Saturday, 26 March 2016 11:09

ከጌታሁን ሄራሞ ጋር የማልስማማባቸው ነጥቦች!

Written by  ተመስገን ካሳዬ፣ ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ
Rate this item
(4 votes)

    ይህች ጽሑፍ ጌታሁን ሄራሞ፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ (መጋቢት 3 እና መጋቢት 10፣ 2008) ‹‹በዕውቀቱና ድፍረቱ›› በሚል ርዕስ ካወጣቸው ሁለት ተከታታይ ጽሑፎች በተለይ በማልስማማባቸው ነጥቦች ላይ የተሰጠች አስተያየት ነች፡፡ የጌታሁን ግምገማ የታሰበበት እንደሆነ ‹‹የበዕውቀቱ መጽሐፍ ግምገማ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ እንደሚቀርብ በልዩ ልዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች ማስታወቂያው ከተለቀቀ ጊዜ አንስቶ›› ከሚለው አገላለጹ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህም ማለት በዝርዝር ባይሆን እንኳ በየጭብጦቹና በየርዕሰ-ነገሮቹ የተደራጀ ሒስ ጠብቄ ነበር ማለት ነው፡፡ (በነገራችን ላይ በመጽሐፉ ላይ የተሰጡ በአዲስ አድማስ ላይ የወጡ ሒሶችን አንብቤያለሁ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ጌታሁን ሄራሞ (ኬሚካል ኢንጂነር) የሚል ስም ሳይ ለማንበብ የቸኮልኩት ከበቀለ መኮንን ጋር በቀለማት ሕብርና አጠቃቀም ላይ ያደረጉትን የጽሑፍ ክርክር አንብቤ ስለነበረ ነው፡፡ መረጃ አቀራረባቸው ማራኪ ነበር፡፡ ብዙ ትምህርት ያገኘሁበት፡፡ ለሁለት ሶስት ሳምንታት የቀጠለ ይመስለኛል፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ በአዲስ አድማስ መጋቢት 23 ቀን 2008 ዕትምም በቀለ ‹‹ወርቅ ቢጠፋ ሚዛን አይጥፋ›› በሚል ጽሑፉና ጌታሁን በ‹‹በዕውቀቱና ድፍረቱ ክፍል 1›› ሒሱ ተገኝተዋል፡፡)
እንደ እውነቱ ከሆነ (ከተወሰኑት በቀር) የጠበኩትን ዓይነት በደንብ የታሰበበትና በአመክንዮ የታሸ ሒስ አላገኘሁም፡፡ (እንዳልኩት አስተያየቴ በማልስማማባቸው ነጥቦች ላይ ነው፤ አስተያየት ያልሰጠሁባቸውን ተስማምቼባቸዋለሁ ወይም የማላውቃቸው ናቸው ማለት ነው) ጌታሁን ግምገማው እንደ ንባቡ አዝናኝ እንደማይሆንለት ያቀረባቸውን ምክንያቶች ብቀበል እንኳ የግምገማው ወጥነትና ተዓማኒነት አላሳመነኝም፡፡ ወጥነት ስል ዓላማውና ትኩረቱ ማለቴ ሲሆን ተዓማኒነት ስል ከተገምጋሚው መጽሐፍ የወሰዳቸው አንዳንድ አገላለጾችና ከፍሮይድ መጽሐፍ የተረጎማቸው ሀሳቦች ፍሬ ነገር መዛባት አለባቸው ማለቴ ነው፡፡
የግምገማው ዓላማና ትኩረት ወጥ አይደለም፡፡
