Saturday, 12 March 2016 11:11

“ባለሰባራ መነፅር”፤ በዕውቀቱ ወይስ ዳዊት?

Written by  ዒዛና ዓብርሃ
Rate this item
(5 votes)

     አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ቃላትን ሰካክተው የሆነ ነገር ማለት ስለሚችሉ ብቻ ቀናነት የጎደለው፣ፍርደ-ገምድል እንዲያም ሲል ከዕውቀት ነፃ የሆነ ጽሁፍ መጻፋቸው ይገርመኛል፣ ያመኛልም፡፡ ስለዚህም እንደው ዝም ከማለት በሚል ይህችን ጽሁፍ አሰናዳኋት፡፡
በቅርቡ ደራሲ በዕውቀቱ ስዩም ባወጣው ከአሜን ባሻገር መፅሀፍ ላይ በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ የካቲት 27 ቀን 2008 ዕትም፣ አስተያየታቸውን ያሰፈሩ ዳዊት ግርማ የተባሉ ጸሀፊ ከእነዚህ እንደ አንዱ ሆነውብኛል፡፡ እኔ በዚህ ፅሁፍ ውስጥ የከአሜን ባሻገርን ባለመብት “ደራሲ” በሚለው ማዕረግ እንድጠራ ይፈቀድልኝ፡፡ ከላይ የጠቀስኳቸው ጸሀፊ፣ ልጅ በዕውቀቱ በሚል ተጠቅመዋል፣ በርግጥ ደራሲውን ለማቃለል ይሁነኝ ብለው የተጠቀሙት ይሁን ወይም ሌላ ዓላማ ይኑረው አላውቅም፤ ይኽንንም በመገመት ራሴን አላደክምም፡፡
ነገር ግን አንድ ጥያቄ ቢጤ ሰንዘር ባደርግስ? ጎበዝ ቢያንስ ሌላውን ለማረም ብዕሩን ያሾለ አንድ ጸሀፊ እራሱ በተመሳሳይ ችግር ተተብትቦ ሲታይ አያሳዝንም ወይ? ይሁንና የዚህ የማዕረግ ነገር መላቅጡ ከጠፋ የሰነባበተ መሰለኝ፡፡ እንዲያው ዝም ብሎ ከማለፍ፣ በእግረ-መንገድ ጫር ማድረጉ መልካም ይመስለኛል። እንዲያው  ምኑንም ምኑንም የጫጫረ ሁሉ ብድግ ብሎ ደራሲ፣ ባለቅኔ፣ ገጣሚ…ምኑንም ምኑንም የለቀለቀ፣ የፈላለጠ  ሁሉ ሰዓሊ፣ ቀራፂ እየተባለ በየመድረኩና በየብዙሃን መገናኛው የሚሰጥ የማዕረግ ድርደራ አደብ ማስገዛት ካልተቻለ የሜሪት ነገር ድራሹ እየጠፋ፣ የቲፎዞ ነገር ደግሞ እየተንሰራፋ መሄዱ አይቀሬ ይመስላል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ወደ ርዕሰ ነገሬ ስገባ በደራሲ በዕውቀቱ አዲስ ስራ ላይ ሂስ አይሉት ዳሰሳ መላቅጡ የጠፋው ነገር ያቀረቡልን ጸሃፊ፤ ደራሲ በዕውቀቱን ምንም እንኳ ልጅ እያሉ ለማሳነስ ቢሞክሩም ስለ ደራሲው የድርሰት ችሎታና አቅም አጠያያቂ አለመሆን ጠንከር አድርገው ሊያስጨብጡን ሞክረዋል፡፡ የእኔ ጥያቄ ደግሞ እዚህ ላይ ይጀምርና አንዴ እያቃለሉ ሌላ ጊዜ ደግሞ እያገዘፉ የሚያሳዩን ደራሲ ዕውን እንዳሉት ችሎታው አጠያያቂ እንዳልሆነ በምን መስፈርት ለክተውት ይሆን? እንደዚህ አይነቱን ደረጃ ምደባ አዲስ አበባ ላይ በሚታተም ጋዜጣ ማወጅስ የማን ስራ ይሆን? ለመሆኑ ዳጎስ ያለ የስነ-ፅሁፍ ትምህርትና ልምድ ያላቸው ምሁራን ባሉበት ከተማ የደረጃውን ነገር ለነእርሱና ለሚሰሩበት ተቋማት ብንተወው  የሚበጅ አይሆንም? አለበለዚያ የግል አድናቆታችንን ተቋማዊ ቅርፅ ሰጥቶ እመኑኝ ማለት ማኅበረሰባችንን አብዝቶ ይጎዳዋል----ነገርዬው የእኩል ቤት እንዳይሆን፣ መማርም ሆነ አለመማር፣ ተግቶ መስራትም ሆነ አለመስራት እኩል ዋጋ የሚያገኙበት ዓይነት። ያለበለዚያ ግን አሁንም ተቋማቱ ምንም አላሉም ተብሎ ግለሰቦች የደረጃ ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ሰጪ ከሆንን አሁንም  ይኽ ሜሪት የሚባል ነገር ገደል ይገባላ። ይህንን ስል ግን የደራሲውን ችሎታ አኔም ለማሳነስ የፈለግሁ እንዳይመስልብኝ። እኔ በግሌም፣ እንዲሁም ከእኔም የተሻሉና ዐዋቂ የሆኑና የምቀርባቸው ምሁራን ጭምር በችሎታው እንደምንደመም መናገር እችላለሁ።
