ለመገንዘብ እንችላለን፡፡
እንዳለጌታ አፈላልጎ ካገኛቸው የደርግ ባለስልጣናት የበዓሉ የልጅነት ጓደኛሞችና ሌሎች ግለሰቦች ውጪ አብዛኞቹ ምስክሮች የእንዳለጌታ ከበደ የቅርብ ወዳጆች ናቸው፡፡ እሱም ለእነርሱ እንደዚያው ነው፡፡ በተፈለገ ጊዜና ሰዓት ፈጥኖ የሚደርስ! ታዲያ ለእኛም ተረፈና! በየዓይነቱ ሰዎች እየደረደረ፣ በየአይነቱ መረጃዎችን ልባችን ሙልት እስኪል ድረስ አጉርሶናል!
ሰፊና ጥልቅ የንባብ ችሎታ…መረጃን ለመፈለግ መባዘን፡- በግዛው ዘውዱ የተፃፈውና በ1996 ዓ.ም ለህትመት የበቃው “ጋዜጠኝነት ሙያውና ስነምግባሩ” የሚለው መፅሃፍ ገፅ 71 ላይ ይህንን ያስነብበናል፡-
በቂ ልምድና ዕውቀት ከመገኘቱ በፊት አንዳንድ ስራዎችን መነካካት አይበጅም፡፡ ብዙዎቹ ጋዜጠኞች ከመራመዳቸው በፊት መሮጥ ስለሚከጅሉ ሳይሳካ ሲቀር ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ ገና ከመጀመራቸው ከጋዜጣ ግንባር ላይ የሚወጣ ትልቅ ዜና ወይም ዘገባ ማውጣት ይፈልጋሉ፡፡ ሆኖም ለዚህ ለመብቃት የሚጠይቀውን የላቀ የቋንቋና የማጠናቀር ችሎታ ሲገነዘቡ ትንፋሻቸው ያጥራል፡፡
እውነት ነው ጥላሁን ገሰሰ ብሎ ጀምሮ፣ ፀጋዬ ገ/መድህንን አንስቶ፣ አፈወርቅ ተክሌን አንስቶ ወዘተ ኋላ ላይ የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ ከማለት ባይጀመር፣ ባይነካካ፣ ባይቆሰቆስ ይሻላል፡፡ እዚህ ጋ የበዓሉን መፅሃፍ ማንበብ ከመጀመራችን በፊት እንዳለጌታ ከበደ በመፅሃፉ መግቢያ ላይ ያሰፈረውን የሚከተለውን መስመር ልብ ማለቱ ለቀጣዮቻችን ግድ ይሆናል፡፡ እንዲህ አለ እንዳለጌታ፡-
ይህን መፅሃፍ የማሰናዳት ግፊት በውስጤ ከተቀሰቀሰና መንፈሴ መነሳሳት ከጀመረ ብዙ ዓመታት አልፈዋል፡፡ ስራዬ ብዬ በበዓሉ ግርማ ሕይወትና ስራዎች ላይ ሙሉ ቀልቤን አሳርፌ መረጃዎችን መመርመር፣ ሰነዶችን ማገላበጥና በዓሉን በቅርበትም ሆነ በርቀት ያውቁታል ብዬ የምገምታቸውን ማነጋገር ከጀመርኩ ግን አራት ዓመታት አስቆጥሬያለሁ፡፡
ይህ አንቀፅ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ በስነ-ፅሁፉና ጋዜጠኝነት ዓለሙ ታላቅ ዕውቅናን ያተረፈውና ድንገት ከቤተሰቡና ከስራ ገበታው ተሰውሮ እንዴት እንደተገደለ ያልታወቀው በዓሉ ግርማን ማንነትና ስራዎች ለማስቃኘት ቆርጦ ሲነሳ ተገቢውን ጊዜ እንደመደበና ልምዱንም ከዘጠኝ መፅሃፍት ማሳተም በሁዋላ አዳብሮ፣ ራሱንም በቀለም ትምህርት አሳድጎ መሆኑን ልብ እንድንል ያስችለናል፡፡
በመፅሃፉ ከተጠቀሱ አስገራሚና ያልተሰሙ አዳዲስ ታሪኮች፣ በዓሉን እናውቀዋለን ከሚሉ ግለሰቦች ብዛትና ከሰጡትም የማይናቁ መረጃዎች አንፃር፣ ስለ ቤተሰቡ ካደረገው ቅኝት፣ ስራዎቹን ለመተንተን ከሚወስድበት ጊዜ፣ የተለያዩ ሰነዶችን ለማፈላለግና ለማገላበጥ እንደዚሁም ለመፅሃፉ አግባብነት ያላቸውን ታሪኮች መዞ ለማውጣት፣ ወዘተ ከሚወስደው መጠነ ሰፊ ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት አንፃር እንዳለጌታ በዓሉን በሚገባው ጥልቀት ሊመረምረው አስቀድሞ ቆርጦ እንደተነሳ በልበሙሉነት እንድንመሰክር ያደርገናል፡፡ እሱም በዝግጅቱ ተኩራርቶ ይመስላል “ማለዳ”፣ “ቀትር”፣ “ምሽት”፣ “ውድቀት” ብሎ የበዓሉ ግርማን ህይወትና ስራዎች በርዕስ በመከፋፈል እንደ ጉድ ያስኮመኮመን!
