Saturday, 26 March 2016 11:15

ታሪክ መሰረታዊ ፍጆታ በሆነባት ሀገር፤ ታሪክ ፀሐፊ ማጣት!

Written by  ዓለማየሁ ገላጋይ
Rate this item
(8 votes)

አንድ ስምዖን የሚባል የሸዋ ልዑል ከሁለት ዓመታት በፊት በግዕዝ እንዲህ ብሎ ነበር፡-
“ለምንት አይጽሕፉ ዜናሆሙ ሰብአ ኢትዮጵያ
ወይከውነ ነገሮሙ ቀሊለ ወሐላፌ”
ሲተረጎም፡-
/የኢትዮጵያ ሰዎች ታሪካቸውን ለምን አይጽፉም? (ባለመፃፋቸው) ነገራቸው የተናቀና ኃላፊ (ተረስቶ የሚቀር) ይሆናል/
ይሄን የሚነግሩን ዶክተር ጌታቸው ሐይሌ የልዑሉን አባባል ካደነቁ በኋላ የተግባር ጉዳይ አንስተው መልሰው ተናጋሪውን ይተቻሉ፡፡ “የሚያሳዝነው ልዑል ስምዖን ዕውቀቱ ከፍተኛ ዐዋቂዎችን ሰብስቦ ለማስፃፍ ሥልጣኑና ሀብቱ ሰፊ ሆኖ ሳለ ያወረሰን ፅሁፍ ከአሥር የብራና ቅጠሎች አይበልጥም፡፡ እነዚህ ቅጠሎች በጨለማ ጊዜ አንድ ቦታ ላይ ያተኮረን የባትሪ ብርሃን ይመስላሉ፡፡”
ታሪክ በጭንቆራ የሚታይ የሽንቁር ብርሃን ከሆነ ሀገርና ዜጋ በየትኛው ቅጥልጥሎሽ አንድነት ይሰማቸዋል? ዶ/ር ጌታቸው ኃይሌን ያሳሰባቸው ይሄ ነው፡፡
ትውልድ ከዝርያ ጋር የሚያያዘው ደመነፍስ እንስሳት ዘንድ ብቻ ነው፡፡ የሰው ልጅ የትውልድ ብሎም የሀገር ህብር እንዲኖረው ከዝርያም በላይ ታሪክ ላይ የተመሰረተ የልምድና የተመክሮ ቅብብል ግድ ይለዋል፡፡
ይሄንን በመገንዘብ ሰር አይዛክ ኒውተን እንዲህ ብሏል፡- “If I have seen a little farther than others, it is because I have stood on the shoulders of giants.” /”ከሌሎች በላይ በጥቂቱ አሻግሬ ማየት ከቻልኩ፣ ምክንያቱ ሌላ ሳይሆን በነባሮቹ ግዙፋን ትከሻ ላይ በመቀመጤ ነው፡፡”/
ታሪክ ላይ የተመሰረተ የልምድና የተመክሮ ቅብብላችን እጅግ ደካማ በመሆኑ ከቁመታችን በላይ አሻግረን ለመመልከት እንደተቸገርን አለን። በይበልጥ የውጭ ባዕዳን ታሪካችንን ከትቦ በማስቀረት ስራ ላይ ባይሳተፉ ኖሮ ከአንድ ሰው ትውስታ በላይ ፈቅ ያለ ታሪክ ባልኖረንም ነበር፡፡ ዶ/ር ጌታቸው፤ የልዑል ስምዖንን አስር ገፅ ብራና በባትሪ ብርሃን ከመሰሉ በኋላ እንዲህ በማለት የባዕዳንን ተሳትፎ ያሞካሻሉ፡፡
“በብርሃኑ አካባቢ ያለው ዓለማችን (ታሪካችን) የእነ አልቫሬዝን (Alvareze) መፅሐፉ ባናገኝ የጨለማ ጨለማ ሆኖ በቀር ነበር፡፡”
ታሪካችን የባዕዳን ማደጎ የመሆኑን መጠን ስናሰላው፣ የኋላ እኛነታችን የእጓለሞውታንን ያህል የስጋ ዘመድ መጠጊያነት ያጣብናል፡፡ ከግሪኩ ሄሮዱተስ አንስቶ እስከ ላፔንሰር ድረስ ያሉት የባዕዳን ድርድሮች በጣልቃ ካልሆነ በስተቀር ሀበሾችን የማይቀላቅሉ መሆናቸው ልብ ላለው የሀፍረት ምንጭ ነው፡፡ ከሀፍረትም በላይ አደገኝነት እንዳለውም የሚገልፁ ብዙ ተቆርቋሪዎች አሉ። ደጃዝማች ከበደ ተሰማ፤ “የታሪክ ማስታወሻ” መፅሐፋቸው ውስጥ ይሄን ተቆርቋሪነት ንዑስ ርዕስ ሰጥተው ይተነትኑታል፡፡ “ምስጢር ለባዕዳን ማባከን እንደማይገባ” በሚል ርዕስ ሥር፤ “ያልወለደ አጋድሞ አረደ” የተሰኘ ኃይለቃል ይጠቀማሉ። ለካስ ታሪክ ከባዕዳን የሚገኝ ጨለማ መግፈፊያ ብርሃን ብቻ ሳይሆን አጋድሞ ማረጃ “ካራ”ም ጭምር ነው፡፡
ደጃዝማች ከበደ ለዚህ ምሳሌ የሚያደርጉት ፓሊኦሎግ ይባል የነበረ የግሪክ ተወላጅን ነው። በኢትዮጵያ ቤተ መንግስት ውስጥ መወደድ ብቻ ሳይሆን መታመንን አግኝቶ ኖሯል፡፡ በኋላ ኢጣሊያ አገራችንን ስትወር፣ ፓሊኦሎግ ለጠላት መሳሪያ ሆኖ እውነትና ሀሰቱን እየቀላቀለ መፅሐፉ ፃፈ። የሀገሪቱን፣ የንጉሰ ነገስቱን ብሎም በዘመኑ የነበሩትን ባለሥልጣኖች ሥም እያከፋና እያበላሸ ገለፀ፡፡ በድርጊቱ እጅግ ያዘኑት ደጃዝማች፤ በቁጭት “ራሳችንን ችለን ቢሆን ኖሮ (ባዕዶቹን) እንውደዳቸው ብሎ ለመፃፍ ህሊናዬ ባላሰበም ነበር” ይላሉ፡፡ ኃይለቃላቸው ሲቀጥል፡-
“ያልወለደ አጋድሞ አረደ እንደሚባለው ሁሉ የፓሊኦሎግ አፃፃፍ እንደዚሁ ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ጊዜ አጋጥሞ መፅሀፉን ስለአነበብኩ የአንዱን ፀሐፊ ስም ብቻ ጠቅሼ ፃፍሁ እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ አደግን፣ ኖሮን የሚሉ የእንጀራ ልጆች ሁሉ እንደ ፓሊኦሎግ የጊዜ መሳሪያ ሆነው መፃፋቸው አልቀረም፡፡”
ታሪክ እንደ ካራ “ያልወለደ አጋድሞ የሚያርድበት” መሳሪያ የሚሆነው “የእንጀራ ልጆቹ” የጊዜ መሳሪያ ሆነው ለመፃፍ ወደ ኋላ ባለማለታቸው ነው፡፡ እኛ ግን “ጠላት” እጅ የገባው “ካራ” ሳይረብሸን በጥልቅ እንቅልፍ ውስጥ መኖር አልተቸገርንም፡፡ የወቅቱ ፖለቲካችን በቆይታ ታሪክ ሲሆን የእንቅልፍ ልብ ክንውን ይመስል ድርጊታችንን ከሌሎች መስማት፣ ሰምቶም ማመን ግዴታችን ሆነ፡፡
ታሪክ እንደ ቤተ - ዘመድ ጉባኤ ሰልፉ የሚበላሸው ባዕዳን ሲቀላቀሉበት ነው እያልኩ እንዳልሆነ ግልፅ ነው፡፡ ከጠላት በላይ ለጠላት ወገኖቹን የሚወጋ ባንዳ እንዳለ ሁሉ የታሪክ ጦር ሜዳም ላይ ይኸው ይፈፀማል፡፡ ለምሳሉ ፍሌቪየስ ጆሴፈስ (Flavius Josephus) የአይሁድ ተወላጅ ይሁን እንጂ የአይሁዶችን ታሪክ የፃፈው ከአሳዳሪዎቹ ከሮማውያን ፍላጎት አንፃር ነው እየተባለ ይተቻል፡፡
