Saturday, 16 January 2016 10:37

ሙዚቃን ከፍላሽ ሜሞሪ ዲስክ የሚያጫውቱ …

Written by  ደረጀ ምንላርግህ
Rate this item
(0 votes)

       ከሁለት ሳምንት በፊት፣ በዚህ ኪነ ጥበብን ጨምሮ ባህልን በሚያንጸባርቅ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ‹‹ኤፍሬም ታምሩ & ሮሃ ባንድ እንደገና- እጹብ ድንቅ ልዕልና!!!›› ብዬ በጻፍኩት ጽሑፍ ላይ፣ በባለፈው ሳምንት የጋዜጣው እትም- ‹‹የኤፍሬም ታምሩ አልበም ያለቅጥ ተሞገሰ›› በሚል ርዕስ “አቶ” ብለውኝ፣ ትችታቸውን ጽሑፉ ላይ ሳይሆን እኔ ላይ አተኩረው፣ ከሆነ ቡና ቤት እየተሳለቁብኝ የጻፉትን የሁለት ልጆችን የጋራ ጽሑፍ ሳይ፣ ትችቱ ምንም ይሁን ምን፣ ይሄ በለጋ ብዕሬ የከተብኩት ጽሑፍ፤ ለ”ትችት” በመብቃቱ ደስ አለኝ፡፡ ለዚህም ብቻ ትችቱን የጻፉትን ሁለቱንም- ጥበቃና አሽቃሩ የተባሉትን ልጆች! አመስግኛቸዋለሁ፡፡
በነገራቸው ላይ ግን፣ የመማማሪያ መድረክ እንዲሆን፣ አንድ ሰው በሰራው ስራ ላይ አስተያየት ሲሰጥ በአማርኛችን “ገድሎ ማዳን” ወይም “አድኖ መግደል” እንደሚባለው ዓይነት ነገር፣ በእንግሊዘኛውም ለምሳሌ- “Sandwich Approach” ወይም “Kiss - Kick - Kiss Approach” የሚባለውን የአስተያየት አሰጣጥ መንገድ መጠቀሙ ጤናማና ገንቢ የሀሳብ ልውውጥ እንደሆነ ሳልጠቁማቸው አላልፍም፡፡ ማለትም፣ ልክ በእንቁላል ሳንድዊች አቀራረብ ላይ፣ የዚህ ምግብ ዋናው የሆነው እንቁላሉ መሐል ላይ ይቀመጥና ከስርና ከላዩ ደግሞ ዳቦ እንደሚሸፈንበት ሁሉ፤ እንደዚሁ፣ አንድን ሰውም በሰራው ስራ ስንተቸው፣ ዋናውን ድክመቱንና ስህተቱን ከላይ በማድረግ ወይም መጀመሪያ ላይ አስቀድመን በማምጣት በቀጥታ መንገር ሳይሆን፣ እንደ እንቁላል ሳንድዊቹ አቀራረብ መሐል ላይ እናደርገውና፣ የመግቢያውን ንግግር ግን ያ ሰው ስለሰራው በጎ ወይም መልካም ነገር ወይም ጥንካሬውን በመንገር እንጀምራለን። በመቀጠልም፣ የንግግሩም ሆነ የጽሑፉ ዋናው ዓላማችን ችግሩን ወይም ስህተቱን ለመተቸት ነውና፤ ነገር ግን፣ ብለን ልንነግረው የፈለግነውን ዋናውን ድክመቱንም ሆነ ስህተቱን በደንብ እንነግረዋለን ማለት ነው፡፡ በመሆኑም፣ ይህ ሰው በጎ ነገሩንም አስቀድመን የነገርነው ስለሆነ በዚህ በተሰጠው ትችት አይደናገጥም