Saturday, 19 March 2016 11:45

“ሰማይ የላሱት” የመስፍን ግጥሞች

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(3 votes)

 በድዳቸው የሚስቁ ኮበሌዎችን ለዛ፣በጠውላጋ ሳቅ ስር የወደቁ የብርሃን ፍንክቶችን ጸጋ፣ወደ ድንግል ተፈጥሯቸው መልሶ፣በውበት ድንኳን ቀለም ነስንሶ፣ ሃረግ ቀንጥሶ ለማሽሞንሞን ከያኒን ማን ብሎት!! አጥራቸው የፈረሰ ዝርክርክ የህይወት መልኮችን ብርቱ ከያኒ ካገኛቸው በውበት ተወልውለው፣በቀለማት ይደምቃሉ፤በአበቦች ሽታ ደም ያገኛሉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ገጣሚ ዋናው ነው፡፡ የግጥም ሊቁ ፐረኔ እንደሚሉት፤ አሳዛኙንና መቅኖ የራቀውን ነገር ለዛ ሰጥቶ እንባውን ጠርጎ ማቅናትና መሸላለም የግጥም ተፈጥሮ ነው፡፡ እኛ ሃገር ደግሞ ለዚህ ዐይነቱ ነገር በእውቀቱ ስዩም ቀሽት ነው፡፡
ታዲያ ገጣሚያኑም አንዱ-በአንዱ ይወሰዳል፡፡ ለምሳሌ፡- ካርሊሌ በሃሳብ ይመሰጣል፤ ኤድጋር አለንም በውበት፣ ማቲው አርኖልድ ደግሞ ትርጓሜ ላይ፡፡ እነዚህ ሁሉ ባንድ ክር የተሰፉ ዶቃዎች ናቸው፡፡ ልዩ-ልዩ መልክ ግን አንድ ጌጥ!  
ለግጥም ጨርቅ ጥለው የሚያብዱ፣ ነፍሳቸውን ደመና ላይ ጠቅለው፣ እየተሰነጠሩ፣ መልሰው መሬት ላይ የሚሰኩ ሞልተዋል፡፡ አንዳንዶች ግን ዓይናቸውን በጨው አጥበው እንዲህ ይላሉ፡፡ ካርሊ ኢ ቤይን፣ ጄሮም ቤቲ፣ ጂ ፖል ሀንተር በፃፉት ጥራዝ፤
“Those who love it (poetry) sometimes gives the impression that it is an adequate Substitute for food, shelter, and love” የዚህን ተቃራኒ የሚሉ ደግሞ አሉ፤ እርሱን አናነሳም፣ ግን ግጥም ምን ያህል ልብን አንዛሪ፣ ነፍስ ቆፋሪ መሆኑን መጭረፋችን ግድ ነው፡፡ ሰማይ የሚልስ ምላስ ያላቸው ግጥሞች፤ የምድርን እንብርት ያደሙ ቅኔያት በዘመን መከሰታቸው አዲስ አይደለም፡፡ ወደፊትም አዲስ አይሆንም፡፡ አንዳንዴ ግን በየዘመናቱ ግጥሞች ምዕተ ዓመታት አስቆጥረው ብቅ ሊሉም ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ በሚልተን ሞት ተኝቶ የነበረው ሶኔት ግጥም፤ በወርድስ ዎርዝ ግጥሞች ነገ ተመልሰው እንደመጡ፡፡
