Saturday, 27 February 2016 11:52

“ምን አዲስ ነገር አለ…”

Written by  ኤፍሬም እንዳለ
Rate this item
(37 votes)

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ስሙኝማ…በሰላምታ ልውውጣችን ላይ የሆነ ኮንፍረንስ ይዘጋጅልን እንጂ! ከዚህ በፊት እንዳወራነው የእውነት የሆነ የመልካም ምኞት መግለጫ እየጠፋ ነው። ሰላምታችን ሁሉ በ“ምን አዲስ ነገር አለ!” እያለቀ ነዋ፡፡ የምር ግን…
“ለመሆኑ በጎ ሰነበትክ ወይ?”   
“እንደው ዘመድ አዝማድ ሁሉ ለጤናቸው ደህና ከርመዋል?”
“ባለቤትሽ ልጆችሽ በጤና ከረሙ?”
“እኛ ደህና ነን፣ እናንተስ እንዴት ናችሁ?” ምናምን አይነት ነገር መባባል የሆነ የሚያሳድረው ነገር አለ፡፡
እናላችሁ… በምናምነኛው ‘ኤሌከሽን’ (ቂ…ቂ…ቂ…) ጊዜ ያገኛችሁ ሰው ገና ሲያያችሁ…
“እንዴት ከረምክ፣  ለመሆኑ ቤተሰብ፣ ዘመድ አዝማድ ደህና ነው?” ምናምን ከማለት ይልቅ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ምን አዲስ ነገር አለ!”
ልክ አይደለማ! መጨረሻ ጊዜ ከተገናችሁ በኋላ የአክስታችሁ ልጅ ሦስት ወልዳ አራተኛውን እየጠበቀች “ምን አዲስ ነገር?” አለ ብሎ ሰላምታ ምንድነው!
ደግሞላችሁ…ከዚህ በፊት እንዳወራነው ግራ የገባው ነገር የሰላምታው ነገር ብቻ ሳይሆን ተከትለው የሚመጡት ነገሮች ናቸው፡፡ አለ አይደል…ምን አይነት ህይወት እያሳለፋችሁ እንደሆነ ሳያውቅ፣ ሳትተያዩ በከረማችሁባቸው ዓመታት ምን እንደገጠማችሁ ምናምን ይቺን ታክል ሳያውቅ ዘሎ ህይወታችሁ ውስጥ ሊገባ ይሞክራል፡፡
“ስማ፣ ያቺ ሚስትህ አለች?”  ያቺ ሚስትህ! እንዴት ነው ነገሩ! መቼም ጊዜው የፈለገው ያህል ግራ ሲሉት ቀኝ እየሆነ ቢያስቸግርም ያቺ የቀረችው ይሉኝታ የሚሏት ነገር ከአንደበታችሁ ሰብሰብ ታደርጋችኋለች፡፡
“አዎ፣ አለች…” ቀጥሎ ‘ሳምልኝ’ ‘እንዴት ነሽ ብሎሻል’ በልልኝ ይላል ብላችሁ ስትጠብቁ ምን ቢል ጥሩ ነው…
“ዩ ዶንት ሚን ኢት!  እስከ ዛሬ አንድ ላይ ናችሁ?” ይላል፡፡ “እስከ ዛሬ አንድ ላይ ናችሁ?” ብሎ ነገር ምን ማለት ነው! ይሄን ጊዜ ቀዳዳ ያገኘው ሉሲፈር… ምን አለፋችሁ… አምሯችሁን ሰርስሮ ይገባና ለሽ ይላል፡፡
“እኔ እኮ… የመጀመሪያዎቹ ሁለት ልጆቼን ምንም እኔን የሚመስል ነገር ሳጣባቸው ደስ አላለኝም ነበር! ሰውየው እኔ ሳልኖር እየገባ ‘ዋን ፎር ዘ ሮድ’ ይል ነበር እንዴ!” (እግረ መንገዴን…የሆነ ነገር ትዝ አለኝማ… ለበርካታ ዓመታት ጎን ለጎን ይኖሩ የነበሩ ጎረቤታሞች ነበሩ፡፡ እናማ…ሴትዮዋ ይቺን ዓለም ሊሰናበቱ አልጋ ይዘው በመጨረሻዋ ሰዓት ምን ቢያደርጉ ጥሩ ነው…የአሥራ ምናምን ዓመት ወንድ ልጃቸው የ‘አባትየው’ ሳይሆን የጎረቤትየው እንደሆነ ተናዘዙ ሲባል ሰምተናል፡፡)  
“ስለ እኔ ሚስት ምነው እንዲህ ተቆረቆረ! ይቺ ሴትዮ ቤተ ጸሎት በመሄጃዋ ጊዜ ወደ ሌላ ቤተ ምናምን መሄድ ጀምራለች እንዴ!”
