Saturday, 19 March 2016 11:24

የ“ከአሜን ባሻገር” ---- ጥቂት ውሸቶች?!

Written by  ዶኖ ኢበሮ
Rate this item
(17 votes)

      የበዕውቀቱ ስዩምን “ከአሜን ባሻገር” የመጀመሪያ እትም ለማግኘት ባለመቻሌ ሁለተኛው እስኪታተም በከፍተኛ ጉጉት ስጠባበቅ ቆየሁኝ፡፡ ስለ መጽሐፉ የተሰነዘሩ ሙገሳዎች (ለምሳሌ አዲስ አድማስ ጥር 14 እና የካቲት 5 ቀን 2008 እትሞች) ጉጉቴን ጨመሩት። ከብዙ ያልተሳኩ የመጽሐፍት በረንዳ ጉብኝቶች በኋላ መጽሐፉ የካቲት አጋማሽ 2008 ከእጄ ገባች፡፡
ስለ ራስ ጎበና የተጻፈውን የጎበና ቅኝት የተሰኘውን የመጽሐፉን ክፍል እያነበብኩ ሳለ ከሚከተለው አንቀጽ ጋር ተፋጠጥኩ፡፡ እንዲህ ይላል፡-
“በከፋ አንድ ሰው በጥንቁልና ከተወነጀለ ከነቤተሰቡ ይቃጠል ነበር፡፡ የከፋው ንጉስ ምግቡን በእጁ ቆርሶ መብላትን እንደ ውርደት ስለሚቆጥረው አጉራሽ ሎሌ ነበረው፡፡ አጉራሹ ባርያ ንጉሡን ከማጉረስ ሌላ የሕይወት ተልዕኮ ስላልነበረው፣ ንጉሡን የሚያጎርስበት እጁን በከረጢት ጠቅልሎ መኖር ነበረበት፡፡ በንጉሡ ዓይን ይህ ሎሌ ሰው ሳይሆን ተንቀሳቃሽ ማንካ ነበር፡፡ ስለዚህ በኒያ ግዛቶች ሲኖሩ የነበሩ ህዝቦች ነፃነታቸውንና ሰላማቸውን በጎበና ምኒልክ እንደተቀሙ ሊቆጠር አይገባም፡፡ ሲጀመር ከሰላምና ከነፃነት ጋራ መች ይተዋወቁና፡፡”
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ከላይ በሰፈረው አንቀጽ ላይ የተቀመጡት የበዕውቀቱ ውሸቶችና ዘለፋዎች ላይ ቅሬታዬን ለመግለጽና ስህተቶቹን የማውቀዉን ያህል ለማሳየት ነው፡፡ መጽሐፉን የሚያነቡ ወገኖቼንም ከተዛባ አሉታዊ አመለካከት በመከላከልና በመመለስ የበኩሌን ለመወጣት ነዉ፡፡ እንደ ካፋ ብሔር ተወላጅነቴም (ትክክለኛው አጠራር ካፋ እንጂ ከፋ አይደለም) ሆነ ኢትዮጵያዊነቴ በዝምታ ባልፈው የህሊና ወቀሳው ዘወትር አይለቀኝም፡፡
የጎበና ቅኝት ጎበናን ለማወደስ የተጻፈ ከሆነ፣ ከላይ የተቀመጠው አንቀጽ አላማውን የሳተ ለመሆኑ አመዛዛኝ አንባቢ የሚገነዘበው ሀቅ ነዉ፡፡ አንባቢ ሆይ፤ ይህ አንቀጽ የጎበናን ታላቅነት ምን ያህል ያሳያል? ለእኔ በካፋና በሌሎች የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ላይ የተሰነዘረ በውሸት የታጀበ ስድብ ነዉ፡፡ ጎበናን ለማወደስ የፈፀማቸውን መልካም ተግባራትና ጀግንነቱን ማሳየት ይበቃል፡፡ በነገራችን ላይ ከላይ የተቀመጠው አንቀፅ ሙሉ በሙሉ ማስረጃ ያልተጠቀሰለት መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ በዕውቀቱ ስዩም፤ በካፋ ንጉስና ህዝብ ላይ ያቀረባቸው ውንጀላዎች ከተዛባ አስተሳሰቡና ከአላጋጭነቱ የመነጩ ስድቦችና ውሸቶች ናቸዉ፡፡
