Saturday, 06 February 2016 11:08

የኮሜዲያን አለባቸው ተካ የ11ኛ ዓመት መታሰቢያ በ “ብሔራዊ” ይከበራል

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(2 votes)

   ኮሜዲያን አለባቸው ተካ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ህይወቱ ያለፈበት የ11ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል በነገው ዕለት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በብሔራዊ ቲያትር አዳራሽ በተለያዩ ጥበባዊ ዝግጅቶች ይከበራል፡፡
የመታሰቢያ በዓሉ “አለቤ አንረሳህም” በሚል ቃል የኮሜዲያኑን ሥራዎች በመዘከርና በማስታወስ ይከበራል ተብሏል፡፡ የበዓሉ አስተባባሪ ደራሲ ኃይሉ ፀጋዬ ለአዲስ አድማስ እንደገለፀው፤ “አለባቸው ለኢትዮጵያ ብዙ ሰርቷል፡፡ የመጀመሪያው የቶክ ሾው አቅራቢ ነው፡፡ ከልመንህ ጋር በመሆን የስታንድ አፕ ኮሜዲ ጀማሪ ነው፡፡ በስሙ የሴቶች የእግር ኳስ ቡድን አቋቁሟል፡፡ ስለዚህም ‹አለቤ አንረሳህም› ብለን እንዘክረዋለን” ብሏል፡፡
በመታሰቢያ ፕሮግራሙ ላይ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንዲሁም የአርቲስቱ ቤተሰቦች፣ ወዳጆችና አድናቂዎች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።የዛሬ 11 ዓመት ወደ ጅማ ሲጓዙ በድንገተኛ የመኪና አደጋ ኮሜዲያን አለባቸው ተካና የካሜራና ኤዲቲንግ ባለሙያው ይልማ ቀለመወርቅ ህይወታቸው ሲያልፍ ከሞት የተረፈው ኤፍሬም ደስታ፤ የመታሰቢያ በዓሉ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል ሲሆን ለአዲስ አድማስ በሰጠው አስተያየት፤ “የደግነት ትርጉሙን የማውቀው በአለቤ ነው፤ የሰው ችግር ያመዋል፤ የለኝም ማለት አይችልም፤ ለራሱ ከመኖር ይልቅ ለሌሎች መኖርን ይመርጥ ነበር” ሲል አለባቸውን አስታውሷል፡፡
የመታሰቢያ በዓሉን ያዘጋጁት ደራሲ ኃይሉ ፀጋዬ፣ የክላርኔት ተጫዋቹ ዳዊት ፍሬው፣ ፕሮሞተር ሙሉቀን ተሾመ - እና ኤፍሬም ደስታ ሲሆኑ ብሄራዊ ቴአትር አዳራሽና ሙሉ የሙዚቃ ባንዱን በነፃ እንደፈቀደላቸው የፕሮግራሙ አስተባባሪ አስታውቋል፡፡

Read 1784 times