Saturday, 12 March 2016 10:29

‹‹ወንዶች ያልተጠናቀቁ ሴቶች ናቸው››

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(5 votes)

    ባለፈው ሳምንት፤ ከእሸቴ አሰፋ ጋር የአድዋን ድል በጊዮርጊስ እያከበርን ነበር፡፡ እሸቴ ታሪክ እያስተማረኝ ነበር፡፡ ‹‹በጠቢቡ ሰለሞን›› ጠረጴዛ ተቀምጠናል፡፡ በዙሪያችን ብዙ ሰው አለ፡፡ በዚህ መሐል ለደረጀ ደወልንለት፡፡ ከደረጀ ደስታ ጋር በስልክ ተነጋገርኩ፡፡ ከረጅም ጊዜ በኋላ ድምፁን ሰማሁት፡፡ ድምፁን ስሰማው፤ ‹‹አፈረሱት አሉ፤ ውቤ በርሃን…›› የሚል ዘፈን በሰማ ሰው ህሊና ሊፈጠር የሚችል ስሜት ነግሶብኝ ነበር፡፡ ከእርሱ ጋር አውርቼ ስጨርስ፤ ያለፈ ህይወታችን ትዝ አለኝ። ህይወታችን ‹‹በግል አብዮት›› ይናጥ የነበረ ህይወት ነበር፡፡
ከደረጀ ጋር አውርቼ ስጨርስ፤ ደምቆ የታወሰኝ አንድ ነገር ነው፡፡ ደረጀ አንዳንድ የሐሳብ ‹‹ጉዊሎቲን››ን (Guillotine) የማለፍ ልዩ ብቃት አለው፡፡ ደረጀ ሁሌም ሚዛን አለው፡፡ እኛንም ሚዛን ያስጠብቀናል፡፡ እርሱ ከባህር ጠለል ባላይ በአራት ሺህ (ወይም በላይ) ሜትር ከፍታ ላይ ለመተንፈስ ይችላል፡፡ ዳሎል ወርዶም እንደ ልቡ ይሆናል። ሳንባው ከባህር ጠለል በታች ወርዶ፤ እንጦጦም ወጥቶ አለ ችግር ያገለግለዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ፤ ትኩስ ጎረምሳ እና የሰከነ አዛውንት በአንድ ደረት ይዟል፡፡ በውስጡ ያለችውን ሴት እየቀሰቀሰ ሚዛኑን ይጠብቃል፡፡ እረኛ እንደ ሌለው ከብት በሐሳብ ዱር ልንጠፋ ስንባዝን፤ እረኛ ሆኖ አስታዋሽ ሐሳብ ያመጣል፡፡  
ከዚህ ቀደም የሰው ህሊና ረግጦት ከማያውቅ (?) የሐሳብ ዱር ገብተን ስንባዝን፤ በተቦጫጨቁ የፍልስፍና ሐሳቦች ሰክረን፤ የስሜት ጽዋ አንስተን ስንጯጯህ፤ አንዳንድ የምስጢር ስንኞች እያነበነብን ስንቃዥ፤ እርሱም እስኪበቃው ከቃዠ በኋላ፤  ከእንቅልፍ ይቀሰቅሰናል፡፡ እርሱ ነፃነቱን የሚጠቀመው፤ ራሱን በረጅም ገመድ አስሮ ነው፡፡ ስለዚህ፤ እንዳንባዝን እንደ እረኛ ይመልሰናል፡፡ እሸቴ ከጉብታ ሆኖ ይመለከተናል፡፡    
ታዲያ አንድ ቀን ደረጀ እንዲህ አለኝ፤ ‹‹እኛ ወንዶች መሬት ለቅቀን ለመባከን የተጋለጥን ነን። በመባዘን አደጋ የተከበብን ነን፡፡ ስለዚህ ሴቶች ሁሌም ከአጠገባችን ሊኖሩ ያስፈልገናል፡፡ ሴት ሚዛን ታስጠብቅሃለች፡፡ አንተ ኒቼ እንዲህ ብሎ፣ ይህን አድርጎ ስትል፤ ዝም ብላ ትሰማሃለች፡፡ አንተ በሐሳብ አብደህ ልትጠፋ ስትል፤ ‹መቼ ነው ላንጋኖ የምትወስደኝ› ብላ ከሰማይ ወደ መሬት ታወርድሃለች፡፡ አንተ እንደ ደስተዮቪስኪ ሰማይ ሰማዩን ስታይ፤ እንደ ሄንሪ ሚለር ወደ መሬት ትመልስሃለች›› አለኝ፡፡
በአዲሱ (ደረጀ በማያውቀው) የሜክሲኮ ጎዳና በታክሲ ስጓዝ፤ ይህን የደረጀን ንግግር እየከለስኩ ነበር፡፡ ደረጀ ‹‹ሴት ሚዛን ታስጠብቅሃለች›› ይላል። ዛሬ (ጽሑፉ  ሲፃፍ) ማርች 8 ነው፡፡ ስለዚህ የጓደኛዬን ንግግር ዛሬ ማስታወሴ፤ ‹‹መለኮታዊ ዲዛይን›› ይመስላል፡፡ ተገቢ ነው፡፡