በከፋ አንድ ሰው በጥንቁልና ከተወነጀለ ከነቤተሰቡ ይቃጠል ነበር ያለው ማስረጃ ያልጠቀሰለት ውንጀላ ነዉ፡፡ በተቃራኒው በካፋ ግዛተ ዓጼ፣ ቃልቾች ከፍተኛ ከበሬታና ስልጣን ነበራቸው፡፡ ሩስያዊዉ ወታደር አሌክሳንደር ቡላቶቪች፣ በካፋ አረማዊ (ፓጋን) እምነት እንደነበርና ከክርስትና እና አይሁድ እምነቶች ድብልቅ ድርጊቶች ይፈጽሙ እንደነበር ዘግቧል፡፡ የመጨረሻዎቹ ስድስት ነገስታት  እምነት ይህ ነበር፡፡ (ከዚያ በፊት ንጉሡም ሆነ የካፋ መንግስት የክርስትና እምነት ተከታይ ነበር፡፡)  በተጨማሪም እምነታቸውን አጥብቀዉ ሲከተሉ የነበሩ ኦርቶዶክስ ክርስትያኖችና በሚሲዮናዊያን (አባ ማሳያ) የተለወጡ ካቶሊኮችም እንደነበሩ ቡላቶቪች ጽፏል። ሙስሊሞችም ሆኑ ዐረቦችም ነበሩ፡፡ ጥቂትም ቢሆኑ (ጥንታዊውን የባሃ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያንም ጨምሮ) ጥንታዊ አብያተ ክርስትያናት ነበሩ፡፡ (አሁንም አሉ።) በካፋ አንፃራዊ የእምነት ነፃነት እንደነበረ ከቡላቶቪች መረዳት ይቻላል፡፡
የካፋ ንጉስ ምግቡን ከሰው እጅ መጉረሱ ለበዕውቀቱ እንዴት ከጭፍጨፋና ባርያ ፍንገላ እኩል ኢ-ሰብአዊ ድርጊት ሆኖ እንደታየው ሊገባኝ አልቻለም። ኢትዮጵያዊ እንደመሆናችን አጉራሽ ማለት የፍቅርና አክብሮት መግለጫ ነዉ፡፡ እኔ እንደሚገባኝ ከአንድ ሰው እጅ መጉረስ ላጉራሹ ያለንን ፍቅር፣ እምነትና አክብሮት ያመለክታል፡፡ የካፋው ንጉሥም ቆርሶ መመገብን እንደ ዉርደት ስለሚቆጥር ተብሎ ሊወገዝ አይገባም፡፡ ይህ ስርአት ንጉሱን ራሱን ሊጎዳ የሚችልበት እድል እንዳለ ግልጽ ነዉ፡፡ ነገስታት የገዛ ቤተሰቦቻቸውን እንኩዋን በማያምኑበትና ለስልጣናቸው ሲሉ ወንድም እህት፣ እናት አባት በሚያግዙበትና በሚያጠፉበት ዘመን፣ የካፋው ንጉስ ምግቡን ከሎሌዉ እጅ መጉረሱ ላጉራሹ ያለውን እምነትና ክብር የሚያሳይ፣ የሚገርምና የሚያስደንቅ ስርአት ነዉ፡፡ ምክንያቱም አጉራሹ ታማኝነት የጎደለው ከሆነና ንጉሡን መጉዳት ከፈለገ ምን ሊያደርግ እንደሚችል ግልፅ ነዉ፡፡   
የካፋው ንጉሥ መጋቢ፣ ባርያ ሳይሆን በታማኝነቱ የተመረጠ ሹም ነበር፡፡ ንጉሱ ግብር በሚያበላበት ጊዜ ከታዳሚው ከሚለየው መጋረጃ፣ ከንጉሱ ጋር ገበታ የሚቀመጠው ይህ ሰዉ ብቻ ነበር (ቡላቶቪችም እንዳስቀመጠዉ)፡፡ የንጉሡ መጋቢ ንጉሱን የሚያጎርስበትን እጁን በጨርቅ  የሚሸፍነዉ በዕውቀቱ አጣሞ እንዳቀረበው፣ ሌላ የሕይወት ተልዕኮ ስላልነበረው አይደለም፡፡ ቡላቶቪች እንደጻፈዉ፡-
‘During the time when he was away from his main duties, his right arm was tied in a canvas sack, in order that  this arm, which fed the king, not contract some illness or be bewitched.’  