Saturday, 05 March 2016 10:55

“ዓላማችን ትራንስፖርቱን ከታክሲ ተፅዕኖ ማላቀቅ ነው”

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው ሰኞ የታክሲ አሽከርካሪዎች በ2003 ዓ.ም ፀድቆ በቅርቡ በተግባር ላይ የዋለውን “የመንገድ
ትራፊክ ደህንነት ደንብ በመቃወም የስራ ማቆም አድማ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡ ማክሰኞ ዕለትም
በተለይ ጠዋት ሙሉ ለሙሉ ሥራ አልጀመሩም ነበር፡፡ የአሽከርካሪዎቹ አድማ ከመደረጉ ሁለት ቀናት
ቀደም ብሎ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የደንቡን ተፈፃሚነት ለሶስት ወር ማራዘሙን ማስታወቁ
ይታወሳል፡፡ ደንቡ ለ3 ወር የተራዘመው ለምንድን ነው? የታክሲ አሽከርካሪዎች እንደጠየቁት ደንቡ
ይሻሻል ይሆን? የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ናፍቆት ዮሴፍ ጠመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ
ያብባል አዲስን በእነዚህና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋራቸዋለች፡፡

    በ2003 ዓ.ም የፀደቀው የትራፊክ ደህንነት ደንብ ተፈፃሚ የሆነው ዘንድሮ (ሰሞኑን) ነው፡፡ ከአምስት አመታት በኋላ ተፈፃሚ እንዲሆን የተወሰነው በምን ምክንያት ነው?
ደንቡ ሥራ የጀመረው በ2003 ዓ.ም እንደወጣ ሰሞን እንጂ አሁን አይደለም፡፡ ሰሞኑን የተጀመረው የደንቡን ተግባራዊነት ይበልጥ የሚያጠናክር ሥርዓት ነው፡፡ ደንቡማ አገር አቀፍ በመሆኑ ከ2003 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባም በሌሎች ክልሎችም ተግባራዊ ሲሆን ቆይቷል፡፡ የትራፊክ ደንብ ተላላፊዎችም በደንቡ መሰረት ሲቀጡ ቆይተዋል፡፡ ያን ጊዜ ሲቀጡ አይመዘገብምም፤ መረጃ አይወሰድም ነበር፡፡ ቅጣቱም የጥፋት ድግግሞሽን መሰረት ያደረገ አልነበረም፣ አሁን ግን አንድ አሽከርካሪ ደንብ ተላልፎ ሲቀጣ ይመዘገባል፡፡ አሽከርካሪው ዛሬ ሲያጠፋ ይቀጣል፤ ዳግም ሲያጠፋ በየጥፋቱ መጠን ከበድ ያለ ቅጣት ይቀጣል፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለ የአሽከርካሪው ጥፋት ገደቡ ላይ ሲደርስ መንጃ ፈቃድ ሊነጠቅ ይችላል፡፡
ደንቡ ሰሞኑን መተግበር ሲጀምር ግን የታክሲ አሽከርካሪዎችን እስከማስቆጣት ብሎም እስከ ስራ ማቆም አድማ አድርሷል፡፡ በሌላ በኩል መንግስት የደንቡን ተፈፃሚነት ለሶስት ወራት ማራዘሙን ገልጿል፡፡ የመንገድ ደህንነት ደንቡ ለምን ተራዘመ? ደንቡን ለማሻሻል ታስቧል?
እንግዲህ ለ3 ወራት የተራዘመበት ዋና ምክንያት ታክሲ አሽከርካሪዎች አንዳንድ ቅሬታዎችን በማንሳታቸው ነው፡፡ አሽከርካሪዎቹ 24 ሰዓት ስለምንሰራ የቅጣት ድግግሞሹ ተመዝግቦ ከተያዘና ተግባራዊ ከሆነ የጥፋት ሪከርዳችን ስለሚበዛ በአንድ ጊዜ መንጃ ፈቃዳችንን እንድንቀማ ያደርጋል፤ ይሄ ደግሞ እኛንም ከስራ ውጭ ያደርጋል፤ ቤተሰቦቻችንም ለችግር ይዳረጋሉ። የጥፋት ድግግሞሻችን እንዳይበዛ አንዳንድ ተጨባጭ ሁኔታዎች መስተካከል አለባቸው ብለው በውይይታችን ወቅት አንስተዋል፡፡
ተጨባጭ  ሁኔታዎች ሲሉ ምን ማለታቸው ነው?
