ባለፉት 4 ወራት በኦሮሚያ ክልል የተፈጠረው ተቃውሞና ግጭት በፍጥነት እያደገ ባለው የሀገሪቱ
ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል “ፎሬይን ፖሊሲ” መፅሄት ጠቆመ፡፡ “ዘ
ኢኮኖሚስት” በበኩሉ፤ “ወትሮም ጠንካራ ያልሆነውን የፌደራል ስርአት ግጭቶች እየተፈታተኑት ነው” ብሏል፡፡
በፍጥነት እያደገ የመጣው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ለግጭቱ መነሻ ከሆኑት ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ የጠቆመው የ “ፍሬይን ፖሊሲ” ተንታኟ ጄሲ ፎርቲን ፅሁፍ፤ ለኢንዱስትሪ መስፋፋት ሲባል ሀገሪቱ ከውጭ ለምትጋብዛቸው ኢንቨስተሮች የምታቀርበው መሬት፣ የሚሊዮኖችን ህይወት አናግቶና አፈናቅሎ ለግጭቱ ሰበብ መሆኑን ያብራራል፡፡ መንግሥት የዜጎቹን ጥያቄ ከመስማት ይልቅ ጥያቄዎችን በኃይል ለማዳፈን ጥረት ማድረጉን የሚቀጥል ከሆነ ሀገሪቱ የፖለቲካ መረጋጋት እንደሚርቃት፣ የታለመው ኢኮኖሚያዊ እድገትና የውጭ ኢንቨስትመንትም እንቅፋት ሊገጥመው እንደሚችል ትንተናው ያስረዳል፡፡
ግጭቱ ተቀስቅሶባቸው በነበሩ አካባቢዎች ሰዎች ስለተፈጠረው ነገር ለማስረዳት በከፍተኛ ፍርሃት መሸበባቸውን ጄሲ ፎርቲን በፅሁፏ ትገልፃለች፡፡ ዘ ኢኮኖሚስት በበኩሉ፤ በክልሉ የተከሰተው ግጭት ከመሬት ባለቤትነት፣ ከሙስና፣ ከፖለቲካ ምህዳር መጥበብና ድህነት ጋር በቀጥታ የሚገናኝ ነው ብሏል፡፡ ለ4 ወራት በዘለቀው ተቃውሞና ግጭት 250 የሚደርሱ ሰዎች መገደላቸውን የሰብአዊ መብት ተቋማት መግለፃቸውን የጠቀሰው መፅሄቱ፤ መንግስት ለ ቁጥሩ የተጋነነ ነው በሚል መቃወሙን አመልክቷል፡፡
ግጭቶቹ የተፈጠሩት በመልካም አስተዳደር እጦት መሆኑን በተደጋጋሚ የገለፀው መንግስት፤ ከህብረተሰቡ ጋር በሰፊው በመወያየትና ድክመቶችን በማረም፣ ለችግሩ እልባት ለመስጠት እየሰራ
መሆኑን ይናገራል፡፡
Saturday, 26 March 2016 10:24
በኦሮሚያ የተፈጠረው ግጭት በኢንቨስትመንት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳይፈጥር ተሰግቷል
Written by አለማየሁ አንበሴ
Published in
ዜና