የግምገማው ዓላማና ትኩረት በመጽሐፉ አጠቃላይ ጭብጥ (ከአርዕስቶቹ አንፃር) ላይ ቢሆን ኖሮ በእግረመንገድ የተነሱ ነገሮችን አስተካክሎ (በጽሑፉ እንዳለው ተጓዡ መንገዱን የዘጋበትን ድንጋይ አንስቶ ሲያበቃ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ እኔ በሌላ አማራጭ አልፎት ወደመንገዱ ሊገባ ይችላል እላለሁ) የመጽሐፉን ሙሉ ስዕል ለማግኘት ይሞክር ነበር፡፡ ጌታሁን ግን መጽሐፉ ላይ ያገኘውን ስለ ኃይማኖት የተነገረ የንባብ እንቅፋት አንስቶ ለመጣል እንደሔደ ወደ ሌሎች ጭብጦች አልተመለሰም። ወደፊት ይመለስ እንደሆነም ፍንጭ አልሰጠም፡፡ ሌላው ቀርቶ ስለ ኃይማኖት ጉዳይ ለበዕውቀቱ ላነሳቸው አራት ጥያቄዎች መልስ ልጠብቅ ሳይል (ርግጥ የጥያቄዎች ምላሽ ሙግቱን ከዋናው ጉዳይ አውጥቶ ወደ ኃይማኖት ክርክር ይወስደው ይሆናል፤ በዕውቀቱም መልስ ለመስጠት ቢፈልግ እንኳ በሚዲያ ላይ በይፋ ለመከራከር መፈለጉን ርግጠኛ መሆን አልችልም) ‹‹እነሆ በዕውቄ ተሸውዶአል›› ብሎ ማወጅን መረጠ፡፡ ሒሱን ያጠናቀቀውም ሌላውን ጭብጥ ሁሉ ትቶ (ታሪክ ቀመሱንም ለታሪክ ባለሙያዎች ትቶ) በእግረ-መንገድም ሆነ ሆን ተብሎ ስለኃይማኖት የተጻፉ ቃላትና ዓ.ነገሮችን እየመረጠ በኃይማኖት ጉዳይ ነው፡፡
እውነትም ግምገማው በዝርዝር ጉዳዮች ላይ (ይበልጡንም በኃይማኖት ላይ) ያተኮረ ይመስላል፡፡ በመጽሐፉ ርዕሰ-ነገሮች ውስጥ ስለ ኃይማኖት በቀጥታ ወይ በተዘዋዋሪ የተጻፉ ነጥቦችን አግኝቷቸዋል፤ ማግኘት ብቻ ሳይሆን አንደምታቸውንም አሳይቷል፡፡ የሒሱ ድርና ማግ የተሰራው ከእነዚህ ቅንጥብጣቢ ሀሳቦች ይመስላል፡፡ ነገር ግን መጽሐፉን የገመገመበትን አካሔድ ሲናገር ወይም ልገመግም ነው ብሎ ማስታወቂያ ሲለቅ ‹‹ከመጽሐፉ የትረካ መዋቅር ቅርጽ›› አንጻር ግምገማዬ የሚያተኩረው ከርዕሶች ውስጥ በዚህኛው ላይ ከዚህኛውም በእግረ መንገድ የተነሳ ቢሆንም እንኳ በኃይማኖት ጉዳይ ነው ቢል የተሻለ ነበር፡፡ እኔም ቢያንስ በዚሁ አካሔዱ እከተለው ነበር፡፡ ያደረገው ነገር ከዚያም ከዚህም ከዕምነት ጋር የተገናኙ የሚመስሉ ትረካ ለመባል የማይበቁ ነገሮች መጠነቋቆል ነው፡፡ ‹‹ይህች ቃል ምንድናት? ይህች ዓ.ነገር አልተመቸችኝም፡፡ ይህን አባባል እዚህ ምን አመጣው?›› የመሳሰሉ ጸጉር-ስንጠቃ ባልላቸውም ‹‹በዕውቀቱና ድፍረቱ›› በሚል ትልቅ ርዕስ ስር ለመውጣት አቅም የሚያንሳቸው ቁርጥራጭ ነገሮችን መቀጣጠል ነው። ሊቀጣጥላቸው የሞከረው ደግሞ ከጉዳዩ ጋር ሳያገናኝ በተዋቸው የደራሲው የኮሜዲያንነት ባህርይ፣ የሒስ ሚና፣ የደራሲነት ፈቃድ፣ አንተስ እንዲህ ታደርግ የለም ወይ፣ ይኸኛውን ከነካህ ያኛውንስ ለምን ተውክ፣ የኋሊት ኢንጂነሪንግ፣ በደራሲው ዙሪያ የተሰባሰቡ አድናቂዎች ማንነት፣ ወዘተ በመሳሰሉ መስፈርት በሚመስሉ ጽንሰ-ሀሳቦች ነው፡፡