ትርጉሙም፡- ‘ከዋና ግዳጆቹ የተለየ እንደሆነ ንጉሡን የሚያጎርስበትን ቀኝ እጁን ከበሽታና ከክፉ ድግምት (ጥንቆላ) ለመከላከል በጨርቅ ይሸፍን ነበር፡፡’ ይህ የቡላቶቪች ዘገባ በራሱ ግለሰቡ ሌሎች ስራዎች (duties) እንደነበሩት የሚያሳይና የበዕውቀቱን ውሸት የሚያስረዳ ነወ፡፡ ይህ የስራ ድርሻ ከፍተኛ ዋጋ  የነበረዉ መሆኑን ቡላቶቪች ዘግቧል፡፡ ;This post was considered very important in the court hierarchy. This dignitary had to be distinguished for the best moral qualities so as not to in any way harm the king.;  ትርጉሙም፡ ይህ የስራ ድርሻ በንጉሱ / ቤተመንግስቱ በጣም ከፍ ያለ ስልጣን ነበረ፡፡ ሹሙም ንጉሱን በምንም አይነት የማይጎዳ መሆኑ በመልካም ምግባሩ ልቀት የተረጋገጠ ነበረ፡፡
በንጉሡ ዐይን ይህ ሎሌ ሰዉ ሳይሆን ተንቀሳቃሽ ማንካ ነበር ማለቱ የበዕውቀቱ ተሳዳቢነትን ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ ሰው አብሮት ማእድ የሚቀመጥ የሚያከብረው ሰው ነበር እንጂ ንጉሱ እንደ ባርያ ወይም ግኡዝ እቃ የሚያየው አልነበረም፡፡ በዕውቀቱ፤ ንጉሡ ስለ አጉራሹ ይህ አመለካከት ነበረው ለማለት እንዴት ቻለ? ከየትስ አመጣው? ምንጭ ሳይጠቅሱ የራስን አስተሳሰብና የተዛባ ሚዛን በመያዝ መሳደብና ማላገጥ ስለፈለገ ብቻ ይመስለኛል፡፡ ይህን ስርአት ጥፋት ብሎ ከመፈረጅ በፊት የዚህ ስርአት መነሻ ምንድነው፣ ንጉሡ ስለ ግለሰቡ የነበረው አመለካከትስ፣ ሰውየውስ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ክብርና ቦታ ምንድነው፣ ይህ ተግባርስ ሁሌ ነው ወይስ አንዳንዴ ነው የሚፈጸመው፣ ስራውስ በአካልና በስነልቦናው ላይ ያስከተለው ጉዳት ነበር ወይ፣ ድርጊቱንስ በፍላጎት ነዉ ወይስ በግድ ነበር የሚፈፅመው፣ የራሱ ቤተሰብና ሕይወትስ ነበረው? የሚሉትንና ሌሎች ጥያቄዎችን መመለስ ያስፈልጋል፡፡ በዕውቀቱ ይህን ሳያደርግ መዛለፉ ከተለመደው  ጨዋነት የተፋታ ለመሆኑ አብይ ማረጋገጫ ነዉ፡፡
ሌላዉ በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ “በኒያ ግዛቶች ሲኖሩ የነበሩ ህዝቦች ነፃነታቸውንና ሰላማቸውን በጎበና ምኒልክ እንደተቀሙ ሊቆጠር አይገባም፡፡ ሲጀመር ከሰላምና ከነፃነት ጋር መች ይተዋወቁና፡፡” ብሎ መፃፉ ነዉ፡፡ ይህ አባባል ፈፅሞ ሀሰት ነዉ፡፡ ላገራችን ህዝቦችም ያለውን ታላቅ ንቀት ያሳያል፡፡ ለመሆኑ ሰላም ምንድነው? ነፃነትስ? በዕውቀቱ አላብራራም፡፡ ሰላም ማለት ከጦርነት፣ ከግጭትና ብጥብጥ ነፃ መሆን ነዉ፡፡ ነፃነትም ሰዎች በምርጫቸውና ፍላጎታቸዉ መኖር ማለት ነዉ፡፡ በተለይ ነፃነት አንፃራዊ ነዉ፡፡ በዕውቀቱ፤ ሲኖሩ የነበሩ ሲል አሁንም ያሉ መሆናቸውን መዘንጋቱን ያሳያል፡፡ ለመሆኑ የተለየ ልማድ የሰላምና ነፃነት መጥፋት ማሳያ ነዉ እንዴ? እንዲያ ከሆነማ ኢትዮጵያውያን በርካታ ልዩ ልማዶች ስላሉን፣ ከሰላምና ነፃነት ጋር አንተዋወቅም ማለት ነዉ፡፡    