አንደኛ ህብረተሰቡ በጉዳዩ ላይ ግንዛቤ መውሰድ አለበት፡፡ ደንቡም ተፈፃሚ መሆን ያለበት በአሽከርካሪዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በህብረተሰቡም ላይ መሆን አለበት፡፡ ሁሉም ባለድርሻ አካል  ሃላፊነቱን እንዲወጣ ግንዛቤ ሊፈጠርለት ይገባል። አሽከርካሪው ብቻ ተገንዝቦት ሌላው አካል ካላወቀው በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ነው። እኛም የምናጠፋው ጥፋት እየበዛ ይመጣል፤ ለምሳሌ እግረኛው የእግረኛ መንገድን ይዞ ካልተጓዘ፣ ዜብራ መንገድ ላይ ለማቋረጥ ፈቃደኛ ካልሆነና ባገኘው መንገድ ላይ የሚያቋርጥ ከሆነ የእኛን ጥፋት እያበዛው ይሄዳል፡፡ ስለሆነም ሰፊ የግንዛቤ ስራ ሊሰራ ይገባል … የሚል ሃሳብ አንስተዋል። ሁለተኛው ለተሽከርካሪዎች በቂ የሆነ ምልክትና የማመላከቻ ስራዎች በየመንገዱ ሊተከል ይገባል ብለዋል፡፡ በሶስተኛነት ለታክሲዎች መቆሚያና ማውረጃ የሚሆኑ ተርሚናሎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል፤  በተጨማሪም ታሪፉ አዋጭ ስላልሆነ ሊሻሻልልን ይገባል፤ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት የተፈጠረው ስርዓት እኛን ከገበያ ያስወጣናል ሲሉ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡ የደንቡ ተግባራዊነት ለ3 ወር የተራዘመውም በዚህ ጊዜ ውስጥ በመንግስት ደረጃ ሊሰሩ የሚገባቸውን ቅድመ ዝግጅቶች ለመስራትና በሁሉም ህብረተሰብ ዘንድ የተሟላ ግንዛቤ ለመፍጠር ነው፡፡
በአሽከርካሪዎች የተነሱት ቅድመ ሁኔታዎች በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ተሟልተው ይጠናቀቃሉ ብለው ያስባሉ?
እንግዲህ በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቁት ይጠናቀቃሉ፤ ለምሳሌ የግንዛቤ ስራው፣ ይተከሉ የተባሉት ምልክቶችና መሰል ስራዎች ቶሎ ቶሎ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ ቀሪዎቹና ረዘም ያለ ጊዜ የሚጠይቁት ደግሞ ታክሲዎቹ ሥራቸውን እየሰሩ የሚስተካከሉ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡
ሰሞኑን ያነጋገርናቸው አድማ ያደረጉ የታክሲ አሽከርካሪዎች ህጉ ለ3 ወር ቢራዘምም ካልተሻሻለ ለህብረተሰቡም ለአሽከርካሪዎችም አስቸጋሪ ነው፤ መሻሻል አለበት ብለዋል፡፡ መንግስት በዚህ ዙሪያ ምን ያሰበው ነገር አለ?
ቀደም ሲል እንደተናገርኩት ደንቡ አገር አቀፍ ደንብ ነው፤ በአማራ ክልል፣ በደቡብና ሌሎች ቦታዎች ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ቆይቷል፡፡ ይሄ የቅጣት ድግግሞሽ ምዝገባና የመንጃ ፈቃድ መነጠቁ ጉዳይ ተግባራዊ ሳይሆን የቆየው በአዲስ አበባና በኦሮምያ ብቻ ነው፡፡ እንግዲህ መሻሻል አለበት ወይ? ለሚለው፣ መንግስት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በሰፊው ተወያይቶ መሻሻል ያለበት ነገር ካለ ፌደራል መንግስት የማያሻሽልበት ምክንያት የለም፡፡ ይሄ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል አይደለም፡፡ በግልጽ ተወያይተን አስተካክሉ የተባለውን ጉዳይ ተቀብለነዋል፡፡ እንደነገርኩሽ ችግሩን በአጭር፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ለመፍታት ዝግጁ ነን፡፡
ውይይቱ የተካሄደውና አሉ የተባሉ ችግሮች የተነገራችሁ ደንቡ ተግባራዊ ከመሆኑ በፊት ነው። ችግሮቹ ደንቡን ተግባራዊ ከማድረጋችሁና የስራ ማቆም አድማው ከመምጣቱ በፊት ለምን አልተፈቱም?
