Saturday, 05 March 2016 10:50

“በሀገሪቱ የተፈጠሩ ግጭቶች፤ የዲሞክራሲና መብት እጦት መገለጫዎች ናቸው” - ቃዋሚዎች “የሀገር ሽማግሌዎች በጉዳዩ ጣልቃ መግባት አለባቸው” የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ - ወ/ጊዮርጊስ

Written by  አለማየሁ አንበሴ
Rate this item
(28 votes)

    ዘንድሮ ኦሮሚያን ጨምሮ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ ተቃውሞዎችና ግጭቶች ዋነኛ መነሻቸው የዲሞክራሲና የመብት ጥያቄዎች መሆናቸውን አንጋፋ ፖለቲከኞችና ተቃዋሚዎች ገለፁ፡፡
የህዝብ ድምጽ መወከያ የሆኑ ተቋማት በገዥው ፓርቲ ብቻ በመያዛቸውና የሚዲያ ተቋማት እየቀጨጩ በመምጣታቸው፣ ህዝቡ ጥያቄውን፣ ብሶቱንና ሀሳቡን የሚገልጽባቸው መድረኮችን በማሳጣታቸው፣ ተቃውሞዎችና ግጭቶች መበራከታቸውን የገለፁት ፖለቲከኞቹ፤ መንግስት የህዝቡን ጥያቄዎችና ብሶቶች በሃይል ለማዳፈን መሞከሩ፣ ለሀገሪቱ ሠላም ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጣ ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ የተፈጠረው ችግር መነሻው “የማስተር ፕላን” ጉዳይ ይሁን እንጂ፣ ዋናው የመብትና የዲሞክራሲ ጥያቄ መሆኑን የገለፁት የአረና ፓርቲ አባል አቶ ገብሩ አስራት፤ ግጭቶቹ የተባባሱት፣ በመሬት ጥያቄ ውስብስብነት፣ በኢኮኖሚ አጠቃቀም ልዩነትና መንግስት ጥያቄውን እያስተናገደበት ባለው ጉድለት ሳቢያ ነው ብለዋል፡፡
የመሬት ባለቤትነትና የኑሮ ዋስትና ጥያቄ በኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን በሁሉም ክልሎች እንዳለ የጠቆሙት አቶ ገብሩ፤ መንግስት ይሄን ጥያቄ ላለፉት 25 አመታት መመለስ ካለመቻሉም በላይ፣ ህዝቡ ሃሳብና አስተያየት የመስጠት ነፃነቱን በመነፈጉ፣ ሃገሪቱን ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ እየመራት ነው የሚል ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡
“ማስተር ፕላን” ወይም “የወልቃይት ጥያቄ” የሚለው ከብዙ ሌሎች ጥያቄዎች መሃል የሚሰነቀር ቁንፅል ጥያቄ ነው የሚሉት አቶ ገብሩ፤ “ዋናው ጥያቄ የመብት፣ የዲሞክራሲና የነፃነት ነው” ብለዋል፡፡
መንግስት የህዝቡን ጥያቄ ጠንቅቆ እንዳላወቀና ለችግሩ እየሰጠ ያለው መፍትሔም ዘላቂ ሰላም እንደማያሰፍን የሚያስረዱት ፖለቲከኛው፤ መንግስት የራሱን መሠረታዊ ውስጣዊ ችግር ከመመልከት ይልቅ ሻዕቢያ፣ የውጭ ፀረ ሠላም ሃይሎች እያለ ወደ ሌሎች ጣቱን መቀሰሩ የህዝቡን ጥያቄ በአግባቡ እንዳይገነዘብና ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት እንዳይችል አድርጐታል ብለዋል፡፡
በሀገሪቱ ያለው የብሔር ጥያቄ የቆየ ጉዳይ መሆኑን፤ ምላሽ አግኝቷል ብለው ግን እንደማያምኑ የጠቆሙት አቶ ገብሩ፤ ሆኖም፤ ግጭቶቹ በጽንፈኛ ብሔርተኝነት ጥያቄ የተፈጠሩ ናቸው በሚለው ሃሳብ እንደማይስማሙና የጥያቄዎቹ ማጠንጠኛ የዲሞክራሲና የመብት እጦት መሆኑን ይናገራሉ፡፡
መንግስት ለተቃውሞው የሃይል ምላሽ መስጠቱ አግባብ አለመሆኑን የገለፁት አቶ ገብሩ፤ ጥያቄዎች በሃይል ቢዳፈኑም አይጠፉም” ብለዋል፡፡ ወደ ሻዕቢያና የውጭ ሃይሎች ማላከክ አቅጣጫ ከማሳጣት ውጪ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም እንደማይበጅም ገልፀዋል፡፡
“አረና” በቅርቡ በትግራይ ክልል ሠላማዊ ሠልፍ እንዳያደርግ መከልከሉን የጠቀሱት አቶ ገብሩ፤ ይሄ አይነቱ አፈና ለህዝባዊ አመፆች በር ከፋች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መንግስት ይሄን አካሄድ መምረጡ ለሀገሪቱ የማይበጅና ከፍተኛ ስጋት የሚያጭር ነው ያሉት ፖለቲከኛው፤ መንግስት የፖለቲከኞችና የህዝቡን ጥያቄ አጢኖ በውይይት መፍትሔ የማበጀትና ሀገሪቷን ከጥፋት የመታደግ ሃላፊነት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የኢዴፓ አባል አቶ ልደቱ አያሌው በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩት ተቃውሞዎችና አመፆች መነሻቸው ማስተር ፕላኑን የመሳሰሉት ምክንያቶች ይሁኑ እንጂ በዋነኛነት የዲሞክራሲ እጦትና የመብት ጥሠቶች የፈጠሩት ነው” ይላሉ፡፡
