Saturday, 20 February 2016 09:29

“የግል ት/ቤቶችን በዘመቻ መክሰስ”፣ መፍትሄ ይሆናል?

Written by  ዩሃንስ ሰ.
Rate this item
(7 votes)

• የንግድ ሚኒስቴር፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ት/ቤቶች ለመክሰስ እንደወሰነ ገልጿል።
• በትምህርት ቤት ክፍያ የተማረሩ ወላጆች ቅሬታ አቅርበዋል ብሏል - ሚኒስቴሩ።
• ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ግል ት/ቤት የሚያስገቧቸው፣ ከመንግስት በመሸሽ ነው።
• አሁን እንደገና፣ መንግስት እንዲመጣባቸው መጋበዝና መወትወት ያዋጣቸዋል?
የወላጆች ቅሬታ፤ “የትምህርት ክፍያ ናረ። ዘንድሮ፣ ከፍተኛ የክፍያ ጭማሪ አድርገዋል።
በትርፍ ተንበሸበሹ”...
• የበርካታ ት/ቤቶች ምላሽ፤ “ወጪያችን በዛ። በተለይ የቤት ኪራይ አራቆተን። ት/ቤት
የከፈትነው ለትርፍ አይደለም”
• ቅሬታና ምላሽ ከመረጃ ጋር ሲተያይ፡ክፍያ ናረ?

   ምን ያልናረ ዋጋ አለ! በአጠቃላይ፣ “ብር ረከሰ፣ ዋጋ ናረ፣ ኑሮ ከበደ” ቢባል ይሻላል። ባለፉት አራት አመታት፣ የእህል፣ የቁሳቁስ፣ የልብስ፣ የህክምና... ወዘተ ዋጋ፣ በአዲስ አበባ በ50% ንሯል። የትምህርት ወጪም በ50% ገደማ።
ከፍተኛ የክፍያ ጭማሪ ተደርጓል? አዎ። በአዲስ አበባ፣ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን፣ በአማካይ ከ30% በላይ የክፍያ ጭማሪ ታይቷል። ነገር ግን፣ አምናና ካቻምና፣ የክፍያ ጭማሪ አልነበረም ማለት ይቻላል - የሌሎች ነገሮች ዋጋ ቢንርም። የቤት ኪራይ ንረት፣ ለግል ትምህርት ቤቶች ትልቁ የራስ ምታት ነው። ነገርዬው፣ መፍትሄ የሌለው ከባድ አጣብቂኝ ይመስላል።
በአንድ በኩል፣ ባለፉት አስር ዓመታት፣ በትምህርት ክፍያ ላይ የሚታየው ጭማሪ፣ በየመስኩ ከሚታዩት የዋጋ ንረቶች የተለየ አይደለም። እንደማንኛውም ሥራ፣ የትምህርት ቤት ስራም፣ በዋጋ ንረት ሳቢያ፣ ከአመት አመት፣ ወጪ እየከበደው ይመጣል - ለምሳሌ በቤት ኪራይ ንረት ሳቢያ።
በሌላ በኩል ደግሞ፣ የትምህርት ቤት ክፍያ፣ ለብዙ ወላጆች ከባድ ፈተና ነው። በጣም ሃብታሞች ብቻ አይደሉም፤ ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት። በአዲስ አበባ፣ ከአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች መካከል፤ ግማሽ ያህሉ፣ የግል ትምህርት ቤት ተማሪዎች ናቸው።
ባለፈው ሰኔ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ያቀረበው አመታዊ ሪፖርት እንደሚያሳየው፤ ከ640ሺ የአዲስ አበባ ተማሪዎች መካከል፣ ግማሾቹ (320ሺ) ያህሉ፣ በግል ትምህርት ቤቶች የሚማሩት ናቸው (Education Statistics Annual Abstract Sene 2007 E.C - ገፅ 108 እና 116)።
 የኮንስትራክሽን ኩባንያ ባለቤት ብቻ ሳይሆን፣ በኩባንያው የተቀጠሩ መሃንዲሶችና ቴክኒሻኖች፤... ትልቆቹ አስመጪና ላኪ ነጋዴዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ አትክልትና ፍራፍሬ በመሸጥ ወይም አነስተኛ ሱቅ በመክፈት የሚተዳደሩ ሰዎችም ናቸው፣ እንደምንም ተቸግረው ልጆቻቸውን፣ ወደ ግል ትምህርት ቤት የሚያስገቡት።
በርካታ የጭነት መኪኖችን የሚያንቀሳቅስ ባለሃብት ብቻ ሳይሆን፣ ሾፌሮችና ሜካኒኮችም ጭምር፤... የማተሚያ ቤት፣ የሬዲዮ ጣቢያና የትልቅ ስቱዲዮ ባለቤቶች ብቻ ሳይሆኑ፣ ተዋናዮች፣ ጋዜጠኞችና ተቀጣሪዎች ጭምር ናቸው፤ ልጆቻቸውን በክፍያ ለማስተማር የሚጣጣሩት። ለምን?
