Saturday, 05 March 2016 11:07

አድዋ - አድዋ!

Written by  ተፈሪ መኮንን
Rate this item
(5 votes)

አድዋ ትንግርት ነች፡፡ አድዋ አርማ ነች፡፡ አድዋ ታሪክ ነች፡፡

     ‹‹ነብይ በሐገሩ አይከበርም›› እንደሚባለው ሆኖ እንጂ፣ ኢትዮጵያ ድንቅ ሐገር ነች፡፡ የራሳችን ሰዎች የሚጽፉትን ድንቅ መቀበል ይቸግረናል፡፡ ለምሣሌ፣ ከንግስተ ሳባ ጋር የተያያዙ ታሪኮችን እኛ እናጣጥለዋለን። አንዳንድ የውጭ ሐገር ምሁራን ደግሞ ቁም ነገር አድርገው ያጠኑታል፡፡ ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሳባ የቀረበውን ታሪክ የጻፉት ኢትዮጵያውያን አይደሉም፡፡ በታላቁ መጽሐፍ የሰፈረ ታሪክ ነው፡፡
ኢትዮጵያን ከሩቅ ሆኖ ለሚያያት፤ አማላይ ታሪክ፣ ገጽታና ተረት መሰል ዝና ያላት ሐገር ነች። የአማልክት ምድር ይላታል-ሆመር፡፡ የገነት ምንጭ ያደርጋታል-ሶደንቦርጅ፡፡ ብዙ የአረብ ባለቅኔዎች የቅኔ መወድስ የጻፉላት ሐገር ነች፡፡ ‹‹ፍትህ የማይጓደልባት ምድር ነች›› ይሏታል፡፡ እውነትም የእውነት ምድር፡፡ ችግራችን ታሪኩ አሁን ከሚታየው ነገር ጋር አልጣጣም ማለቱ ይመስለኛል፡፡
እንጂ ኢትዮጵያ የፍትህ ምድር መሆኗን ለማረጋገጥ፤ የመጀመሪያዎቹን የነብዩ መሐመድ ተከታዮች ታሪክ ማንበቡ ብቻ በቂ ነው፡፡ እንዲያውም ኤድዋርድ ጊቦን በዚህ ይወቅሳታል፡፡ ‹‹አረቦች ለማጥፋት የታገሉለትን የእስልምና ሐይማኖት ከጥፋት በመጠበቅ፤ በዓለም ውስጥ ኃያል ማህበራዊ አብዮት እንዲፈጠር ያደረገች ሀገር ኢትዮጵያ ነች›› ይላታል፡፡
ኢትዮጵያ፤ በምዕራብ አውሮፓ ህዝቦች ምናብ የህልም ሸማ ደርባ የኖረች የተምኔት ሐገር ናት፡፡ አንዳንድ አንትሮፖሎጂስቶች፤ ህዝቧን በተለየ ወገን ሊመድቡት ይሞክራሉ፡፡ የተለየ የሒሳብ ቀመር ስርዓት ያላት ሐገር መሆኗን ፈረንጆቹ ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን ዜሮ በሌለበት የሒሳብ ቀመር ስርዓት ይደምራሉ፣ ይቀንሳሉ፣ ያባዛሉ፣ ያካፍላሉ፡፡ ፈረንጆች፣ ልጆቻቸው ሒሳብን እየተዝናኑ ይማሩ ዘንድ፣ በኢትዮጵያ የሒሳብ ቀመር እንዲያሰሉ ያደርጋሉ፡፡ ቢቢሲ በሰራው አጭር ዶኩመንታሪ፤ ኮምፒውተርና የሒሳብ ማሽን የሚሰሩበትን ስርዓት ኢትዮጵያውያን ለምዕተ ዓመታት ያውቁት ነበር ብሏል፡፡