እናላችሁ…እንኳን ሰበብ ተገኝቶ ዘንድሮ በሁሉም ነገር ተጠራጣሪ ነን አይደል…ከእንትኑ አርቆ የማያስብ ሰው በተናገረው ትረባበሻላችሁ፡፡
አንድ ወዳጄ በዛ ሰሞን አንድ የሚያውቀውን ሰው ከረጅም ጊዜ በኋላ ድንገት የሆነ ቡና ቤት ነገር ላይ ያገኘዋል፡፡ እመኑም አትመኑም አይነት ነገር ባልልም ሰላምታ እንኳን ሳይሰጠው ምን አለው መሰላችሁ…
“ስማ ትናንት ማታ ቲቪ አይተሀል?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡ ወዳጄ ግራ ይጋባል፡፡ እንዲህ አይነት ጥያቄ የሚጠብቅ የለማ!
“አላየሁም…” ሰውየው ቆጣ እንደማለት ይላል፡፡
“ለምን አላየህም?” እንዴት፣ እንዴት ነው ነገሩ። “ሰውስ ምን ይለኛል!” የሚለው ነገር ወዳጄን ባይሸብበው ኖሮ ትክክለኛው መልሱ “ምን አ…ክ አገባህ!” ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን “ምን አ…ቱ አገባው!” የሚያሰኝ ነው፡፡
ወዳጄ “ይቺ ሰውዬ ወይ ‘ትኩስ ሌኒን’ ምናምን ነች፣ ወይ በአንዳንድ የአዲስ አበባ ነዋሪነት በቲቪ ብቅ ብላለች” ብሎ ያስብና ምን ቢለው ጥሩ ነው…
“እኔ የአገር ውስጥ ሚዲያ አልከታተልም፡፡”
ሰውየው ትንሽ ግር እንደማለት ይለውና ሳይሰናበት እንኳን በቆመበት ትቶት ሄደ፡፡ ወዳጄ በኋላ ቆጭቶት “ምን አለ እኔም ‘ትናንት ማታ ቢቢሲ አይተሀል’ ብለው ኖሮ!” እያለ ሲቆጭ ነበር፡፡
የምር…ዘንድሮ ብዙ ‘ኦድ’፣ በጣም ‘ኦድ’ የሆንን ሰዎች በዝተን የለ… እንዲህ አይነት ሰው ደግሞ የባሰበት ነው፡፡ ካልጠፋ ጥያቄ “ማታ ቲቪ አይተሀል ወይ?” ብሎ ጥያቄ አለ እንዴ! የምር ግን “ለምን አላየህም?” “ለምን አልሰማህም?” ብሎ ሙግት የሚገጥም ሰው ሲኖር አሪፉ መልስ ምን መሰላችሁ…
“ሀኪም ከልክሎኝ!”
አሪፍ አይደል!
