Saturday, 12 March 2016 11:14

“ወርቅ ቢጠፋ ሚዛን አይጥፋ”

Written by  በቀለ መኮንን
Rate this item
(1 Vote)

        ማዕረግ፥ ከመጠሪያ (ከተጸውዖ) ስም  በፊት  እየገባ  የአንድን  ሰው  የሙያ፡ የዕውቀት፡  የሃላፊነት ወይም  የሹመት  ደረጃንና ድርሻን የሚያመለክት  ቃል ወይም ሀረግ ነው። ማዕረግ፡ በተለያዩ ሀገራት  የተለያየ  አጠቃቀም ቢኖረውም  እንኳ  ሁሉንም  ማዕረጎች የሚያመሳስላቸው የጋራ ምንነት   ግን ክብደትን በቁጥር እንደሚተረጉም ሚዛን  ማዕረግነቱን  የፈጠረ  ተመጣጣኝ የድርጊት ምንዛሪ  ከጀርባቸው መኖሩ ነው።
በኔ ዕድሜ  በውትድርና፡ በመምህርነት፡ በሃይማኖት፡ በሌላም ልዩ ልዩ ሙያ  በሹመትና ሃላፊነት መስክ  በየተዋረዱ  ደረጃን የሚያመለክቱን  ማዕረጎች  እንደነበሩ አውቃለሁ።
ለምሳሌ በቅርብ እማኝነት ጠንቅቄ በማውቀው አካባቢ፥ የውትድርና ማዕረግ  ከሌሎች  ሀገሮች  ተመሳሳይ ማዕረጎች ስያሜና አሰያየም ጋር  የሚመሳሰል ነው። ከነዚያ ሁሉ ማዕረጎች አንዱ ቢጠራ እንኳ ወዲያው  የማዕረጉ ተመጣጣኝ  ምንዛሬ የዕውቀት ደረጃው፡ የስራ ድርሻውና ክፍሉ፡  የአገልግሎት ጊዜው፡ የጀብዱው  አይነትና ክብደቱ (ጀብዱ ከተሰራ) ያለ አስተርጓሚ ማንም  በቀላሉና  ወዲያው  ይለየው እንደነበር አስታውሳለሁ። ሰሚው ብቻ ሳይሆን ጠሪውም ይህንኑ ተመጣጣኝ ምንዛሬ ታሳቢ አድርጎ ነበር  ከተገቢው ጥንቃቄና አክብሮት ጋር ሁሉንም ማዕረግ የሚያነሳው።
 በዚህ ጥብቅ ሚዛን የደመወዝ  ጣሪያ ብቻ ሳይሆን  በማህበረሰቡ ውስጥ ያለው የመከበርና የመፈራት  ጣሪያም  አብሮ  ይወሰን ነበር።
ምሳሌነቱ ለሌሎች ዲሲፕሊኖች  የሚተርፈው የዚህ ጥንቁቅና  ቁጥብ ሚዛን  ባልተለመደ አኳሁዋን  ሲሰበር  ያየሁት በሰባዎቹ  ዓመተምህረቶች ውስጥ ነበር። በዚያን ጊዜ የወታደር ማዕረግ ስሙና ከጀርባው ያለው ምንዛሬ  ተለያይተው  እንዲነበቡ   ሆነ።  በወቅቱ አንድ ወታደር  ከደረሰበት  የመቶ እልቅና ማዕረግ ደረጃ ሶስት አራት  እርከን  ዘሎ  ባልዋለበት /ባልኖረበት/ በሌለበት  ክብርና ሞገስ ከፍ ያለውን   ማዕረግ እንዲያገኝ  በጉልበት ተደነገገ። ብዙዎቻችንም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ  ክብደት በሌለበት የክብደት ንባብ  ማንበቡን  ተለማመድን።  ምንም ዓይነት የክብደት  ንባብ  ምንም ክብደት በሌለበት ሊጻፍ መቻሉ  ብርቅ መሆኑ እየቀረ መጣ። እያደር  እንዲያውም ከዚያ በቀለለ መንገድ ከአቶ ወደ   ጄኔራል ወይም የተገላቢጦሽ ቁልቁል  ከጄኔራል  ወደ አቶ  ባንድ ጀምበር  መውረድና መውጣት  እንደ አናጺ መሰላል ቀላል ሆነ። ይህም  ስለማዕረግ ደረጃን  የየደረጃው የክብርና የጥቅም፣ የዕድሜና የተግባር ምንዛሬ  ያለንን ግንዛቤ ከመሰረቱ አሳክሮታል። ቀድሞ ስለማውቀው  የውትድርና ታሪክ  እንደምሳሌ አነሳሁ እንጂ  የክብደትና  የንባቡ መሳከር  ምሁራኑና ባለሙያዎቹ ዘንድም  ብሶበታል።