ከዚህ ቀደም እንዳልነው የዚህ ዘመን ግጥሞች ወደ ስሜት የተጠጉ፣ አጫጭርና የቅርብ ልብ ናቸው፡፡ ባብዛኛው ሌሪክ የዘመናችን መለያ ነው፡፡ ሌሪክ ደግሞ ብዙ ነው፤ አንዳንዶቹ ቅርፃቸው እንደየሀገሩ ሁኔታ ይለያያልም፡፡ እኛም የግጥሞችን ድንኳን ስንበረብር በጮሌ ቃላትና በዜማ ምትሃት ብቻ መስከር የለብንም። ለግጥም የተፈጠሩ ውብ ቃላት ቢኖሩ፣ ቤት መምቻና መድፊያ ላይ እሳት የሚጭሩ ምቶች ቢገኙ፣ምርጥ ሃሳብ ከጠፋ ንፋስ እንደመጎሰም ነው፡፡ ብዙ ጊዜም ገጣሚያን አንዱ-ከአንዱ በዚህ ይለያየል፡፡ በዕወቀቱ ስዩም በሃሳብ ልዕቀት ሠማይ ሲነካ፣ ታገል ሰይፉ በምቱ ዜማ ክዋክብት ይጠቅሳል፡፡ ዳዊት ፀጋዬ በፍልስፍና የእግዜር በር ያንኳኳል፡፡ ሌሎቹም እንደዚሁ ይለያያሉ፡፡ በተለይ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ግጥሞች ቢጠኑ ለአደባባይ የተወለዱና ድንቅ ሃሳብና ፍልስፍና ያላቸው፣ልዩ ስንኞች ሁሉ አሉ፡፡
የዛሬው የቅኝት እንግዳዬ መስፍን ወንድወሰን የተባለው ወጣት ገጣሚም ባብዛኛው በሌሪክ ዝርያ ተደምሞ፤ “የኔ ቢጤ ሰማይ” በሚል ርዕስ ግጥሞች ለህትመት አብቅቷል፡፡ ሌሪክ ደግሞ ስሜት-ንክር ነው፤ ባለ ብዙ ፈርጅም፡፡…
እስቲ ግጥሞቹን በጥቂቱ እንያቸው፡፡
“ጎርፍ”  ከሚለው እንጀምር፡፡
ጎርፍ አፈሳሰሱ ጎኑ እየቆሰለ እምቢ በምላሱ
ጎርፍ አወራረዱ
እየተንገላታ ፉከራ መውደዱ፡፡
የጎርፍ ኩሩ ድምጽ ቢመስልም የጸሎት
… ኑሮው ግን የስቃይ
የአለት ጥፊ መቅመስ
ከገደል መፈጥፈጥ መላተም ከድንጋይ!
ግጥሙ - ስለጎርፍ ያወራል፡፡ ጎርፍ ውሃ ነው፡፡ ግን ግራና ቀኝ ከመልካው ጋር እየተጋጨ  ሲፈስስ፣ ድምፁ ግን ይጮሃል፡፡ ያቅራራል፡፡ ድምፁ ደልቃቃ ቢመስልም፣ ኑሮው የሥቃይ ደወል ነው ይላል፣ እለት ድንጋይ በጥፊ ያጮለዋል፡፡ ህይወቱ የእንባ፣ጀርባው የእንባ አንቀልባ ነው፤ ዜማው ግን የሆታ መስሎ ያታልላል! … ይህ በጣም ብዙ መልክ አለው፡፡ ብዙ ያሣስባል፡፡ ትኩረቱም ውሃ አይደለም፡፡ ውስጠ ወይራ ካደረግነው ሺህ የህይወት መልክ፣ሺህ ቦታ የሚበርሩ ሺህ ክንፎች አሉት፡ ይህ ደግሞ ከገጣሚው ስሜት፣ የህይወት ገጠመኝና ቁርኝት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ “Poetry presents the emotions of the poet as they are aroused by some scene of beauty, some experiences, some attachment” እንዲሉ፡፡ይህ ሃሳብ እንዴትና በምን ሁኔታ እንደመጣ ራሱ ገጣሚው ያውቃል፡፡ ሮበርት ሂሊየር ግን ስለ ግጥም ውልደት እንዲህ ጽፈዋል፡- ‹‹እያንዳንዱ ግጥም የሚወለድበት የራሱ መንገድ አለው፤ አንዳንዱ በረዥም ምጥ፣ሌላው በፈጣን ሁኔታ ያፈተልካል፡፡