በአጭሩ ድህነት ይዟት፣ ኋላቀርነት አድክሟት፣ ችጋር ጠብሷት፣ ረሃብ መልኳን አርግፎት፣ የሰላም እጦት መጻጉዕ አድርጓት እንጂ ልዩ ጸጋ ያላቸው ህዝቦች የሚኖርባት ሐገር ነች- ኢትዮጵያ፡፡ ታላቁ እስክንድር አልደፈራትም፣ ጁሊየስ ቄሳር ተመኝቶ አልተጋፋትም። ኢትዮጵያ በግርማዋ የምትፈራ፣ የምርጥ ጦር ጀነራሎች ሐገር ነበረች (ነች)፡፡ ለዚህ ደግሞ ከአድዋው ድል የተሻለ ምስክር መጥራት አይቻልም፡፡
ታዲያ ስለ አድዋ ማወቅ ከፈለጋችሁ፤ አንድ ምክር አለኝ፡፡ ስለ አድዋ ብዙ ነገሮች ተጽፈዋል፡፡ ሆኖም እኔ የምመክራችሁ፤ ሐበሻ ወይም ፈረንጅ የጻፈውን የታሪክ ሰነድ እንድታነቡ አይደለም፡፡ እኔ የምመክራችሁ፤ እጅጋየሁ ሽባባን እንድታዳምጡ ብቻ ነው፡፡
‹‹ምስጋና ለአድዋ ጀግኖች፣ ለዛሬው ነፃነት ላበቁኝ ወገኖች›› እያለች የምታዜመውን እጅጋየሁ ሽባባውን አድምጡ፡፡ ሂዱ እጅጋየሁ ‹‹አድዋ›› ስትል ልብ አድርጋችሁ አድምጡ፡፡ ሌሎች የታሪክ መጻህፍት ሁሉ የእጅጋየሁ ዝማሬ የግርጌ ማስታወሻዎች ናቸው። የእጅጋየሁ፤ ዘፈን በኃይል ይናገራል፡፡ በኃይል ያናግራል፡፡ ‹‹ትናገር አድዋ ትናገር ሐገሬ፤ እንዴት እንደቆምኩኝ ከፊታችሁ ዛሬ›› ትላለች እጅጋየሁ። አዎ፤ አድዋ ትናገር፡፡ አድዋ ትንግርት ነች፡፡ አድዋ አርማ ነች፡፡ አድዋ ታሪክ ነች፡፡ አድዋ የነፃነት አርማ ምልክት ነች፡፡ አድዋ የጥቁር ህዝቦች የአርነት ኃይል ነች፡፡ አድዋ የሐገራችን ምልክት ነች፡፡
ባለሦስት ቀለሙ የሐገራችን ባንዲራ የኢትዮጵያ መለያ የሆነው ከአድዋ ድል አንድ ዓመት በኋላ ነው። እርግጥ፤ ባለሦስቱ ቀለም ባንዲራ ቀደም ሲልም የኢትዮጵያ ኤምፓየር መለያ ሆኖ ያገለግል ነበር፡፡ የታሪክ ፀሐፊዎች እንደሚሉት፤ ይህ ባንዲራ የሐገሪቱ ብሔራዊ ዓርማ መሆን የጀመረው ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ነው፡፡ ሆኖም፤ በአሁኑ አደራደር (አረንጓዴ - ቢጫ - ቀይ)›› አልነበረም፡፡ ይልቅስ፤ ቀይ - ቢጫ - አረንጓዴ የሆነ አደራደር ነበረው፡፡ ይህም የሰሎሞናዊው ስርወ መንግስት ምልከት ሆኖ ያገለግል እንደነበር የታሪክ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