ባለፉት 25 አመታት ስርአቱ እየተከተለ ያለው አቅጣጫ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን የሚያሰፋ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ልደቱ፤ ግጭቶቹም የዚሁ ቀጥተኛ ውጤት ናቸው ይላሉ፡፡ የሀገሪቱ ሁኔታ በእጅጉ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን የጠቀሱት ፖለቲከኛው፤ ልዩነቶችና ቅራኔዎች እየተባባሱ ለመምጣታቸው የስርአቱ ድርሻ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
በምርጫ 2007 ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፓርላማ አንድም የተቃውሞ ድምጽ ማስተናገድ የማይችል ስርአት መፈጠሩን የጠቀሱት አቶ ልደቱ፤ የግል ሚዲያዎች መቀጨጭ ተደምሮበት ቅሬታዎች፣ ሃሳቦችና ጥያቄዎች የሚቀርቡበት አማራጮች በሙሉ መዘጋታቸው የችግሩ ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው ይላሉ፡፡
መንግስት ራሱን ለእውነተኛ ተሃድሶ ማዘጋጀት እንዳለበት የመከሩት ፖለቲከኛው፤ እየተከተለ ያለውን አቅጣጫ እንዲሁም የፌደራል ስርአቱን በእርጋታ በመመርመር፤ ህብረተሰቡ ብሶቱን የሚያሰማበት ዲሞክራሲያዊ መድረክ ማመቻቸት አለበት ብለዋል፡፡
የችግሩ መንስኤ የህገ መንግስቱ በትክክል አለመተግበር ነው የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በበኩላቸው፤ በ21 አመት ውስጥ ህገ መንግስቱ ለሀገሪቱ ህዝቦች ምን አዎንታዊ፣ ምን አሉታዊ ውጤት አመጣ የሚለው አለመገምገሙና የህገ መንግስቱ አቅም አለመፈተሹ የዲሞክራሲና የመብት ጥያቄዎች አይለው እንዲወጡ አድርጓል ይላሉ፡፡
የኢኮኖሚና የሃብት ክፍልልም የተቃውሞና የግጭቶቹ መንስኤ ሊሆን ይችላል ያሉት ፖለቲከኛው፤ በአዲስ አበባ ብቻ ሣይሆን ከክልል ከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞም በዙሪያቸው ለሚነሱ ገበሬዎች በቂ ማቋቋሚያ ካሣ እየተከፈለ ነው ወይ የሚለው መመለስ ያለበት ጥያቄ ነው ብለዋል፡፡ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚነሱት ጥያቄዎች የብሔር ይምሰሉ እንጂ ከጀርባ ያለው ጥያቄ የዲሞክራሲ፣ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት፣ የህገመንግስት አፈፃፀምና አተገባበር ጥያቄዎች ናቸው ይላሉ፤ ዶ/ር ነጋሶ፡፡
በተለይ በኦሮሚያ ያለው ችግር ቀላል አይደለም የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ፤ ችግሮቹ  ባለስልጣናትን በመሾምና በመሻር ብቻ ይፈታሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው ጠቁመው፣ በክልሉ ጉዳይ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሀገር ውስጥም በውጭም ያሉ፣ የሚሳተፉበት ሰፊ የውይይት መድረክ ቢፈጠር መልካም ነው ብለዋል፡፡
“አሁን ክልሉን እያስተዳደረ ያለው ኦህዴድ ምን ያህል የህዝብ ተቀባይነት አለው?” የሚለውን መመርመር እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡ “መንግስት ነገሮች ከእጁ እያመለጡና እየተቀደመ ይመስለኛል” ያሉት ፖለቲከኛው፤ ችግሩን በሃይል ለመፍታት የሚደረገው ሙከራ ዘላቂ መፍትሔ አያመጣም ሲሉ መክረዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በበኩላቸው፤ መንግስት የችግሩ ፈጣሪዎችን በተደጋጋሚ እያስጠነቀቀ፣ ነገሮችን በትዕግስት እየተመለከተ መሆኑን ጠቅሰው፣ ችግሮቹ ሃገሪቱን ወደበለጠ አደጋ ሳይከቱ በእንጭጩ መቀጨት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ለሚነሱ ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠትና ግጭቶች እንዳይፈጠሩ ለመከላከል በየአካባቢው የሀገር ሽማግሌዎች ህብረት እየተመሠረተ መመከር አለበት ያሉት የቀድሞው ፕሬዚዳንት፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ያሉ የሽምግልና ማህበራትም በጉዳዩ ጣልቃ መግባት አለባቸው ብለዋል፡፡  

Read 5814 times