የካፋ፣ ጎማ፣ ሸካና ሌሎች የደቡብ ምዕራብ አትዮጵያ ህዝቦች የራሳቸው አስተዳደር፣ ባህል፣ አኗኗር የነበራቸው ሲሆኑ በራሳቸው ሀገር በሰላምና በነፃነት ይኖሩ ነበር፡፡ እንደማንኛዉም መንግስት የራሳቸው ጠንካራና ደካማ ጎኖች ነበራቸው፡፡ በየትኛውም ዘመንና ስርዓት ስህተት አይጠፋም። በአሉባልታና ድርጊቶችን አዛብቶ በማቅረብ ከሰላምና ነፃነት ጋር የማይተዋወቁ ማለት ስህተት ነዉ፡፡
በካፋ ለብዙ ምዕተ ዓመታት  ፀንቶ የኖረ ጠንካራ የንጉስ አስተዳደር ነበር፡፡ ካፋ በ12 ወራፎዎች (ክፍለ ሀገር) ተከፋፍላ ትተዳደር ነበር፡፡ እያንዳንዱም የራሱ አስተዳዳሪ (ራሻ) ነበረው። በወራፎዎችም ስር አካባቢያዊ አስተዳደሮች ነበሩ፡፡ ንጉሱም እለታዊ አስተዳደራዊ ስራዎችን የሚያከናውኑ ሰባት ሹሞች (ሚኪሬቾ) ነበሩት፡፡ ሰባቱ ሚክረቾ ከስድስት ቶሞ (ጎሳዎች/clan) የሚመረጡ ናቸው፡፡ እርሻና እደ-ጥበብም በሰፊዉ ይካሄዱ ነበር፡፡ ካፋ ከፍተኛ የንግድ ማዕከል እንደነበረች በስፋት የሚታወቅ ነው፡፡ ቡና፣ ሰብል፣ ማር፣ ቅመማ ቅመም፣ የእደ-ጥበብ ዉጤቶች፣ የዝሆን ጥርስ ወዘተ የሚገበይባት ነበረች፡፡ እነዚህ እውነታዎች የሰላምና ነፃነት ማሳያ ናቸዉ። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ከሰላምና ነፃነት ጋር የማይተዋወቁ ማለት ያፈጠጠ ውሸት ነው፡፡  በአንጻሩ በወራሪው ሰራዊት ብዙኃን ተገድለዋል፡፡ ዝርፍያና ውድመትም ተካሂዷል፡፡ እጅግ ትልቅ የነበረው የዋና ከተማዉ የአንደራቻ ቤተ መንግስትም በራስ ወ/ጊዮርጊስ ከተያዘ በኋላ በቃጠሎ አውድመውታል። የቦንጋ ቤተ መንግስትም በወራሪው ወድሟል፡ ረሃብና ባርያ ፍንገላ በመስፋፋታቸው ለምና ምቹ የነበረችው ምድር ሰው አልባ ሆነች፡፡ (ይህን ከቡላቶቪች መጽሀፍ ማግኘት ይቻላል፡፡ Alexander Bulatovich: With the Armies of Menelik II Emperor of Ethiopia. Translated by Richard Seltzer)
 የመጨረሻው የካፋ ንጉስ ታቶ ጪኒቶ ጋሊቶ (ጋኪ ሻረቾ) ከ9 ወራት ጦርነት በኋላ ነሐሴ 1897 ተይዞ በአንኮበርና አዲስ አበባ በእስር ሲማቅቅ ቆይቶ በ1919 ህይወቱ አልፏል፡፡ (ተመርዞ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል) ምኒሊክ የካፋን ታሪክ ለማጥፋት የካፋውን ንጉስ ዘውድ ወደ ስዊዘርላድ እስከመላክ ደርሰዋል፡፡ ካፋና ህዝቧ ከዚያ እልቂትና ጉዳት እስካሁን አላገገሙም፡፡ ይህን ነው በዕውቀቱ አንፃራዊ ሰላም ሰፍኖ ነበር የሚለን፡፡ ከግራኝ ወረራ በፊት ከኢትዮጵያ ነገስታት ጋር ግኑኙነት የነበረውና ንግስናው የተከበረለት የካፋው ንጉስ፣ ከዐፄ ምኒልክ የቀረበለት የሰላም