ወጪው ቀላል ስለሆነ ነው? ለትልልቅ ባለሃብቶች፣ ላይከብድ ቢችልም፤ ለአብዛኛው ወላጅ ግን ከባድ ነው። ሌላ አማራጭ ስለሌለ ነው? አይደለም። በነፃ የሚያስተምሩ የመንግስት ትምህርት ቤቶች አሉ፤... ነገር ግን፣ ደካማ ናቸው። እናም፣ ብዙ ወላጆች፣ እንደምንም ወጪውን ተቋቁመው ልጆቻቸውን የግል ትምህርት ለማስገባት ይጣጣራሉ። ከወር ወር እንደምንም አብቃቅተው ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች፣ ዓመቱን እንዴት እንደሚዘልቁት መጨነቃቸው አንሶ፣... ክፍያ እንደተጨመረባቸው ሲሰሙ ምን ያህል እንደሚያናጋቸው አስቡት።
እና ምን ተሻለ? “በትርፍ ተንበሸበሹ” የሚል ቅሬታ አንጠልጥሎ፣ የግል ትምህርት ቤቶች ላይ የክስ ዘመቻ ማወጅ መፍትሄ ይሆናል? “የምንሰራው ለትርፍ አይደለም” የሚል ምላሽ ማዜምስ፣ አሳማኝ መከራከሪያ ይሆናል?
    “በትርፍ መንበሽበሽ?”
በግል ትምህርት ቤቶች ላይ፣ የማጥላላት ዘመቻ እየተባባሰ የመጣው ከሐምሌ ወር ወዲህ ነው። ባለፈው ነሐሴ ወር በሄራልድ የታተመውን ፅሁፍ ተመልከቱ። መንግስት ከ20 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን ታዳጊዎች፣ ትምህርት በነፃ እያቀረበ እንደሆነ ፅሁፉ ገልፆ፣ ትምህርት እንደሸቀጥ መታየት የለበትም በማለት የግል ትምህርት ቤቶችን ይወርፋል። የትርፍ ክምር እያግበሰበሱ መሆናቸውንም ለማሳየት፤ የአንዳንዶቹ ትምህርት ቤቶች ክፍያ፣ እስከ ግማሽ ሚሊዮን መድረሱን ፅሁፉ ገልጿል። እንዲህ አይነት ክፍያ፣ ከሁለት ወይም ከሦስት ትምህርት ቤቶች ውጭ እንደሌለ ግን አልተገለፀም። “ኢንተርናሽናል ኮሙኒቲ ስኩል” የተሰኘው የአሜሪካ ትምህርት ቤት፤ እና ሳንፎርድ... በቃ። ሌሎቹ 500 የሚሆኑ የግል ትምህርት ቤቶች፣ እንደየደረጃቸው በአመት ከአስር ሺ እስከ አርባ ሺ ብር የሚያስከፍሉ ናቸው።
ደግሞስ፣ “በነፃ የቀረበ ትምህርት” መኖሩን የሚያውጅ ፅሁፍ፤ የአሜሪካ ት/ቤት ብዙ ገንዘብ ያስከፍላል ብሎ ለምን ያማርራል? በአብዛኛው፣ የውጭ አገር ዲፕሎማቶች ናቸው፤ ልጆቻቸውን በዚሁ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት። ኢትዮጵያውያንን በገፍ የሚያስተምር ቢሆንስ፣ ለምን ክፍያው ያስጨንቀናል? መክፈል የፈለገና የቻለ ሰው ነው የሚከፍላቸው እንጂ፣ በግዴታ አንቀው አያስከፍሉን!
