Saturday, 12 March 2016 10:20

የቀድሞ ባለቤቱንና ህፃን ልጇን የገደለው ሞት ተፈረደበት

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(14 votes)

ከሌላ ወንድ ጋር አይቻታለሁ በሚል የቆየ ቂም በቀል ከተለያዩ ከ6 ዓመታት በኋላ እንደገና የቀረባትን የ3 ልጆቹን እናትና ከሱ ከተለያየች በኋላ የወለደቻትን የ6 ዓመት ህፃን በአሰቃቂ ሁኔታ የገደለው ግለሰብ ላይ የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ሰሞኑን የሞት ፍርድ ወስኗል፡፡
የድሬደዋ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ዲቪዥን ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ገመቹ ካቻ ለአዲስ አድማስ እንደገለጹት፤አብደላ መሃመድ አሊ የተባለው ግለሰብ መስከረም 14 ቀን 2008 ዓ.ም ከምሽቱ 2 ሰዓት ሲሆን በድሬደዋ ከተማ ቀበሌ 09 ልዩ ቦታው አዲሱ ኬላ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ወደ ሟች መኖሪያ ቤት በመሄድና ሆን ብሎ ፀብ በመፍጠር ነው ግድያውን የፈጸመው፡፡  
ገዳይና ሟች ከ6 ዓመት በፊት በትዳር ሲኖሩ 3 ልጆች ያፈሩ ሲሆን በመሃል ከሌላ  ወንድ ጋር አይቻታለሁ በሚል አለመግባባት ተለያይተው፣ ሚስትም ወደ ሌላ አካባቢ በማቅናት አዲስ ህይወት መስርታ ልጅ የወለደች ሲሆን እሱም ሌላ ሚስት አግብቶ ኑሮውን ቀጥሏል፡፡  በመሃል በወለዷቸው ልጆች አማካይነት መገናኘት መጀመራቸውን የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ያስረዳል፡፡  
የሟችን መኖሪያ ቤት ያወቀው ገዳይ ማታ ማታ ተሸፋፍኖ ይከታተላት ነበር፤በኋላም ከቀድሞ ሚስቱ ጋር ሰላማዊ ቅርርብ ይፈጥራል፡፡ ለጓደኞቹ ግን “የቀረብኳት መስሏታል፤ቆይ እሰራላታለሁ” እያለ ይዝት እንደነበር የፖሊስ ማስረጃ ይጠቁማል፡፡  
መስከረም 14 ቀን ምሽት ወደ መኖሪያ ቤቷ በማምራት ፀብ ይፈጥራል፡፡ በያዘው ስለትም የቀድሞ ሚስቱን አንገቷ ላይ ይወጋታል፡፡ ይህን የተመለከተችው ህፃን ልጇ፤“ለምን እንዲህ ታደርጋለህ?” ብላ ስትጠይቀው፣ እሷንም በያዘው ስለት ይወጋታል፡፡ ከዚያም እጅግ አሰቃቂ  በሆነ ሁኔታ ሁለቱንም ገድሎ አስከሬናቸውን ቤት ውስጥ ቆልፎበት ይሰወራል፡፡ ከ3 ቀን በኋላ  አስከሬኑ በአካባቢው ላይ መጥፎ ጠረን መፍጠሩን ተከትሎ ፖሊስ ከህብረተሰቡ በደረሰው ጥቆማ መሰረት በሩን ከፍቶ በመግባት የሟቾችን በዘግናኝ ሁኔታ የተቆራረጠ አስከሬን ያገኛል፡፡
ገዳይ ለጊዜው ቢሰወርም ህብረተሰቡ ለፖሊስ ባደረሰው መረጃ፣ ከተደበቀበት መኖሪያ ቤቱ  ወዲያው በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን ምርመራው ተጣርቶ፣ በፍ/ቤት ክስ እንደተመሰረተበትና ማክሰኞ የካቲት 30 ቀን 2008 ዓ.ም ፍ/ቤት የሞት ቅጣት ውሳኔ እንዳስተላለፈበት ዋና ኢንስፔክተር ገመቹ ካቻ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

Read 3364 times