ወይም ክው!! አይልም፡፡ አሁንም እንደገና፣ ድክመቱንና ስህተቱን ነግረነው ስናበቃ፣ አስተያየታችንን በዚሁ ከዘጋነው- “አድኖ መግደል” እንደ ማለት ነው- የስህተቱንና ድክመቶቹን ስሜት ብቻ ይዞ እንዳይሔድና ተደናግጦ እንዳይቀር ብሎም የስራ ተነሳሽነቱም ሆነ አጠቃላይ ስነ ልቦናው እንዳይጎዳ፣ ‹‹ነገር ግን፣ ከእነኚህ ስህተቶችህ ባሻገር እነኚህ ጠንካራ ወይም መልካም ነገሮችህ እንዳሉ ናቸውና የበለጠ በርታ!!! የተሻለም ስራ እንደምትሰራ እርግጠኞች ነን!!!›› ዓይነት ነገር ብለን የአስተያየታችንን መደምደሚያ በመልካሙ ንግግራችን ከዘጋንለት፣ መልካምና ገንቢ የመማሪያ ልውውጥ አስተያየት ይሆናል ማለት ነው። ማለትም፡- መጀመሪያ ላይ መልካሙን ነገሩን አስቀድመን በመንገር ሳምነው- Kiss አደረግነው፣ ቀጥለን ደግሞ ድክመቱ ላይ አስረግጠን ደበደብነው- Kick አደረግነው፣ ከዚያም በመጨረሻውና መዝጊያው ላይም ስመነው ወጣን- Kiss አደረግነው ማለት ነው - ይሄ የ “Kiss - Kick - Kiss Approach” ማለት፡፡
እንግዲህ ይሄን ካልኩ በኋላ፣ እነኚህ እኔን በጋራ ጽሑፋቸው የተቹኝ ሁለቱ ጥበቃና አሽቃሩ የተባሉት ልጆች ግን፣ ከላይ ባወራነው መልኩ ሳይሆን በተቃራኒው፣ ሲጀምሩም- መሐሉም- መጨረሻውም ስድብ አዘል በሆነ ትችትና ጨለምተኝነት ነው አስተያየት ባሉት ጋጠ ወጥነታቸው ምላሽ የሰጡኝ፡፡
ወደ ቁምነገሩ የምላሽ ነጥቤ ስመጣ፣ ባለፈው በጻፍኩት ጽሑፍ ላይ ዓላማዬ ስለ ኤፍሬምና ሮሃ ባንድ እንደገና አልበም እጹብ ድንቅነት ብቻ በደምሳሳው ለማውራት ሳይሆን፣ አጋጣሚውን ተጠቅሜ እግረ መንገዴን ሙዚቃ ሙያቸው ላልሆነና ስለ ሙዚቃ ስራ ሙያዊ ግብዓቶች ግንዛቤ ለሌላቸው ላገራችን ሰፊው አዳማጮች፣ ያቅሜን ያህል በሚገባና ቀለል ባለ መንገድ በመንገር ግንዛቤ እንዲያገኙና፣ ያገራችንን ጥራት ያለውንና የሌለውን የሙዚቃ ምርት ለይተው በማወቅ ተገቢውን ዋጋ እንዲሰጡ ለማድረግ፣ ከብዙ የሙዚቃ ስራ ክንውኖች መሐከል፣ ከዓባይ ወንዝ በጭልፋ እንደመቀንጨብ ያህል፣ በሙዚቃ አልበም ስራ ላይ እጅግ ወሳኝ ስለሆኑት ሶስቱ ተግባራት- ማለትም፡- ስለ የሙዚቃ ቅንብር፣ የሙዚቃ ሚክሲንግ እና የሙዚቃ ማስተሪንግ ምንነትና ሚና መሬት ላይ በወረደ ቀላል የምሳሌ አገላለጽ ለማስቀመጥ ነበር የሞከርኩት፡፡ (ያላነበባችሁት ወደ ኋላ ሔዳችሁ ብታነቡት ደስ ይለኛል!!!)
