Saturday, 30 January 2016 12:54

ቢል ጌትስ የዓለማችን ቀዳሚ ቢሊየነር ሆነ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

   87.4 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት አለው
    87.4 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት ያካበተው የማይክሮሶፍት መስራቹ አሜሪካዊው ቢሊየነር ቢል ጌትስ፣ በዘንድሮው የፈረንጆች አመት 2016 የዓለማችን 50 ቀዳሚ ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ አንደኛ ደረጃን መያዙን ታይም መጽሄት ዘገበ፡፡
ዌልዝ ኤክስ የተባለውና የአለማችንን ባለጸጎች የሃብት ደረጃ በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ተቋም ከሰሞኑ በድረገጹ ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ በአመቱ ከቢል ጌትስ በመቀጠል ሁለተኛ ደረጃን የያዙት ስፔናዊው ቢሊየነር አማኒኮ ኦርቴጋ ሲሆኑ ባለጸጋው 66.8 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት አላቸው፡፡
አሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን ቡፌት በ60.7 ቢሊዮን ዶላር የሶስተኛነት ደረጃን መያዛቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ 42.8 ዶላር የተጣራ ሃብት አለው የተባለው የፌስቡኩ መስራች ማርክ ዙክበርግም ስምንተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ዘገባው ገልጿል፡፡
በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት ማይክል ብሉምበርግ በ42 ቢሊዮን ዶላር ዘጠነኛ ደረጃ መያዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፣ 33.2 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሃብት በማካበት ከአለማችን ሴቶች በሃብት ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው የዎልማርት ኩባንያዋ አሊስ ዋልተን በአለማችን 50 ቀዳሚ ቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ 15ኛ ደረጃ ላይ መቀመጧንም አመልክቷል፡፡

Read 2767 times