በሌሎቹ የግል ትምህርት ቤቶች የሚታየው የክፍያ መጠንስ?
የግል ትምህርት ቤቶች እንዲበራከቱና የውድድር መንፈስ እንዲጠናከር መጣር፤ በተለይ የመሬት አቅርቦትንና የቤት ግንባታን የሚያስተጓጉሉ እንቅፋቶችን ማስወገድ፣ ለዘለቄታው ሁነኛ መፍትሄ ነው። እስከዚያው ደግሞ፣ የትምህርት ክፍያ አነስተኛ እንዲሆን በመመኘት፣ ተፎካካሪና አማራጭ ትምህርት ቤቶችን ማፈላለግ፣ ክፍያ እንዲቀነስ ለመደራደር መሞከር ያስፈልጋል። ከዚህ ውጭ፣ የግል ትምህርት ቤቶችን የማጥላላት ዘመቻ ማካሄድና በክስ ለማጥለቅለቅ ማቀድ ግን፣... አንድም አላዋቂነት ነው፤ አልያም ክፋት ነው። ትምህርት ቤቶች ላይ ተጨማሪ ችግር በመፍጠር፣ ለተጨማሪ የቢሮክራሲ እንግልትና ለሙስና ጥቃት እንዲጋለጡ ማድረግ፣ መፍትሄ አያመጣም።
በተለይ ወላጆች፣ በዚሁ ፈተናና ግርግር ምክንያት፣ ዋና አላማቸውን መዘንጋት የለባቸውም። ለምን ልጆቻቸውን ወደ ግል ትምህርት ቤት ለማስገባት እንደመረጡ ማስታወስ አለባቸው።
ወላጆች፣ የመንግስት ት/ቤትን ሸሽተው፣ ለልጆቻቸው የግል ት/ቤትን የመረጡት፣ ገንዘብ የመክፈል ሱስ ስለያዛቸው አይደለም። የተሻለ ነገር እናገኝበታለን በሚል ሃሳብ ነው።በእርግጥም፣ በርካታ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት፣ የመንግስት ትምህርት ቤቶች፣ በጣም ደካማ ናቸው። አንዳንድ መረጃዎችን እንጥቀስ።ከሦስተኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል፣ ሲሶ ያህሉ ጨርሶ ማንበብ የማይችሉ ሆነው እንደተገኙ፣ በመንግስት እንዲሁም በዩኤስኤይድ የተደረጉ ጥናቶች አረጋግጠዋል።      
በ2006 ዓ.ም፣ ለአስረኛ ክፍል ፈተና ከቀረቡ ተማሪዎች መካከል፣ የማለፊያ ውጤት ለማምጣት የቻሉት፣ ግማሽ ያህሉ ብቻ ናቸው (ከመቶ ተማሪዎች 53ቱ ያህል ብቻ)።
በ12ኛ ክፍል ፈተናም እንዲሁ፣ የተማሪዎች ውጤት ዝቅተኛ እንደሆነ፤ ቀደም ብዬ የጠቀስኩት የትምህርት ሚኒስቴር አመታዊ ሪፖርት ያረጋግጣል (Table 4.36 Grade 12 Examination Summary Results of 2006 EC - ገፅ 62)። ከሰባት መቶ ከሚታሰበው የፈተና ውጤት፣ ከ350 ነጥብ በላይ ያገኙ ተማሪዎች፣ ሩብ ያህል ገደማ ናቸው።
በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዙሪያ፣ ከጥቂት ወራት በፊት የታተመ የጥናት ውጤትንም ተመልከቱ።
በአለም ባንክ እና በትምህርት ሚኒስትር ባለሙያዎች ከተካሄደው ጥናት፣ ሁለት ቀለል ያሉ መረጃዎችን ብቻ ልጠቁማችሁ። መንግስት የሚያሳትማቸው የመማሪያ መፃህፍት ምን ያህል ደካማ እንደሆኑ ለመገንዘብ ብዙ ርቀት መጓዝ አያስፈልግም። ቢያንስ ቢያንስ፣ የመልመጃ ጥያቄዎችን በብዛት ለማቅረብ እንኳ አልበቁም። ግን፣ እነዚሁ መፃህፍትም፣ በአግባቡ አልተሰራጩም። በእርግጥ፣ የመማሪያ መፃህፍት፣ ለእያንዳንዱ ተማሪ እንዳዳረሰ መንግስት በተደጋጋሚ ይገልፃል። ገንዘብ ወጪ ተደርጓል። አጥኚዎቹም ይህን ጠቅሰዋል። ነገር ግን፣ በተግባር በየትምህርት ቤቱ ሄደው ሲያጠኑ ግን፣ አንድ መፅሃፍ ለአንድ ተማሪ የተዳረሰው፣ 60 በመቶ ያህል ነው። ሌሎቹ ተማሪዎች መፅሃፍ እየተዋዋሱ ነው የሚጠቀሙት።
አስተማሪዎችን ለመቅጠርም፣ ገንዘብ ወጪ ይደረጋል። ከአራት መቶ ሺ በላይ አስተማሪዎች ተቀጥረዋል። ነገር ግን፣ ሁልጊዜ በአግባቡ ያስተምራሉ ማለት አይደለም። ገሚሶቹ በትጋት ያስተምራሉ፤ ገሚሶቹ አያስተምሩም። ‘ገሚሶቹ’ የሚለው ቃል፣ ግምታዊ አይደለም።
የአለም ባንክና የትምህርት ሚኒስትር አጥኚዎች፣ ከየትምህርት ቤቱ የሰበሰቡትን መረጃ በቁጥር አስፍረውታል። አንድ ቀን፣ ወደ አንዱ የመንግስት ትምህርት ቤት ጎራ ብትሉ፤ ከመቶ አስተማሪዎች መካከል፣ 12ቱ ከነጭራሹ ወደ ትምህርት ቤት አይመጡም። 28ቱ ወደ ትምህርት ቤት ቢመጡም፣ ክፍል ገብተው አያስተምሩም። 7ቱ፣ ክፍል ቢገቡም፣ ሌላ ነገር ይሰራሉ እንጂ አያስተምሩም። በድምሩ፣ ከመቶ አስተማሪዎች መካከል፣ 47ቱ አያስተምሩም።
State of Service Delivery in Ethiopian Primary Schools; Wendmsyamregne Mekasha (The World Bank Office), Bereket Kelemu (Ministry of Education);  Middle Eastern & African Journal of Educational Research, Issue 16 Year 2015; ገፅ 49።ይሄ፣ የመጀመሪያ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶችን ሁኔታ የሚጠቁም መረጃ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትስ?