እንዲያውም፤ ሦስቱ ቀለማት ከ17ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ጀምሮ፤ ከአሁኑ በተለየ ሁኔታ እንደ ምልክት ያገለግሉ ነበር፡፡ ሆኖም የባንዲራው አረንጓዴ - ቢጫ - ቀይ አደራደር የፀናው በአድዋው ድል ማግስት ነበር፡፡ ከአድዋ ድል በኋላ፤ ይህ ባንዲራ የኢትዮጵያዊነት ብቻ ሳይሆን የ‹‹ፓን - አፍሪካዊነት›› ምልክት የመሆን ማዕረግም አገኘ፡፡ የኢትዮጵያውያንን የነፃነት ተጋድሎ ለመዘከር በማሰብ ብዙ የአፍሪካ ሐገራት፤ የባንዲራቸውን ቀለም የተለያየ አደራደር የያዘ የአረንጓዴ - ቢጫ - ቀይ ቀለማት ስሪት አደረጉት።
የአድዋ ጦርነት በውጭ ሐገር ብቻ ሳይሆን በሐገር ውስጥም ብዙ ለውጦችን አስከትሏል፡፡ የመንግስት አደረጃጀት የተለወጠው ከአድዋ ድል በኋላ ነው፡፡ ቀደም ሲል የጀመረው የውጭ ግፊትና ተፅዕኖ ከአድዋ ድል በኋላ ይበልጥ ተጠናክሮ ቀጥሎ ነበር፡፡ የቆንሲል መሥሪያ ቤቶችና ፍርድ ቤት የተቋቋሙት ከአድዋ ጦርነት በኋላ ነበር፡፡ የፍትህ አስተዳደሩ ራሱን ችሎ እንዲደራጅ የማድረጉ ጥረት ከመጀመሪያው ካቢኔ መቋቋም ጋር በ1900 ዓ.ም ተጀመረ፡፡ ሆኖም ፍርድ ቤቶችን በተዋረድ የማዋቀሩ ሥራ ረጅም ዓመታት የወሰደ ሥራ ነበር፡፡ መሠረታዊና የሥነ ስርዓት ሕጎችን የመደንገጉ፣ የዐቃቤ ሕግ መስሪያ ቤቶችን የማቋቋሙ ተግባር ከ1934-1952 ባሉት ዓመታት የተከናወነ ሥራ ነበር፡፡
እንዲህ ዓይነት አደረጃጀት ከመፈጠሩ በፊት ንጉሡ የሚዳኘው ጉዳይ ገደብ አልነበረውም፡፡ በ1900 ዓ.ም መጀመሪያ በኢትዮጵያ የነበረ አንድ ዲፕሎማት በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ በሰጠው አስተያየት፤ ‹‹በአስተዳደሩ ውስጥ አፄ ምኒልክን የማይመለከት ሥራ ዝርዝር የለም። ንጉሡ ለማየትም ሆነ መመሪያ ለመስጠት የሚሹት በማናቸውም ጉዳይ ላይ ነበር። አንድ ሚሊየን ብር ዋጋ ባለው የዳኝነት ጉዳይ ላይ ውሳኔ እየሰጡ፤ አንዱ ብቅ ብሎ አንድ ጆንያ ዱቄት ወይም አንድ ነጠላ ሳንቃ ለመውሰድ እንዲፈቀድለት ጥያቄ ያቀርባል፡፡ በሣምንት ሁለት ቀን ለአምስት ወይም ስድስት ሰዓታት ያለ ማቋረጥ ዳኝነት ይሰየማሉ። ባለጉዳዮችንም ይቀበላሉ›› ሲል ተችቶ ነበር፡፡
የዳኝነት ነገር ከተነሳ፤ የማጫውታችሁ ነገር አለኝ፡፡
ከ1900 ዓ.ም በፊት ድሬዳዋ ውስጥ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ይታተም በነበረ ‹‹ለስሜር ዲቲዮፒ›› በተባለ አንድ ጋዜጣ እንደ ተጠቀሰው፤ አዋጅ ነጋሪው ለንጉሡ ሥልጣን ህያው መገለጫ ምልክት የሆነ አንድ ግልገል አንበሳ አስከትሎ ወደ ገበያ ይወጣል፡፡ ከዚያ በኋላ ነጋሪት ይመታል፡፡ ከዚያም አዋጅ ነጋሪው፤