እዚህ ሰፈርማ  ከናካቴው  በሙያ መጠሪያና በደረጃ መስፈሪያ መካከል ያለው ልዩነት ሳይቀር መልኩን እያጣ መጥቷዋል። ለምሳሌ እንደነ አሰልጣኝነት፡ እንደነ መሐንዲስነት እና ሌሎችም የሙያ ስሞች  በቀጥታ ራሳቸው ማዕረግ  ሆነውበብዙሃን መገናኛ ሳይቀር መስማቱን ለምደነዋል። ይህ ምስቅልቅል የሚጠቁመን፡  ማዕረግ  የምንዛሬ ክብደቱ ብቻ ሳይሆን  ምንነቱ ራሱ  ከመሰረቱ ስለመናጋቱ   ይመስለኛል።
በአካዳሚክ መድረኮች ለምሳሌ ዶክተር የሚለው ማዕረግ  ከመጣበት የባህር ማዶ ምንጩ  ያለው  የአጠቃቀም ስርዓትና  እዚህ በኛ ዘመን እየሰራንበት ያለው ዘይቤ የምስቅልቅሉ ሌላ ገጽ ሊሆን ይችላል።  ሲሆን ሲሆን ወይ እንደሰለጠነው ወገን ከምንጩ በተሰራበት ስርዓት መጠቀም አልሆነልንም። አለያም እንደ አባቶቻችን ወደ አገርኛው ዘይቤ   አላምደን የራሳችን ማድረጉም አልተሳካልንም። “ዶክተር “መችና በየትኛው ሙያ ውስጥ በምን  ሁናቴ  ሰለሚጠራበት ስርዓት በራሱ በትምህርት ትቋማት ውስጥ እንኳ  ወጥ አሰራር አይታይም።  ይሁን እንጂ ይህ መዘበራረቅ  ቢበዛ ባንድ ሰሞን የማስተካከያ ትዕዛዝ ሊታረም ይችላል። የሚያስፈራው ስብራት ሌላ ነው። ባሁኑ ወቅት ወደ ዱክትርና  የሚያደርሰው የፈተና መንገድ የውጣውረዱ አይነትና ደረጃው ብዙ ያልበቁ ጭንቅላቶችን  እንደዋዛ አሾልኮ   የሚያሳልፍ ቀዳዳ  ከጊዜ ወደ ጊዜ እየበዛበት  መጥቷል።  በዚህም ምክንያት አሁን አሁን  የዱክትርና ስሙና  የክብደቱ መጠን  ሲመሳከር  የነበረውን ክብርና ሞገስ  አልመጥን የሚልበት አጋጣሚ ጥቂት ስላልሆነ  አልፎ አልፎ “…..ታዲያ  ብርቅ ነው እንዴ  እገሌምኮ ዶክተር ነው ….“ መባል ተጀምሩዋል። በርግጥ  ዶክተር ሁሉ  ዱሮም  ቢሆን መደዳውን  ሊቅ አልነበረምና በጣም አልፎ አልፎ ዶክተር የሆነ  ዋዘኛ ላይጠፋ ይችላል። ይህ ተፈጥሮአዊ እንከን ነው። ነገር ግን መደዳውን  ብዙ ብዙ ዱክትርና  በዕውቀት አደባባይ  ተጋልጦ  ከሚዛን በታች  ሲገኝ  በማዕረግ ስምና በክብደት ምንዛሬው መካከል ያለውን  ሰፊ የመጣረስ ችግር   አሳምሮ  ያሳየናል። የዚህ መዘዝ  ደግሞ  የት  ሊደርስ እንደሚችል  መገመት አይከብድም። ወይ የለየልን ባለጸጋ ሆነን እንኳ እንደነ ቶዮታ የጎደለ ለማስተካከል  ካለም ዙሪያ  ሰባራ ማዕረግ የተሸከምክ ወደ ፋብሪካ ተመለስ አንል  ነገር።