ደራሲው ሔንሪ ሚለር፤ ‹‹ኔክሰስ›› ሲል በሰየመው መጽሐፉ፤ ደስተዮቭስኪን ይፎግረዋል፡፡ ‹‹እርሱ ሰማየ-ሰማያት ወጥቶ ረቂቅ ሐሳቦችን እንደ ጥጥ ሲያባዝት ይውላል፡፡ ግን አንድ ቀን እንኳን በሴቶች ቦርሳ  ውስጥ ምን እንዳለ ለማየት ሞክሮ አያውቅም›› ይለዋል፡፡ ደስተዮቭስኪ ትልቅ ደራሲ ነው፡፡ ግን ‹‹አየራዊ ዕጽ›› (Aerial Plant) ነው፡፡ ዋርካ ደራሲ ነው፡፡ ‹‹ግን መሬት ያልዘ ዋርካ ነው›› ለማለት የፈለገ ይመስለኛል፡፡ ደስተዮቭስኪ፤ ከአየር ሳይሆን ከመሬት የበቀለ ዋርካ እንዲሆን የሴቶችን ቦርሳ ማየት አለበት፡፡ እንደ ደረጀ ሐሳብ ጤና ያገኛል፡፡
‹‹ፍልስፍናን የምትወድ ከሆነ›› ይላል ደረጀ፤ ‹‹ፍልስፍናን የምትወድ ከሆነ፤ ሁሌም አንዲት ሴት ከአጠገብህ ልትኖር ይገባል›› ይላል፡፡ ‹‹ሄግል፣ ስፒኖዛ፣ ካንት እያልክ መሬት ለመልቀቅ ስታቆበቁብ፤ እርሷ ‹የኔ ፍቅር ፂምህን አትላጭም፤ ያቺ መኪና አታምርም› ትልሃለች፡፡ መሬት ትይዛለህ።
‹‹ሾፐንአወር ምን እንዳለ ታውቂያለሽ ማለት ስትጀምር፤ ‹አንተ እከሊት እንዴት ተስማምቷታል›› ትልሃለች፡፡ ከሰው ጋር ትቀላቅልሃለች፡፡ ሳርትር፤ ‹Man is condemned to be free› የሚለው….ብለህ መሬት ለመልቀቅ ስትዘጋጅ፤ ‹በቀደም እንትና ሱቅ ያየሁት ሹራብ…› ትልሃለች፡፡ ቤትህን ለቅቀህ እንዳትሄድ ትጠብቅሃለች፡፡ ጨርቅህን ጥለህ እንዳትሄድ አደብ ታስገዛሃለች›› ይለኝ ነበር፡፡
የተነሳው ሐሳብ ጠበቅ አድርገው ሲይዙት ችግር ይኖረው ይሆናል፡፡ ግን የሆነ የእውነት ጥላ እንዳረፈበት አያለሁ፡፡ የዚህ ወሬ ትክክለኛው ዓውድ ካፌ ወይም የቢራ ጠረጴዛ ሆኖ የተሰማችሁ ካላችሁ፤ የወንድ ህይወት የሚቃናው በሴቶች መሆኑን ለመግለጽ የተነገረ ጨዋታ ነው፡፡
ፍልስፍና የዕውቀት ጉጉት ከሆነ፤ ሴቶች የመፈላሰፍ ፍላጎታቸውን በአዳም ፊት ጨርሰውታል። እፈላሰፋለሁ የሚለውን ወንድ በማህፀኗ ይዛ ለምትወልድ ሴት ፍልስፍና ምንድነው? አሻንጉሊቷ የሚጫወትበት ዕቃ ነው። አንዳንድ ሰዎች፤ ብዙ ወንዶች በኪነት አምባ ውርውር የሚሉት በሴቷ የመፍጠር ብቃት እየቀኑ ነው›› ይላሉ፡፡  እውነት ነው፤ ሴት ሰውን የመሰለ ረቂቅ ፍጡር ከወለደች በኋላ፤ የልብ ወለድ ገፀ ባህርይ የመፍጠር ፍላጎት ሊኖራት አይችልም፡፡
ህይወት፤ በሴቶች ማህጸን ለዘጠኝ ወር ቆይታ፤ ጡታቸውን ጠብታ፤ በእነሱ እጅ ጎርሳ፣ በእነሱ ምክር ጉዞዋን ትቀጥላለች፡፡ ሴቶች ስለህይወት ኃላፊነት ይሰማቸዋል፡፡ ስለዚህ ይጠነቀቃሉ። ወሲብ በወንዱ ዓይን ከደስታ ስሜት የተሻገረ ምዕራፍ የሌለው ጨዋታ ተደርጎ ሊታይ ይችላል፡፡ ለሴቶች ግን ከባድ ኃላፊነትን የሚያስከትል ግብር ነው። ወንዱ አስረግዞ ዘወር ሊል ይችላል፡፡ ሴቷ ግን አምጣ መውለድና አቅፋ ማጥባት ይኖርባታል። ስለዚህ ከአልጋ ለመውደቅ ስታስብ፤ ይህ ሰው ‹‹የምወልደውን ልጅ ለማሳደግ የሚችል ሰው ነው?