Saturday, 20 February 2016 10:01

“እንቀጥልበታለን እንጂ ወደኋላ መሄድ የለም”

Written by  መንግሥቱ አበበ
Rate this item
(2 votes)

    አክሽን ኤይድ ኢትዮጵያ ወየም ልዩ ወረዳ የገባው በ1994 ዓ.ም ነው፡፡ እንደገባ ወዲያው ሥራ አልጀመረም፡፡ ከኅብረተሰቡና ከመንግሥት ተወካዮች ጋር ቁጭ ብሎ ዋና ዋና ችግሮቻችሁ ምንድናቸው? ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡትስ የትኞቹ ናቸው? … በማለት ተወያየ፡፡ ተወካዮቹም ዋና ዋና ችግሮቻቸው ብዙ ቢሆኑም ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ብለው የጠቀሱት በዋናናነት ውሃን ነው፡፡
አክሽን ኤይድ ለ12 ዓመታት 50 ሚሊዮን ብር ያህል ወጪ በማድረግ፣ በአራት ዘርፎች ሲሰራ ቆይቶና ለየም ልዩ ወረዳ ያዘጋጀውን የልማት ፕሮግራም አጠናቅቆ፣ በ2015 መጨረሻ ወጥቷል፡፡ ለመሆኑ ያከናወናቸው ተግባራት ምንድናቸው?
የምግብ ዋስትና፡- ልዩ ወረዳው ከፍተኛ የምግብ ዋስትና እጥረት ነበረበት፡፡ ስለዚህ ማኅበራትን (ኮኦፖሬቲቭ ዴቨሎፕመንት) አደራጀ፡፡ 29 መሰረታዊ ማኅበራትን በማቋቋም አስፈላጊ ድጋፍ በማድረግና በማሰልጠን ከመሰረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራት እስከ ገበሬዎች ኅብረት ሥራ ዩኒየን ማድረሱን የአክሽን ኤይድ የየም ልዩ ወረዳ የልማት አስተባባሪ አቶ ሰለሞን አየለ ገልጿል፡፡
በሰብል ልማት አነስተኛ መስኖዎችን በመስራት የተጠቃሚዎች ማኅበራት እንዲቋቋሙ አድርጓል፡፡ ከተለያዩ አካባቢዎች አፕል (ፖም) በማምጣት ለገበሬዎች አከፋፍሏል፡፡ የጊቤን ተፋሰስ ዙሪያን ይዞ አካባቢው ለብዙ ዘመናት የገንዲ በሽታ የሚያመጣው የቆላ ዝንብ መናኸሪያ ነበር፡፡ በዚህ የተነሳ ሕዝቡ አንድ ቦታ አይቀመጥም፡፡ ሰው፣ “ለምን አንድ ቦታ ተቀምጠህ አታርስም?” ሲባል፣ “በምን በሬ አርሳለሁ?” ይላል፡፡ ስለዚህ ሳጃና ቶባ በተባሉ አካባቢዎች ሁለት የቆላ ዝንብ መከላከያና መቆጣጠሪያ ማኅበር ስላቋቋሙ አሁን ሕዝቡ እፎይታ አግኝቷል፡፡
የሴቶች ልማት፡- ይህን ዘርፍ በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ ሴቶችን በኢኮኖሚ የበላይ ማድረግና በሴቶች ጥቃት ተከላካይ ቡድን፡፡ ሴቶች ገንዘብ ቢያገኙም በገንዘቡ አይጠቀሙም፤ ውሳኔ መስጠት አይችሉም፡፡ አንዱ የአክሽን ኤይድ ስኬት ሴቶችን ወደ ውሳኔ ሰጪነት ወይም ለመሪነት ለማብቃት የሰራው ሥራ ነው፡፡ በማስተማርና የሊደርሺፕ ሥልጠና በመስጠት ብዙ ሴቶችን ለአመራር ስፍራ አብቅቷል፡፡ በ29ኙም ማኅበራት በአመራር ላይ ያሉት ሴቶች ናቸው፡፡
ቀደም ሲል ሴቶች ምንም ዓይነት መብት አልነበራቸውም፡፡ ይደፈራሉ፣ በባሎቻቸው ይደበደባሉ፡፡ ሲፋቱ እንኳ እጅና እግራቸውን ይዘው  ከመውጣት በስተቀር የንብረት ክፍያ የሚባል ነገር የለም፡፡ ሌላው ቀርቶ በወለዷቸው ልጆቿ ላይ እንኳ የማዘዝ መብት የላትም፡፡ ልጀቿን ጥላ እንዲትወጣ ነው የሚደረገው፡፡
አሁን ግን ዕድሜ ለአክሽን አይድ፣ ሁኔታዎች ተለውጠዋል፡፡ በልዩ ወረዳው በሚገኙ 34 ቀበሌዎች 6፣ 6 የጥቃት ተከላካይ ኮሚቴ አባላት ተመርጠዋል፡፡ በአንዲት ሴት ላይ ጥቃት ሲፈፀም በቀጥታ ለኮሚቴው ይነገራል፡፡ ጥቃት ተከላካዮቹ ራሳቸው በመሸምገል መፍታት የሚችሉት ችግር ከሆነ እዚያው ይፈቱታል፡፡ ከአቅም በላይ ከሆነ ከቀበሌ ኃላፊዎች ጋር በመመካከር ጉዳዩን  ለፖሊስ ይመራሉ፡፡ ጉዳዩ ፍ/ቤት ደርሶ ወደ ፍቺ የሚያመራ ከሆነ ንብረት እንድትካፈል ጉዳዩን መልሶ ለጥቃት ተከላካይ ኮሚቴው ይመራል፡፡ ኮሚቴው፣ ባልና ሚስቱ በጋራ ያፈሩትን እንዲናገሩ አድርገው፣ ሴቷ የሚገባት የንብረት ድርሻ አንድ በአንድ ቀጥረው ያስረክቧታል፡፡  