ስማ ስማ መስማሚያ ይንሳው ያድባርን ያውጋርን ጠላት፤
ስማ ስማ መስማሚያ ይንሳው የማርያምን ጠላት፤
ስማ ስማ መስማሚያ ይንሳው የጌታችንን ጠላት፤ (ማኅተመ ወልደ መስቀል እንደዘገቡት) ብሎ ይጀምርና አስከትሎ አዋጁን ያነባል፡፡ አዋጁ አማርኛ ተናጋሪ ባልሆኑ አካባቢዎች ሲነገር በአካባቢው ቋንቋ ይተረጎማል፡፡ ለምሣሌ ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጋዜጣ፤ በድሬዳዋ አካባቢ የነበረውን ሁኔታ ሲያስረዳ፤ ‹‹አዋጁ በአማርኛ ይነበባል፡፡ ወዲያውኑም በሐረሪ፣ [በኦፋን ኦሮሞ] እና በሱማልኛ ይተረጎማል›› ሲል ገልጧል፡፡
በመጨረሻ፤ የምኒልክን ፍርድ አዋቂነት የሚያሳይ አንድ ታሪክ ላጫውታችሁ፡፡
የጎጃም ንጉስ ተክለ ሐይማኖት ያረፉት ከአድዋ ጦርነት በኋላ በ1893 ዓ.ም ነበር፡፡ ንጉስ ተክለ ሐይማኖት እንዳረፉ፤ የአባታቸውን ክብርና ግዛት ለመያዝ በልጆቻቸው መካከል ከፍተኛ ትግል ተካሂደ። በዚህ የተነሳ ምኒልክ የሹመቱን ነገር ለጊዜው አዘግይተው፤ ከግዛቱ በጥቂቱ ቀንሰው ለራስ መንገሻ ሰጡ፡፡ ከዚያም ነገሩ እስኪሰክን ትንሽ ከጠበቁ በኋላ በመጨረሻ ሥዩም ተክለሃይማኖትን የጎጃም ገዥ አድርገው ሾሙ፡፡ ሥዩም ተክለሃይማኖትም ወዲያውኑ ራስ ወርቄና ራስ መስፍን የሚባሉ የጎጃም መኳንንትን አሰሩ፡፡ ራስ ወርቄና ራስ መስፍን ባልሆነ ሥራ ተጠርጥረው መታሰራቸው ተሰማ፡፡ አፄ ምኒልክም ይህንን ሲሰሙ፤ ዳጃች ሥዩም ተክለሃይማኖት የአባታቸውን የንጉሥ ተክለሃይማኖትን ሙት ዓመት ካወጡ በኋላ ወደ እርሳቸው እንዲመጡ አዘዙ፡፡
በዚህ መሠረት፤ የንጉሥ ተክለሃይማኖት ልጅ የሆኑት ደጃች ሥዩም ያሰሯቸውን መኳንንት ይዘው በ1894 ዓ.ም ወደ አፄ ምኒልክ መጡ፡፡ አፄም እንደ ቀድሞ አክብረው ተቀበሏቸው፡፡ ዕለት ዕለት እየተጠሩ በፍቅር ሲነጋገሩ ሰንብተው ከጥቂት ቀን በኋላ ከጎጃም ታስረው ለመጡት መኳንንት ጉባኤ አደረጉ፡፡