ባሁኑ ወቅት በከፍተኛ ትምህርት ተከታታዮች ዘንድ የሰፈነ  እያዩ ለመቀበል የሚያዳግት ክፉ ተስቦ  በመስፈን ላይ ነው። የከፍተኛ ትምህርት ስል በተለይ የድህረ-ምረቃ ትምህርትን ማለቴ ነው። በዚህ መስክ  ለሁለተኛና ለሶስተኛ ዲግሪ  የሚማሩ ተማሪዎች በአንጻራዊነት   ምራቃቸውን ዋጥ ያደረጉ  ናቸው። የድህረ-ምረቃ ትምህርት ባንድ ወይም ከዚያ በላይ በሆነ  መስክ  ቀድማ የተገለጠችን የእውቀት ጭላንጭል እልህ  አስጨራሽ በሆነ የምርምር  ጉዞ በጥልቅና ጠባብ ጎዳና አልፎ ወደ ደማቅ  የብርሃን ከፍታ የሚያሸጋግሩበት  የፍለጋ፡ ጉዞ ነው። ሆኖም ይህ  ጉዞ  እያደር፡ ለላቀ ብርሃን   ፍለጋ የሚደረግ  ጉዞ  ከመሆን ይልቅወደ ላቀ ማዕረግ  የሚያደርሱ  የነጥብ /የማርክ  ሰረገላዎች  ፍለጋ የሚደረግ  ግብግብ  ወደ መሆን በማዘንበል ላይ ነው። በዚህ የማርክ  ልመና፡ ጭቅጭቅና   ክስ  በኩል አቋርጠው  እዚያ የፈረደበት  የዱክትርና ማማ ላይ የደረሱ፡ ለመድረስም እየተዋደቁ ያሉ ቁጥራቸው  ከሚገመተው በላይ የበዛ ነው። ይህ የቆረጣ መንገድም እያደር ተመራጭ ዘዴ እየሆነ መምጣቱን በመራጩ ብዛት እንመለከታለን። በማዕረግ ስሞች ውስጥ የተደበቁ  ክብደት አልባ ሊቃውንት  በአካዴሚኩ መድረክ ላይ እንደዋዛ ሁሌም ለትዝብት  መጋለጡ ከመለመድም (እነሱም ከመልመዳቸው) አልፎ  የዕለት ተለት ተራ ልማድ እየሆናቸው ነው። ከሁሉ ከሁሉ ግን የነዚህ  ወገኖች  የማዕረግ ሰቀቀን  ይፋ የሚወጣው  በስልክ ወይም  ሌላ ያደባባይ ባልሆነ ኢመደበኛንግግር ወቅት ነው። በንግግራቸው መጀመሪያ፡ (ምንም እንኳ የሚያናግሩት ሰው የቅርብ ወዳጃቸውና ዘመዳቸውም ቢሆን)፤ እገሌ ነኝ  ወይም እገሌ እባላለሁ ለማለት ስማቸውን በፍጹም  ያለ ዶክተር  ሊጠሩት አይደፍሩም።
እንግዲህ ከላይ ጀምሮ የተመለከትነው   ማዕረግን የሚያስገኙ ተመጣጣኝ የድርጊት  መስዋዕትነቶች ወይም ምንዛሪዎች ምንኛ እየተዛቡ መምጣታቸውንና በዚያም የተነሳ ማዕረግ ሁሉ (የምሩም የሀሰቱም) ጥርጣሬ ላይ እየወደቀ  የመሄዱን መዘዝ  ነው።
ለምሳሌ እውቀት ተመንዝሮ ሊያስገኝ የሚገባውን  ክብርና ዳቦ በማያስገኝበት  ስፍራ፡ ወይም   ጉልበትና ድፍረት ብቻ እውቀትን ተክተው  በሚሰሩበት ቦታ        
“ …….የኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ ወሰደሽ አስተማሪ…..”  ተብሎ እንዲዘፈን አይጠበቅም። ምክንያቱም  እውቀት ከፍ ባላለበት  ስፍራ መምህርነት ሊከበር ስለማይችል ነው። በርግጥ ይህ ያንድ መምህር ችግር የፈጠረው የማዕረግ መቅለል ሳይሆን  በጅምላ ስርዓት ውስጥ  የተፈጠረ  ማህበረሰባዊ  ድህቀት ሊባል ይችላል። እዚህ ላይ ማሳየት የፈለግሁት፡ ማዕረግ ያለ ተመጣጣኝ  ምንዛሬ  የቅሌት መዘዝ ያለው ደረቅ ቼክ አይነት መሆኑን  ነው።
