Saturday, 30 January 2016 12:57

የአፍሪካ ሙስና መሻሻል አላሳየም ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

   ሶማሊያና ሰሜን ኮርያ በሙስና አለምን ይመራሉ
    ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለው አለማቀፍ ተቋም በአፍሪካ አህጉር ያለው የሙስና ችግር መሻሻል አለማሳየቱንና ሙስና በአህጉሪቱ በሚገኙ አርባ አገራት ውስጥ እጅግ የከፋ ችግር መሆኑን ሰሞኑን ባወጣው አመታዊ ሪፖርት አስታወቀ፡፡
  በአህጉሪቱ የሙስና ችግር ስር እየሰደደ መምጣቱን እንዳስታወቀ የዘገበው ቢቢሲ፣ ሶማሊያ በአፍሪካም ብቻ ሳይሆን በመላው አለም የከፋ የሙስና ችግር ያለባት ቀዳሚዋ አገር ናት መባሉንና ሰሜን ኮርያም በሙስና ከሶማሊያ ጋር የዓለማችን ቀዳሚ ሙሰኛ አገር  መሆኗን ጠቁሟል፡፡
በአህጉሪቱ ሙስና በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋባቸው አብዛኞቹ አገራት በግጭት ውስጥ ያሉ፣ ፖሊስና ፍርድ ቤትን የመሳሰሉ ተቋማት ደካማ የሆኑባቸውና ገለልተኛ ሚዲያ የሌሉባቸው ናቸው ያለው ተቋሙ፤  ከአፍሪካ አገራት በሙስና ከፍተኛው መሻሻል የታየው በሴኔጋል መሆኑንና፣ አገሪቱ የተለያዩ የጸረ ሙስና ህጎችን ተግባራዊ ማድረጓ በሙስናው ላይ መሻሻል ማሳየቱን አስታውቋል፡፡
በአለማችን ከሶማሊያና ሰሜን ኮርያ በመቀጠል በሙስና መስፋፋት ከሁለተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ የያዙት አፍጋኒስታን፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ አንጎላ፣ ሊቢያ፣ ቬንዙዌላ፣ ጊኒ ቢሳውና ሃይቲ ናቸው ተብሏል፡፡አነስተኛ ሙስና አለባቸው ከተባሉት የአለማችን አገራት መካከልም ከአንደኛ እስከ አምስተኛ ደረጃ የያዙት ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ስዊድን፣ ኒውዚላንድና ኒዘርላንድስ እንደሆኑ የተቋሙ አመታዊ የሙስና ሪፖርት አስታውቋል፡፡

Read 1526 times