በመሰረቱ የጸሀፊው (ዳዊት) አካሄድ ለምን ሀይማኖት ተነካ፣ ለምን ደራሲው እራሱን ኢ-አማኒ አለ፡፡ ይህንንስ ካለ ለምን የሰውን ሀይማኖት ይነካል? የሚመስል ይዘት አለው፡፡ ስለነ ዓለምአየሁ ቴዎድሮስና የመሳሰሉት ጉዳዮች ላይ የሰነዘረውን ከዳሰሱልን በኋላ የበዕውቀቱ አብዛኛው የተዛባ አስተሳሰብ ከሀይማኖት እንደሚመነጭ ይነግሩናል፡፡ እንዲህ አይነቱ ለሀይማኖት ተቆርቋሪ መሳይነት ከምን እንደሚመጣ ለመገንዘብ አልቻልኩም፡፡ ከተቆረቆሩም ደግሞ ፍሬ ባለው ጉዳይ ላይ እንጂ ትንሹም ትልቁም ነገር ላይ መሆኑ ምንም ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ለምሳሌ “አንድ ፍሬ ቄስ” …ባለው ላይ ይኽንን ያኽል ከመቆጣት ለምን እንደዚህ አይነት አገላለፅ ተጠቀመ ብሎ ለመመርመር መሞከር ይሻላል። ነገሩ ትክክል ነው፣ የቄሱ ቁመትና ውፍረት፣ቅላትና ጥቁረት ሳይሆን ስልጣኑ ገዢ መሆኑን እርሳቸው እንዳሉት በሰባራ መነፅር ሳይሆን በተስተካከለና ፍንትው ባለ መልኩ አሳይቶበታል፣ ከዚህ ውጪ ግን ሃይማኖታዊ ጉዳይ ውስጥ ገብቶ… የግዝት ስልጣን ተገቢነት ላይ፣ ወይም ስልጣነ ክኅነት ላይ ጥያቄ አላነሳም፡፡
ሌላው የፀሀፊው ግድፈት ደግሞ የመሬት ፀሀይን መዞር ላይ ያጠነጥናል፡፡ ደራሲው ስነፅሁፋዊ ፋይዳውን ለማጉላት የተጠቀመውን ዘዴ ሁሉ አንስቶና ከሌላ ትልቅ ጉዳይ ጋር አጋብቶ ፍርድ ለመስጠት መቸኮል ፍርደ ገምድል ያሰኛል፡፡ መቼም ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ፣ አንዳንድ ሰዎች ወደ ድግስ ተጠርተው ሲሄዱ በጠረጴዛው ላይ የተደረደረውን የምግብ ዓይነት ሁሉ መቆለል ያለባቸው የሚመስላቸው አሉ። ደጋሾቹ እንዲያው ለዓይን ደስ እንዲል በሚል መሃል መሃል የሚሰትሩትን ወይም ዲኮሬሽኑን ሁሉ የሚሰበስቡትን ዓይነት ማለቴ ነው፡፡ እዚህ ጋም እንደዚሁ የሆነ ይመስለኛል፣ ዋና ሃሳቡ ላይ ከማተኮር ይልቅ ፅሁፉን ለማዋዛት  የተጠቀማቸውን አገላለፆች ሁሉ እየጠቀሱ ዋና ሀሳቡ በማስመሰል አንባቢን ለመሸወድ ሳይጠቀሙባት አልቀረም፡፡ ከሆነም ደግሞ ትንሽ ስለቤተ ክርስቲያኒቱ የባህረ-ሃሳብ ትምሕርት ማንሳት ይሻል ነበር፡፡ ምክንያቱም በከዋክብት ምግብና፣ በጨረቃና ፀሀይ ዑደት  ላይ ተመስርተው ስለንፋሱ፣ ስለዝናቡ፣ስለሰዓቱና የመሳሰሉት ላይ ጥልቅ ትንታኔ የሚሰጡ ዐዋቂዎች እንዳሉ ስለሚታወቅ፡፡ የዚህ አይነቱ ዕውቀት ባለቤቶች ከአዲያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን በኋላ እምብዛም አልታዩምም ይባላል፡፡ ለማንኛውም ገና’ኮ ብዙ ይቀረናል …ገና ፈረንጅ የሰጠንን የዓለም ካርታና ሉል አሜን ብለን የተቀበልን ሰዎች እንደሆንን ማወቅም አለብን፣ በአሁኑም ዘመን ዓለማችንን በአንድ አቅጣጫ እንዳሳዩን፣ ያንኑ ይዘን አውሮፓን ካናታችን፣ እኛ ከስር አይደለን እንዴ? እንዲያው ሳይንስ አረጋገጠ እንላለን እንጂ ኤሮፕሌኖቻችን ከሚጓዙበት እርቀት በላይ ከፍ ብሎ እውነታውን የሚያስጨብጠን ነገርስ ፈጥረናል እንዴ? ስለዚህ የብዙ ዕውቀት ባለቤቶች ነን ብለን በባዶ ሜዳ የተቋም ወገንተኝነት ከምናሳይ ተቋሟ ያጠራቀመችውን ዳጎስ ያለ ዕውቀት ብንበረብርና ያለውን ነገር በደኽናው መነፅር ብናሳይ ተመራጭ አይሆንም ወይ?