ወንድዬ ዓሊ “ወፌ ቆመች” በሚል መጽሃፉ ስለ ስንኞች ምጥ እንዲህ ብሎ ነበር፡-
ከዚህ ጎን -እዚያ ጎን…ድረሱን መሰበቅ፣
ውስጠ-ውጭ-ፍልቀቃ…ከሩህ መተናነቅ፣
እንዲህ ነው ምስጢሩ፣
በስንኝ ሲሰክሩ፡፡
ግጥሞች አንዳንዴ ከራሳችን አዙሪቶች፣ ከማህበረሰባችን ሳሎኖች,ኧ ከሰፈራችን ሥነ ቃሎች ይነሳሉ፣ የራሳችንን ጉዳይ ያሾራሉ፡፡ “የኔ ቢጤ ሰማይ”ም ከዚህ የጥበብ ክብ አይወጣም፡፡ ለምሳሌ
‹‹ጓደኛ መስታወት ነው›› የሚለውን እንዲህ ተጠቅሞበታል፡-
ጓድ መስታወት ነው ራስ መታዘቢያ
… ጉድፍን ነጋሪ
ጓድ መስታወት ነው ቶሎም ተሰባሪ፡፡
አንድ - አንድ መስታወት ጓደኛ ክፋቱ
ከእጅ ነጥቆ ወድቆ …
… ከተሰባበረ
ዞሮ መዋጋቱ፡፡
ይህ አጭር ግጥም ጓደኛ ዋልታ ነው፣ ማገር ነው እያለን ነው፤ ግን በዚያ አይዘልቅም ቶሎ ይሰበራል ይላል። እንደ ተጨባበጡ፣ በትኩስ ከንፈር እንደተሳሳሙ፣ በሳቅ ፍም እንደተፍነከነኩ አይዘልቁም፡፡ ይልቅስ ይሰባበራሉ፤ ይበታተናሉ፤ምስላቸው ይፈርሳል-ቃላቸው ይከሳል፡፡ በአንዳች ነገር እንዳልነበር ይሆናል፡፡ ወይ እርሱ ሲያገኝ፣ … አሊያም አንተ ስታጣ፣ እርሱ የለም፡፡ … ሣቁ አድማስ ይርቃል፡፡ … ከጓደኛም ደግ የባሰበት አለ፡፡ መፈራረሱ ብቻ ሳይሆን ዘልቆ ስሜትህን ይወጋል፣ ልብህን ያቆስልሃል ነው-ግጥሙ፡፡ በዝርው ቢሆን እንዲህ አይደንቅም!… እንዲህ አይጥምም! … ግጥም ግን ስባቱ፣ ዜማና ስዕሉ ነው፡፡ ለነገሩ ሌሪኮች ስዕላቸው ደማቅ አይደለም፡፡ ዜማና ምታቸው ግን ከተሳካ፣ስሜታቸው ከጠለቀ በቃ! የግጥም ተመራማሪው ብርሃኑ ገበየሁ እንደሚለው፤ ‹‹ሌሪክ ግጥሞች እጅጉን ሙዚቃዊ፣እጅጉን ዜማዊ ናቸው፡፡››
“ብዕረኛ ቀበሮ” በሚል ርዕስ የተፃፈው ግጥም የምትጭረው መገረም፣ ልብ ውስጥ የምትቆሰቁሰው እሳት አላት፡፡ ሰው ውስጥ ገጠመኝ ጀንበር ያቦካው እርሾ፣የቀን ቁጥር የቀረጸው መልክ፣የጋገረው፣ ትዝታ አለ፡፡ ሀዘን  ወይም ደስታ! … ያንን ብዕር ታነፈርቃለች … ርቃኑን ትገልባለች፡፡
… ቀበሮ በዝርው፣ ቀበሮ በግጥም
“ፍቅር ህብስት ነው፤ ምን ያደርጋል ቅልጥም?”
እያለች ሰበከች …
ግን ሰላም አልታየም!
ፍቅር አልታየም!
