Saturday, 26 March 2016 10:46

ጋዜጠኝነት በሙስና የተዘፈቀ ነው ተባለ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

90 በመቶ ጋዜጠኞች በሥራቸው እርካታ የላቸውም
   በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ሙያ በጥቅማ ጥቅም የታሠረና በሙስና የተዘፈቀ መሆኑን የፌደራል ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የቀረበ ጥናት አመለከተ፡፡
“በመገናኛ ብዙኃን መልዕክቶች ዙሪያ የሚታዩ ተግዳሮቶችና መፍትሔዎቻቸው” በሚል ርዕስ ከትናንት በስቲያ ኮሚሽኑ ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን መምህርና የዩኒቨርስቲው የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፍ፤ ጋዜጠኞች ዘገባ ለማቅረብ ጉቦና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞችን እንደሚቀበሉ ጠቁመዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለይ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ትንሹ ስራቸው በሚዲያዎች ተጋኖ እንዲቀርብላቸው ጋዜጠኞችን ለመደለያ በእቅዳቸው ውስጥ በጀት እስከ መያዝ ደርሰዋል ያሉት አጥኚው፤ በዚህ ምክንያት ጋዜጠኞች ህብረተሰባዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዳይወጡ ተፅዕኖ ውስጥ ወድቀዋል ብለዋል፡፡
ችግሩ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም በስፋት እንደሚንፀባረቅ የጠቆሙት ጥናት አቅራቢው፤ በፖስታ ታሽጐ ከሚሠጥ ገንዘብ ጀምሮ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች፣ ከልብስና ጫማ ጀምሮ ውድ ስጦታዎች ድረስ እንዲሁም ለአንድ የዘገባ ስራ የትራንስፖርት፣ የማደሪያና የምግብ … የመሳሰሉ ወጪዎችን መሸፈን በኢትዮጵያም ይሁን በአህጉሪቱ የተለመደ መሆኑን በመግለፅ፣ ይሄም ከሙያው ስነምግባሮቹ ጋር የሚጋጭ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በብርሃኑ ሌዳሞ ለሁለተኛ ድግሪ ማሟያ የተሠራን ጥናት የጠቀሱት ጽሑፍ አቅራቢው፤ ስለ መደለያ ገንዘብና ሌሎች ስጦታዎችን ስለመቀበል ከተጠየቁ ጋዜጠኞች መካከል 83.3 በመቶ ያህሉ ለሚሰሩት ዘገባ ገንዘብ ወይም ሌሎች ጥቅማ ጥቅም እንዲሠጣቸው እንደሚፈልጉ ተናግረዋል ብለዋል፡፡
ጋዜጠኞች ገንዘብና ጥቅማ ጥቅም የሚገኝባቸውን “ቡጬ ያለው” በሚል እንደሚለዩ የጠቀሱት አጥኚው፤ ገንዘብም ሆነ ጥቅማ ጥቅም የሌላቸው ተቋማት “ደረቅ ጣቢያዎች” የሚል ስያሜ ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡ ገንዘብና ጥቅማ ጥቅም የማይቀበሉ ጋዜጠኞች፣ በተቀባዮቹ የተለያዩ ስያሜዎች እንደሚሠጣቸው ሲገልፁም፤ “በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢትዮጵያና የኤርትራ መልዕክተኛ” ወይም “ወጋሚ” የሚሉ ስያሜዎች እንዳላቸው ጥናት አቅራቢው አብራርተዋል፡፡
በአሁን ወቅት ጥቅም የተገኘባቸው ዘገባዎችና ፕሮግራሞች በቀላሉ እየተለዩና እየታወቁ እንደመጡ ያመለከቱት አጥኚው፤ ጥቅም የተገኘባቸው ዘገባዎችና ፕሮግራሞች ሳቢና ማራኪ ተደርገው ሲቀርቡ ያልተገኘባቸው ደግሞ “እንደነገሩ” ይቀርባሉ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ጋዜጠኞች ለገንዘብና ጥቅማ ጥቅም ተገዢ እየሆኑ የመጡበት ምክንያት በዋናነት ከመስሪያ ቤታቸው የሚያገኙት ደሞዝና ጥቅማጥቅም ዝቅተኛ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡
በሀገሪቱ 89.6 በመቶ የሚሆኑት ጋዜጠኞች በስራቸው እርካታ እንደሌላቸው የጠቆመው ጥናቱ፤ ይሄም ለሚዲያ ባለሙያዎች ከሚከፈለው ደሞዝ ጋር የተገናኘ መሆኑን አመልክቷል፡፡
ጋዜጠኞች ከሙስና ፀድተው በሙያቸው እንዲሠሩ በቂ ስልጠና ማግኘት ይኖርባቸዋል ያሉት አጥኚው፤ በየተቋሞቻቸው የስነ ምግባር መመሪያ መዘጋጀት እንዳለበትና ደሞዛቸውም ከፍ ሊል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

Read 8208 times