Saturday, 06 February 2016 10:37

ለአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ተቋማት የወጣው አዲስ መመሪያ ቅሬታ አስነስቷል

Written by  ማህሌት ኪዳነወልድ
Rate this item
(4 votes)

ሰልጣኞች ጭነት በጫነ ተሽከርካሪ እንዲፈተኑ ያዛል
              የሥልጠና ወጪው ከ30ሺ እስከ 40ሺ ብር ይደርሳል ተብሏል
                           
    የትራንስፖርት ሚኒስቴር ብቁ አሽከርካሪዎችን ለማፍራት ይበጃል በሚል ያወጣውን አዲስ መመሪያ የአሽከርካሪ

ማሰልጠኛ ተቋማት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲተገብሩት ያዘዘ ሲሆን ማሰልጠኛ ተቋማቱ መመሪያውን ለመተግበር

አስቸጋሪ መሆኑን በመግለጽ ቅሬታቸውን ሰንዝረዋል፡፡  
የሰልጣኞች የፈተና መስጫ ቦታ፤ የትራፊክ ፍሰት ያለበት፣ ዋና መንገድ ላይ ፣ ዳገት ቁልቁለት እንዲሁም ጠመዝማዛ

ቦታ ተመርጦ እንዲሆን የሚያዘው አዲሱ መመሪያ፤ ሰልጣኞች ጭነት በጫነ ተሽከርካሪ በዝቅተኛና በከፍተኛ ፍጥነት

መፈተን እንዳለባቸው ያስገድዳል፡፡
የአዲስ አበባ አሽከርካሪዎች ማሰልጠኛ ተቋማት ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ተስፋዬ ንጉሴ በበኩላቸው፤ ሰልጣኞችን

መሃል ከተማ ማስገባት የሚያስከትለው አደጋ ሊታሰብበት ይገባል ብለዋል፡፡ “ሰልጣኞች በደርሶ መልስ 80 ኪ.ሜ

በሰዓት እንዲነዱ የሚያስገድደው መመሪያ፤ ለሚደርሰው አደጋና ጉዳት ሃላፊነቱን የሚወስደው አካል ማን እንደሆነ

በግልጽ አላስቀመጠም” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
አንድን አሽከርካሪ ጭነት ሲጭን ሊያደርግ የሚገባውን ነገር ለምሳሌ ማርሽ አስሮ ቁልቁለት መውረድን፣ መኪናው

ሳይጭንም ማድረግ ስለሚቻል ባለሙያዎች መመሪያውን በድጋሚ ሊያጤኑት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡
እስካሁን ሥልጠናው ከ8ሺ -10ሺ ብር ያስከፍል እንደበር የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ፤ መመሪያው ሲተገበር ግን

የተሽከርካሪዎች ጭነት፣ የሚፈጀው ነዳጅና ሌላ ሌላው ሲጨማመር የማሰልጠኛ ዋጋውን ወደ 30 እና 40 ሺህ ብር

ከፍ ስለሚያደርገው በህብረተሰቡ ላይ የሚያደርሰው ጫናም ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
አዲሱ መመሪያ ሰልጣኞች ሊመዘገቡ ሲመጡ የመታወቂያቸውን ትክክለኛነት /ፎርጅድ መሆኑንና አለመሆኑን/

የማረጋገጡን ሀላፊነት ለኛ ሰጥናል ያሉት የማህበሩ ፕሬዚዳንት፤ እኛ ኦርጂናሉን አይተን ኮፒውን ከመቀበል ውጭ

ሌላውን ለማረጋገጥ የሚያስችል ቴክኖሎጂና አቅም የለንም ብለዋል፡፡
መመሪያው በፅሁፍ ፈተና እንዲሁም በስልጠና መሸራረፍ ችግሮችና በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የነበሩ ጉድለቶችን

የሚያስወግድ እንደሆነ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፤ ከላይ የተጠቀሱት ዋና ነጥቦች ላይ ግን ሊታሰብባቸው ይገባል

ብለዋል፡፡
የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣን በበኩሉ መመሪያው የተዘጋጀው በየስብሰባና ውይይቱ ላይ የሚነሱ አስተያየቶችና

ሀሳቦችን በማሰባሰብ ጉድለቶችን በመሙላት ብቁ አሽከርካሪዎችን ለማፍራት ነው ብሏል፡፡
የባለስልጣኑ የማስታወቂያና የህዝብ ግንኙነት ተወካይ ኃላፊ ወ/ሮ ይርጋለም ጥላሁን ሰልጣኞች በዋና መንገድ ላይ

የመሰልጠናቸውን ፋይዳ ሲያስረዱ፤ ከዚህ ቀደም ሰልጣኞች ቃሊቲ አካባቢ ብቻ በመሰልጠናቸው ወደ ከተማ ሲገቡ

ይታይባቸው የነበረውን መደናበር ያስቀራል ብለዋል፡፡
ሰልጣኞቹ ከተማ ላይ ጭነት ጭነው በዚህ ፍጥነት ሲሄዱ ለሚደርሰው አደጋ ተጠያቂው ማነው በሚል የተጠየቁት

ተወካይዋ፤ “አሁን ሰልጣኞቹ ቀድመው ከተማውን እንዲለምዱ በመደረጋቸው አደጋ የመድረስ እድሉ እጅግ አነስተኛ

ነው፡፡ ሆኖም አደጋ ከደረሰ ተጠያቂ የሚሆነው በየደረጃው እያሰለጠነና ብቁ እያደረገ እዛ ያደረሰው አካል ወይም

አሰልጣኙ ይሆናል” ብለዋል፡፡
ጭነት የመጫን ህጉ የሚተገበረው በሁሉም ተሸከርካሪ ላይ ነው ያሉት ወ/ሮ ይርጋለም፤ የህዝብ ማመላለሻ

ተሽከርካሪዎች በዛው ኪሎ ልክ የሚሆን ጭነት ጭነው መለማመድ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
መታወቂያና የትምህርት ማስረጃዎችን በተመለከተም ማሰልጠኛ ተቋሙ ሄዶም ሆነ ደውሎ ማረጋገጥ እንደሚኖርበት

አሳስበዋል፡፡ የማሰልጠኛ ገንዘቡም በዚህ ደረጃ ሊጨምር ይችላል ብለን አናምንም ያሉት ተወካይ፤ መመሪያው

ሲተገበር የሚታዩ ክፍተቶች ካሉም በሂደት እንደሚስተካከሉ ገልፀዋል፡፡

Read 4095 times