ለውጥ አልተገበየም … ጽሁፎቿ መና
የብዕሯ ቀለም የበግ ደም ነውና፡፡
ያስደምማል ብዕር የቀበሮውን  አውሬነት አይቀይረውም፣ የደግነቱ ዳር፣ የውበቱ ጫፍ መድረሻ የበግ ደም ነው፡፡ የቅኖች እንባ ነው፡፡ መርዙን ያልነቀለ፣ ጥርሶቹ ደም የተነከሩ ጨካኝ፣ሳቆቹ መቃብር የሚያንቀጠቅጡ፣…ጋኔን የሚጠቅሱ ናቸው፡፡ በምንም መለኪያ፣ ቅዱስ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለዚህ የቀበሮ ባህታዊ ትንታኔ የትም አያደርስ፡፡ ይህ ደግሞ በብዙ የኑሯችን ፈርጆች የዕለት ገጠመኞቻችን ሃዲድ … የነፍሳችን ትዝብቶች የተጋገረ አነባበሮና ክምር ነው፡፡ ዛሬ ዛሬ ደግ ዘመኑና እኛ ወደ ባሰ ቀበሮነት ገብተናል፡፡ የለየልን ቀበሮ ብንሆን ችግር ባልኖረው! … ግን በጎቹን ገድለን በደማቸው የራሳችንን ታሪክና ገድል እንጽፋለን፡፡ መልካም እረኛ መስለን፣ በመንጋው ደም እንቀኛለን፤በቁርበቱ እንጠበባለን፡፡
መስፍን በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ የጻፋቸው ግጥሞች ሲታዩ ባንድ ምጣድ የተጋገሩ፣እልፍ ዓይን ያላቸው ናቸው፡፡ ችክ ያሉና ፈጣጣ አይደሉም፡፡ ግጥሞቹ ውስጥ የሚፈስሰው እንባ እንኳ ከውስጥ ብዙ ታሪክና ትዝታ፣ ብዙ ሃውልት አለው፡፡
የስሜት ጥላ ያጠላባቸው፣ የሳቅ ብርሃን ያሸረጡ፣ የእንባ ጠብታ ያዘሉ ሊሆኑ ይችላሉ ሌሪኮች፡፡ ሀሳብ ለመልቀም፣ … ጎንበስ ቀና ብለው አያምጡም፣ ብዙ ለታሪኮች ለመልክዐ ምድር አይባትሉም! … በወጥ ጣል እንደሚደረግ ቅመም፣ ብዙ ያጣፍጣሉ! …
የመስፍን ወንድ ወሰንም በ“የኔ ቢጤ ሰማዩ” ያደረገው ይህንኑ ነው፡፡ቃላቱ ኮስማናና መናኛ አይደሉም፤ልብ የሚያስደነግጡ ገለጻዎች አሉት‹‹ቃላትን ማሽኮርመም›› የሚለው ዓይነት፡፡ ረጃጂሞቹ ግጥሞች ሽግግራቸው አንካሳ ዔደሉም ከነሙሉ አቅማቸው ነው ማዶ የሚገኙት፡፡ ዶቃዎቻቸው ያምራሉ፣ ቃጭሎ ቻቸው ነፍስ ያስደንሳሉ፡፡ ብዙዎቹን ጥፍራቸውን ከርክሞ፣ ልብ እንዳይቧጭሩ በዜማ አላልቷቸዋል፡፡ ስኳር ነስንሶባቸዋል፣ ለሞገስ የሚሆን አበባ ደረታቸው ላይ ሰክተዋል፡፡
አንዳንድ ቦታ ዘ - አርጌ ግጥሞችም አሉት፡፡ ለምሳሌ የ “አሮጌው ባልሽ ዘፈን” ዓይነት! … የመጨረሻው ዓረፍተ ስንኝ - እንደዚያ ሊታይ ይችላል፡፡
አግብተሻል አሉ የናጠጠ ሀብታም
… ባለብዙ ዝና፣
ባለብዙ ካዝና፣
ብር የሚተነፍስ “ዶላር” የሚሸና!
እኔ ግን ደሃ ነኝ ..
አብረሽኝ ብትውዪ አብሬሽ ባመሽም
እንደ አዲሱ ባልሽ አበል አልከፍልሽም!
ግን … እወድሻለሁ፡፡
የተንጠራራ ፍቅር፣ ተራራ ላይ የተቀለሰ ህልም ነው። የማይቧጠጥበት የወጣ ተስፋ! … ግን ትዝታ ሆኖ የቀረ የማይቆፈር ዓለት ዓይነት! … እርሷ ሄዳለች፤ ትዝታዋ መጥቷል፡፡ ትዝታ መምጣቱን በር ማንኳኳቱን የሚያሳዩ  ስንኞች እንዲህ ይላሉ፡-
ስሚ እንጂ
አንቺ ስትሄጂ ….