እንዳለጌታ ሰፊና ጥልቅ የንባብ ችሎታ እንዳለው፣ ያነበበውን እንደማይረሳ ወይንም ተገቢውን መረጃ ከትቦ እንደሚያስቀር፣ መረጃን ለማግኘት ባተሌ እንደሆነ “ማእቀብ”ንም ሆነ የበዓሉን መፅሃፍትም ባነበብን ወቅት ዳግም የምንገነዘበው ሃቅ ነው፡፡ ያገላበጣቸው ሰነዶች፣ በአስረጅነት የጠቃቀሰልን መፅሃፍት፣ ጋዜጦችና መፅሄቶች ብዛትና ዓይነት፣ መታተማቸውን እንኩዋን ያልሰማናቸው ውስን ስፍራ ብቻ የሚገኙ ጥራዞች፣ በዓሉን በገፀ-ባህሪነት ተጠቅመው ስለተሰሩ መፅሃፍትና የመድረክ ስራዎች ወዘተ ሲተነትንልን ልባችን በሃሴት ይሞላል፡፡
ራሴንና ዕድሌን አመሰገንኩት!፡-  እንዳለጌታ ከበደ እድለኛም ነው፡፡ ምክንያቱም አንድም ለረጅም ጊዜያት ጉልበቱንና ገንዘቡን ሰውቶ ሲያፈላልገው የነበረው ማንነት የበዓሉ ግርማ ነውና፣ በዓሉ ግርማ ደግሞ ታዋቂ ጋዜጠኛና ደራሲም ጭምር ነውና፣ ድርሰቶቹም አነጋጋሪ ናቸውና፣ ከእነዚህም ውስጥ ደግሞ “ኦሮማይ” የተባለው የመጨረሻ ስራው ደራሲውን ለሞት ያበቃው በመሆኑ፣ አንድም ደግሞ በጋዜጠኝነት ስራው በኩል የደርጉ ሊቀመንበርና የወቅቱ የአገሪቱ ሊቀመንበር ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምን ጨምሮ ከበርካታ ታላላቅ ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች ጋር  ጭምር የቅርብ ትውውቅ የነበረው ባለሙያ በመሆኑ ስለበዓሉ ጉዳይ ለመዘገብና ታሪኩ ይኸው ነው ለማለት እንዳለጌታ ያገኛቸውን ጉምቱ ጉምቱ ሰዎች /የወቅቱ ባለስልጣናትን/ ስንመለከት፣ ለአፍታም ቢሆን እነዚህ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አይረሴ ስፍራ ያላቸውን ሰዎች በህይወት ማግኘትና ማውራት መቻል በእርግጥም ዕድለኛ ነው ያስብለዋል፡፡ እንዳለጌታም ራሱ በመፅሃፉ ገፅ 406 ላይ እንዲህ ይላል፡-
ለአንዳፍታ ለ17 ዓመታት ያህል ሀገሪቱን ከመሩት ሰዎች መካከል ዋነኞቹ ከጓድ መንግስቱ ኃ/ማርያም በስተቀር የመገናኘትና በዚሁ ጉዳይ ለመወያየት በመብቃቴ ራሴንና ዕድሌን አመሰገንኩት፡፡