ደጃች ሥዩምም መኳንንቱን ያሰሩበትን አመለከቱ። እንዲህም አሉ፤ ‹‹ሁለቱ መኳንንት የዓባይ ውሃ ከሞላ ቶሎ አይጎድልም፡፡ እስከዚያ ራስ መንገሻን ወግተን ካባትህ ግዛት ተከፍሎ የቀረብህን አገር እጅ እንዳርጋለን ብለው ማኅተማቸውን ቢልኩብኝ፤ ሣሙኤል ከዕሤይ ልጆች ትንሹን ልጁን ዳዊትን መርጦ እንደቀባ እኔንም አፄ ምኒልክ ዘለግ ያሉ ታላላቅ ወንድሞች ሳሉኝ እኔን ትንሹን መርጠው ባባቴ አልጋ ለመቀመጥ ቢያበቁኝ እንደዚህ ያለውን ነገር አላደርገውም፤ ወርቅ ለሰጠ ጠጠር፣ እህል ላበደረ አፈር መመለስ ይገባዋልን? ብዬ አሰርኋቸው፡፡ የላኩብኝንም ማኅተም ይኸው ይዤዋለሁ ይታይልኝ›› ብለው አመለከቱ፡፡ ማስረጃቸውንም አቀረቡ፡፡
እስረኞቹም፤ ‹‹እንደዚህ ያለውን ቃል፣ እንኳን ማኅተም ልንልክ፣ በልቦናችንም አላሰብነው›› አሉ። አክለውም፤ ‹‹ነገር ግን ጠላትን አጥፍቶ፣ አገር አስፋፍቶ ያነገሰዎ የጃንሆይ አምላክ እውነት ፍርዱን አይነሣዎምና እንደ ገለፀልዎ ይመርምሩልን›› ብለው መለሱ፡፡
በዚህ ጊዜ በመኳንንቱም በሠራዊቱም ዘንድ ክርክር ሆነ፡፡ እኩሌቶቹ መኳንንት ‹‹ከማኅተሙ ወዲያ ምን ምስክር አለ›› አሉ፡፡ እኩሌቶቹም፤ ‹‹ማኅተም የያዘውን አሽከር በገንዘብ ገዝቶ ቢያደርገው ይሆን የለምን›› ተባባሉ፡፡ እኩሌቶቹም፤ ‹‹እግዚአብሔር ቀብቶ ያነገሠው ንጉሥ ይመርምር እንጂ ይህንን ሌላ ሰው መርምሮ አያገኘውም›› አሉ፡፡
ጃንሆይም፤ ‹‹እስቲ ማኅተሙን አሳዩኝ›› አሉ፡፡
ስለዚሁ ጉዳይ ያተቱት የህግ ባለሙያው ታምሩ ወንድም አገኘሁ (ሕጋዊነት፣ ቅጽ 3፣ ቁጥር 5)፤ የሚከተለውን ይላሉ፤
‹‹በነዚያ ማኅተም ከሌላ ወረቀት ላይ አትመው እሱም ላኩብኝ ያለውን ማኅተም አቅርበው ሲያስተያዩት አንድ ኅብር ሆነ፡፡ ጃንሆይም የዳኝነት ነገር ጭንቅ ነውና ብዙ ብልሃት አሰቡ፡፡ ከብዙ አሳብ የተነሳ ሕጽል ከል [ኮምፓስ] አምጡልኝ ብለው ቢለኩት ስፋቱም ክበቡም ልክ ሆነ፡፡ ኋላ ግን፣ ቀለምና ቀለሙ የወደቀበትን በሕጽል ከል ቢለኩት ደጃች ሥዩም ያመጣውና የስሮቹ ማኅተም ልዩ ሆኖ ተገኘ፡፡ ከዚህ በኋላ ማኅተሙስ በመልኩም በክበቡም ልክ ሆነ፡፡ [ግን] ቀለምና ቀለሙ ያረፈበትን ብለካው ልዩ ሆኖ ተገኘ፡፡ ይህ ነገር አንተ የሠራኸው ነውና እውነቱን ንገረኝ ብለው አንድ ቃል ደጃች ሥዩምን ቢጠይቁ፤ ፊት አሌ ብዬ ኋላ አዎን ያልኩ እንደሆነ ቅጣት ይጠናብኛል ብሎ፤ ‹አዎን እንዱን እኔ አሠርቼ አተምሁት፡፡ ሁለተኛውም ሌላ ቃል ተጽፎ በመጣበት ወረቀት ከማኅተም በታች ትርፍ ወረቀት ባገኝበት የተፃፈበትን ቆርጬ ጥዬ ወረቀቱን አዙሬ ማኅተሙን ዘቅዝቄ ይህን ቃል ጻፍኩበት፡፡ ሦስተኛም እንዲህ ያለውን እግዚአብሔር ከገለፀልዎ በኋላ እንደ ምህረትዎና እንደ ቸርነትዎ ያድርጉ እንጂ እኔማ ምን እሠውርዎ አለሁ› ብሎ ተናገረ፡፡