ምንም እንኳ የባዕድ እና ሩቅ ቢሆንም ምሳሌነቱን መላ ዓለም  በእማኝነት የሚጠራውን  የኬምብሪጁን  የሒሳብ ክፍለ-ትምህርት ሊቀመንበርነት  እዚህ  ላይ መጥቀስ ይጠቅማል። ይህ የአካዳሚክ  ቦታ በዓለም ከተከበሩና ሞገሳቸው ከተመሰከረ ማዕረጎች መካከል አንዱ ነው። ይህን ክብር ከትውልድ ትውልድ እያሸጋገረ እንደተከበረ ስለክብሩና ሚዛኑም ጥርጣሬ ሳያስገባ ዛሬ ድረስ አቆይቶታል።  ማዕረጉን የማይመጥን  የእውቀት ምንዛሬ ይዞ ደጅ ለሚጠና ሁሉ ደጃፉ  ሁሌም ዝግ እንዲሆን  ከሀገሪትዋ መሪ ጀምሮ መላው የአካዴሚው ማህበረሰብ  ጠብቀው ስላቆዩት  ብቻ ነው ሞገሱን ይዞ  የዘለቀው። እስቲ የዚህን ለመስፈሪያ  የመጠንቀቅ   ምንነት  በጣም በሚገባን ቋንቋ  እናፍታታው።
…በምንወደውና በለመድነው  የሩጫ ውድድር ውስጥ አንድ ሩዋጭ ሮጦ ለማሸነፍ የተመደበለትን ዙር በሚችለው ፍጥነት ጨርሶ ከርቀቱ መጨረሻ ላይ የታሰረውን ክር ቀድሞ መበጠስ ይጠበቅበታል። ይህንን አሟልቶ ዙሩን የጨረሰ ሯጭ ክሩን ሌላ ሰው ቀድሞ ጨርሶ ቢበጥስበት እንኳ በደረጃ ሰንጠረዡ  ዝቅ ይላል እንጂ ውድድሩን ተሳትፎ ዙሩንም ስለመጨረሱ ሊካድ  አይችልም። ነገር ግን ሌላ አንድ  ተወዳዳሪ በውድድሩ እንዲሙዋላ የሚጠበቀውን ዙር ሳይጨርስ  ጥቂት ሲቀረው ደክሞ ማጠናቀቅ ቢሳነው አቋርጦ መውጣት ይኖርበታል። በውድድሩም ታሪክ፣ ያቋረጠ ተወዳዳሪ ተብሎ ይጠቀሳል። ይሁን እንጂ ሩዋጩ የማቋረጡን እውነት አግባብ ባልሆነ መንገድ ለውጦ ዙሩን ጨርሱዋል ለማሰኘት  ሲባል ሩጫው የሚያልቅበትን መስመር አንስቶ ሩዋጩ ደክሞ ወደወደቀበት ጎትቶ  በማምጣት  የጨረሰ ማስመሰል  ከወንጀሎች የከበደ ወንጀል ይሆናል። በማዕረግና በምንዛሬው መካከል እየተፈጸመ ያለው ጥፋትም  ከዚህ ፍጹም የተለየ አይደለም። የሩጫን መደበኛ ርቀት ቀንሶ  በደካማ ሩዋጭ ልክ በማሸማቀቅና የእውቀትን ሚዛን አንሻፎ  ባልተገባ  ማዕረግ  በመመንዘር  መካከል አንዳችም ልዩነት የለም። በአንድ ዝነኛ ያገራችን ምሳሌ ጉዳያችንን እንደምድም። ሕግና  ስርዓት ደርዙን ይዞ በሚጓዝበት ዘመን “ወርቅና ሚዛን” “የተግባርና  የማዕረግ” መናበብ  ምሳሌዎች ነበሩ።  የሚመዘን ክብር  እንኳ ለጊዜው ቢጠፋ ክብርን መስፈሪያ ሚዛን እንዳይጠፋ አጥብቆ ይፈለግ  ነበር። የወርቅን  ክብር ከነሀስ ሚዛን ጋር ማሳከርን  ለማውገዝ  እንዲህ ሲባል ተተርቷል።  “ወርቁ  ቢጠፋ  ሚዛኑ  አይጥፋ!”። የሚዛን መጥፋት ወርቅን አራክሶ ጠጠር  ያደርጋል። የወርቅ መጥፋት ግን  ነሀስና ጠጠርን ወርቅ  አያደርግም። ሚዛን አለና!

Read 2600 times