ስበበኛው ልቤ ህመሙ አገረሸ
አረቄ እየጠጣሁ እያሰብኩሽ መሸ
ቢሆንም ያለፈ ነገር ነው፡፡ በአረቄ ማወራረድ ማውጣት ማውረድ ግን ይቻላል፡፡ ትዝታ ሀብት ነው። ግጥም ለወርድወርዝ ጠንካራ ስሜት ነው እንዲሉ ይህ ግጥም፣ ብዙ ልቦች ውስጥ፣ በተለይ በዚህ ገንዳ ውስጥ ላሉ፣ የሚፈጥረው ስሜት ቀላል አይደለም!! … የገጣሚም ዕጣ ፈንታ ይህ ነው፡፡ በሰዎች ጫማ ቆሞ፣ ህመሙንና ፍስሀውን መጋራትና በሌሎች ልብ መዝራት፡፡
ስለ ግጥምም መስፍን ፅፏል፡፡ “ቀን መሸኛ ቅፅ” በሚል ርዕስ፡፡ ከጅማሬው ጥቂት ስንኞች እንመልከት።  
ግጥም እንፅፍ ነበር - መልከኛ መልከኛ
ከዚያ ደግ ዘመን የተባረክን እኛ
ዛሬ ዘመን ከፍቶ ውቃቢ ተገፈን
ቅኔ መዝረፍ ቀርቶ ቀን መርገም ተረፈን፡፡
እዩት ሕዝቡ መሃል … ቅኔ ያጣ ጆሮ … ግጥም የጠማው አፍ፤
በእኛም አትፍረዱ! … እኛ ምን እንጻፍ?
ከላይ ባየናቸው ስንኞች ቅኔ ለምን ጠፋ? … ውበት ለምን ነጠፈ ስንል፣ ገጣሚው ወረድ ብሎ፣ ሰቆቃውን ይነግረናል፣ መፀየፉን ያጋራናል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ…
አንደ’ዜ እንዲህ ሆነ …
የልጅነትን ወግ
የልጅነትን ጣም በግጥም ልንቀምም
ፊደል ስናባብል ቃል ስናሽኮረምም፣
ምን እንሰማለን?
“የአፍሪካ ሕፃናት ገና ንፍጣቸውን በወጉ ያልጣሉ
ነፍጥ አንጠለጠሉ!”
እንግዲህ ስለዚህ ምን ይፃፋል? … ባይሆን እንጉርጉሮ፣ ካልሆነ ሙሾ ማውረድ እንጂ! .. ጡጦ በሚጠቡበት ዕድሜ - አፈሙዝ እየጠቡ ያደጉ ልጆች ሰው ሆነው፣ … ለሰው መኖርን ከየት ያመጡታል? … ለዚህ ነው ገጣሚው መስፍን እንዲህ የሚለን ፡-
ዋ!
የዛሬ ልጅነት ማር ሲሉት ግራዋ፡፡
ብለን ከማላዘን፣ ከመቆዘም በቀር
ትንኝ ታህል ስንኝ አልቋጠርንም ነበር… እያለ ይቀጥላል፡፡
“የኔ ቢጤ ሰማይ” አጠር ያሉና ዘለግ ያሉ ግጥሞችንም በጥሩ ዜማና ውበት ይዛለች። ሃሳቦችዋም ላቅ ያሉና፣ ለፈተፈታቸው ብዙ የሚያጠግቡ ናቸው፡፡
መጽሐፉ በ2007 ዓ.ም የመጀመሪያ እትም ታትሞ፣ በ2008 ዓ.ም ድጋሚ ሲታተምም እጄ አልገባም ነበር። ሳላገኘው አለመቅረቱ ደግሞ የጥሩ ዕድል ያህል የሚቆጠር ነው፡፡ ወጣቱ ገጣሚ በዓይን አውጣ ዘመን፣ ዓይን አፋር የሆነ ይመስለኛል፡፡ መሰላሉ ላይ ከፍ ካለ ቦታ የጀመረና የሚፍለቀለቅ ተሰጥኦ ያለው ግን አደባባይን የሚሸሽ፡፡ እንዲያ ባይሆን ተደብቆ መቅረት ያለበት አይደለማ!!
ችግሮቹ እንደ ጀማሪ ብዙ ያፈጠጡና ጉልህ አይደሉም -ግን በዚህ አቅም ላይ ንባብ ይጨመርበት።… ንባብ - ንባብ - ንባብ! 

Read 4301 times