ደራሲ በዕውቀቱ በዚህኛው ስራው ውስጥ የልብ ወለድ ስብስብ ብቻ ይዞ አልመጣም፡፡ እንዲያውም እንደ ታሪክ ተመራማሪ አይነት አካዳሚያዊ ጉዳይ ይዞ ብቅ ብሏል፡፡ ምናልባትም የዘርፉ ምሁራን ሊያዳብሩት የሚችሉት ርዕሰ ጉዳይም አንስቷል፡፡ በርግጥ አንድ አካዳሚያዊ ፅሁፍ ማለፍ ባለበት መስመር ቢያልፍ ደግሞ የበለጠ ይሆን ነበር፡፡ ለምሳሌ ስለ አገራችን ገዢዎች የጦርነት ታሪክ ከዐፄ ምንይልክ የመስፋፋት ዘመቻዎች ጋር በማያያዝ ያነሳሳቸው ጉዳዮች አሉ፡፡ እኔ በበኩሌ እንደ ግለሰብ የጽሁፉ አካሄድ ቢመቸኝም የተጠቀማቸው ዋቢ መጻሕፍት ተገቢነት፣ ተዓማኒነት እና የመሳሰሉት በአካዳሚያዊ ውይይት ላይ ቀርቦ፣ ተተችቶና ታርሞ ቢሆን የፅሁፉ ግኝቶችም የበለጠ ዋጋ ሊያገኙ የሚችሉ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን እዚህ ላይም ጸሀፊው (ዳዊት) በግርድፉ ጥሩ አድርጎ እንደፃፈ በመናገር የተባሉት ነገሮች ሁሉ ከህፀጽ የፀዱ ያስመስሏቸዋል፡፡ እንግዲህ አገም ጠገም የሆነው ፅሁፍ ሲያሰኘው ይተቻል ሲለው ደግሞ ይነቅፋል፡፡ ለምን…?
እንደኔ እንደኔ ማንም ሰው ሀሳቡን ገልጦ እስከፃፈ ድረስ ከትችት ያመልጣል ማለት አልችልም፡፡ ይቅርታ ይደረግልኝና እኝህ ጸሃፊ ግን የቤተክርስቲያን ተቆርቋሪ መስለው ደራሲውን በማንቋሸሽ፣ ከምዕመናን ለማላተም አስበው ይሆን ብዬ ማሰቤ አልቀረም። ደራሲው ኢ-አማኒ መሆን መብቱ ነው፣ ለጻፈው ጽሁፍም ከትችት እስከ ቡጢ የሚደርስ ሃላፊነትን የመሸከም አቅም እንዳለው ከዚህ ቀደም አይተናል፡፡ ነገር ግን እኚህ ፀሀፊ ተችተው ላይተቹ ጊዜአቸውንና ጊዜአችንን ከንቱ ስላደረጉብን ሳላመሰግናቸው እንዴት ልለፍ፡፡
ያም ሆኖ እኔ ገና ከበሰሉ ብዕረኞች በደራሲው ጽሁፍ ላይ አዎንታዊና አሉታዊ አስተያየቶችን  እጠብቃለሁ፣ታዲያ እንደ እኝህ ፀሃፊ ዳውላ ዳውላውን ሳይሆን አህያ አህያው ላይ ነው፡፡ መፅሀፉ ላይ እጅግ አንኳር ጉዳዮች ተነስተዋል፣እነሱ ላይ ብዙ መወያየት እየቻልን ትንኝ ትንኙን እያነሳን ብናነኩረው ቢያሰክረን እንጂ ጥማችንን አይቆርጥልንም ባይ ነኝ፡፡ በደንብ ሊተኮርባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን “ፕሮፌሰሮቹ እንኳ ያልደፈሩት” በምትል ሃረግ ማሰናበት ሳይሆን ይህ ዓይነቱ ክርክር ወደ አደባባይ እንዲመጣና ፈር እንዲይዝ ማድረግ አስፈላጊ ይመስለኛል፡፡ ቸር ይግጠመን!!


Read 2438 times