›› ብሎ የማሰብ ኢቮልዩሽናዊ ዕዳ አለባት። ኢቮልዩሽን፤ ‹‹ብቁ የሆነ ይለፍ›› ሲል አውጇል፡፡ ስለዚህ የተጣማጇን አካላዊ ብቁነት ብቻ ሳይሆን፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ብቃቱንም ለማረጋገጥ ትሻለች፡፡ ምክንያቱም፤ ወንዱ በመኮብለል ወይም በሞት ቢለይ፤ አለያም ቤተሰቡን ለመደገፍ ባይችል፤ ከፍተኛ ጉዳት የሚደርሳባት ሴቷ ነች፡፡
ስለዚህ ሴቷ መሬት ባልለቀቀ መንገድ የማሰብ ወይም የመመዘን ዝንባሌ አላት፡፡ አንዳንዱ ወንድ ይህችን ሴት በውስጡ ሊያገኛት ይችላል፡፡ ግን ይህች ውስጣዊ ሴት ስታንቀላፋበት ውጫዊ ሴት ታስፈልገዋለች፡፡
በእርግጥ ህይወት ሙሉ የምትሆነው በሴት እና በወንድ ህብረት ነው፡፡ እንደ ቻይናውያን አስተሳሰብ ህይወት Yin and Yang ነች፡፡ Yin and Yang የታኦ የህይወት ህግ ወይም ቀመር ነው፡፡ የህይወት ዚቅ በሳቅ እና በለቅሶ፤ በተስፋ እና በቀቢፀ ተስፋ፤ በመውደቅ እና በመነሳት የተቀናበረ መሆኑን የሚገልጽ ህግ ነው፡፡
ህይወት በዚህ ገጽ እንደምታዩት ስዕል ያለ ይዘት አላት፡፡ ጥቁር እና ነጭ ነች፡፡ ወንድ እና ሴት ነች። የጥቁሩ መጀመሪያ የነጩ መጨረሻ ነው፡፡ የነጩ መጀመሪያ የጥቁሩ መጨረሻ ነው፡፡ አንዱን ብቻ የያዘች ህይወት አትገኝም፡፡ እንዲህ መሆኗ ሙላት እንጂ ጉድለት አይደለም፡፡ በህይወት ጎዳና ረጋ ብሎ ለመጓዝ ይህን እውነታ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ ህይወት Yin and Yang መሆኗን የተቀበለ ጤነኛ፣ አስተዋይ እና ጠቢብ ነው፡፡  ይህ የታኦ የህይወት ህግ ነው፡፡ ሴቶችን ማክበር ህይወትን ማክበር ነው፡፡
በእኔ አስተሳሰብ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ከሰለጠነው ዓለም የምዕራቡ ዓለም የተሻለ ሴትነትን ያከብራል። በኢትዮጵያ ታሪክ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው ብዙ ሴቶች እናገኛለን፡፡ ንግስተ ሳባን፣ በፖለቲካ ጥበባቸው የላቀ ብቃት የነበራቸው የሐድያ ተወላጅ ንግስት ኢሌኒ፣ በዘመነ ጎንደር የምናውቃቸው እቴጌ መነን፣ የወሎዋ መስታይት፣ እቴጌ ጣይቱ እንዲሁም የምኒልክ ልጅ ንግስት ዘውዲቱ ሊጠቀሱ የሚችሉ ሴቶች ናቸው፡፡ የአሜሪካን ወይም የእንግሊዝን ታሪክ ብትገልጡ አንድ ሴት አታገኙም፡፡ አሜሪካ ወ/ሮ ክሊንተንን ከመረጠች አዲስ ታሪክ ትሰራለች፡፡ በዚህ ረገድ ከኢትዮጵያ ልትማር ትችላለች፡፡ ተመስገን፡፡
ኢትዮጵያውያን የሴቶችን ትልቅነት ለመቀበል የሚቸገሩ አይደሉም፡፡ እኛ ወንዶች (የደረጀን ምክር ተቀብለን) ሴቶችን በማክበር ኢትዮጵያን ራሳችንን ከጥፋት እንጠብቃለን፡፡ ኢትዮጵያን የተሻለች ሐገር እናደርጋታለን፡፡ ሴቶችን ለማክበር፤ የፍሬድሪክ ኒቼን አባባል በመቀየር፤ ‹‹ወንዶች ያልተጠናቀቁ ሴቶች ናቸው›› እላለሁ፡፡


Read 4996 times