ችግሮቹ በሂደት እንደሚፈቱና መንግስት በጉዳዩ ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ተማምነናል፡፡ በነገራችን ላይ አንድ አገር ላይ ደንብ ሲወጣ ደንቡ ሁሉንም ሊያስደስት አይችልም፡፡ ሆኖም ደስተኛ ያልሆነው አካል ሥራውን እየሰራ ቅር የተሰኘበትን ነገር መጠየቅ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ማንኛውም ሰው ከህግ በታች ነው፡፡ አሽከርካሪዎች ሙሉ ለሙሉ ሥራ ማቆማቸው አግባብ አይደለም፤ በአገር ኢኮኖሚም ሆነ በማህበረሰቡ ላይ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ ነው፡፡
ባለፈው ሰኞ የስራ ማቆም አድማው ሲደረግ የትራንስፖርት ተቆጣጣሪዎች ለስራ የወጡትን ታክሲዎች ታርጋ ሲመዘግቡና በአድማው በተሳተፉት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ ባልተሰማሩት ላይ ምን እርምጃ ተወሰደ? በአድማው ዕለት ምን ያህሉ ስራ ላይ ነበሩ?
በአዲስ አበባ ውስጥ ኮድ አንድና ኮድ ሶስት የሚባሉ ታክሲዎች አሉ፤ በአጠቃላይ ቁጥራቸው 10ሺህ አካባቢ ነው፡፡ ከነዚህ መካከል በአድማው ዕለት ስራ ላይ የነበሩት  ከ1500 አይበልጡም ነበር፡፡ ታክሲዎች ሙሉ ለሙሉ ሥራ አቁመው ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ይህ ደግሞ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውስ ቀላል አይደለም፡፡ ምን እርምጃ ወሰዳችሁ ላልሽው መንግስት ከቅጣት ይልቅ ማስተማርን ያስቀድማል፤ ከማስጠንቀቅ ውጭ አድማ በመቱት ላይ ምንም እርምጃ አልወሰድንም፡፡     
የደንቡ ተፈፃሚ መሆን በማህበረሰቡና በአሽከርካሪዎቹ ዘንድ እንደ ትልቅ ስጋት  ታይቷል። ብልሹ አሰራርንና ሙሰኝነትን ያስፋፋል የሚል አስተያየት ይሰነዘራል፡ አንድ አሽከርካሪ ለስድስት ወር ወይም ለሁለት ዓመት መንጃ ፈቃዱን ከሚቀማ ከትራፊክ ፖሊሱ ጋር መደራደርንና ገንዘብ መስጠትን ይመርጣል… የሚል ስጋት በስፋት ይንፀባረቃል፡፡ ቢሯችሁ ስጋቱን እንዴት ያየዋል? ይሄንን ለመቆጣጠርስ ምን አይነት ስልት አዘጋጅቷል?
ሥጋቱ የለም ለማለት አይቻልም፡፡ ሙሰኛ ትራፊክም የለም ለማለት ይከብዳል፡፡ አብዛኛውን ህጋዊ የትራፊክ ፖሊስ ባይመለከትም፡፡ በነገራችን ላይ የደንቡ ዋነኛ አላማ እየተባባሰ የመጣውን የትራፊክ አደጋ እንዲሁም በህይወትና ንብረት ላይ እየደረሰ ያለውን ጥፋት ለመቀነስ ነው፡፡ ደንቡ በዚህ መንገድ መታየት አለበት፡፡ ከዚያ አልፎ ደንብ እየተላለፈ ብዙ ስህተት የሚሰራ አሽከርካሪ፤ ከስንቱ ትራፊክ ፖሊስ ጋር ተደራድሮ ይችለዋል? አቅሙም አይፈቅድም፡፡ አንድ ቦታ ላይ አጥፍቶ ለአንድ ትራፊክ ጉቦ ቢከፍል ካልተጠነቀቀ ሌላም ምግባረ ብልሹ የትራፊክ ፖሊስ ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ከዚህ ሁሉ የሚሻለው ደንብና ስርዓቱን አክብሮ ማሽከርከር ነው፡፡ አንዳንድ ምግባረ ብልሹ የትራፊክ ፖሊሶችም የቱንም ያህል ቢጠነቀቁ ከህግ አይን አያመልጡም፤ ከነሱም በላይ እነሱን መቆጣጠሪያ ስልቶች አሉ፡፡ ነገር ግን አሽከርካሪውም ሆነ እግረኛውም እንዲሁም ህግ አስከባሪው አካል ሃላፊነታቸውን ተወጥተው ቢሰሩ የሰው ህይወትም የንብረት ጥፋትም ይቀርና አገር በኢኮኖሚም በማህበራዊም ጐን ታድጋለች፡፡
አንዳንድ የታክሲ ባለንብረቶች ሹፌሮቻቸው አድማ አድርገው ታክሲያቸውን ግቢያቸው ስላቆሙ ብቻ ታርጋ እንደተፈታባቸውና በዚህም ማዘናቸውን ተናግረዋል፡፡ ይህስ አግባብ ነው ይላሉ?
