Saturday, 26 March 2016 10:58

‹‹አባ ሴና››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

     ህይወት፤ ታሪክ ሲሆን የሚቀንሰውና የሚጨምረው ነገር ይኖራል፡፡ ይህ ጽሑፍ የጉዞ ማስታወሻ ነው፡፡ ስለዚህ የታሪክ የመጀመሪያ ረቂቅ ተደርጎ ሊታሰብ ይችላል፡፡ የታሪክ ረቂቅ ከሆነ፤ የሚቀንሰውና የሚጨምረው ነገር ይኖራል፡፡ ሆኖም በእኔ በኩል፤  የመጨመሩና የመቀነሱ ጉዳይ ከይዘት ጋር የተያዘዘ አይደለም፤ ከስሜት እንጂ፡፡
አሁን የምጽፈው ነገር ስኖረው እንደ ተጎዘጎዘ ትኩስ ቄጠማ ነበር፡፡ እየቆየ ቄጠማው ደረቀ። ስኖረው እንደ እርጥብ ቄጠማ የነበረው፤ ዓመት በዓሉ አልፎ በእግረ ህሊና ብዙ ተረጋግጦ፣ የትዝታ ትርፍራፊ ተበታትኖበት፣ የትውስታ ቅራሬ ተደፍቶበት፤ እንደ ተረጋገጠ ሣር ሆኖ ነበር፤ ወይም የተጋጠ አጥንት፡፡
አንትሮፖሎጂስቶች፤ “gone native” የሚሉት ችግር አለ፡፡ አንትሮፖሎጂስቱ ሊያጠናው ከሚፈልገው ህብረተሰብ ውስጥ ገብቶ ኖሮ፤ በጊዜ ብዛት ከእነሱ እንዳንዱ ሲሆን የጥናት ሥራውን ለመስራት ይቸገራል ይባላል፡፡ እንደተኖረ ስላልተጻፈ፤ “gone native” የሚሉት ዓይነት ችግር እንዳይገጥመኝ እየሰጋሁ መጻፍ ጀመርኩ፡፡  
በሻልና በአሪቲ የተዋበው የጉዞ ልምድ፤ ቆይቶ ሲጻፍ በሙሉ ኃይሉና መዐዛው መምጣት ይሳነዋል፡፡ እናም የስሜት ቄጤማው ሲጎዘጎዝ የነበረው ህይወት ተዳክሞ ታየኝ፡፡ ክብደቱ ቀንሶ ተሰማኝ፡፡ ግን ጨርሶ  ቅልል - ክሽልል ያለ ስላልነበር፤ መፃፍ ከጀመርኩ በኋላ ደረቅና መዐዛ አልባ ህይወት አልሆነብኝም፡፡ ሆኖም ከችግር የታደገኝ አንድ ጥሩ ዕድል ነበረኝ፡፡
ይህ ማስታወሻ፤ እኔ ያየሁ -የሰማሁትን የገለጽኩበት ማስታወሻ አይደለም - በአብዛኛው፡፡ በጉዞ ውስጥ ሌላ ጉዞ ነበር፡፡ ወደ ነቀምት እየተጓዝኩ ሳለሁ፤ የምመለከተው የአሁኗን ነቀምቴን መንገድ አልነበረም፡፡ በ‹‹አባ ሴና›› የህይወት ዘመን ትውስታ ወደ ኋላ ሄጄ በትናንቷ ነቀምቴ ጎዳና እመላለስ ነበር። ‹‹አባ ሴና›› የድሮ ታሪኩን ያጫውተኛል፡፡
‹‹አባ ሴና›› ሲያወራ፤ እንደ ሳር የደረቀው ሙት ህይወት ለምለም ማዕዛ ያገኛል፡፡ ወጉ አሁን ታጭዶ ታስሮ እንደ ተቀመጠ ሣር፤ ለመንፈስ የሚተርፍ ኃይል ይኖረዋል፡፡ ስለዚህ የሚሸታችሁ አሁን የተጎዘጎዘ ቄጠማ መዐዛ እንጂ፤ ላመትባል ተጎዝጉዞ ሦስት ቀን የሞላው የደረቅ ሣር ሽታ አይደለም፡፡