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…የምር ምናለ ‘ይህንን አትመልከት፣’ ‘ይህንን አትስማ’ የሚል ሀኪም በመጣና በገላገለን የሚያሰኙ ነገሮች አሉ፡፡
እናላችሁ…“ምን አዲስ ነገር አለ?” ብሎ ‘ሰላምታ’ አልበቃ ብሎ ተከትለው የሚመጡ ነገሮች አስቸጋሪ እየሆኑ ነው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል… አንድ ጊዜ ሰው በተሰበሰበበት… “አጅሬ እንደ ድሮው ሴቶችን ታሰልፋለህ?” ስለተባለ ሰው ሰምተናል፡፡ ሰውየው እኮ የተረጋጋ ትዳር ያለውና የልጆች አባት ነው፡፡
እናላችሁ…እያንዳንዷ የስልክ ጥሪና የጽሁፍ መልእክት ጥርጣሬ በምትፈጥርበት በዚህ ዘመን ሚስት ይህንን ብትሰማ ምን ልታስብ እንደምትችል አስቡት፡፡ ምንም እንኳን ከመገናኘታቸው በፊት የነበረው ህይወት የየራሳቸው የግል ጉዳይ ቢሆንም ሉሲፈር መች እጁን አጣጣፎ ቁጭ ይላል! የእሷዬዋን አእምሮ ዘይት ያነሰው ሞተር አድርጎ ዝብርቅርቁን ነው የሚጭንባት፡፡
“አጅሬው ድሮ እንዲህ አይነት ጠባይ የነበረው ከሆነ አሁንም እኔ ሳላየው እየማገጠ ይሆናል፡፡”
“ያቺ የአብሮ አድጌ እህት ነች የሚላት የድሮ እንትኑ ሳትሆን አትቀርም፡፡”
“በዛ ሰሞን ደከመኝ እያለ ጀርባውን ሲያዞር የነበረው ለካስ ውጪ እየተንከባለለልኝ ነው!”
ደግሞ አንዳንዱ አለላችሁ…ገና ሲያገኛችሁ…
“አንተ ሰውዬ ግን እዚህ አገር ቆርበሀል እንዴ! ለምን አትወጣም!” ይላችኋል፡፡ የምር… ልክ እኮ ለሁሉም አገር የሚሆን ቪዛ የሚሰጣችሁ ነው የሚመስለው፡፡
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እንደ እኛ ደግሞ የሚሞነጫጭር… አለ አይደል….ገና ሲያገኛችሁ ልክ የሆነ ሬድዮ ጣቢያ በሰው ተመስሎ የመጣ ያስመስለዋል፡፡ በቅጡ እንኳን ሰላምታ ሳይሰጣችሁ…
“ስማ፣ የአገራችን ሁኔታ እንዴት ነው?” ምናምን ይላችኋል፡፡ ቤቱ ሬድዮ ከሌለው ሻይ ቤት ምናምን ሄዶ አይሰማም! ወይንም… “ኑሮ እንዴት እያደረገህ ነው?” ምናምን አይነት ነገር ሳይላችሁ ይዘልና…
“ስማ መቼም ወሬ ማነፍነፍ የሚችላችሁ የለም…” ይልና ወይ…
“እንትና የሚሉት ሰውዬ ታሟል የሚሉት እውነት ነው?” ይላችኋል፡፡ እናንተ የሆስፒታል መዝጋቢ ናችሁ! ድሬሰር ናችሁ! ልምድ ‘አዋላጅ’ ናችሁ!…ለምን ሄዶ የሰውየውን ‘ዋይፍ’ ምናምን አይጠይቅም፡፡ ወይ ደግሞ…
“ስማ… ሰውየው አውስትራሊያ ነው ምናምን ከዳ የሚባለው እውነት ነው?” ይላችኋል፡፡ ልክ እኮ ሰውየውን አበባ ይዛችሁ ቦሌ ላይ…አለ አይደል… “በሰላም ለመክዳት ያብቃህ!” ብላችሁ የሸኛችሁት ያስመስሉታል፡፡ እግረ መንገዴን…ሚዲያ ላይ ያሉ ሰዎች ሁሉንም ነገር ያውቃሉ ብሎ ማሰብ አሪፍ አይደለም፡፡ ልክ ነዋ… አይደለም ከህብረተሰቡ የተሻለ፣ የህብረተሰቡን ያህል የማናውቅ መአት መሆናችን ግንዛቤ ይያዝልንማ!
ሀሳብ አለን…“ምን አዲስ ነገር አለ” የሚለው ሰላምታ ይለወጥልን፡፡ ምናልባትም ተከትለው የሚመጡት ነገሮች ይሻሉ ይሆናል፡፡
ደህና ሰንብቱልኝማ!

Read 20534 times