ይሄ ርዕሰ ጉዳይ እኛን የማይመለከት አይደለም። አስረስ የኔ ሰው “ትቤ አክሱም መኑ አንተ” የተሰኘ መፅሐፋቸው ላይ የሰው ስም እያነሱና የመፅሐፍ ርዕስ እየጠቆሙ የሚተቹት ለጠላት ወገኑ ያሏቸውን የታሪክ ሰዎች ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ጆሴፍሶችን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምም በሀይለቃል ይተቻሉ፡፡ “መክሸፍ እንደ ኢትዮጵያ ታሪክ” ውስጥ “ጆሴፍሶቹ” እዚህ ዘመን ላይ እንዳሉ ጠቁመው “የኢትዮጵያ ህዝብ ከታሪክ ለመማር አልታደለም” ይላሉ፡፡ ታሪክን ለውጭ ባዕዳን፣ በባዕዳን ቋንቋ፣ ከባዕዳን ታሪክ መዛግብት እያጣቀሱ የሚፅፉ መሆናቸው ፕሮፌሰርን በንዴት አትከንክኗል፤ “የጥንቶቹ ደባትራን በግዕዝ ይፅፉ ነበር፤ የዘመኑ ደባትራን ደግሞ ታሪክን በእንግሊዝኛ ብቻ ያቀርባሉ” ይላሉ፡፡ ይሄ አዝማሚያ ታሪክ ለዳቦ ማብሰያነት መዋሉን የሚጠቁም እንደሆነም ያምናሉ፡፡ ለዚህ አቋማቸው ማምከኛ የሚሆን መረጃ ማግኘት እንደሚከብድ ይሰማኛል፡፡ እራሳቸውን “የታሪክ ተመራማሪ” ያሉትም ማጠፊያው ሲያጥራቸው በአደባባይ ያየነው ነው፡፡
ሌላም የታሪክ ችግር አለ፡፡ እንደ ታሪክ ፀሐፊው ግድ እና ፍላጎት፤ ታሪክ የአንድ አቅጣጫ ትኩረት ይይዛል፡፤ ይሄ በተደጋጋሚ ሲነገር የምናደምጠው “ታሪክ ሰሪው ሰፊው ህዝብ” ተዘንግቶ ነገስታቱና ሹማምንቱ መንቆለጳጰሳቸው ነው፡፡ ይሄንን ገልብጦ የሚመለከት አላጋጠመኝም፡፡ ነገሥታቱና ሹማምንቱ የሚተውኑትን “የታሪክ ጠባሳ” የሚባል ተውኔት ማን እንደፃፈውና ማን እንዳዘጋጀው አለመታወቁ ነው፡፡ ይሄንን በምሳሌ ላስረዳ፡-
ብላታ ወልደማሪያም አየለ፤ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሥልጣን የነበራቸው ሰው ነበሩ፡፡ ከአፄው ጋር የሚፃፃፉት ደብዳቤ ተገኝቶ “ከቤተመንግሥት ዶሴ” በሚል ርዕስ በመፅሐፉ ታትሟል፡፡ እዚህ መፅሐፍ ውስጥ ንጉሱን ወደአልተፈለገ አቅጣጫ የሚመራና የታሪክ ጠባሳ ያልነው ጉዳይ እንዲከሰት የሚገፋፋ አንድ አንቀፅ አለ፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“… ኃይልና ጭካኔ ካልተጨመረበት የኢትዮጵያ ሕዝብ በግልፅነትና በርህራሄ ብቻ ተመርቶ ወደ መልካም ነገር የሚደርስ ህዝብ አለመሆኑን ግርማዊነትዎ ከማንም ይልቅ ያውቃሉና የኃይልዎን ልክ በዚህ ማሳየት የሚገባ ይመስለኛል፡፡”
የብዙ ነገሥታቶቻችንን የጭካኔ ድርጊት ምንጭ የሚጠቁም አንቀፅ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የአፄዎቹን ሥጋት፣ ጭንቀትና ፍርሃት ጭምር በሚያባብሱ በእነዚህ መካሪያን ሥንት ንጉስ “ሐዲዱን” ስቶ ወደ ኃይልና ጭካኔ ገብቶ ይሆን?