በአዲስ አበባ፣ በቦሌ ክፍለከተማ የሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ላይ፣ ባለፈው ሰኔ ወር የቀረበ ጥናት ውስጥ፣ አንዲት መረጃ ብቻ እንውሰድ። ከመቶ ተማሪዎች መካከል ሰላሳ ያህሉ፣ ከክፍል ወደ ክፍል መሸጋገር አቅቷቸው ይወድቃሉ። (AN ASSESSMENT OF THE STATUS OF QUALITY OF EDUCATION IN GOVERNMENT SECONDARY SCHOOLS OF BOLE SUB-CITY; ABIY FETENE; JUNE 2015, ADDIS ABABA UNIVERSITY SCHOOLOF GRADUATE STUDIES ገፅ 42)
 እንግዲህ፣ በርካታ የአዲስ አበባ ወላጆች፣ ከእንዲህ አይነት የመንግስት ትምህርት ቤት ውድቀት በመሸሽና የተሻለ ነገር ለማግኘት በማሰብ ነው፤ የአቅማቸውን ያህል፣ ልጆቻቸውን ወደ ግል ትምህርት ቤት ለማስገባት የሚሞክሩት።
ታዲያ፣ የግል ትምህርት ቤቶች፣ በእርግጥም የተሻለ ነገር የሚያቀርቡ ከሆነ፣... በትርፍ ቢንበሸበሹ፣ እንደ ወንጀል ወይም እንደ ነውር የሚቆጠርበት ምክንያት ምንድነው? ትርፋማ መሆን፣ የስኬት አንድ መመዘኛ እንጂ ነውር መሆን የለበትም። “ገበሬ፣ የመቶ ብር ጤፍ ዘርቶ፣ 10ሺ ብር የሚያወጣ ጤፍ አምርቶ ሸጠ” ብሎ እንደመኮነን ነው። ይልቅ፣ ካላተረፈ ነው ነውር የሚሆነው። እንዲህ ስል ግን፣ ትምህርት ቤቶቹ፣ “ትርፋማነት ነውር አይደለም” ብለው የሚከራከሩ እንዳይመስላችሁ።
እንዲያውም፣ ት/ቤት የከፈቱ ሰዎች ዘንድ የሚታየው አስተሳሰብ፣ በአብዛኛው ትርፋማነትን የሚያከብር ሳይሆን፣ እንደ ነውር የሚቆጥር አስተሳሰብ ነው። “ለገንዘብ አይደለም የምሰራው። ትርፍ ለማግኘት አስቤ አይደለም ት/ቤት የከፈትኩት” እያሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ እንሰማ የለ! እና፣ ጥረታቸው ለኪሳራ ነው? ወይስ ለምፅዋት?
ለነገሩ፤ለክርክር የሚያበቃ፣ የትርፍ ክምር በሌለበት አገር ነው፣ ብዙ የምንወዛገበው። ትርፋማነት፣ እንዲህ በቀላሉ የሚቀዳጁት ስኬት አይደለም። በትርፍ መንበሽበሽማ፣ በምናብና በምኞት ብቻ ካልሆነ በቀር፣ በዋዛ አይገኝም። በየቦታውና በየእለቱ፣ በትርፍ የመንበሽበሽ አጋጣሚ የሚገኝ ቢሆን ኖሮማ፣ ኢትዮጵያ እጅግ የበለፀገች አገር በሆነች ነበር።
እንዲሁ ስታስቡት፣ ትምህርት ቤት የከፈተ ሰው ሁሉ፣ በትርፍ የሚንበሸበሽ ቢሆን ኖሮ፣ በየአመቱ በሺ የሚቆጠሩ ት/ቤቶችን ለመክፈት ሩጫና እሽቅድምድም ማየት ነበረብን። ግን፣ እያየን አይደለም። ለምን?
ትምህርት ቤት ከመክፈት ይልቅ፣ ህንፃ ሰርቶ ማከራየት ይቀላል። ወይም፣ የጅምላ ንግድ ይሻላል። እንዲህ ሲባል ግን፣ ህንፃ ሰርቶ ማከራየትና የጅምላ ንግድ፣ ‘የቀልድ’ ያህል ቀላል ነው ማለት አይደለም። የሞከሩ እልፍ አእላፍ ሰዎች ሁሉ፣ በሃብት ሲመጥቁና ሲመነጠቁ የማናየው፣ የቢዝነስ ስራ ‘ቀላል’ ስላልሆነ ነው። አይነቱና መጠኑ ቢለያይም፣ የቢዝነስ ስኬት፣ ጥረትንና ብቃትን ይጠይቃል።


Read 4459 times