 እነኝህ የመገምገሚያ መስፈርት የሚመስሉ ጽንሰ-ሀሳቦች ለቸኮለ አንባቢ ገምጋሚው ጉዳዩን ከተለያየ ዕይታ አንፃር ያየው ያስመስሉ እንጂ ሕገ-አልዮታዊ ጠቀሜታ አላገኘሁባቸውም፡፡ ካላቸውም (እንደሚኖራቸውም ርግጥ ነው) ሳያገናኝ በአየር ላይ በትኗቸዋል፡፡ ለምሣሌ ደራሲውን የደራሲነት መብትህን ተጠቅመሃል (ያለ አግባብ?) ካለ በኋላ የደራሲነት መብቱን ተጠቅሞ ያዛባውን ዕውነታ አላሳየኝም፡፡ አለዚያም የደራሲነት ፈቃዱን አክብሮ አላለፈውም፡፡ እንዲያውም ደራሲው እግረ መንገዱን ስለ ኢ-አማኒነቱ የጻፈውን (ምናልባትም የደራሲነት መብቱን በአግባቡ ወይም ያለአግባቡ ተጠቅሞ) የመጽሐፉ መነሻና መድረሻ አድርጎ ስለወሰደው ይመስላል “ከአሜን ባሻገር” ለጌታሁን ‹‹የሽግግር ትረካ መጽሐፍ ነው››፡፡ ደራሲ በዕውቀቱ ከአማኒነት ወደ ኢ-አማኒነት የተሸጋገረበት እንጂ ሌላ አላገኘበትም ማለት ነው፡፡
በኔ በኩል ገምጋሚው ከመረጠ ጸጉር-ስንጠቃ በሚያሰኝ መልኩ ቢሔስ ችግር የለብኝም፡፡ ነገር ግን ‹ከአክራሪ ደጋፊዎች›› ጋር ብሽሽቅ የገጠመ ወይም የእነርሱ ስድብ የሒሱን ተጨባጭነት እንዲያረጋግጥለት የፈለገ ይመስል ሒሱ የተሰጠው ‹‹በስድብ የሚያምኑ አክራሪ›› ሲል ለጠራቸው ደጋፊዎች ይመስላል፡፡ እነሱንና ስድባቸውን ወደ ጎን ትቶ ‹‹ሐሳባቸውን ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ማስረዳት የሚችሉ በሳል አድናቂዎች››ንም ታሳቢ ያደረገ አይመስለኝም፡፡ ቢሆን ኖሮ ስለ አድናቂዎች ካነሳ አይቀር (ለግምገማው ተዓማኒነት አስፈላጊ ባይሆንም) መጽሐፉን በተመለከተ ከበሳል አድናቂዎች ምን በሳል አስተያየት እንዳገኘ፣ ምን ላይ እንደተለያዩና ምን ላይስ እንደተስማሙ ቢያንስ በአንድ አንቀጽ በነገረን ነበር። ሚዛናዊ ሐያሲ ስለ ጭፍን ድጋፍና ተቃውሞ ግድ ያለው አይመስለኝም፡፡ ቢሰድቡትም እንኳ ሚዛናዊ ሒስ ለሚፈልጉ አንባቢዎች ሲል ስድቡን እንቶ-ፈንቶ ነው ብሎ ወዲያ ትቶ ርዕሰ-ጉዳዩ ላይ ያተኩራል፡፡ ስለ አዳም ወዳጆችና ስለ በዕውቀቱ ተሳዳቢ አድናቂዎች ጉዳይ ጊዜ ወስዶ ያወራው በመጽሐፉ ላይ ብቻ ባለማተኮሩ ይመስለኛል፡፡ መጽሐፉን ብቻውን፣ መጽሐፉን ከጸሐፊው ጋር፣ ጸሐፊውን ከአድናቂዎች አንጻር ወዘተ መርምሮት ከሆነም ይህንኑ ወጥ በሆነ አቀራረቡ ማየት ነበረብን፡፡ ለጸሐፊው ያነሳቸውን ጥያቄዎች ጨምሮ መጽሐፉን የገመገመው በእግረ-መንገድ በገቡ አባባሎች እንጂ በመጽሐፉ ከተካተቱ ከመግቢያው ጋር 20 ‹‹ቀመስ›› ርዕሰ-ነገሮች ውስጥ በርዕስነት ባልሰፈረው ነገር ነው፡፡ ይህን እንደ ሁለንተናዊ ሒስ ለመቀበል ይቸግረኛል፡፡
ግምገማው የተዓማኒነት ችግር አለበት፡፡
የተዓማኒነት ችግር የገጠመኝ ከመጽሐፉ የተወሰዱት ስህተት የተባሉ ጉዳዮች ስህተትነታቸው ስላጠራጠረኝና ከሲግመንድ ፍሮይድ The Future of an Illusion የወሰዳቸውን አንቀጾች ሲተረጉምና ሲተነትን ስላንሸዋረራቸው ነው፡፡ ለምሣሌ ጌታሁን በዕውቀቱ በክርስትና ላይ ‹‹የአላዋቂነት ድፍረት›› መፈጸሙን ለማሳየት ብሎ ከመጽሐፉ የጠቀሰው ጽሑፍ ሙሉ አይደለም፡፡ ‹‹የስም ለውጡ በዋናነት ከጥምቀት ልጅነት ጋር የተያያዘ ነበር›› የሚለውን ዓ.ነገር ሆን ብሎ ለክርክር እንዲመቸው ይሁን ወይም ይዘቱ ተመሳሳይ መስሎት ልዩነት የለውም ብሎ በሶስት ነጠብጣቦች ተክቶ አልፎታል፡፡ በ‹‹ከአሜን ባሻገር›› ገጽ 105 ላይ የሰፈረው ሙሉ ጽሑፍ ሲመጣ ግን እርሱ ከደረሰበት ማጠቃለያ ይለያል፡፡