ጥሪ ሆነ እውቅና የነበረ አይመስለኝም፡፡ (ከተሳሳትኩ በማስረጃ ልታረም እችላለሁ) ይልቁንም ተደጋጋሚ ወረራ በማካሄድና በላዩ ላይ ሌላ ንጉስ በመሾም በጦርነት ማስገበርን መርጠዋል፡፡ (ራስ ወልደ ጊዮርጊስ የካፋ ንጉስ ተብለው ተሹመው ነበር ወደ ካፋ የዘመቱት፤አፄ ዮሐንስም የጎጃሙን ንጉስ ተክለሐይማኖት በካፋ ላይ ሾመዋል፡፡) በዚህም የምኒልክ አካሄድ ስህተት እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በካፋ ለደረሰው ጥፋትና እልቂትም ምኒሊክ ተጠያቂ ናቸው፡፡
ጎበና በካፋ ተሸንፎ መመለሱ የታወቀ ነዉ፡፡ ራስ ወልደጊዮርጊስም በመጀመሪያ ሙከራቸው ተሸንፈው ወደ ሸዋ ተመልሰዋል፡፡ የካፋ መንግስት የተሸነፈው በራስ ወልደ ጊዮርጊስ በተመራውና ራስ ተሰማ፣ ደጃዝማች ደምሰው እና የጅማዉ አባ ጅፋር በተሳተፉበት ጦርነት ነዉ፡፡ ያኔ ራስ ጎበና በህይወት አልነበረም፡፡ ስለሆነም በዕውቀቱ ታሪክ ሳያውቅ ስለ ታሪክ መፃፉን አንባቢው ሊረዳ ይገባል፡፡ ሌሎች ግድፈቶችም አሉ፡፡ መዘርዘሩ የዚህ ፅሁፍ አላማ ስላልሆነ ትቸዋለሁ፡፡
በዕውቀቱ፤ አፈወርቅ ገብረየሱስንና ገብረሕይወት ባይከዳኝን ስለ ሌላው ህዝብ በጣም ግልብ እውቀት ያላቸው ብሎ ይዘልፋል፡፡ የራሱ ዘለፋዎችና ውሸቶች “ከጥልቅ እውቀቱ” የመነጩ መሆናቸው ነው? በዕውቀቱ መረጃ በእጅ ጫፍ (A click away) በሆነበት በዚህ ዘመን፣ ለዚያውም አሜሪካ ቁጭ ብሎ (ሌላዉ ቢቀር ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘዉ ኮንግረስ ላይብረሪ የአለማችን ትልቁ ቤተ መጻህፍት ነዉ)  ይህን የዘለፋና ውሸት  ስብስብ መፃፉ አሳፋሪ  ተግባር ነው፡፡ በአንድ አዳራሽ የተነገሩ ብሔር ተኮር ቀልዶችን የወቀሰው በዕውቀቱ፣ የርሱ በጽሁፍ የተቀመጡ ስድቦችስ ምን ይባሉ ይሆን? የራስ ዐይን ውስጥ ያለ ግንድ ሳያዩ ከሌላ አይን ጉድፍ ማውጣት ይሏል ይህ ነዉ፡፡ ስለ ታሪክ ለመፃፍ ሰፊ የታሪክ ዕውቀት፣ ጥናትና ምርምር ይጠይቃል፡፡ የታሪክ አፃፃፍም የራሱ ስርአት አለው፡፡ በሀገራችን ያልተፃፈ ታሪክ የበዛ እንደመሆኑ በርካታ ሰዎችን ማነጋገር ያስፈልጋል፡፡ ከሁሉም በላይ ሚዛናዊነትንና አክብሮትን ይጠይቃል፡፡ በዕውቀቱ ስዩም የፈጸመው ድርጊት ግን በተቃራኒው ከስነምግባር ውጭ የሆነና በጥብቅ ሊወገዝ የሚገባው ነዉ፡፡ በዕውቀቱ በዚህ መጽሐፉ ከባድ ጥፋት እንደፈጸመ ለመጠቆም ሞክሬያለሁኝ፡፡ በኔ እምነት ሀሳብን የመግለፅ ነፃነት፣ ስድብንና ውሸትን በሌሎች ላይ መሰንዘርን አይጨምርም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በቂ የሆነ ምላሽ ሰጥቻለሁ ብዬም መሉ በሙሉ አልተማመንም፡፡ ስለሆነም ሌሎች በተለይም የታሪክና የህግ ምሑራን አስተያየት ቢሰጡበት መልካም ነው እላለሁ፡፡           


Read 9513 times