በመንገድ ስንሄድ፤ ‹‹እንቅቡም - ሰፌዱም›› የትዝታ ተላላኪ እየሆነበት፤ ገጠመኞቹን ያጫወተኝ ነበር፡፡ በእርሱ የትረካ ጎዳና እየተጓዝኩ፤ በየመሐሉ ከተማ ያደረቀውን መንፈስን ከሚያለዝብ የድንግል ተፈጥሮ ጽዋ ጎንጨት አደርግ ነበር፡፡ በዚህ ጉዞ ‹‹አባ ሴና›› ባይኖር፤ የጉዞዬ ጣዕም ፍጹም የተለየ በሆነ ነበር። እናም የተጓዝኩት በእርሱ የምናብ ጎዳና እና በእርሱ የታሪክ ገለጻ ፈለግ ነበር፡፡  
መኪናዋ ትከንፋለች፡፡ አሁን አዲስ አበባን ለቅቀን እየወጣን ነው፡፡ ገና ከመነሻችን፤ ‹‹ይህ የምታየው የመናገሻ ጥብቅ ደን ብዙ ዘመን አለው›› በማለት ታሪክንና ትዝታን ከጂኦግራፊ ጋር እያዋደደ ያጫውተኝ ጀመር፡፡ አንድ ነገር ብሎ ትንፋሽ እንድወስድ ወይም ከራሴ ጋር እንድጫወት ይተወኛል። መኪናዋ ትከንፋለች፡፡ አንዳንድ ነገሮች በመኪናዋ ድምጽ እየተደፈጠጡ ያመልጡኛል። የመኪናዋ እንቅስቃሴና ድምጧ ወሬ ይሰርቀኛል። ከትረካው ባህር አውጥቶ ይጥለኛል፡፡ እንደገና ተመልሼ እገባለሁ። አካሌ በመኪና፤ ምናቤ በ‹‹አባ ሴና›› ተረክ ጉዟቸውን ቀጥለዋል፡፡ መኪናው ይከንፋል፡፡
‹‹አባ ሴና›› እንዲህ አለኝ፤ ‹‹የሚገርምህ ይህ የመናገሻ ጥብቅ ደን፤ ጥሩ የተራራ ሽርሽር ሥፍራ ሊሆን የሚችል ውብ ቦታ ነው፡፡ ሆኖም የአዲስ አበባ ሰው ወደዚህ ዝር አይልም፡፡ የሚገርመው ፈረንጆቹ ይመጣሉ፡፡
አሁን GTZ ነው የያዘው፡፡›› አስገምጋሚው የ‹‹አባ ሴና›› ድምጽ የማለዳውን ድባብ ካስጌጠው የፀሐይ ብርሃን ጋር እየተሻሼ ወደ ጆሮዬ ይመጣል፡፡ መኪናው በጣም ይሮጣል፡፡
‹‹አባ ሴና››፤ ስለ ወጨጫ ተራራ፣ ስለ በቾ ሜዳ፣ ስለ ሆለታ ገነት የጦር ት/ቤት (መጀመሪያ)፤ ወይም ስለ ሙሉጌታ ቡሊ የጦር አካዳሚ (አሁን ኃየሎም) እያጫወተኝ እንደ ጉድ እየከነፍን ነው፡፡ ያማረውን የሆለታ ግብርና ምርምር መስክ እየቃኘሁ ስጓዝ፤ ‹‹ይህ ወደ ሙገር ይወስዳል›› አለኝ፡፡ ሆለታን ሰንጥቀን አዲስ ዓለም ገባን፡፡
ከአዲስ አበባ ቀድማ የኢትዮጵያ መዲና የመሆን ማዕረግ አግኝታ ስለነበረችው አዲስ ዓለም ታሪክ አጫወተኝ፡፡ ከአዲስ ዓለም ከተማ ዳርቻ ያለ አንድ ቤት በጣቱ እያመለከተኝ፤ ‹‹ተመልከት ያ የአባ መላ፤ የፊታውራሪ ኃብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ቤት ነበር›› አለኝ። ስለ ገረሱ ዱኪ፣ ስለ ብርጋዴር ጀነራል ጃገማ ኬሎ፣ ስለ ከበደ ብዙነሽ አጫወተኝ፡፡ እንዲህ አድርጎ ከታላቁ ባለቅኔ ከሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን የትውልድ ሐገር አምቦ አደረሰኝ፡፡ ስለ ባለቅኔው ታሪክም አጫወተኝ። ዘወትር ከአጠገቡ ከማይለየው የባለቅኔው የግጥም መድበል (እሣት ወይ አበባ) አንዳንድ ግጥሞችን በቃሉ ያነበንብ ነበር፡፡ ‹‹ልክፍቷ እንደሁ አልለቀቀኝ፤ ደግሞ መሼ አምባ ልውጣ›› የሚለው ስንኝ፤ እንደ ማለዳ የወፎች ዜማ በህሊናዬ ሰማይ እያስተጋባ አምቦ ደረስኩ፡፡  
አምቦ ጥሩ ቁርስ በላን፡፡ ቡና ጠጣን፡፡ ጉዞ ቀጠልን።
መቼም፤ ‹‹የአባ ሴና›› የአካባቢ ገለጻ ችሎታና የመልክዐ ምድር ንባብ ብቃቱ (ዕውቀቱ) ይገርመኛል። እኔ የእናቴ ተጽዕኖ በዝቶ መሰለኝ፤ ጅኦግራፊ ላይ እስተዚህም ነኝ፡፡ እንደሚባለው ሴቶች ጅኦግራፊ ይቸግራቸዋል፡፡ ትክክል ይመስለኛል፡፡ ስለ ጅኦግራፊ ‹‹አደሞ›› (አደን) የሚወጣው ወንድ ይጨነቅ እንጂ ለእነርሱ ምን ይሰራላቸዋል፡፡ ወደ ቤት የመጣችሁ እንደሁ፤ ወንድ እውር ነው፡፡ ካልሲ ከአጠገቡ አስቀምጦ፤ ሲፈልግ አንድ ቀን ሊፈጅ ይችላል። ከአጠገቡ ሴት ከሌለች ሲፈልግ ይባጃል፡፡ ለማንኛውም፤ ‹‹አባ ሴና›› ጅኦግራፊ ይገባዋል፡፡  
እናም እንዲህ አለኝ፤ የአዋሽ ወንዝ መነሻ የተራራ ሰንሰለትን እያሳየኝ፤ ‹‹ከተራራው በስተምሥራቅ የሚፈሱት ጅረቶች ሁሉ የአዋሽ ገባሮች ናቸው። ከተራራው በስተምዕራብ የሚወርዱት ደግሞ የአባይ ገባሮች ይሆናሉ፡፡›› የደን ባለሙያዎች፤ ‹‹እርጥብ ብርድ ልብስ›› የሚሉት የተራራ ሰንሰለት ነው፡፡ እንደ ዘበት እመለከተው የነበረው የተራራ ሰንሰለት፤ አሁን የተለየ ነገር ሆኖ ታየኝ፡፡ ‹‹አባ ሴና›› ስለ ዴዴሳ፣ ሙገርና ዳቡስ ወንዞች ተፋሰስ ብዙ አጫወተኝ፡፡
ደግሞ ግንደ በረትን አነሳ፡፡ የባርያ ንግድ ማዕከል እንደነበረች አወሳ፡፡ አውቃለሁ፤ ግንደ በረት የባርያ ንግድ ማዕከል ነበረች- (እኔም ታሪክ ላይ ምንም አልልም)፡፡ የአምቦ አካባቢን ጨምሮ፤ በዚያ ግድም የሚኖረው ህዝብ አትንኩኝ ባይ መሆኑና በደርግ ዘመንም ትጥቅ ያልፈታ ህዝብ እንደነበር ነገረኝ፡፡ እንዲህ እያልን፤ ‹‹አባ ሴና›› ‹‹ምላጭ ከመሰለ ሥፍራ የተቆረቆረች ከተማ›› ሲል ከገለፃት ከተማ ደረስን። ጌዶ ነች፡፡ የከተማዋ ግራና በቀኝ ገደል ነው፡፡ ስለዚህ በገጣሚ ዓይን ምላጭ ላይ የቆመች ከተማ ተብላ ልትገለጽ ትችላለች፡፡ እኔ ደግሞ ራቅ ብዬ ስመለከታት፤ የአንገት ሐብል ያደረገ ተራራ መስላ ታየችኝ፡፡ የጌዶ ከተማ እስክንደርስ ድረስ ለ75 ኪ.ሜ ያህል ሽቅብ እየወጣን ነበር፡፡ ከጌዶ በኋላ የቁልቁለት መንገድ ጀመርን፡፡ ደልዳላው የአስፋልት መንገድ አቁሞ፤ ለአፍታ በአስፋልት እየተጓዝን የሚበዛውን በተለዋጭ መንገድ የምናደርገው ጉዞ በዛ፡፡ ወደ ነቀምት እየከነፍን ነው፡፡