በቀደሙት ንጉሠ ነገሥታት ዘመን የማእከላዊው መንግስት ርእዮተ ዓለም ክርስትና ነበር። ክርስትና መነሳት የሙሉ ዜግነት መሥፈርት ነበር ሊባል ይችላል፡፡ የስም ለውጡ በዋናነት ከጥምቀት ልጅነት ጋር የተያያዘ ነበር፡፡ ሳውል የተባለ ይሁዲ ወደ ክርስትና ሲመጣ አሮጌ ስሙን ካሮጌ እምነቱ ጋር አራግፎ ጳውሎስ የሚል አዲስ ስም እንደተቀበለ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ተተርልኮናል፡፡ (ያሰመርኩበት እኔ ነኝ)
ከጽሑፉ የምንረዳው ጌታሁን እንደሚለው፤ ‹‹በዕውቀቱ በቀደሙት ንጉሠ ነገሥታት ዘመን ክርስትና በመንግስት ደረጃ የነበረውን ሚና በሐዋርያት ዘመን ከነበረው ጋር ተመሳሳይ አድርጎ ማቅረቡ›› ሳይሆን የሳውል ስም ወደ ጳውሎስ መቀየር ‹‹በዋናነት ከጥምቀት ልጅነት ጋር የተያያዘ›› መሆኑን ለማሳየት ይበልጥ ይቀርባል፡፡ ይልቁንም ክርስቲያን ነገሥታት የስም ለውጥን የወሰዱት ጳውሎስ የተባለውን ሳውል ምሣሌ አድርገው ነው ለማለት ያስችላል፡፡ እኔ እንደ አንባቢ የሚገባኝ እንደዚህ ነው፡፡ ይህችን ወሳኝ ዓ.ነገር ነጥሎ በመግደፍ የሳውልን ጉዳይ ከመጀመሪያው ዓ.ነገር ጋር ለማገናኘት የሞከረው ጌታሁን ነው፤ ይህም ማለት የበዕውቀቱ አጻጻፍ በአንባቢዎች መካከል የአረዳድ ልዩነት ፈጥሮ እንደሆነ እንጂ በክርስትና ላይ የተፈጸመ ድፍረት አይደለም ማለት ነው፡፡ እኔም ቢያንስ ከክርስትና ታሪክ እንደተረዳሁት፣ በክርስቶስ አስተምህሮ የተመሰረተው ክርስትና መጀመሪያ የድሆችና ጌታሁንም እንዳለው የአናሳዎቹ እምነት ነበር። ‹‹ከክርስትና ጋር ጋብቻ ፈጽሜ ነበር ከሚል ሰው›› የተባለው በዕውቀቱም ይኼ ዕውቀት የሚጠፋው አይመስለኝም፡፡ በበኩሌ ከገለጻው ይህን የሚያስተባብል ድፍረት አላገኘሁበትም፡፡ (ስለተባለም ክርስትና በተለይ በንጉሣውን አደባባይ የኃይለኞች ኃይማኖት ከሆነ በኋላ ክርስቶስ በምድር በተመላለሰበትና በሐዋርያት ዘመን ተጎናጽፎት የነበረው ትህትና አብሮት እንዳልነበረ -ቢያንስ ተከታዮቹ ነን በሚሉት ክርስቲያኖች- የምንግባባ ይመስለኛል፡፡ በመስቀል ጦርነት ስም አንዱ ክርስቲያን ሌላውን ክርስቲያን የጨፈጨፈበትን ዕልቂት ጨምሮ በክርስትና ስም ዐለም ተቸግራ ነበር፡፡ ርግጥ ክርስትናና ክርስቲያን ነን ባዮች የተለያዩ ናቸው የሚለው ይገባኛል። ይህም ቢሆን ሙግት አያጣውም)፡፡ ወደ ነጥቤ ስመለስ ጽሑፉን በቀጥታም (direct association) ወሰድነው በተዘዋዋሪ (by way of transitivity) አረዳዱ ‹‹ሳውል ስሙን የለወጠው በመንግሥት ለመሸለም ነው›› ለማለት አይመችም፡፡ ጌታሁን አንቀጹን እንደገና እንዲያነበውና ‹‹ስምና ማንነት›› ከሚለው ጽሑፍ አጠቃላይ መንፈስ አንጻር እንዲያየው እጠይቃለሁ፡፡