በተለይም በሀገራችን ላይ ከባለፉት አስር ዓመታት በላይ፣ የባንድ የሙዚቃ ቅንብር ቀርቶ የኪቦርድ ወይም ድራም ማሽን ቅንብር ከተንሰራፋ ጀምሮ፣ ፍሬውን ከገለባው መለየት ሳይሆን ገለባውን ከፍሬው መለየት ሆነና፤ ጥቂት በማይባሉ ብዙ የሀገራችን የአሁን ትውልድ ወጣቶችም ሆነ ከፍ ያሉት ዘንድ፣ የተበላሹ የቅንብር ስራዎችና የሙዚቃ ድምጫዎች እንደ ትክክለኛ፣ ትክክለኛው ሙሉ የባንድ ሙዚቃ ስራና ደረጃውን የጠበቀ የሙዚቃ ድምጽ ደግሞ እንደ ብልሽት እየተቆጠሩ በመታየታቸው፤ እኔም ራሴ በዙሪያዬ ካሉ ብዙ ሰዎች ይሄን የተሳሳተ አመለካከት ስለማይ፤ እንደማንኛውም የሀገራችንን ሙዚቃ በፍቅር እንደሚወድና ለሀገራችን የሙዚቃ ዕድገት በእጅጉ እንደሚቆረቆር ሰው ሁሉ፣ እኔም የማውቀውን ያህል የሙዚቃ ዕውቀቴን ተጠቅሜ ነበር ጽሑፉን የጻፍኩት፡፡ በእርግጥም ይህ የሙከራ ጽሑፌ በዚህ የኤፍሬምና ሮሃ ባንድ እንደገና አልበም ላይ ተሳካልኝ እንጂ፣ ሀሳቡን ጀምሬ የተውኩት ያኔ የፀጋዬ እሸቱ እንደገና በኤክስፕረስ ሙሉ ባንድ የተቀናበረው፣ ደረጃውን የጠበቀው ጥሩ የሙዚቃ ስራ አልበም በወጣ ጊዜ ነበር፡፡
እናም፣ አንድ የታንዛኒያኖች አባባል፡- የሆነ የተማርከውን ትምህርትም ሆነ ያወቅኸውን ዕውቀት በደንብ እንዳወቅኸውና ያም እውቀት በውስጥህ የተዋሐደ መሆኑ የሚታወቀው፣ ያንን ያወቅኸውን ዕውቀት ቢያንስ ለቅድመ አያትህ ሊገባ በሚችል ቀላል መልኩ ማስረዳት ስትችል ነው፤ አለበለዚያ ግን ያ አውቀዋለሁ የምትለው ዕውቀት በላይህ ላይ ተንሳፍፎ እንዳለ እንጂ እንዳወቅኸው አይቆጠርም!! እንደሚለው ሁሉ፤ እኔም እንዳቅሚቲ፣ሁሉም ያገራችን ሰው የሚያውቀው ነው ባልኩት የምግባችንን የወጥ አሰራር ሙያን ምሳሌ አድርጌ ስለ ሶስቱ ወሳኝ የሙዚቃ ስራዎች ምንነትና ጠቀሜታነት በቀላሉ ለመግለጽ ከሞከርኩ በኋላ፣ ይሄም የኤፍሬም ታምሩ እና ሮሃ ባንድ እንደገና የሙዚቃ አልበም፣ ሶስቱንም ስራዎች ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ያሟላ ዕጹብ ድንቅ ልዕልና የተሞላበት ስራ ነው ስላልኩኝ፤ እነኚህ በሙዚቃ ዙሪያ ውስጥ ያሉ የሚመስሉት ጥበቃና አሽቃሩ የተባሉት ልጆች በጻፍኩት ጉዳይ ላይ፣ የሀገራችን ሙዚቃ ኢንዱስትሪ እንዲህ በታመመበት ወቅት፣ የበኩሉን ግንዛቤ ሊፈጥር ጥሯል ብለው ደስ ሊላቸው ሲገባና ባጎደልኩት ላይ ሊሞሉ ሲገባ፣ ጭራሹኑ ቁምነገሬን ጆሮ ዳባ ብለው በእኔ ላይ በማሾፍ እየተሳለቁ- ‹‹አንዴ ጥጥ፣ አንዴ ወጥ፣ አንዴ ሙሽራ፣. . . እያለ በመዘባረቅ አንድም ነገር ላያሳውቀን እንዲሁ አደከመን፣ ወዘተ›› ብለው ዘለፋቸውን በመጻፋቸው በጣም ነው የገረመኝና ያሳዘነኝ፤ ብሎም የመዚቃችንን ኦሪጅናል