ይሄ እንግዲህ ታሪክ የሚፅፉ ተገኝቶ ተጓድሎም ቢሆን ሲደርሰን የምናነሳው ቅሬታ ነው፡፡ ተቀናጣን እንጂ አንድ ሰው ገና ታሪክ ለመፃፍ ሲወስን ያለበት እንቅፋት ብዙ ነው፡፡ ፅፎና ተናግሮ እጅና ምላስ የማስቆረጥ “የበላይ” አደጋ እንዳለ ሆኖ፤ ይሄንን ቢያልፍ የህዝቡና የጓደኛ ተቃውሞ ከፊቱ ይጋረጣል፡፡ ዶክተር ጌታቸው ኃይሉ፤ ለዚህ ምሳሌ የሚሆነን ከስመ ጥሩው ፀሐፊ አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ታሪክ ይጠቅሳሉ፡፡
“አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የገጠማቸው ትልቁ ችግር እሱ ማን ሆኖ ነው የሚፅፍልን የሚለው የሙያ እኩዮቻቸው ተቃውሞ ነበረ፡፡ ሞተው በሰማይ ቤት በነበሩበት ጊዜ ይህ የምፀት አነጋገር በጆሮአቸው ደርሶ ኖሮ አቤቱታቸውን ለእግዝእትነ ማሪያም አመለከቱ፡፡ እሷም በተለየ አንዱን የደብር አለቃ ከሰማይ ቤት ድረስ አስጠርታ (በራእዩ ነው) አፋርዳ ወቅሳ ተቆጥታ መለሰችው ይላል ተአምረ ማርያም፡፡ (ሰአሊ ለነ ቅድስት)”
“የኢትዮጵያ ሰዎች ታሪካቸውን ለምን አይፅፉም?” የሚለው ጥያቄ የልዑል ስምዖን ብቻ አይደለምና ምላሹ ለእኛም ጭምር ነው። ያኔ በአባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ የታየው የህዝብና የሙያ እኩዮች ተቃውሞ፣ ዛሬም በሚፅፉ ላይ እየተደገመ ነው፡፡ ከመሰረታዊ ፍላጎቶቿ መካከል አንዱ “ታሪክ” የሆነባት ሀገር ላይ ተቀምጠን፤ የ“ታሪክ ተመራማሪዎቹ” መገኘት የሚገባቸው ቦታ ላይ የታጡበት ሀገር ይዘን፤ እንደ ባቢሎናውያን ቋንቋችን የተዛነቀ ህዝቦች ሆነን … ክፍተት ለመሙላት ብቅ ያለን “ኳ!” ምን ይሉት መፍትሄ ይሆን? ሰማይ ቤት ድረስ ባያካስስም፣ ምድር ላይ ከማስተዛዘብ አያስቦዝንም፡፡

Read 7453 times