ከሲግመንድ ፍሮይድ The Future of an Illusion የተወሰዱ ሁለት አንቀጾችም ተራ የሚመስሉ ነገር ግን ጌታሁን በፍሮይድ ስም የሰጠውን ማስጠንቀቂያ የወለዱ የትርጉምና የትንታኔ ችግር አለባቸው፡፡ ከፍሮይድ መጽሐፍ ሲጠቅስ ከበዕውቀቱ መጽሐፍ የጠቀሳትን አንቀጽ ባሳሳተበት መንገድ ከመሔዱ ሌላ ሲተረጉም ደግሞ የራሱን ጨምሯል፤ አለዚያም የፍሮይድን ቀንሷል። ከፍሮይድ በወሰደው ግማሽ እውነት ላይ የእርሱን ማጠቃለያ ቸልሶበታል፡፡ ይህ ለምን እንደሆነ አልገባኝም። ያነበብነው መጽሐፍ የተለያየ ይሆን? እኔ ያነበብኩት ከጀርመንኛ ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመውንና ጀምስ ስትራቼ በተባለ ሰው የተዘጋጀውን በ1961 (እ.ኤ.አ) የታተመውን ነው፡፡ ወይስ ከችኮላ ነው? ለምሣሌ ፍሮይድ ሥልጣኔ ከመቅጽበት የሰውን ልጅ ወደ ሰይጣንነት ሊቀይረው እንደሚችል መግለጹ ላይ ትክክል ነው፡፡ Human creations are easily destroyed, and science and technology, which have built them up, can also be used for their annihilation ብሏል፡፡
ነገር ግን
…But you must admit that there is here the justification for a hope for the future…Should it prove unsatisfactory, I am ready to give up the reform and to return to the earlier: man is a creature of weak intelligence who is governed by his instinctual wishes
የሚለውን ‹‹ይህም ዕውን ሆኖ ከተገኘ የሰው ልጅ በዕውቀት ከመመራት ይልቅ በደመ ነፍስ መመራትን ስለመረጠ ምልከታዬን ፉርሽ አድርጉት ብሎናል፡፡›› ብሎ ሲተረጉመው ቃል በቃል አለመሆኑ ብቻ ሳይሆን ሲጠቅስ ይዘቱን ቆራርጦታል፡፡ ሲተረጉም መልዕክቱን አዛብቶታል፡፡ ጌታሁን ከጠቀሰው ጀምሬ ከገጽ 48ና 49 ብጠቅስ የሚከተለው ነው፡፡
But you must  admit that here we  are justified  in having  a  hope for  the future-that perhaps  there is a  treasure  to be dug up capable of enriching  civilization  and  that  it  is  worth  making  the  experiment of an irreligious education.  Should  the  experiment prove unsatisfactory I  am  ready  to  give  up  the  reform  and  to  return to  my  earlier,  purely  descriptive  judgement  that man  is  a creature of weak  intelligence  who  is  ruled  by his  instinctual wishes.