ሲዲ ሽፋን መረጃ አይተው የማያውቁ እንደሆኑም የገባኝ። ሲቀጥልም፣ እንደ የሀገራችን መንግስታት ታሪክ፣ በባለፈው መንግስት የነበሩትን መልካም የሀገር ነገሮችን በጎደለው ላይ ሞልተው፣ መስተካከል ያለበትን አስተካክለው በዚያው ላይ እንዳለ መቀጠል ሲገባቸው፣ ያንን መልካም ነገር በስድብ ድምጥማጡን አጥፍተው በማፍረስ፣ የውሾን ነገር ያነሳ ውሾ!! ብለው፣ የራሳቸውን ነገር ሀ ብለው ከዜሮ እንደሚጀምሩትና ሀገር እንደሚያምሱት ሁሉ፤ እነኚህ ከሆነ ቡና ቤት ነን ያሉት ሁለቱ ጥበቃና አሽቃሩ የተባሉ ልጆችም፣ እኔ ከጻፍኩት የሙዚቃ ቁም ነገር ላይ አንዲትም ሰበዝ ሳይመዙለት በዘለፋ ድባቅ ከመቱት በኋላ፤ በጽሑፌ ላይ ሳይሆን በእኔ ላይ- ‹‹በጸሐፊው ላይ ያለንን አስተያየት በዚሁ እናብቃና ስለ ሙዚቃ አንዳንድ ነገሮችን እናንሳ›› ብለው፣ ይሄን የማህበረሰብ ጋዜጣ ለሚያነብ ሰፊው ማህበረሰብ ሊገባው በሚችልና በጠቃሚነት ሊያውቀው በሚገባ አስፈላጊ የሙዚቃ ጉዳዮች ላይ ሳይሆን፣ ለሙዚቃ ሙያተኞች ብቻ የሚሆንን- ሙዚቀኞቻችንም ቢሆን የሚያውቁትን ችክ ያለ የሙዚቃ ዕውቀታቸውን ከዜሮ ጀምረው የራሳቸውን ጻፉ፡፡ ውድ አንባቢዎች!! እስኪ ወደ እነርሱ ልመለስ፡፡
እናንተ ጥበቃና አሽቃሩ!!
ከጠማማነታችሁ የመነጨ የዘለፋ እስር ችቧችሁ ውስጥ ሁሉ በተለይ የገረመኝና ያሳቀኝ ነገራችሁ- መቼም፣ ማንኛውም ሙዚቃም ሆነ ዜማ ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ ‹‹ኧ ኧ ኧ ኧ. . . . .›› ብቻ እያለ የሚቀጥል የቀጥታ መስመር ድምጽ ሳይሆን፣ ከዝቅተኛው የድምጽ እርከን ወደ ላይኛው ድምጽ እየወጣ የሚወርድ፣ እጥፋቶችን እየሰራ የሚምዘገዘግ- “ከርቭ” የሚሰራ እንደሆነ እያወቃችሁት ሳለ፣ ‹‹አሁን ዘፋኞቻችን “የድምጽ ከርቭ” ማለት ምን ማለት ነው? ብለው ቢጠይቁት ምን ብሎ ይመልስ ይሆን?!›› ብላችሁ በመሳለቃችሁ፣ አይገርማችሁም?!! በደንብ ተሳልቄባችኋለሁ!!! እንዴ. . . በዚህ የማህበረስብ ገጸ ዓምድ ላይ ለብዙሃኑ አንባቢ ሰው የማይጠቅም እንካ ስላንትያ እንደሆነ አውቃለሁና፤ በዚህም አንባቢዎችን ይቅርታ እየጠየኩ፤ “ንገረኝ ካልሽማ” እንዳለው ዘፋኛችን፣ ይልቅስ እናንተ ስለሙዚቃ ከጻፋችሁት ውስጥ ለምሳሌ ስለ ትዝታ ቅኝት አገላለጻችሁ ላይ በሀሜት ሳይሆን በእውነተኛው መንገድ ልሳለቅባችሁ፡፡ ይሄውም፡- እናንተ ትዝታ 2nd  እና ትዝታ 5th ብላችሁ የገለጻችሁትን ላንድ ፕሮፌሽናል ሙዚቀኛ ብትነግሩት እንዲህ የሚባል ሳይንቲፊክ key Signature Name (ስያሜ) የለም ብሎ ጆሮውን እንደሚይዝባችሁ ያለጥርጥር አውቃለሁ፡፡ እኔ ግን በሀገርኛ የእውቀት ስያሜ መግባቢያ ምን ለማለት