የጥቃት ተከላካይ ኮሚቴ ሴቶች ሳምንቱን፣ ወሩን፣ ዓመቱን ሥራቸው ይኼው ነው፡፡ ለራሳቸው ገቢ ማግኛ የሚሠሩበት ጊዜ የላቸውም፡፡ የሰው ጉዳይ ሳማስል የእኔ ያርራል በማለት ኮሚቴ ሥራውን ችላ እንዳይሉ አክሽን ኤይድ እነሱን ተጠቃሚ የሚያደርግ ተዘዋዋሪ ብድር አዘጋጅቷል፡፡ ሴቶቹ ባገኙት ከድር ሁለት ፍየልና አንድ በግ ይገዛሉ፡፡ እንስሳቱ ሲወልዱ ወይም አደልበው ይሸጡና ሌላ ይገዛሉ፡፡ በዚህ ዓይነት አደልበው በመሸጥ የበሬና የላም ባለቤት የሆኑ አሉ፡፡
የውሃ ፕሮጀክት፡- ፎፋና (የቀድሞ የየም ወረዳ ዋና ከተማ) ሳጃ ከተሞች ላይ ትላልቅ የውሃ ፕሮጀክቶች ተሠርተዋል፡፡ የውሃ ተቋማቱ የሚመሩት በሴቶች ነው፡፡ ቧንቧ እየዘረጉ በየቤቱ ቆጣሪ የሚያስገቡት፣ ሲበላሽ የሚጠግኑት፣ የማስፋፊያ ሥራ የሚሠሩት፣ በአጠቃላይ ውሃን በተመለከተ ሁሉንም ነገር የሚያከናውኑት ሴቶች ናቸው፡፡
የውሃው ፕሮጀክት እንደተቋቋመ በሴቶችና በወንዶች መካከል ኃይለኛ ፀብ ተፈጥሮ ነበር አሉ፡፡ ወንዶች፣ ሴቶች የመምራትና የማስተዳደር ብቃት ስለሌላቸው በማዘጋጃ ቤት ስር ይተዳደር አሉ፡፡ ሴቶቹ ግን “ምን ሲደረግ? በማለት ሽንጣቸውን ገትረው ተከራከሩ፡፡ የውሃ ችግር የመጀመሪያ ደረጃ ገፈት ቀማሳች እኛ ነን፡፡
ሌሊት ወጥተን፣ ወንዝ ወርደን፣ በጀርባ ተሸክመን የምናመጣ እኛ፣ በዱርዬ የመደብደብና የመደፈር አደጋ የሚደርስብን እኛ፤ ኧረ እንዴት ተደርጐ ነው እናንተ አመራር ላይ የምትቀመጡት?” በማለት አምርረው ተከራክረው ነው መሪነቱን ያገኙት፡፡
በተጨማሪም ከሕዝቡና ከመንግሥት ጋር በመሆን በ51 የገጠር ቀበሌዎች ምንጭ ማጐልበታቸውን አቶ ሰለሞን ተናግሯል፡፡ የውሃው ፕሮጀክቱ ቀጣይነት እንዲኖረው 51ዱ ምንጮች በክላስተር ኔትዎርክ እንዲተሳሰሩ ተደርጓል፡፡ የከተሞቹ የውሃ ፕሮጀክቶች ገቢ የሚያገኙት ከውሃ ሽያጭ ነው፡፡
ገቢያቸውን ለማሳደግ ሻወር ቤት እንዲከፍቱ፣ ሰው በየቤቱ ውሃ ሲያስገባ ዕቃዎችን ከእነሱ እንዲገዛ መደረጉን አቶ ሰለሞን ገልጿል፡፡
ትምህርት ፡- መጀመሪያ ላይ ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ልጆች እንደምንም ትምህርት እንዲያገኙ በ1ዐ ማዕከሎች 16 ብሎኮች ተገንብተው ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ከ16ቱ ውስጥ 11ዱ መደበኛ ት/ቤት ቤት ሆነው መንግሥት ተረክቧቸዋል፡፡ ከለጋሾች ባገኙት ድጋፍ በአንድ ት/ቤት 15 ክፍሎች ያሉት 4 ብሎክ፣ አንድ ቤተመጻሕፍት ከነሙሉ ቁሳቁስ ከመቀመጫ ጋር አማልተው ማስረከባቸውን ፕሮግራም አስተባባሪው ተናግሯል፡፡ በርካታ የልጃገረዶች ክበባት ተቋቁመዋል፡፡ ክበባቱ ስለሞዴስ አጠቃቀምና አዘጋጃጀት፣ ሴቶችን ብቻ የሚመለከቱ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሥልጠና ይሰጣል፡፡
አንዲት ልጃገረድ በት/ቤትም ሆነ በመኖሪያ አካባቢ ጥቃት ቢደርስባት ወይም ወላጆቿ ሊድሯት ቢፈልጉ እነዚህ ክበባት ከጥቃት ተከላካይ ኮሚቴ ጋር በመሆን ፈጣን ርምጃ ይወስዳሉ፡፡ በሁለት ት/ቤቶች ደግሞ የልጃገረዶችና የወንዶች ቤተመጻሕፍት ተለያይተው ተሠርተዋል፡፡  

Read 1266 times