ይህን ከጌታሁን አተረጓጎምና ሀሳብ ጋር ስናስተያየው፤ ‹‹ይህም ዕውን ሆኖ ከተገኘ የሰው ልጅ በዕውቀት ከመመራት ይልቅ በደመ ነፍስ መመራትን ስለመረጠ ምልከታዬን ፉርሽ አድርጉት›› የሚል ነገር እዚህ የለም። ፍሮይድ ሙከራውን እዚያው አይቶ ውድቅ ያደረገው አስመስሎታል፡፡ ፍሮይድ የሚለው ‹‹ከኃይማኖት ነጻ የሆነ ትምህርትን መሞከር ያዋጣ ይሆናል፤ ሙከራው ካልሰራ (ካላሳመናችሁ) ሪፎርሙን ለመተውና ወደ ጥንቱ የሰው ልጅ በደመነፍስ የሚመራና ደካማ አዕምሮ ያለው ፍጡር ነው ወደሚለው ሀሳብ ለመመለስ ዝግጁ ነኝ›› ነው፡፡ ለእኔ እንደሚገባኝ እንወራረድ የማለት ያህል ነው የፍሮይድ አባባል፡፡ ምልከታዬን አይታችሁ ትፈርዳላችሁ ነው፡፡ አሁን በዕውቀቱና ጌታሁን ምልከታውን አይተው ይከራከራሉ ማለት ነው፡፡ ጌታሁን ፍሮይድ ይህን ሀሳብ ያስገባበትን አውድ ሳያሳይ ስለቆራረጠው ወይም ራሱ ስላላብራራው ከፍ ያለ የመረዳት ችግር የፈጠረ ይመስለኛል፡፡
ሌላው፡-
It is, to be sure, a senseless proceeding to try and do away with religion by force and at one blow –more especially as it is a hopeless one. The believer will not let his faith be taken from him, neither by arguments nor by prohibitions. And even if it did succeed with some, it would be a cruel thing to do.
በግርድፉ ስንተረጉመው፡-
ሃይማኖትን ራስን በመጫን በአንድ ጥይት ለመተው መሞከር ስሜት አልባነትን የሚያመላክት ድርጊት ነው… አማኝ እምነቱን በክርክርም ይሁን በክልከላ እንዲወሰድበት አይፈቅድም ምናልባት አንዳንዶች ይህን አድርገውት ከሆነ ድርጊታቸው የጭካኔ ሥራ ነው
የሚለውን የጌታሁንን መልዕክት አይሰጥም፡፡ የሚቀርበው፡-
ይህ በእውነቱ ኃይማኖትን በኃይል ወይም በአንድ ምት ለማስወገድ የመሞከር ትርጉም የለሽ አካሔድ  ነው- በተለይ የሚሳካ ስለማይሆን፡፡ አማኝ እምነቱ በክርክርም ይሁን በክልከላ እንዲወሰድበት አይፈቅድም፡፡ በአንዳንዶች ቢሳካም እንኳ ይህን ማድረግ አረመኔነት (የጭካኔ ሥራ) ነው፡፡
ለሚለው ነው፡፡ ነገርየው ጉንጭ አልፋ ቢመስልም ጌታሁን በተለይ ፍሮይድ መጽሐፉን አንብበው ኃይማኖታቸውን በችኮላ ለመቀየር እንዳያስቡ አስጠንቅቆ ነበር ብሎ የሚከራከረው በዚህ ማስረጃው ከሆነ የሁለቱ ትርጉሞች መልዕክቶች የተለያዩ ናቸው። ባለ ኃይማኖቱ በራሱ ተነሳሽነት ማመኑን እንዳይተው ለባለኃይማኖቱ ለራሱ ብቻ የተናገረው ነው ብሎ አዞረው እንጂ ፍሮይድ የተናገረው ውጫዊ ኃይል ኃይማኖትን በኃይልና በቅጽበት ለማስተው መሞከር እንደሌለበት የሚያሳይ ምላሽም ነው። ፍሮይድ እንዲያውም ጽሑፉ ቢነበብ ጎጂነት እንደሌለውም ተናግሯል፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ ማስጠንቀቂያው የሚሰራው ‹‹መጽሐፉን አንብበው በችኮላ ከሃይማኖታቸው ጋር ፍቺ ለመፈፀም የሚያስቡ ካሉ እንዳይሞክሩት›› ነው ወይስ ስልጣንና ሀሳብ (እንደ ፍሮይድ) ያላቸው ሰዎች ሌሎችን እንዳያስቸግሩበት ነው? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ ፍሮይድ ወረድ ብሎ እንዳብራራው፤ ኃይማኖትን በኃይልና በቅጽበት ማስተው ማለት በእንቅልፍ ኪኒን እንቅልፍ መተኛት የለመደን ሰው ድንገት ኪኒኑን መንጠቅ ማለት ነው፡፡ ኪኒኑን በፈቃዱ ካቆመውስ? ማለትም እንደ በዕውቄ ኢ-አማኒ ከሆነስ? እንደሚመስለኝ ፍሮይድ ደስታውን አይችለውም፡፡ ሙከራው ሰራ ማለት ነው፡፡
ቸር እንሰንብት!

Read 3646 times