Saturday, 05 March 2016 10:51

የ“ቲያንስ” ኔትዎርክ መሪዎች እየታሰሩ ነው

Written by 
Rate this item
(21 votes)

• 11 ዋና አከፋፋዮች ታስረዋል፤ የዋስትና ጥያቄያቸው በፍ/ቤት ተቀባይነት አላገኘም
• በርካታ ሺ ሰዎች በአባልነት ተመዝግበዋል መግቢያ 4ሺ ብር ይከፈላል
• ቲያንስ 700 ገፅ ደብዳቤ፣ የ15ሺህ ሰዎች የድጋፍ ፊርማ ለጠ/ሚ ቢሮ አስገብቻለሁ ብሏል

   የቻይናው ኩባንያ ቲያንስ፤ ሰፊ የምልመላ ዘመቻ በርካታ ሺ ሰዎችን ያስተሳሰረ መረብ መዘርጋት አለመዘርጋቱ አይደለም አከራካሪው ጉዳይ፡፡ የመረቡ አሰራርና አላማ ነው አወዛጋቢው ጥያቄ። የቪታሚንና የሚኒራል ክኒኖችን እንዲሁም ቅባቶችን እንደሚሸጥ የሚገልፀው ቲያንስ፤ ለዚህም “የኔትዎርክ ግብይት”ን እንደሚጠቀም ይናገራል፡፡
አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ የድርጅቱ አላማ ሸቀጣሸቀጥን መሸጥ ሳይሆን፣ በዚሁ ሽፋን የአባልነት መመዝገቢያ ክፍያ መሰብሰብ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ የተዘረጋው መረብም፣ በፒራሚድ ቅርጽ የተሸረበ ነው ብሏል - አቃቤ ህግ፡፡ ኩባንያው የፒራሚዱ የላይኛውን ጫፍ በመያዝ ይመለምላል፡፡ አስር ሰዎችን ቢመለምል የፒራሚዱ 2ኛ ደረጃ ረድፍ ተፈጠረ ማለት ነው፡፡ ተመልማዮቹ በተራቸው፤ እያንዳንዳቸው አስር አስር ሰው መልምለው በአባልነት እየመዘገቡ ለኩባንያው ያስተላልፋሉ፤ እነሱም ኮሚሽን ያገኛሉ፡፡ መቶ አዳዲስ አባላት ተፈጠሩ ማለት ነው - የፒራሚዱ ሶስተኛ ረድፍ፡፡ እነዚህም  የከፈሉትን 4ሺ ብር ለማካካስ አዳዲስ አባላትን መመልመል አለባቸው፡፡   
መቶዎቹ አባላት አስር አስር ሰዎችን ሲመለምሉ፣ ለራሳቸው ኮሚሽን ያገኛሉ፤ ከነሱ በላይ ላሉት ቀደምት መልማዮችም ክፍያ ይደረግላቸዋል፡፡ ከታች ደግሞ አራተኛ ረድፍ ተፈጥሯል - አንድ ሺ አባላትን ያሳለፈ፡፡
እነዚህም በተራቸው፤ ኮሚሽን ለማግኘት 10ሺ አዳዲስ አባላትን መመልመል ሊኖርባቸው ነው - ከታች አምስተኛ ረድፍ በመፍጠር፡፡ እነዚህም እንዲሁ፣ ለአባልነት የከፈሉት ገንዘብ ቀልጦ እንዳይቀር 100ሺ አባላትን መመልመል የግድ ይሆንባቸዋል፡፡ እነዚህም ከኪሳራ ሊድኑ የሚችሉት አንድ ሚሊዮን አባላትን መልምለው ክፍያ ከተቀበሉ ብቻ ነው፡፡
እነዚህ ግን ለምዝገባ የከፈሉት ገንዘብ ቀልጦ ይቀራል፤ አዲስ አበባ ውስጥ አዲስ አባል ሆኖ ሊመለመል የሚችል 10 ሚሊዮን ሰው የለም፡፡
ከፒራሚዱ የላይኛው ጫፍ ላይ ያለው አውራ፣ ከስሩ ያሉት አስር ሰዎች፣ ምናልባትም ቀጥለው ያሉት መቶ ሰዎች፣ ብዙ ገንዘብ ይሰበስባሉ፤ ከታች ያሉት መቶ ሰዎች፤ ብዙ ገንዘብ ይሰበስባሉ፤ ከታች ያሉት ብዙ ሺ ሰዎች ግን ገንዘባቸው የውሃ ሽታ ሆኖ ይቀራል፡፡ ቲያንስ እንዲህ አይነት በፒራሚድ ቅርጽ የተሸረበ ኔትዎርክ ይጠቀማል ይላል አቃቤ ህግ፡፡ የቲያንስ ሃላፊዎች ግን ያስተባብላሉ፡፡ ጥራት ያለውን ምርት ለመሸጥ የኔትዎርክ ግብይትን አከናውናለሁ በማለትም ይከራከራል፡፡  የኔትዎርክ ግብይትን የሚደግፍም ሆነ የሚከለክል ህግ ስለሌለ፣ የንግድ ፈቃድ የተሰረዘብኝ አላግባብ ነው ብሏል ድርጅቱ፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት 700 ገፅ ደብዳቤ፣ ከ15 ሺህ የድጋፍ ፊርማ ጋር አያይዤ አስገብቻለሁ ይላል፡
አቃቤ ህግ በበኩሉ፣ ቲያንስ በሸቀጥ ሽያጭ ሳይሆን በአዲስ አበባ አስር ክፍለ ከተሞች፣ የአባልነት ክፍያ እየጠየቀ ብዙ ገንዘብ ሰብስቧል ብሏል፡፡ በዚሁ መረብ አቀናባሪና አስፈፃሚ ሆነዋል ያላቸውን 11 ሰዎችንም ያሰረ ሲሆን፣ ተጠርጣሪዎች ከትናንት በስቲያ ፍ/ቤት ቀርበው በዋስ እንዲለቀቁ ጠይቀዋል፡፡ ይህን እንደሚቃወም የገለፀው አቃቤ ህግ፣ ምርመራ ለማጠናቀቅ ተጨማሪ ጊዜ ያስፈልገኛል ብሏል፡፡ ፍ/ቤቱ የሁለት ሳምንት ጊዜ በመፍቀዱ ተጠርጣሪዎቹ በእስር ይቆያሉ ተብሏል፡፡

Read 12084 times