‹‹አባ ሴና›› በሀገር ቤትና በውጭ ሐገር የገጠመውን አጫወተኝ፤ 8፡30 ግድም ነቀምቴ ገባን፡፡ ነቀምቴ ደማቅ ታሪክ ያላት፤ ታዋቂ የንግድ ማዕከል ነበረች። ጣሊያኖችን፣ አርመኖች፣ አረቦችን፣ ህንዶችንና ግሪኮችን ጠርታ፤ የሞቀ ንግድ ታካሂድ የነበረች ባለዝና ከተማ ነበረች፡፡ የማዕከላዊ መንግስቱ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የነበረች፡፡ ነቀምቴ ገብተን በቀጥታ ወደ ሶና ሆቴል ሄድን፡፡
እያንዳንዱ ከተማ የራሱ ሽታ አለው፡፡ ወለጋም እንዲሁ ናት፡፡ አየሩና ድባቡ ይመቻል። ግን ነቀምቴ ልታወራኝ ዝግጁ አልነበረችም። ወግ አምጪ አልኳት። ዝምታን መርጣለች። አዲስ የተዋወቁ ሰዎች የሚገጥማቸው ችግር እንደ ገጠመን አሰብኩ፡፡ እናም ወሬ ለመጫር፤ ዝም ብዬ ወረቀትና ብዕር አነሳሁ። ምንም ሐሳብ አልነበረኝም፡፡ የሚሆነውን ለማየት በመኝታ ክፍሌ ከነበረው ወንበር ተቀመጥኩ፡፡ ለመፃፍ ተቀመጥኩ፡፡ ወለጋ ግን ዝም አለችኝ፡፡ ነቀምቴ፤ ከኔ ጋር ወሬ አልፈለገችም፡፡ ፀጥ ረጭ ብላለች፡፡
ግን ‹‹አባ ሴና›› ያወራልኛል፡፡ የታሪክ ጎዳና ውስጥ ነው፡፡ የትዝታ ሜዳ ውስጥ ነው፡፡ ያስታውሳል። በልጅነት ዘመን የነበረውን ታሪክ ልቅም አድርጎ ያስታውሳል፡፡ አንድ ቀን ትዝታውን የሚነግራት ሚስቱ፤ ‹‹አሁን ይህን ነገር ሁሉ እንዴት ልታስታውስ ትችላለህ?›› እንዳለችው ነገረኝ፡፡ ባለቤቱ፤ ትውስታው ግልጽና ትብ መሆኑ ይገርማታል፡፡ ስለዚህ የሚነግራትን የልጅነት ታሪክ ማመን ያዳግታታል፡፡
ሆኖም ‹‹አባ ሴና›› ባለቤቱ ለምታነሳው ጥያቄ መልስ አለው፡፡ ‹‹እርሷ የልጅነት ዘመኗን ላታስውስ ትችላለች፡፡ ምክንያቱም፤ የእርሷ ህይወት የድግግሞሽ ነው፡፡ ከት/ቤት ወደ ቤት፡፡ ከቤት ወደ ት/ቤት፡፡ በቃ። እንደኔ ሁነት የበዛበት ህይወት የላትም፡፡ ተደጋጋሚ ነገሮችን የሚሰለቸው አዕምሮ፤ በማስታወስ ላያግዛት ይችላል፡፡ በዚህ ነገር እንጨቃጨቃለን፡፡ እያንዳንዷ ቀን ሁነት አጭቃ ወደኔ ትመጣለች፡፡ ስለዚህ ለእኔ አንድ ዓመት 365 ቀናት አይደለም፡፡ 3 ሺ 650 ቀናት እንጂ›› ይላል፡፡

Read 2599 times