‹‹እነዚያም ከጎጃም ታስረው የመጡ መኳንንት ይቀጣልን ብለው ወደ ጃንሆይ ቢለምኑ ተፋረዱ አሏቸው፡፡ የሸዋም፣ የጎጃምም የትግሬም የበጌምድርም መኳንንት ተሰብስቦ ነበርና ከልሂቅ እስከ ደቂቅ አንድ ቃል ሆኖ በቃ እያለ ፈረደ፡፡ እነዚህም ታስረው የነበሩ የጎጃም መኳንንት ተፈትተው በቀድሞ ማዕረጋቸው ገቡ፡፡ ደጃች ሥዩም ታስሮ በደጃች ተሰማ ሥር እንዲጋዝ ተወስኖበት ኢሉባቡር ተላከ፡፡ ከዚህ በኋላ ጎጃምን ለንጉሥ ተክለሃይማኖት ልጅ ለራስ በዛብህ ሸልመው ሰደዱት፡፡
እንደሚታወቀው የነገሥታቱ ዋና ተግባር ሠራዊት ማዝመት ወይም ፍርድ መስጠት ነበር፡፡ አቶ ታምሩ፤ በማጠቃለያቸው፤ ‹‹ይህ ውሳኔ ከንጉሥ የሚጠበቀው ነገር እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታል›› ይላሉ። ንጉሡ በጉባዔም ተቀምጦ ይፈርዳል፡፡ ይግባኝ ያያል፡፡ ቢያስፈልግ ብቻውን ተቀምጦ የመጀመሪያና የመጨረሻ ዳኛ ሆኖ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ክስ ያቀርባል። ጉባዔ ይሰማል፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ የፖሊስንም ሥራ ደርቦ በመርማሪነት ይሠራል›› ይላሉ፡፡
የተደራጀ ፍርድ ቤት ባለመኖሩና የይግባኝና የክርክር ሥርዓትን የሚመራ ህግ ባለመኖሩ ነገር ሁሉ በቀረበበበት መድረክ ይታይ ነበር፡፡ ሆኖም በወቅቱ ትክክለኛ ፍርድ ለመስጠት የሚደረገው ጥረት አስገራሚ ነበር፡፡ እንደ ህግ ባለሙያው አስተያየት፤ ‹‹በተለይ በአንዳንድ ጉዳዮች አፄ ምኒልክ የሚያደርጉት የሰነድ ምርመራ እጅግ የረቀቀ ነበር፡፡ ከ1910 ዓ.ም በኋላ ተቋቁሞ በነበረው በልዩ ፍርድ ቤት ከተደረጉት ውጭ በረቂቅነቱ በወቅቱ በሀገራችን የፍትህ ታሪክ ተወዳዳሪ የሚገኝለት አይመስልም›› ሲሉ የአፄ ምኒልክን ጥበብ አድንቀዋል፡፡ ይሁንና እንዲህ ያለው አሰራር የስራ ጫና በመፍጠር የፍትህ መጓደልን ማስከተሉ አይቀርም፡፡ የአድዋ ድል እንዲህ ያለውን ነገር እንዲቀየር አድርጓል። ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይኑር! አድዋ ለዘላለም ይከበር!     


Read 3398 times