ተወንጃዮቹ፡- ከገፅ 323 ጀምሮ በዝርዝር የሚቀርበው በበዓሉ ሞት ጉዳይ ተደጋግሞ ስማቸው በገዳይና አስገዳይነት የሚነሱትን ግለሰቦች “ተወንጃዮቹ” በሚል ርዕስ ያስነበበን ቦታ እንደ ጥበብ አፍቃሪና የበዓሉ አድናቂ ለእኔ በልዩ ሁኔታ የተመሰጥኩበት ክፍል ነው። በዚህ ክፍል እንዳለጌታ ስማቸው ከበዓሉ ሞት ጋር የሚነሳውን ግለሰቦች ለማፈላለግና ለማነጋገር ያደረገውን እልህ አስጨራሽ ጉዞ አንብበን ለደራሲው ያለን አድናቆት በይበልጥ ይጨምራል፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ሻምበል ፍቅረስላሴ ወግደረስና ኮሎኔል ፍስሃ ደስታን ጨምሮ በርካታ የደርግ ባለስልጣናትን ያገኘበትና ያነጋገረበት ሁናቴ፣ የበዓሉ ባለቤት የወ/ሮ አልማዝ አበራ በአቶ አስፋው ዳምጤ ላይ ለዘመናት የምታነሳውን አንተነህ በመጨረሻው ቀን ጠርተህ የወሰድከውና የት አደረስከው? ጥያቄ እንደዚሁም ደራሲ አበራ ለማ የአልማዝን ሃሳብ በመደገፍ ስላደረገው ክርክር፣ አቶ አስፋው ስለሰጧቸው መልሶች በተፍታታና አንባቢ የግል ግንዛቤውንና ፍርዱን እንዲወስድ በሚያስችል ሁናቴ ማቅረቡ፣ ወያኔንና ሻቢያን በበዓሉ ሞት እጃቸው ቢኖርበትስ? በሚል የሰጠው ቀላል የማይባል ማስረጃ ወዘተ በግሩም ሁናቴ ተቀናጅቶ በመቅረቡ በእጅጉ ተደስቻለሁ፡፡
ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ እርግጠኝነት ቢኖረውም ባይኖረውም በመፅሃፉ የመጨረሻ ገፅ ላይ ኮሎኔል አርጋው እሸቴ የተባለ ጨካኝ ሰው “ያን በዓሉ ግርማ የተባለ ሰው ጨርሼው መጣሁ!” ማለቱ በመፅሃፉ ውስጥ መዘገቡ ቢያንስ ለተወንጃዮቹም የማርያም መንገድ የሚሰጥ ሲሆን፣ የበዓሉም ቤተሰቦችንም በዓሉ መንኖ ባህርዳር ጣና ሃይቅ ተገኘ ወዘተ ከሚል አደናጋሪ ወሬ ይገላግላል፡፡ በተለይም ባለቤቱ ወ/ሮ አልማዝ በአንድ መፅሄት ላይ “በዓሉ ይመጣል ብዬ አሁንም በር በሩን አያለሁ” ያለችውን ስሜትም ይቆርጥላታል የሚል ዕምነት አለኝ፡፡
“ሁሉን ትወዳለህ፣ በመጨረሻም ሁሉን ታጣለህ! ሴላቪ ኦሮማይ! (“ኦሮማይ” መፅሃፍ፣ በዓሉ ግርማ፤ ገፅ 372)
ያደኔ ቲባ- ይህ ሁሉ ያደኔ ቲባ ነው፡፡ ያለፈውን ዘመን ማስታወስ ማለት ነው፡፡ ትተው የሄዱትን ነገር መለስ ብሎ መቃኘት፡፡
ከተሰራ አይቀር በዚህ ደረጃ ነው እንጂ ያስብላል። ለተሰራው ስራም ከመቀመጫ ብድግ ብሎ ባርኔጣን ከአናት አውርዶ ትከሻና ወገብን ዝቅ አድርጎ ቪቫ እንዳለጌታ! ብራቮ! ብራቮ! ብራቮ! እጅህን ቁርጥማት አይንካህ! ረጅም ዕድሜ ይስጥልን ያስብላል!
ሴላቪ ኦሮማይ!

Read 2150 times