እንደፈለጋችሁ ገብቶኛል። ለምሳሌ፡- በትዝታ ሜጀር C ስኬል ውስጥ ሆኖ (ማለትም፡- C D E - G A - C ስኬል ውስጥ ሆኖ) ከ 2ኛው ኪይ(ከD) ወይም ከ 5ኛው ኪይ(ከG) ተነስቶ እዚያው ላይ በማረፍ (Resolution) መጫወት ማለታችሁ ነው፡፡ ነገር ግን፣ በ C ቅኝት ውስጥ ሆነው ሳይሆን፣ ራሳቸውን ችለው በራሳቸው key Signature ስያሜ ነው፡- ትዝታ ሜጀር D ስኬል= D E F# -  A B - D እንዲሁም ትዝታ ሜጀር G ስኬል= G A B – D E – G ሆኖ ቅኝታቸው የሚመሰረትና ማንም ኢትዮጵያዊ ያልሆነ የውጭ ሀገር ፕሮፌሽናል ስያሜውን ብቻ ይዞ ዘፈናችንን የማያውቀው እንኳን ሊጫወት የሚችለው፤ እንጂ እናንተ ያላችሁትን ትዝታ 2nd እና ትዝታ 5th ስያሜ ጆሮውን ብትቆርጡት አይገባውም፡፡ እናም፣ ሙዚቃ ሙያቸውም ሆነ ስራቸው ያልሆነውን ያገራችንን መደበኛ ሙዚቃ አዳማጮች እንዲህ ያለውን ለሙዚቀኛ ብቻ የሚገባውን ዝባዝንኬ በማህበረሰብ ገጽ ጋዜጣ ላይ እየጻፍን አይደለም በከንቱ የምናደነቁረውና ምንም ግንዛቤ እንዳያገኝ የምናደርገው፡፡
በመጨረሻም ሀሳቤን ሳጠቃልል፣ ይሄን ሁሉ የጻፍኩበት ምክንያቴ፣ በዋነኛነት ለእናንተ- ለጥበቃና አሽቃሩ ለተባላችሁት ሁለት ልጆች- የትችትን ባህሪ ለማያሟላው ትችት ሳይሆን ዘለፋችሁ ምላሽ ለመስጠት ሳይሆን፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ጽሑፌን ያነበቡት ሌሎች የተከበሩ አንባቢዎች በከንቱ ያስነበብኳቸው እንዳይመስላቸውና እንዳይደናገሩ ብዬ ነው፡፡ በተረፈ ግን፣ እናንተ ሁለታችሁ አሁንም በጻፍኩት ማብራሪያዬ ላይ አውቆ የተኛን እንዲሉ ላለመማር በሩን በዘጋው ልቦናችሁ አሁንም ደግማችሁ እንደምትሳለቁብኝ እገምታለሁ፡፡
ስሰናበትም፣ ለዚህ ሁሉ ሀሳብ ገለጻ መነሻ ምክንያት የሆነውና፣ ስመ ጥር በሆኑ የሀገራችን ፕሮፌሽናል የሙዚቃ ሀያሲ ባለሙያዎች በኩል አልበሙ ብቻውንና ራሱን የቻለ የሙዚቃ ትንታኔ (Music Analysis) ሊሰራለት የሚገባና መማሪያም ሊሆን የሚችለው ይህ ድንቅ የኤፍሬም ታምሩ እና ሮሃ ባንድ እንደገና የሙዚቃ አልበም፤ ያላዳመጠው ሊያዳምጠው የሚገባ፣ ያዳመጠውም በደንብ እያደጋገመ የሚያጣጥመው ደረጃውን የጠበቀ የሙዚቃ ስራ ነውና፤ አሁንም እኔ በድጋሚ፣ ይህንን አልበም ያለቅጥ ያሞገስኩት ስራ ነው ሳይሆን፣ መጀመሪያም እንዳልኩት፡- እጹብ ድንቅ ልዕልና!!! የተሞላበት ነው እላለሁ፡፡ በዚህ ሁሉ መሐልም፣ በድጋሚ ሌላ ተጨማሪ ሀሳቤን እንድገልጽ ምክንያት ስለሆናችሁኝ ሁለታችሁንም ባመጣችሁ ንፋስ በኩል አመሰግናችኋለሁ፡፡
በሙዚቃ ሰላም እንጂ ንትርክ አያምርም፡፡ . .

Read 1615 times