አንዳንድ የታክሲ ባለንብረቶች ከአሽከርካሪዎች ጋር የሚገቡት ውል ተገቢ ያልሆነ ነው፡፡ ከአሽከርካሪ ጋር ውል ሲገቡ ሹፌሩ በሁሉም ነገር ተጠያቂነቱን መውሰድ አለበት፡፡ ታክሲ ስራ ሲያቆም ህዝቡ አገልግሎት ያጣል፤ ያን ጊዜ ባለቤቱ አሽከርካሪውን ለምን ብሎ መጠየቅና ታክሲው አገልግሎት እንዲሰጥ ካላደረገ ተጠያቂ ነው፡፡ በዚህ አግባብ ይመስለኛል የታክሲው ታርጋ የተፈታው፡፡ ውል ሲዋዋሉ ባለንብረቶች ሹፌሩን ሙሉ ተጠያቂ ካደረጉ እነሱ ነፃ ናቸው፡፡ ካልሆነ ግን ታክሲው ህዝብ ማገልገሉን ሲያቆም የማይጠየቁበት ምክንያት የለም፡፡
ህጉ ካልተሻሻለ አንሰራም ብለው በድጋሚ አድማ ቢመቱ ምን ታደርጋላችሁ?
እንዲህ አይነት አድማ ይደገማል ብለን አናስብም፤ አይደገምምም፡፡
በምን እርግጠኛ መሆን ይቻላል?
መቶ በመቶ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ሊከሰት ይችላል፡፡ መንግስት ግን በዋናነት እየሰራው ያለው ትልቅ ስራ አለ፤ ይህም ትራንስፖርቱን ከታክሲ ተፅዕኖ ማላቀቅ ነው፡፡ ወደፊት ታክሲ አማራጭ ትራንስፖርት እንጂ ዋና የትራንስፖርት አውታር መሆኑ ይቀራል፡፡
እንዴት ነው ትራንስፖርቱን ከታክሲ ተፅዕኖ ለማላቀቅ የታሰበው?
አንደኛው መንገድ የአንበሳ አውቶቡሶችን ቁጥር ማብዛት ነው፡፡ ሌላው የግል የአውቶብስ ድርጅቶችን ማበረታታት ነው፡፡ ለምሳሌ አሊያንስ ትራንስፖርት በስራ ላይ ያለ የትራንስፖርት ድርጅት ነው፡፡ በቅርቡ 300 አውቶብሶችን ጨምሮ ስራውን ይቀጥላል፡፡ መንግስትም በመጪው ግንቦትና ሰኔ ወር አካባቢ “ሸገር የብዙሀን አውቶቡስ ድርጅት” በሚል ድርጅት አማካኝነት 300 አውቶቡሶችን ይዞ ስራ ይጀምራል፡፡ ፐብሊክ አውቶቡሶችም በስፋት እየሰሩ ነው፡፡
አድማው በተከሰተ ጊዜ እነዚሁ ባሶችና አንበሳ አውቶቡስ የማህበረሰቡን የትራንስፖርት ችግር ለመፍታት ከፍተኛ ስራ ሲሰሩ ነበር፡፡ በእነዚህና መሰል አማራጮች ትራንስፖርቱን ከታክሲው ተፅዕኖ ለማውጣት ታስቧል፡፡

Read 3666 times